የኦሮሞ ሕዝብ ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍትህ ለዘመናት ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በመሆን ከፍተኛ ትግል አድርጓል። ለውጡ ስኬታማ እንዲሆንም ታላቅና ውድ መስዋዕትነት ከፍሏል። በዚህም እንደ ሀገር የተጀመረው ለውጥ እያስገኘ ካለው ትሩፋት ተጠቃሚ እየሆነ ነው።
በአንድ በኩል ከይስሙላ እራስን በራስ የማስተዳደር የፖለቲካ ፌዝ ወጥቶ በተጨባጭ እንደ አንድ ፌዴራል የክልል መንግሥት የራሱን ጉዳይ በራሱ የሚወስንበትን፤ ከዚህም ባለፈ በሀገራዊ ጉዳይ ቁመናውን በሚመጥን መልኩ ተሳታፊ የሚሆንበትን የተሻለ ዕድል አግኝቷል።
ለውጡ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ፤ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የኦሮሞ ሕዝብ ሲታገልላቸው የቆዩትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች በማጎናጸፍ፤ ሕዝቡ ወደ ልማት የሚገባበትን አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል፤ ይህንንም ብዙዎች ተገንና ተስፋ አድርገው ወደ ሥራ ገብተዋል። ውጤታማ የሆኑበት እውነታም ታይቷል።
የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ካለው በልማት የመበልጸግ መሻት አንጻር፤ ያለውን የተፈጥሮ እና የሰው ሀብት በማቀናጀት እንደ ሀገር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው ትግል አካል በመሆን ከፍ ባለ መነቃቃት ሲንቀሳቀስም ተስተውሏል።
በክልሉ ካለው ገና ያልተነካ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት እና ብቁ አምራች የሰው ኃይል አንጻር፤ በክልሉ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ የተመዘገቡ ውጤቶች፤ በርግጥም የክልሉ ሕዝብ ለልማት መሻቱ ስኬት የሚሆን ሰላም ካገኘ ድኅነትን ተሻግሮ ከትናንት የተሻለ ሕይወት መምራት ብዙ ፈተና እንዳይሆ ንበት ያመላከቱ ሆነዋል።
ይህ የክልሉ ሕዝብ የመበልጸግ መሻት ግን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በብዙ ፈተናዎች እየተናጠ ስለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ሕዝቡ እንደ ሀገር ለውጡን ካጋጠመው ፈተና ባለፈ በስሙ በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በብዙ ተፈትኗል ፤ ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገድዷል።
በአንድ በኩል በኃይል ሥልጣን ለመያዝ ብረት ያነገቡ ኃይሎች፤ በሌላ በኩል ትናንት እንደ ሀገር ከፍ ያለ ዋጋ እንድንከፍል ያስገደደን የሴራ ፖለቲካ በሚያራምዱ ከአብራኩ በወጡ ልጆቹ፤ ያ ልተገባ ዋጋ ከፍሏል። የዕለት ተዕለት ሕይወቱ ሳይቀር ባልተለመደ መልኩ በስጋት የታጠረ ሆኗል።
ይህን ከኦሮሞ ሕዝብ መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ እሴት ያፈነገጠ የጥፋት መንገድ ለማረም በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በመንግሥትና በራሱ በኦሮሞ ሕዝብ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል። ባልተገባ መንገድ ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በተለያዩ ወቅቶች ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችም ቀርበዋል።
በመንግሥትና በሕዝብ ስለ ሰላም እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በየጊዜው እመርታ እያሳዩ ክልሉ በተሻለ የሰላም መንገድ ላይ ቢሆንም፣ የክልሉ ሕዝብ ለሚፈልገው በሁለንተናዊ ልማት ብልጽግናን ለማምጣት ያለውን መሻት እውን ለማድረግ አሁንም የሰላም ጉዳይ ወሳኝ ስለመሆኑ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ከኦሮሚያ ክልል ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጉት ውይይት በክልሉ ዘላቂ ሰላም በማምጣት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠልና ውጤታማ ለማድረግ ትልቅ ሕዝባዊ አቅም መፍጠር የሚያስችል እንደሚሆን ይታመናል።
በተለይም የክልሉ ሕዝብ ከሰላም ማጣት በስተጀርባ ያሉ እውነታዎችን በአግባቡ ተረድቶ፤ ዘላቂ ሰላም በማስፈን ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን የሚያስችለውና፤ ከተለያዩ ውዥንብሮች ወጥቶ የራሱን ነገዎች ብሩህ አድርጎ መሥራት እንዲችል የተሻለ ዕድል የሚፈጥርለት ነው።
መንግሥትም ቢሆን በሕዝቡ ውስጥ ያሉ ቅሬታዎችን ከባለቤቱ አንደበት በመስማት የማስተካከያ ርምጃዎችን በመውሰድ፤ ከሕዝቡ ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት በማደስ ለቀጣይ ሰላም ማስፈን ሆነ የልማት ሥራዎች የሕዝቡን ልብ መግዛት የሚያስችለውን ዕድል የሚፈጥርለት እንደሚሆን ይታመናል!
አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም