የሀሮማያ ሐይቅ ትሩፋት

በምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍል ብቸኛ ሀይቅ እንደሆነ የሚነገርለት ሀሮማያ ሀይቅ ላለፉት 17 ዓመታት ደርቆ መቆየቱና አሁን ደግሞ መልሶ ካገገመ ወደ አራት ዓመት እንደሆነው ይታወቃል፡፡ ሀይቁ ወደ ቀድሞ ይዘቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲመለስ ክትትሉና የምርምር ሥራው አሁንም እንደተጠናከረ ነው፡፡ ሀይቁ መልሶ ካገገመ ዓመታትን ቢያስቆጥርም የአካባቢው ነዋሪዎች ግን አሁንም መልሶ ይጠፋል የሚል ስጋት አላቸው ፡፡

ሁልጊዜም እየተመላለሱ ሀይቁን በስስት አይተው ይመለሳሉ፡፡ በጀልባ ለመዝናኛነት ውሎ ጎብኚዎችን እያስተናገደ፣ ከሀይቁ የወጣ አሣ እዛው ተጠብሶ ለጎብኚዎች እየቀረበ ይገኛል፡፡ ይህ ሁኔታ ቢያስደስታቸውም አሁንም ዓይናቸውን ከሃይቁ ላይ እንደማይነቅሉ ነው የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዱት፡፡ሀይቁ ጥቅም ባይሰጣቸውም ውሃውን በዓይናቸው ማየታቸው ብቻውን በቂ እንደሆነ ነው ነዋሪዎቹ የነገሩን፡፡

በነዋሪዎቹ እንዲህ ያለው ስሜት የተፈጠረው፤ ሐሮማያ ሀይቅ በማይገመት ሁኔታ ደርቆ ለ17 ዓመታት መቆየቱ በብዙዎች ዘንድ ድንጋጤን በመፍጠሩ ነው፡፡ የተፈጠረው ነገር አገግሞ መልሶ ሀይቅ ሆኖ ለማየት ተስፋ የሚሰጥም አልነበረም፡፡ ሀይቁ ደርቆ የእግረኛ መንገድና ለከብቶች ግጦሽ እስከመዋል ደርሶ ነበር፡፡አሁን ዳግም ማገገሙ በብዙዎች ዘንድ ግርምትን ፈጥሯል፡፡

አንዳንዶችም ስለሀይቁ መመለስ ስሜታቸውን መቆጣጠር እስኪያቅጣቸው እምባ እየተናነቃቸው ነበር አስተያየት የሰጡን። ነዋሪዎቹ እንዳሉት ሀይቁ ብዙ ነገራቸው ነበር፡፡ ልብሳቸውን ያጥባሉ፣ ንጽህናቸውን ይጠብቁበታል፣ የአሣ ሀብት የሚገኝበት በመሆኑም የኢኮኖሚ ምንጫቸውም ነበር። ላለፉት 17 ዓመታት ያጡት ይሄን ብቻ አልነበረም፡፡

ሀይቁ ዳር ሄደው በመዝናናት የሚያሳልፉት የደስታ ጊዜም ጭምር ነበር፡፡ የአካባቢ ስነምህዳር በመጠበቅ ባለው አስተዋጽኦም ንጹህ አየር አጥተው ቆይተዋል፡፡ የዓይናቸው ማረፊያም በመሆኑ የሀይቁ መድረቅ በአካባቢው ማህበረሰብ ስነ ልቦና ላይ ያሳደረው ተጽእኖ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ተስፋ ቆርጠው አሁን ደግሞ አገግሞ መልሰው ለማየት መቻላቸው ነው በደስታ ሲቃ ስሜታቸውን እንዲገልጹ ያደረጋቸው፡፡

ሀይቁ ሲመለስ የአካባቢው ነዋሪ የደስታ ስሜት ከሚገለጸው በላይ ነበር፡፡ የአካባቢው ነዋሪ አቶ ረመዳን አሊ ሀጂ፤ ሀረማያ ሀይቅ ከመድረቁ በፊት ስለነበረው ይዞታም ሆነ ከደረቀ በኋላም ስለነበረው ጉዳት፣ አሁን ደግሞ መልሶ ሲያገግም በስፍራው ነበሩ፡፡

አቶ ረመዳን፤ በቁጭትና በደስታ ስሜት ውስጥ ሆነው ነበር ሃሳባቸውን ያካፈሉን። በተለይም ሀይቁ ደርቆ በነበረበት ወቅት የተሰማቸውን ከፍተኛ ሀዘን ሲያስታውሱ፤ አሁንም እምባ ይቀድማቸዋል፡፡ ሀይቁ መመለሱ መግለጽ ከሚችሉት በላይ ደስታም ተሰምቷቸዋል፡፡

ሀይቁን አሁን የበለጠ በስስት እንደሚያዩትና ሀይቁን ከብክለት ለመከላከልም በየቀኑ ዙሪያውን በማጽዳት፣ በመንከባከብ በኃላፊነት እየሰሩ እንደሆነም ነግረውናል፡፡ በተለያየ ሥራ በአካባበው ላይ በመንቀሳቀስ ተጠቃሚ የሆኑ ታዳጊዎችንና ወጣቶችን በማስተባበር በጋራ እየተጠቀሙ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ሀይቁ በሚገኝበት ስፍራ ተወልዶ ማደጉን የነገረን ወጣት ፋሲካ ሰለሞንም ሀይቁ ደርቆ በነበረበት ጊዜ እጅግ በጣም አዝኖ እንደነበርና መልሶ ሲያገግምም ደስታው ከሚገልጸው በላይ መሆኑን ይናገራል፡፡ ወጣት ፋሲካ አሁንም መልሶ እንዳይደርቅ ስጋት አለው፡፡ በውስጡ የሚገኘው ቄጠማ መጽዳት እንዳለበትና የሀይቁ የውሃ መጠን እንዲጨምር ገባሮች እንደሚያስፈልጉ አስተያየት ሰጥቷል፡፡

ሀይቁን ለማየት ከቅርብም ከሩቅም ጎብኚዎች ወደ ስፍራው ይመጣሉ፡፡ ከፊሉ በሀይቁ ዳር ሆኖ በእይታ ተዝናንቶ የሚመለስ ሲሆን፤ አንዳንዱም ከሀይቁ ተጠምዶ ወዲያው ተጠብሶ የሚቀርብ አሣን እያጣጣመ፣ ሻይ ቡናም እያለ፣ በሀይቁ ውበት ይደመማል፡፡ በጀልባ በሀይቁ ላይ እየተዝናኑ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ እንግዶችንም አይተናል፡፡ የሀይቁ ማገገም እነዚህን ጥቅሞች ከማስገኘቱ በተጨማሪ የአካባቢ ሥነምህዳር እንዲስተካከል አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ለአካባቢው ተዳጊዎች፣ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል የኢኮኖሚ ምንጭ መሆን ጀምሯል፡፡ በአካባቢው በመለስተኛ አገልግሎት ሻይ ቡና በማቅረብ፣ እንዲሁም የጀልባ አገልግሎት በመስጠት ይጠቀማሉ፡፡ በዚህ ተጠቃሚ የሆኑትም አብዛኞቹ ታዳጊዎችና ወጣቶች ናቸው፡፡

በጀልባ አገልግሎት ሲሰጡ ካገኘናቸው ታዳጊዎች ‹‹እኔ የጀልባ ሾፌር ነኝ›› በማለት እራሱን ያስተዋወቀን ታዳጊ ሐምዛ ፎዚ፤ ስለሀሮማያ ሀይቅ ሲነገር እንጂ ታሪኩን በደንብ እንደማያውቅ ነው የገለጸልን፡፡ አሁን ግን ጥቅም እያገኘበት እንደሆነ ነግሮናል፡፡

ታዳጊው እንደገለጸልን፤ አገልግሎት የሚሰጥበት ጀልባ ባለቤቱ ሌላ ሰው ነው። ባለቤቱ ለሰራበት ክፍያ ያስብለታል፡፡ ክፍያ የሚያገኘውም እንደስራው ሁኔታ ነው፡፡ በቀን የሚያገኘው ሁለት መቶ ብርም ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ በሚያገኘው ክፍያም ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ ተማሪ በመሆኑ ለትምህርት ቤት የሚያስፈልገውን ለማሟላት ቤተሰብ አያስቸግርም፡፡ በራሱ ያሟላል፡፡ ቤተሰቡም በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ በመሆናቸው ከሚያገኘው ክፍያ ይደጉማል፡፡

ታዳጊ ሐምዛ ለጎብኚዎች የጀልባ አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ ከተሰማራ አንድ ዓመት ሆኖታል፡፡ እስካሁንም በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ እንደሆነ ይናገራል፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጠውም ከትምህርት ቤት መልስ በሚኖረው ትርፍ ጊዜ ነው ፡፡ አንዳንድ የእድሜ እኩዮቹ ከትምህርት ቤት መልስ የሚያሳልፉባቸው ቦታዎች ለእድሜያቸው የሚመጥን አይደለም፡፡ በሀይቁ የጀልባ አገልግሎት በመስጠት ማሳለፉ ያልሆነ ቦታ እንዳይውል ጠቅሞታል፡፡ ሥራ ሰርቶ፣ ጥሩ ነገርም አይቶ፣ ገንዘብም አግኝቶ ነው ጊዜውን በአግባቡ እንዲጠቀም አድርጎታል።

ለጉብኝት ከሚመጡት ሰዎች በተጨማሪ ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲና ከተለያዩ ተቋማት በሀይቁ ላይ ሥራ የሚሰሩ ሰዎች በስፍራው እንደሚገኙና ከነዚህ ሰዎች ጋር በመዋሉም አንዳንድ ግንዛቤዎችን ለማግኘት አስችሎታል፡፡ ደስተኛ እንደሆነና ወደፊት የራሱ ጀልባ ኖሮት እራሱን ችሎ እንደሚሰራም ተስፋ አድርጓል፡፡

በሀይቁ ላይ በጀልባ በመሄድ በአካባቢው ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ወደ ስፍራው የሚሄዱት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቢሆኑም፤ በቡድንም በተናጠልም ወደ ስፍራው የሚሄዱ ወጣቶች ይበዛሉ፡፡ በተለየ ሁኔታ ያላቸውን ስሜትም በወቅቱ በስፍራው ያገኘናቸውን ወጣቶች ጠይቀናል፡፡

ካነጋገርናቸው ወጣቶች በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነው ወጣት ባጫ አበራ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ነበር ሐይቁን ለመጎብኘትና በጀልባም ለመዝናናት በስፍራው የተገኙት፡፡ እርሱ እንዳለው ወደ ሀይቁ ሲሄዱ የመጀመሪያቸው ነው፡፡ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ መማር እስኪጀምር ድረስ ስለሀይቁ ታሪክ መረጃው አልነበረውም፡፡ ዝናውን ከሰማ በኋላ ግን ሀይቁን ለማየት ጉጉት አደረበት፡፡ በትምህርቱና በተለያየ ምክንያት ሀይቁን ቶሎ ባያየውም አንድ ቀን እንደሚያየው ግን እርግጠኛ ነበር፡፡ ጊዜው ደርሶ ከጓደኞቹ ጋር ሀይቁን ለመጎብኘት ችሏል፡፡

ወጣት ባጫ በሀይቁ ላይ ስለነበረው ቆይታም እንደተናገረው፤ ጊዜውን ከጓደኞቹ ጋር በጥሩ ሁኔታ አሳልፏል፡፡ በትምህርት ላይ የቆየውን አእምሮውንም ዘና አድርጓል፡፡ እንዲህ አእምሮውን አድሶ ሲመለስ ትምህረቱን በጥሩ አእምሮ ለመቀበል ያስችለዋል፡፡ ስለሀይቁ በሰማው ታሪክም ‹‹ሀይቁ እንደደረቀ ቀርቶ ቢሆን ኖሮ እኔም ጓደኞቼም በዚህ ስፍራ ተገኝተን አንዝናናም ነበር፡፡ ታሪኩንም ለማወቅ እድሉ አይኖረንም ነበር፡፡ ሀይቁ መልሶ ማገገሙ እኛንም ጠቅሞናል›› ሲልም ተናግሯል፡፡

ወጣት ባጫ፤ ሀይቁ ዳግመኛ ለመድረቅ ለስጋት እንዳይጋለጥ መንከባከን ያስፈልጋል፡፡ በሀይቁ አካባቢ ለወጣቶች ስለተፈጠረው የሥራ እድል በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሀሮማያ ሀይቅ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዲኔ ረሽድ እንደገለጹልን ፤ሀይቁ ከተመለሰ ወዲህ ያለበትን ሁኔታ ለማየት ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ ነው፡፡ በዓመትም በአማካይ እስከ 50ሺ ሰዎች ይጎበኙታል፡፡ ወደ ቱሪስት መስህብነት እየተቀየረ ይገኛል፡፡

ይህን ተከትሎም ለአካባቢው ወጣቶች የገቢ ምንጭ መሆን ጀምሯል፡፡ በማህበር ተደራጅተው የተለያየ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ ሀይቁ መልሶ ማገገሙ ለአካባቢው ማህበረሰብ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆን ችሏል፡፡ ምንም እንኳን የዩኒቨርሲቲው ዋና ትኩረት ሀይቁ ዘላቂ በሆነ መልኩ ማቆየት ቢሆንም ሀይቁ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን የአካባቢው አስተዳደር ትኩረት አድርጎ ቢሰራበት ወደፊት ለአካባቢው ነዋሪዎች ሰፊ የሥራ እድል ከመፍጠር በተጨማሪ የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ያግዛል፡፡

አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ ጥቅም እንዲሰጥ ሀይቁን ከጉዳት መጠበቅ ይገባል ያሉት አቶ ዲኔ፤ የሥራ እድል የተፈጠረላቸውም ሆኑ ጎብኚዎች በሀይቁ ላይ ጉዳት የሚያስከትል ነገር እንዳያደርጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠት ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበርም የጽዳት ዘመቻ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ወደ ሀይቁ ቆሻሻ እንዳይገባ ለመከላከል የሚያስችሉ የግንባታ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡

ሀይቁ በአሁኑ ጊዜ ስለሚገኝበትና እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራትም አቶ ዲኔ እንዳብራሩት፤ ለሀይቁ መልሶ ማገገም የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተቀናጀ የሀሮማያ ሀይቅ ተፋሰስ ፕሮጀክት ቀርጾ በደን መመናመን የተራቆቱ አካባቢዎችን በተለይም በሀይቁ ዙሪያ ባሉ ተራራማ አካባቢዎች የዛፍ ችግኞችን በመትከል፣ በአፈርና ጥበቃ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

በዚህ በተከናወኑት ተግባራትም ባለፉት አራት ዓመታት ጥሩ የዝናብ ሽፋን ማግኘት በመቻሉ ለሀይቁ መልሶ ማገገም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። የሀይቁ የውሃ መጠንም ከዓመት ዓመት መሻሻል እያሳየ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዲኔ፣ በየጊዜው ክትትል እንደሚደረግና መረጃም እንደሚሰበሰብ ገልጸዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት የሀይቁ ጥልቀት በአማካይ ወደ አራት ሜትር ሲሆን፣ ዙሪያው ደግሞ ወደ 226 ሄክታር ይሆናል፡፡

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን የካቲት 15/2016

Recommended For You