ውይይቱ የአማራ ክልል ሰላምን ለማጽናት ተጨማሪ አቅም ይሆናል!

የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ የመላው ሕዝባችን መሻት የሆነውን ልማት ለማስፈን ሰፊ ሥራዎችን ሠርቷል። ጠብመንጃ አንስተው የትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ ኃይሎችን ጨምሮ በፖለቲካ እሳቤያቸው ምክንያት ለስደት የተዳረጉ ዜጎች ወደሀገራቸው ገብተው የፖለቲካ ትግላቸውን በሰላማዊ መንገድ ተግባራዊ የሚያደርጉበትን አዲስ የፖለቲካ ባህል ፈጥሯል።

ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በሰላም የመኖር መርህ በተለይም ከኤርትራ ጋር የነበረውን ውጥረት በዚሁ መንፈስ በመቃኘት ለሁለት አስርት ዓመታት ያለ መፍትሔ የቆየውን የኢትዮ- ኤርትራ ችግር በሰላማዊ መንገድ ፤ በወንድማማችነት መንፈስ በመፍታት በቀጣናው የነበረውን የግጭት ስጋት ማስወገድ ችሏል። በዚህም ሰላም ከሀገር ባለፈ ለቀጣናው ሕዝቦች ሰላም ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ በተጨባጭ ማሳየት ችሏል።

ይህም ሆኖ ግን መንግሥት ረጅም ርቀት የሄደበት የሰላም መንገድ ብዙም ሊራመድ አልቻለም። መንግሥት ይዞት የመጣውን አዲስ የፖለቲካ እሳቤና መንገድ ከመጣንበት ኋላቀር የፖለቲካ ባህል / ከአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት በመመዘን የአቅመቢስነት መገለጫ አድርገው የወሰዱ ኃይሎች እንደ ሀገር የተፈጠረውን ይህን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ ሳንጠቀምበት ተመልሰን ወደ ግጭት አዙሪት እንድንገባ አድርገውናል።

በዚህም እንደሀገር የፈለግነውን ልማት ከማስፋት ይልቅ ወዳልተገባ ጦርነት ገብተን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ለስደትና ለመፈናቀል፤ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብትም ለውድመት ተዳርጓል። ይህም እስከ አሁን ባልተሻገርነው ሀገራዊ ስብራት ውስጥ ለመቆየት የተገደድንበት ታሪካዊ ክስተትን ፈጥሯል።

ይህንን ክስተት በመጠቀምም የለውጡ መንፈስና ጉዞ ያልተመቻቸው የውጭና የውስጥ ኃይሎች በመቀናጀት፤ ሀገርን እንደ ሀገር የህልውና ስጋት ውስጥ የከተቱበት ሁኔታ ተፈጥሯል ። ይህንን ስጋት ለመቀልበስ በተደረገው ጥረትም መላው ሕዝባችን ባለው አቅም ሁሉ ክቡር መስዋዕትነት ከፍሏል። በዚህም ሀገርን መታደግ ብቻ ሳይሆን ከአፍራሽ አደጋ መከላከል የሚያስችል አቅም መገንባት ተችሏል።

የሰላም ሐዋርያ ከመሆን ባለፈ፤ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ልማትን አስተማማኝ ለማድረግ የሀገሪቱን የመከላከያ እና የጸጥታ ኃይሎችን አቅም በመገንባት፤ በሁለንተናዊ መንገድ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉበትን ቁመና እንዲላበሱ በስፋት በመሥራት ሀገሪቱን ከህልውና ስጋት አውጥቶ አስተማማኝ በሆነ የህልውና መሠረት ላይ ማቆም ችሏል።

በዚህ ሂደት ውስጥም ለሰላም ካለው ከፍ ያለ መሻት አንጻር፤ በግጭት ወቅቶች ሳይቀር ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት፤ የተደጋገሙ የሰላም ጥሪዎችን በማቅረብ በተጨባጭ አሳይቷል። ከአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ወጥቶ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለዘለቄታው እንዲቋጩ ካለው የጸና እምነት የተነሳም ተነሳሽነቱን ቀድሞ በመውሰድ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እውን እንዲሆን ረጅም መንገድ ተጉዟል።

ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላም የሚያጋጥሙ፤ ስምምነቱን የሚጎዱ ተግባራትን በሆደ ሰፊነት በማለፍ፤ ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ መላው ሕዝባችን ከጦርነት ሊያተርፈው የሚችለው አንዳች ነገር እንደማይኖር በተግባር አሳይቷል፤ እያሳየም ነው።

በተመሳሳይ መልኩ በተሳሳተ እሳቤና ባልተገባ ትርክት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር በውይይት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችሉ የሰላም ጥሪዎችን በማቅረብ፤ ለሰላማዊ ድርድር ዝግጁ መሆኑን በተለያዩ ወቅቶች አስታውቋል።

ለሰላም ካለው የጸና አቋም በመነሳት ከአሸባሪው ሸኔ ጋር በሰላማዊ መንገድ በውይይት ችግሮችን ለመፍታት ከአንድም ሁለት ጊዜ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በተገኙበት ድርድሮችን አድርጓል። በየወቅቱም በተለያዩ መንገዶች ለቡድኑ የሰላም ጥሪዎችን በማድረግ፤ በአካባቢው ሰላም ሰፍኖ ሕዝቦች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያለውን ቁርጠኝነት አሳውቋል።

ይህ የመንግሥት ሰላም ቁርጠኝነት አሁንም የተጠበቀ ስለመሆኑም በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው፤ ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት በግልጽ አስታውቀዋል። ይህ የመንግሥት አቋም መቼም እንደማይለወጥ አመላክተዋል።

መንግሥት ገና ከጅምሩ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ለሕዝቡ የሰላምና ልማት ፍላጎት ተገዥ በመሆን፤ ከጥፋት መንገዳቸው ወጥተው አሉ የሚሏቸውን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በውይይት መፍታት የሚቻልበት የሰላም መንገድ መኖሩን በተደጋጋሚ አስታውቋል። በጉዳዩ ዙሪያ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን ሳይቀር በማሳተፍ በክልሉ ያለው ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሷል።

ሕዝቡ ለሰላምና ለልማት ካለው ፍላጎት የተነሳ በክልሉ በየጊዜው መሻሻሎች ቢኖሩም የአማራ ሕዝብ ከሚፈልገው ልማት አንጻር የሰላም ጉዳይ አሁንም የክልሉ ዋነኛ አጀንዳ ነው። ከዚህ አንጻር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን ከአማራ ክልል ሁሉም ዞን ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይትና ከውይይቱ በኋላ የተደረሰበት ስምምነት በክልሉ የተሻለ ሰላም ለማስፈን ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ይታመናል!

አዲስ ዘመን የካቲት 14/2016

Recommended For You