እኤአ 1871 ቅኝ ገዢ ሀገራት አፍሪካን ለመቀራመት በርሊን ላይ ስምምነት አደረጉ። በስምምነቱ መሰረትም የወቅቱ ቅኝ ገዢዎች የአፍሪካ ሀገራትን ቀስ በቀስ በመዳፋቸው ስር ማድረግ ጀመሩ፡፡ የአፍሪካ ሀገራትም ስር ለሰደደ ጭቆና፤ ባርነት፤ ጉስቁልናና እንግልት ተዳረጉ፡፡
የቅኝ ገዚዎቹ አንዷ አካል የነበረውም የጣሊያን ወራሪ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመግዛት ተነሳ፡፡ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ቀስ በቀስ የወረራ አቅሙን እያጠናከረ በኢትዮጵያ ላይ የበላይነቱን ለማሳየት ሞከረ፡፡ ይህንኑ በተግባር ለመሞከርም የውጫሌ የአማርኛና የጣሊያንኛ ትርጉሙ የተለያየ እንዲሆን በማድረግ በአንቀጽ 17 ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ማንኛውንም ግንኙነት ሲያደርግ በጣሊያን በኩል ይሆናል›› የሚል ሀረግ በመሸንቆር ኢትዮጵያን በመዳፉ ስር ለማድረግ የሚያስችል አንቀጽ አሰፈረ።
የወቅቱ መሪ አጼ ምኒልክ የጣሊያንን ሴራ በመረዳት አንቀጹ እንዲስተካከል ቢወተውቱም ጣሊያን አሻፈረኝ በማለቱ የካቲት 23 ቀን 1988 ዓድዋ ላይ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ገጠሙ። ኢትዮጵያውያንም እስከ አፍንጫው ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን ወራሪ የጣሊያን ኃይልን በሰዓታት ውስጥ ድባቅ መቱት ፡፡ለመጀመሪያ ጊዜም ጥቁር ሕዝብ በነጭ ገዢዎች ላይ የድል አክሊል ተቀዳጀ፡፡ ጥቁሮች ከተባበሩ ማንኛውንም ኃይል ድል መንሳት እንደሚችሉ ለዓለም አበሰሩ፡፡
የታሪክ ምሁራን ዓድዋን ሲገልጹት “የኢትዮጵያውያን አንድነት መገለጫ፣ የመላው ጥቁር ሕዝቦችና የነፃነት ታጋዮች የድል ታሪክ ነው” ይሉታል። የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ መላው አፍሪካውያን ለነፃነታቸው እንዲተጉና አንድነታቸውን እንዲያጠናከሩ መሰረት የሆነ ታላቅ ድል ስለመሆኑም ይናገራሉ። የጥቁር ሕዝቦች የአሸናፊነት ማሳያም ተደርጎም ይወሰዳል-የዓድዋ ድል።
ዓድዋ ለኢትዮጵያውያን የድል በዓል ሲሆን ለጥቁር ሕዝቦች ደግሞ የነጻነት አርማ ሆኖ ዝንተ አለም ያገለግላል፡፡መላው አፍሪካና የካሪቢያን አካባቢ በቅኝ ገዚዎች መዳፍ ስር ወድቆ የባርነት ህይወት በሚመራበት የጨለማ ወቅት ዓድዋ ብርሃን ሆኖ ጭቁን ሕዝቦችን ለነጻነት ታጋድሎ አነሳስቷል፡፡
በ1871 ከተደረገው የበርሊኑ የቅኝ ግዛት ስምምነት ጀምሮም ጥቁር ሕዝቦች ለከፋ የጉልበት ብዝበዛ፤እንግልትና ኢ ሰብአዊ አካኋን ህይወታቸውን ሲገፉ ኖረዋል፡፡ በሰፋፊ እርሻዎች እግሮቻቸው ታስሮ በመንጋ እንደ እንስሳ ሌት ተቀን እንዲሰሩ ተደርገዋል፡፡ በርካቶችም ከአፍሪካና ከካሪቢያን አካባቢዎች እየተወሰዱ ለምዕራባውያን ስልጣኔ ሻማ ሆነው ነደው አልቀዋል፡፡
የአፍሪካ ሀገራትም የሲኦል ተምሳሌቶች ነበሩ። በቅኝ አገዛዝ ጦስ ምክንያት በርካታ አንጡራ ሀብት ወደ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ በገፍ እንዲጓዝ ከመደረጉም በሻገር አፍሪካውያን በገዛ ሀገራቸው የነጮችን የበላይነት አምነው እጅ እንዲነሱ፤እንዲታዘዙና በአጠቃላይም የቅኝ ገዚዎች ንብረት መሆናቸውን እንዲያምኑ በርካታ ተጽዕኖዎች ይደረጉባቸው ነበር፡፡
ሆኖም የቅኝ ግዛትን ቀንበር መሸከም ያቃታቸው ጥቁር ሕዝቦች ከዓድዋ የአይበገሬነትን መንፈስ በመውሰድ ለነጻነታቸው መታገል ጀምሩ። ብዙዎችም በ1960ዎቹ ነጻነታቸውን አወጁ። በምትኩም ዓድዋ ከነጻነት ባሻገርም የፓን አፍሪካኒዝም መነሻ መሰረትም ሆነ። አፍሪካውያንም ወደ አንድነትና ዕድገት እንዲያመሩ መንገዱን የሚጠርገው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም እውን ሆነ፡፡
የዓድዋ ድል ከአፍሪካና ከካሪቢያን ሀገሮች
ባሻገርም በየቦታው ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት የሚሟገቱ ታዋቂ ሰዎችንም አፍርቷል፡፡ እንደ ማርቲን ሉተር የመሳሰሉ ታዋቂ የነጻነት ታጋዮችም በዓድዋ መንፈስ ለነጻነት ታግለው አሸንፈዋል። ታሪካቸውም ዘወተር ከዓድዋ ጋር ተያይዞ ይወሳል።
የዓድዋ ድል በየካቲት የተገኘ የድል እና የነጻነት በዓል በመሆኑም በአሜሪካውያን ዘንድ የየካቲት ወር የጥቁር ሕዝቦች የታሪክ ወር ተብሎ በየዓመቱ ለመዘከር በቅቷል፡፡አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራትም ቀኑን በመዘከር ነጻነታቸውን በማጣጣም ላይ ይገኛሉ፡፡
በአጠቃላይ ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ህልውና የተረጋገጠበት የድልና የነጻነት በዓል ከመሆኑም ባሻገር በቀጣይ የአፍሪካ ሀገራት ለሚመሰርቱት የኢኮኖሚ ውህደት ጉልበት ሆኖ ያገለግላል። ትናንት ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ለነጻነታቸው እንዲታገሉ እንዳነሳሳ ሁሉ ዛሬም የአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ነጻነታቸውን እንዲያውጁ ብርታት ይሆናቸዋል፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሉአላዊነቱ ቀናኢ ነው። በየዘመናቱም ከውስጥና ከውጭ የተቃጡ ሉአላዊነትንና የግዛት አንድነትን የሚፈታተኑ ተግባራትን በጽኑ ታግሎ ሀገሪቱን ከነሙሉ ክብሯ ለአሁኑ ትውልድ አስረክቧል፡፡
ከጥንት እስከ ዛሬ የቅርብ እና የሩቅ ጠላቶች ከሀገር ውስጥ ባንዳዎች ጋር ተባብረው ኢትዮጵያን ለመበታተን መሄድ እስከሚችሉት ድረስ ተጉዘዋል። ሆኖም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገሩ ዳር ድንበር የሚዋደቅ፤ ከራሱ በፊት ሀገሩን የሚያስቀድም፤ቀኝ ገዢዎችንና ሌሎች ወራሪ ኃይላትን አሳፍሮ የሚመለስ ጀግና ሕዝብ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሀገራት ነጻነትና እኩልነት የሚታገሉ፤በአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የሆኑ ኩሩ ሕዝቦች ናቸው። ይህም ጀግንነትና አይበገሬነት በተባበሩት መንግሥታት ጭምር እውቅና አግኝቶ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን በሩዋንዳ፤ በቡርንዲ፤በላይቤረያና በሶማሊያ ተሰማርቶ ጀግንነቱን አስምስክሯል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ እስከ ማይጨው፤ዶጋሊና ሶማሊያ ወረራ ድረስ ህይወታቸውን በመገበር፤ደማቸውን በማፍሰስ እና አጥንታቸውን በመከስከስ በመስዋዕትነት ሀገራቸውን አጽንተዋል፡፡ታሪክም ሰርተዋል፡፡
ይህስ ትውልድ ምን ይመስላል፡፡ለታሪክ እየሰራ ነው ወይስ ታሪክ እየዘከረ መኖር መርጧል። የአባቶቻችን ታሪክ ሁልጊዜም ቢነሳና ቢዘከር እንኳን ለእኛ ለመላው ሕዝብ በሙሉ የሚሰለች አይደለም። ሆኖም ትውልዱ ይህንን ታሪክ ብቻ በማወደስ መጠመድ የለበትም፡፡የራሱን ታሪክ መጻፍ መጀመር አለበት፡፡ታሪክ አውሪ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ሰሪም ሊሆን ይገባል፡፡
ሀገር የምትቀጥለው በትናንት ታሪክ ብቻ ሳይሆን በዛሬም ተግባራዊ ሥራ ነው፡፡ ዛሬ ካልተሠራ ነገን ማየት አይቻለም፡፡ወይንም ዛሬ ያላስቀመጡት ነገ ታሪክ አይሆንም፡፡ ትናንት አባቶቻችን የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር በዱር በገደሉ አጥንታቸውን ከስክሰዋል፤ደማቸውን አፈረስሰዋል፤ህይወታቸውን ሰጥዋል፡፡ ምናልባት የዛሬው ትውልድ ይህ የሕይወት መስዋዕትነት መክፈል ላያስፈልገው ይቻላል፡፡
የዛሬው ትውልድ መሆን ያለበት የሰላም አርበኛ መሆን ብቻ ነው፡፡ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለግዛት አንድነት የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች ውለታ የሚመለሰው የሰላምና የልማት አርበኛ መሆን ስንችል ነው፡፡ በተለይም ሰላም ለራቃት ሀገራችን የሰላም አምባሳደር በመሆን የአባቶቻችንን መስዋዕትነት ከንቱ እንዳይሆን የበኩላችንን ጥረት ልናደርግ ይገባል፡፡ የግጭት፣የጦርነት፣ያለመግባባት ታሪካችን ተዘግቶ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የምንግባባ፤ለጋራ ሀገራችን የምንተጋ፣ ለልጆቻችንም የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማውረስ የጋራ ዕሳቤ የጨበጥን አዲስ ትውልድ መሆን ይገባናል፡፡
ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በምክክርና በመግባባት ነው፡፡ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባትም እንደሀገር የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ አንድ አመት ከስድስት ወራት አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም ምክክሩ የሚመራበትን አቅጣጫ ከመቀየስ ጀምሮ የሌለችን ሀገራት ተሞክሮዎችን የመቀመርና በምክክሩ የሚሳተፉ ሰዎችን የመለየት ስራዎች ተከናውነዋል።በቀጣይም የምክክሩን አጀንዳዎችን ከህብረተሰቡ የመቀበልና ምክክሩን ወደ መሬት የማውረድ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡
ስለሆነም ሀገራዊ ምክክሩ የቀድሞ ችግሮቻችን፤ አሁን ያሉት ችግሮቻችን መፍቻና በቀጣይም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳያጋጥሙን የመፍትሄ አቅጣጫን የሚጠቁመን መድህን መሆኑን ማመን ይጠበቅብናል፡፡ በሀገሪቱም መተማመን የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት ለመመስረትም እርሾ ሆኖ እንደሚያግዝ እምነት መጣል አለብን፡፡
በቅድሚያ ሁሉም ነገር በንግግር እና በምክክር ይፈታል የሚል እምነት ማዳበር ይጠበቅብናል፡፡ ወሰንም ሆነ የማንነት ጥያቄ እንዲሁም ራስን በራስ ማስተዳደር እና የፍትህ ጥያቄዎች በአጠቃላይ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በሙሉ በሀገራዊ ምክክር ሊፈቱ የማይችሉበት ምክንያት አይኖርም፡፡
አሁን ያሉት አለመግባባቶች ተወግደው በፍቃደኝነት እና በመግባባት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ምክክሩ የማይተካ ሚና አለው፡፡ሀገራዊ ምክክሩ ከዘመን ወደ ዘመን ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታትና የመወያየትና የመነጋገር ባህልንም ለማዳበር ይረዳል። በመወቃቀስ ላይ የሚያተኩረውንም የፖለቲካ ባህላችንንም ወደ መነጋገር፤መተባበርና መደጋገፍ እንዲመጣ ያደርጋል፡፡
ስለዚህም ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን በርካታ ችግሮችን አስከትሎብናል፡፡ ከመነጋገር ይልቅ በር ዘግቶ መወቃቀስና አልፎ ተርፎም ነፍጥ እስከማንሳትና መገዳደል ድረስ አድርሶናል፡፡አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ግጭት፤ጦርነትና መወነጃጀል ሳይሆን ውይይትና ምክክር ብቻ ነው።
ስለዚህም ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልም እንደሀገር ሊጎለብት ይገባል፡፡ የስልጣኔም አንዱ መለኪያም ይኸው ነውና፡፡ በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ወገኖች፣ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት ሀገር ናት፡፡ የሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው፡፡ ጽንፍ ለጽንፍ ሆኖ ቃላት መወራወርና ይዋጣላን ማለት እንደሀገር ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ በዚህም መንገድ ለዘመናት ተጉዘን ያተረፍነው ድህነትን፤ኋላቀርነትና ዕልቂትን ብቻ ነው።
ስለሆነም የታሪካችን አንዱ ክፋይ ሆኖ ዘመናትን የተሻገረውን ጦርነትና ግጭትን ለማስወገድና የተረጋጋች፤ ሰላሟ የተጠበቀ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማውረስ ሀገራዊ ምክክሩ ይዞ የመጣውን ዕድል ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን በአባቶቻችንና እናቶቻችን ተጋድሎ ያገኘነው ኩራትና ነጻነታችን ሙሉ እንዲሆን ሀገሪቱን በልማት ማበልጸግ ያስፈልጋል። ይህ ትውልድ ታላቁን የዓባይ ግድብ ሰርቶ እያገባደደ ነው፡፡ ይህን የሀገር ኩራት የሆነ ግድብ አጠናቆ ለሀገር ብሎም ለአፍሪካ ብርሃን ማጎናጸፍ የዚህ ትውልድ አንዱ አደራ ነው፡፡
በግብርና ልማት በተለይም በስንዴ የተገኘውን አኩሪ እንቅስቃሴ ዘላቂ ማድረግና ከኢትዮጵያም አልፎ አፍሪካን መመገብ ሌላው የዚህ ትውልድ አሻራ ሊሆን ይገባል፡፡ በርካታ የውጭ ኃይላት ኢትዮጵያ ስንዴ ማምረቷ ከተጽዕኖና ከተንበርካኪነት እንድተወጣና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ፈለጓን ይከተላሉ በሚል ስጋት ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ሲፈጥሩ ቆይተዋል፡፡ሆኖም ጫናዎችን መቋቋም በመቻሉ ዛሬ ኢትዮጵያ በስንዴ ዘርፍ ባሳየችው ውጤታማነት በዓለም መድረክ ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች፡፡
አረንጓዴ አሻራ በማኖር ረገድ ኢትዮጵያውን ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ ታሪክ በመጻፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ አኩሪ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት የማይወዱ አካላት ሊያጣጥሉት ቢሞክሩም ተግባሩ የሚደበቅ አይደለምና ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው መድረኮች ሁሉ በውጤታማነቱ እየተወሳ ይገኛል፡፡ ስለዚህም ትውልዱ ይህንን አንፀበራቂ እንቅስቃሴ ከዳር ማድረስና ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን አረንጓዴ ማልበስ ቀጣይ የቤት ስራው ሊሆን ይገባል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል የሀገርን ዳር ድንበር አላስደፍርም በማለት ደማቸውን በማፍሰስ፤አጥንታቸውን በመከስከስ ውድ ህይወታቸውን መስዋዕት ሲያደርጉ ኖረዋል። የአሁኑ ትውልድም የሀገሩን ዳርድንበርና ሉአላዊነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን በሰላም እና በልማቱም መስክ ሀገሪቱን ወደ ፊት ሊያራምዱ የሚያስችሉ ተግባራትን በመፈጸም መስዋዕት የከፈሉ ቀደምት አባቶቻችንን ፈለግ ሊከተል ይገባል፡፡
አሊሴሮ
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2016