አረንጓዴ ወርቅ የተባለው ቡና የኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት ነው:: በመሆኑም የቡናውን ዘርፍ የሚመራው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ሀብቱን ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲሁም ሀገር ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል:: በዚህም አበረታች የሆኑ ለውጦች ተመዝግበዋል:: ለአብነትም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሀገሪቷ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ከዘርፉ ማግኘት ችላለች:: ለዚህ ውጤትም ባለስልጣኑ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የምርት ጥራትን በማስጠበቅና የኢትዮጵያ ቡናን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ የተሻለ ገቢን ለሀገር ለማምጣት ከሚያከውናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው::
ባለስልጣኑ እነዚህን ሥራዎች ከመሥራት ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ለማስተዋወቅ የተለያዩ ጥረቶችን ያደርጋል:: ከሰሞኑም የመጀመሪያው የአፍሪካ ቡና ሳምንት እና 20ኛው የአፍሪካ ባለልዩ ጣዕም የቡናዎች ማህበር ጉባኤና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል:: ጉባኤውና ኤግዚቢሽኑን በጋራ በመሆን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ የአፍሪካ ባለልዩ ጣዕም ቡናዎች ማህበር /AFCA/ እንዲሁም ኢንተር አፍሪካ ኮፊ ኦርጋናይዜሽን /IACO/ ናቸው።
ለአራት ቀናት በተካሄደው ጉባዔ እና ኤግዚቢሽን ዓለም አቀፍ ቡና ገዥዎች፣ ቡና የሚቆሉ፣ ቡና አምራቾች፣ አልሚዎች፣ ላኪዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የክልልና የፌዴራል መ/ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች፣ የምርምር ተቋማት እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ከ1000 የሚልቁ እንግዶች ተሳትፈዋል::
መድረኩ ቡና አምራቹንና ቡናን በጥሬው እንዲሁም እሴት ጨምረው ከሚልኩ ላኪዎችና ዓለም አቀፍ ቡና ገዢ የሆኑ ሀገራትን በአንድ ያገናኘ መድረክ ነው:: በመድረኩ በርካታ ሁነቶች ተከናውነዋል:: ከእነዚህም መካከል ቡና አምራችና ቡና ላኪ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል:: ለዕይታ የቀረቡት የተለያዩ የቡና አይነቶችም በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ እንግዶች ተጎብኝተዋል፤ ተቀምሰዋል:: በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት እንዲሁም የቡናውን ዘርፍ ከፍ ወዳለ ደረጃ ሊያሳድጉ የሚችሉ የፓናል ውይይቶችም እንዲሁ ከተከናወኑ ሁነቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው::
አቶ ግዛት ወርቁ የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅና የአፍሪካ ፋይን ኮፊ አሶሴሽን የኢትዮጵያ ቻፕተር ቼር ማን ናቸው:: 20ኛው የአፍሪካ ፋይን ኮፊ አሶሴሽን ኤግዚቢሽንና ኮንፈረንስ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣንን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት አካላት ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር እንደሆነ ያስረዳሉ:: የኤግዚቢሽንና ኮንፈረንሱ ዓላማም የኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሆነ ነው ያመላከቱት::
እሳቸው እንዳሉት፤ በኤግዚቢሽንና ኮንፈረንሱ ቡና ሻጩና ቡና ገዢው የሚገናኝበት መድረክ እንደመሆኑ 120 የሚደርሱ በቡና ሥራ የተሰማሩ ድርጅቶች በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ቦታ ተከራይተው እራሳቸውን አስተዋውቀዋል:: ከ900 ሰው በላይ ደግሞ ከተለያዩ የዓለም አገራት ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከኤዢያና ከአፍሪካ አገራት ወደ ኢትዮጵያ ተሰባስበዋል:: ኤግዚቢሽንና ኮንፈረንሱ ቡና ሻጭና ገዢን ከማገናኘት ባለፈ የቡናውን ሽያጭና ግዢ የሚያበረታቱ መረጃዎች ተላልፈዋል:: ስለ ቡና የቀረቡት መረጃዎችም በፓናል ውይይቶችና በጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ናቸው::
አገሪቷ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሪ አንድ ሶስተኛውን የሚሸፍነው ቡና መሆኑን የገለጹት አቶ ግዛት፤ የመድረኩ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ለሚገኙ ቡና ገዢዎች ማስተዋወቅ እንደሆነ ያስረዳሉ:: ከመላው ዓለም ለመጡ ቡና ገዢዎች የኢትዮጵያንም ሆነ ከሌሎች አፍሪካ አገራት የመጡ ቡና አምራቾችን ቡና ማስተዋወቅ፣ መሸጥና ገዢዎችም ስለ ቡና አውቀውና ተረድተው መግዛት እንዲችሉ ማድረግ ነው::
ማንኛውም ሽያጭ የአንድ ቀን ሥራ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ቀጣይነት ያለው የገበያ ትስስር በመፍጠር አዳዲስ ቡና ገዢዎችን ማግኘት እንደሚቻል አንስተዋል:: እንደዚህ አይነት ኤግዚቢሽኖች ቡና ለመግዛትም ሆነ ለመሸጥ የተመቹ በመሆናቸው ነባር ገዥና ሻጮች እንዳሉ ሆነው አዳዲስ ገዢዎች ከአዳዲስ ሻጮች ጋር ተገናኝተው ግብይት መፈጸም እንደቻሉና ቀጣይነት ያለው ትስስር መፍጠር እንደቻሉ ነው ያመላከቱት::
የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ዋና ሥራው የኢትዮጵያን ቡና ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሆነ ያነሱት አቶ ግዛት፤ ከዚህ ባለፈም የማስተማርና ለአባላት መረጃ የመስጠት ሥራ ይሠራል በማለት አስረድተዋል:: በተለይም የኢትዮጵያን ቡና በማስተዋወቅ ረገድ እየተሠራ ያለው ሥራ የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ሲገልጹ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ቡና ሽያጭ ወደ ቢሊዮን ዶላሮች ከፍ ብሏል ነው ያሉት:: ይህ ማለት አሁን አገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የተሻለ እንቅስቃሴ እያሳየ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ግዛት፤ በዘርፉ እየታየ ያለው ለውጥ እንደዚህ አይነት የማስተዋወቅ ሥራዎችና ኤግዚቢሽኖች እንዲሁም ኮንፈረንሶች ያመጡት ውጤት እንደሆነ ነው የሚያምኑት::
የቡና ዘርፍ ትልቅ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው በዕውቀት መመራት እንዳለበት ሲያነሱ፤ በተለይም ዘርፉን ለመምራት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና ህጎች እንዲሁም ማበረታቻዎች ሲወጡ ኤክስፖርቱንና እርሻውን ሊያግዙና ገበሬው ሊጠቀምባቸው የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው ያስረዳሉ:: በተለይም ለግብይቱ ቀልጣፋነት በክልሎችና በፌዴራል መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ፣ ነጻና ግልጽ መሆን እንዳለበትና ተገቢ እንደሆነ ያምናሉ:: በዚህም ቡና በቀላሉ ወደ ውጭ ገበያ ወጥቶ መሸጥ እንዳለበትና ይህም ለሀገሪቱ ጥቅም የላቀ ድርሻ ማበርከት የሚችል በመሆኑ ቀጣይነት ያለው ሥራ ሊሠራ ይገባል ብለዋል::
በቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር፤ የአፍሪካ ቡና ሳምንት በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው ሁነት የቡና መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ መካሄዱ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከልም አንዱና ቡናን የሚያስተዋውቅበት መንገድ እንደሆነ ገልጸዋል:: ባለስልጣኑ ከሚሰራቸው ሥራዎች መካከል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የምርት ጥራትን ማስጠበቅና ቡናውን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት በዋናነት ከሚጠቀሱ ተግባራት መካከል ናቸው::
እነዚህን ተገባራት ከማከናወን አንጻር ሁነቱ በተለይም የኢትዮጵያ ቡናን ለማስተዋወቅና ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ሲያስረዱ፤ ገበያውን በሚመለከት ባለስልጣኑ ነባር ገበያ ውስጥ የመቆየትና አዳዲስ ገበያዎችን የማፈላለግ ስትራቴጂ ነድፎ እየሠራ ነው:: ስለዚህ በርካታ አፍሪካ አገራትና ሌሎች ቡና ገዢ አገራት ሁነቱ ላይ የተገኙ በመሆናቸው የኢትጵያ ቡናን ለማስተዋወቅና ለመሸጥ ትልቅ ዕድል ተፈጥሯል:: በቡና ሳምንት ሁነት ላይ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቡና አይነቶችን ማቅረብ ተችሏል:: በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቡና አይነቶችን የተለያየ ጣዕም ያላቸው በመሆኑ ይህን ማሳየት ተችሏል::
የቡና አይነቶችን በጣዕም በጥራትና በአይነት መለየት እንዲችሉ የተደረገበት ሁነት ስለመሆኑ ያነሱት አቶ ሻፊ፤ በተለይም የኢትዮጵያ ቡና ልዩ የተፈጥሮ ጣዕምና ጥራት ያለው ቡና መሆኑን የተረዱበት ሁነት ስለመሆኑም ተናግረዋል:: ይህን ዕውነትም በኤግዚቢሽንና ባዛር ቡና ላኪዎች ባቀረቡት የቡና አይነት መረዳት ተችሏል:: ከዚህም ባለፈ በተለያዩ ቡና አምራች በሆኑ የኢትጵያ አካባቢዎች ማለትም ሀዋሳና ጅማ ጉብኝት በማድረግ የኢትዮጵያ ቡና እንዴት እየተመረተ ነው፤ አርሶ አደሩ ቡናን እንዴት እያመረተ ነው፤ ቡናውስ ምን ይመስላል፤ በተለይም ጫካ ቡና ምን ይመስላል በምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚሉትንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በሚገባ መረዳት እንዲችሉና የኢትዮጵያ ቡናን እንዲገዙ ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት::
‹‹አፍሪካ ሀገራት ብዙ ቡና አይጠጡም›› ያሉት አቶ ሻፊ፤ አብዛኞቹ አፍሪካ ሀገራት ቡና የሚጠጡ አለመሆናቸውን አንስተው ይሁን እንጂ፤ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የኢትዮጵያ ቡና የመጠጣት ባህል ምን ይመስላል በሚል ልምድ የወሰዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል:: በተለይም በአሁን ወቅት በተለያዩ አፍሪካ አገራት ቡና እየተለመደ መጥቷል ያሉት አቶ ሻፊ፤ አሁን ላይ የተቆላ ቡና ተፈጭቶ ወደ አፍሪካ ሀገራት የመላክ እንቅስቃሴ የተጀመረ መሆኑን አስረድተዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም ወደ ሞሮኮ አልጄሪያና ሌሎች ሀገራትም ይላኩ የነበረ ሲሆን፤ አሁንም በተለይም ተቆልቶ የተፈጨ ቡናን በስፋት ወደ አፍሪካ አገራት ለመላክ እየተሠራ ነው:: ለዚህም የተለያዩ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች አስፈላጊ እንደሆኑ ነው ያስረዱት:: ይህን መሰል ኤግዚቢሽንና ሁነት የአገሪቱን ቡና ለማስተዋወቅና ለመሸጥ ትልቅ ዕድል እንደመሆኑ ይህንኑ ዕድል በመጠቀም ወደፊት የኢትዮጵያ ቡናን በዓለም ገበያ የማስተዋወቅና በስፋት የመሸጥ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አመላክተዋል::
ገበያ ማለት በሰዎች አስተሳሰብ ውስጥ የሚፈጠረው ስሜት እንደሆነ ያነሱት አቶ ሻፊ፤ በሁነቱ የተሳተፉ የውጭ ገዢዎች የኢትዮጵያ ቡናን የማወቅና የመረዳት አጋጣሚን ፈጥሮላቸዋል:: በዚህም የኢትዮጵያ ቡና ከሌሎች ሀገራት ቡና የተለየ መሆኑን እና በተለየ መንገድ የሚመረት እንደሆነ እንዲሁም የተለየ ጣዕም ያለው መሆኑን መረዳት ችለዋል:: ለዚህ ውጤትም በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል:: እያንዳንዱ ቡና ላኪ ሁነቱ በተዘጋጀበት ሚሊኒየም አዳራሽ በመገኘት ቦታ ተከራይቶ ቡናውን አስተዋውቋል:: የገበያ ትስስርም መፍጠር ችሏል:: ከቡና ላኪዎች በተጨማሪም ዩኒየኖች፣ ማህበራትና አርሶ አደሮች በተገኙበት የኢትዮጵያ ቡና መተዋወቅና መሸጥ ችሏል::
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣና በቡና ግብይቱ ከሚሊዮን ወደ ቢሊዮን መግባቱን ያነሱት አቶ ሻፊ፤ ካቻምና አንድ ነጥብ አራት ሁለት አራት ቢሊዮን ዶላር መገኘቱንና ባለፈው ዓመትም ከአንድ ነጥብ ሶስት አንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን አስታውሰው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ አንድ ነጥብ ሰባት አምስት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል:: በስድስት ወራት አፈጻጸምም የተሻለ ገቢ ማግኘት የተቻለ ሲሆን፤ ይህን ዕቅድ ለማሳካትም ነባር ገበያ ውስጥ መቆየትና አዳዲስ ገበያዎች ውስጥ ለመግባት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነና ኤግዚቢሽንና ባዛሩም ለዚህ ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል::
የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ በተለይም አውሮፓ ሀገራት እና አሜሪካ ላይ ሰፊ ድርሻ የነበረውና የቆየ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሻፊ፤ በአሁን ወቅት ከአዳዲስ ገበያዎች መካከል ወደ ኤዥያን ገበያዎች ማለትም ቻይና፣ ታይዋን፣ ኮሪያና አውስትራሊያ የመሳሰሉት ሀገራት ላይ በስፋት እየገባ ነው ብለዋል::
የአፍሪካ የቡና ሳምንት ጉባኤና ኤግዚቢሽን በዘርፉ ያሉ ተዋንያኖችን ቅንጅት ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለው የጠቀሱት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው፤ ባለስልጣኑ የቡና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እንዲሁም ቡናን በጥራት ለማምረትና የተሻለ ገበያ እንዲያገኝ ብርቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው በተለይም ከአርሶ አደሩና በዘርፉ ካሉ ተዋንያኖች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ሲያስረዱ፤
በተለይም ይህን መሰል አህጉራዊ ሁነት በኢትዮጵያ መካሄዱ ኢትዮጵያ በመስኩ ያላትን አቅም ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን በመጥቀስ ነው:: ከዚህም በላይ በአፍሪካ የቡና ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ተዋንያኖችን የበለጠ የሚያቀራርብ የልምድ ልውውጥ መድረክ መሆኑን ተናግረው ፤ከዚህ አንጻር አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚተዳደርበት ቡና በዕውቀት ለመምራት በርካታ ሥራዎች ይቀራሉ ብለዋል::
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ የቡና ኢንዱስትሪ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ቢኖሩም አሁንም አንዳንድ ችግሮች መስተዋላቸውን ሲገልጹ፤ የተለያዩ የቡና በሽታዎች፣ የዝናብ እጥረት፣ የዓለም የቡና ገበያ በየጊዜው መለዋወጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን አስረድተው እነዚህን ችግሮች በጋራ ለማለፍ በትብብር መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። ኢትዮጵያም በአፍሪካ በቡናው ኢንዱስትሪ መስክ የሚገጥሙ ችግሮችን በትብብር ለማስወገድ በሚደረገው አህጉራዊ ጥረት የድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2016