በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መገፋፋት ለችግር የተጋለጡ አርሶ አደሮች

የዛሬው የምርመራ ዘገባችን በቀድሞው የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በአሁኑ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሸካ ዞን የኪ ወረዳ የተፈጠረን አንድ ውዝግብ ያስመለክተናል::

በዚህ ወረዳ ጻኑ፣ ዳርሙ ፣ ሰላም ሰፈር እና በቆ ልማት በተሰኙ አራት ቀበሌዎች የሚኖሩ ከ250 በላይ አርሶ አደሮች ከ10 ጋሻ በላይ የሚሆን በቡና ፣ በዝንጅብል ፣ በእርድ፣ በእንሰት፣ በአገዳ እና መሰል የተለያዩ ፍራፍሬዎች ተሸፍኖ የነበረ ማሳችን ከ36 አመታት በፊት በዶዘር እንዲወድም መደረጉን ፤ የደረሰባቸውን በደል ለተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በየወቅቱ ቢያሳውቁም ለችግራችን መፍትሔ የሚሰጠን አካል ማግኘት ሳይችሉ ለዓመታት ለከፋ ርሀብ እና ለተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች መጋለጣቸውን በመመልከት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደን» ሲሉ የአራቱ ቀበሌ አርሶ አደሮች በተወካያቸው በኩል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ክፍል አቤት ብለዋል::

የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራና ቀኙን አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ ዝግጅት ክፍሉ ተፈጠረ ስለተባለው የመልካም አስተዳደር ችግር ከባለጉዳዮችና እና ሰነድ ያገኛቸውን ማስረጃዎች በጥልቀት መርምሯል:: ከጉዳዩ ስፋት አንጻር የምርመራ ዘገባውን በሁለት ክፍሎች ለአንባቢን ለማድረስ ተገደናል:: በክፍል አንድ በአርሶ አደሮች የቀረቡ መረጃዎችን እና ከሰነዶች ያገኘናቸውን መስረጃዎችን እዲህ ሸክፈናቸዋል:: መልካም ምንባብ::

ከአቤቱታ አቅራቢው አንደበት

በደል ተፈጽሞብናል ያሉት አርሶ አደሮች አቤቱታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ያቀረቡት በተወካያቸው አቶ ሀሰን ሙሔ በኩል ነው:: እንደ አቶ ሀሰን ሙሔ ገለጻ፤ በ1980 ዓ.ም ማለትም በደርግ ዘመነ መንግሥት በየኪ ወረዳ ሥር በሚገኙ ጻኑ፣ ዳርሙ ፣ ሰላም ሰፈር እና በቆ ልማት በተሰኙ አራት ቀበሌዎች ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች በፈጸሙት ሰብአዊነት በጎደለው ተግባር የ250 አርሶ አደሮች ይዞታ የነበረ እና በቡና ፣ በዝንጅብል፣ በእርድ ፣ በእንሰት፣ በአገዳ እና መሰል የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ሲያመርቱበት የነበረ ከ10 ጋሻ በላይ ማሳ በመንጠቅ ያለምንም የካሳ ከፍያ እንዲፈናቀሉ ተደርጓል::

አቶ ሀሰን ስለተፈጠረው ክስተት ሲያብራሩም፤ በቀን 04/13/ 1980ዓ.ም በየኪ ወረዳ ሥር የሚገኙ የአራት ቀበሌ አርሶ አደሮች ከእቅልፋቸው ሲነቁ ለቤተሰባቸው ህይወት እና አጠቃላይ ኑሯቸው ሁሉነገራቸው የሆነውን በቡና፣ በዝንጅብል፣ በእርድ፣ በእንሰት፣ በአገዳ እና መሰል ምርቶች የተሞላውን ከ10 ጋሻ በላይ ማሳቸው ከ50 በላይ በሆኑ ዶዘሮች ሲታረስ ተመለከቱ:: አይናቸውን ማምን አልቻልንም::

በተመለከቱት ነገር ግራ የተጋቡት አርሶ አደሮች ‹‹አንተ ማን ነህ? ለምን የቤታችንን ምሰሶ የሆነውን ማሳችንን ታርሳለህ?›› ሲሉ መጠየቃቸውን ይናገራሉ:: ይሁን እንጂ ማሳቸውን በዶዘር እያወደመ የነበረው አካል ምንም አይነት መልስ ሊሰጣቸው አልቻለም:: ይህን ተከትሎ አርሶ አደሮችም ስለጉዳዩ ለማስረዳት በዶዘር የተነቀለ ቡናቸውን በመያዝ ወደ ቴፒ ወረዳ አስተዳደር እና የግብርና ቢሮ በመሄድ አቤት አሉ::

የቴፒ ከተማ የኪ ወረዳ አስተዳደር እና የግብርና ቢሮ በቦታው ተገኝተው ሁኔታውን ተመለከቱ:: የአርሶ አደሮች ማሳ በዚህ መልኩ በዶዘር ከጥቅም ውጭ ያደረገው አካል ማን ነው ? ለምድን ነው ? የሚለውን ለማጣራት ሞከሩ:: ባደረጉት የማጣራት ሂደት የአርሶ አደሮችን ማሳ በዶዘር ከጥቅም ውጪ ያደረገው አካል የቴፒ ቡና ተክል ፕሮጀክት መሆኑን አረጋገጡ:: ይሁን እንጂ አቤቱታ የቀረበላቸው ተቋማት ስለጉዳዩ እንደማያውቁ እና የተፈጸመው ተግባርም ህገ ወጥ እና ትክክል አለመሆኑን ለህዝቡ አስረዱ :: ይህ በእንዲህ እንዳለ ድርጊቱን የፈጸመው የቴፒ የቡና ተክል ፕሮጀክት ኃላፊ ተይዞ እንዲቀርብ እና ስለጉዳዩ እንዲያብራራ ተጠየቀ::

ከጥቂት ቀናት በኃላ ቦታው ለቡና እርሻ ልማት እንደተፈለገ ለአርሶ አደሮች በቃል ተነገራቸው:: ይህን ተከትሎ “በቦታው እኛስ የምናመርተው ቡና ሆኖ እያለ ባለማነው ማሳ ላይ ለምን ለሌላ አካል ቡና እንዲያለማበት ይሰጣል?” ብለው ጠየቁ:: ነገር ግን ለጥያቄያቸው ምላሽ የሚሰጥ አካል አለመገኘቱን አቶ ሀሰን ያስረዳሉ:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉዳዩ በወረዳ ምክር ቤት እንዲሁም በቀበሌ አስተዳደር እንዲታይ ተደረገ:: በዚህም የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸው፤ ምትክ ቦታ እስከሚሰጣቸው ድረስ ለቀለብ የሚሆን እህል የቴፒ የቡና አትክልት ፕሮጀክት እንዲሰፍርላቸው ስምምነት ላይ ተደረሰ:: ጉዳዩ የሚመለከተቻው አካላት በገመቱት የካሳ ተመን መሰረት ለአርሶ አደሮቹ እንዲከፍል መወሰኑን አቤቱታ አቅራቢው ያስረዳሉ::

ቀለብ ይሰፈርላቸው በተባለው መሰረት የቤተሰብ ቁጥርን መሰረት በማድረግ የቴፒ የቡና ተክል ፕሮጀክት ለአርሶ አደሮች ቀለብ መግዣ የሚሆን ገንዘብ ሰጠ የሚሉት አቶ ሀሰን ፤ ቤተሰብ ለሌለው አርሶ አደር ከ20ብር ጀምሮ የተሰጠው ሲሆን ቤተሰብ ያለው ድግሞ 3ሺ 50 ብር ድረስ መሰጠቱን ይናገራሉ:: ለአብነት ያህል አቶ ሀሰን በወቅቱ ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት ስለነበሩ የ50 ኪሎ በቆሎ መግዣ ግምት 103 ብር ተሰጣቸው:: ይህም ለአንድ ወር ብቻ የቀጠለ እንደነበር ያስረዳሉ::

የመሬታቸውን ካሳ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ እያሉ ለህብረተሰቡ ይሰጥ የነበረው ቀለብ ለአንድ ወር ብቻ ተሰጥቶ ቆመ:: ይህን ተከትሎ ‹‹ለቀለብ የሚሰጠን ገንዘብ ስለምን እንዲቆም ተደረገ? ቤተሰቦቻችንን የምናስተዳድርበት የለማ ማሳ በማን አለብኝነት በዶዘር ተጭፍጭፎ እያለ እንዴት የዕለት ምግብ እንኳን እንከለከላለን?›› ሲሉ የወረዳ መስተዳድሩን መጠየቃቸውን ይናገራሉ:: የወረዳ መስተዳድሩም የአርሶ አደሮችን ማሳ የጨፈጨውን የቴፒ የቡና ተክል ፕሮጀክት ስለጉዳዩ እንዲያብራራ ጠየቀ:: የቴፒ የቡና ተክል ፕሮጀክትም ከ20 ብር ጀምሮ ለአርሶአደሮች የሰጠው ገንዘብ የአንድ ወር የአርሶ አደሮች ቀለብ ሳይሆን አጠቃላይ የመሬቱት ካሳ ነው የሚል ምላሸ ሰጠ:: የወረዳ መስተዳድሩም ለቀለብ ተብሎ ለአንድ ወር ተቆራጭ የተደረገው ገንዘብ የማሳቸው ካሳ መሆኑ ለአርሶ አደሮች ተነገራቸው::

ይህን ተከትሎ የቴፒ የቡና ተክል ፕሮጀክት ማሳቸውን በዶዘር ገብቶ ሲያወድም እውቅናው እንደሌላቸው ፤ ካወደመው በኋላም ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት የካሳ ግምት ያልወጣለት መሆኑን የኪ ወረዳ መስተዳድርን በአካል ተገኝተው ተከራከሩ:: የወረዳ መስተዳድሩም ጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት እየሰራ እያለ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ተደረገ:: የአርሶ አደሮች ችግር ሳይፈታ በይደር መቅረቱን አቶ ሀሰን ያስረዳሉ::

የደርግ መንግሥት ወድቆ ኢህአዴግ በገባ ጊዜም ለተለያዩ ቢሮዎች በተደጋጋሚ አቤቱታቸውን ማሰማታቸውን የሚናገሩት አቶ ሀሰን፤ መጀመሪያም ጉዳዩን ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ማቅረባቸውን ይናገራሉ:: ክልሉም ተፈጠረ ስለተባለው ችግር ለመፍተት በሚል ለካፊቾ ሼክቾ ዞን ስለጉዳዩ አጣርቶ ምላሽ እንዲሰጥ በደብዳቤ አዘዘ:: የካፊቾ ሼክቾ ዞንም የየኪ ወረዳ ስለጉዳዩ አጣርቶ ምላሽ እንዲሰጥ አዘዘ::

በትእዛዙ መሰረት ወረዳው ለዞኑ ፤ ዞኑ ለክልሉ ያገኙትን የሰነድ ማስረጃዎች ተለዋወጡ:: በዚህም ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ አመራሮች አርሶ አደሮች በምን መልኩ ማሳቸውን እንደተነጠቁ በውል መገንዘብ ቻሉ:: ነገር ግን ስለሁኔታው እያንዳንዱን ነገር ጠንቅቀው ቢገነዘቡም ደፍሮ እርምጃ የሚወስድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ግን ማግኘት አልተቻለም:: በዚህም ችግሩ 36 ዓመታት መፍትሄ ሳያገኝ እስከዛሬ ድረስ መቆየቱን ያስረዳሉ::

በሀገሪቱ እና በክልሉ የወጡ አዋጆችን መሰረት በማድረግ የምትክ ቦታ እና የካሳ ክፍያ እንዲሰጡ ቢጠይቁም የሚሰማቸው አካል አልተገኘም:: ከዛሬ ነገ ችግራቸውን የሚፈታልን አካል እናገኛለን በሚል እስካሁን ድረስ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንዳልወሰዱትም ይናገራሉ::

በጉዳዩ ተስፋ ያልቆረጡት አርሶ አደሮቹ ከዛሬ ነገ መልስ እናገኛለን በማለት ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ዕንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታ አስገብተው ነበር:: ሁኔታውን በውል ያጤነው የዕንባ ጠባቂ ተቋም የአርሶ አደሮች ችግር የሚመለከተው የፌዴራል ፕራይቤታይዜሽን እና የመንግሥት ልማት ድርጅት ተቆጣጣሪ ኤጄንሲ በመሆኑ ለአርሶ አደሮች ማረጋገጫ ሰጠ:: ዕንባ ጠባቂ ተቋም በሰጠው ማረጋገጫ መሰረትም ኤጄንሲው የአርሶ አደሮችን ችግር እንዲፈታ በተደጋጋሚ ጠየቀ:: ይሁን እንጂ ኤጀንሲው ስለጉዳዩ ምንም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን አቶ ሀሰን ይናገራሉ::

አሁንም ተስፋ ያልቆረጡት አርሶ አደሮች ችግራቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አሳወቁ :: የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮም ጉዳዩን ወደ ክልል እንደመለሰው እና ክልሉም ጥያቄአቸውን እንደሚያስተናግድ ተገልጾላቸው ነበር :: ወደ ክልላቸው በመጡ ጊዜ ግን ምላሽ የሚሰጣቸው አካል ማጣቸውን ይናገራሉ::

በመጨረሻ ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ በ2011 ዓ.ም የቴፒ ቡና ተክል ድርጅት ቦታው ለግሪን ኮፊ መሸጡን የሚናገሩት አቶ ሀሰን፤ አሁን ላይ ደግሞ ግሪን ኮፊ ቦታውን ለሌላ ባለሀብት መሸጡን ያስረዳሉ:: ነገር ግን አሁን ላይ የገዛውን ባለሀብት ማንነት አርሶ አደሮች እንደማያውቁት ይገልጻሉ::

አሁን ላይ ቦታው ክርክር ያለበት ሆኖ ሳለ ለሌላ ግለሰብ ለምን ይሸጣል? በሚል ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥያቄ አቅርበው እንደነበር የጠቆሙት አቶ ሀሰን፤ ጥያቄውን ተከትሎ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርም ተፈጠረ ስለተባለው ችግር የክልሉ መልካም አስተዳደር አጣርቶ እንዲመለስ ደብዳቤ ጻፈ:: የክልሉ መልካም አስተዳደርም ከካፊቾ ሻኪቾ ዞኑ ጋር በመሆን ጉዳዩን ያጣራል ብንልም እስካሁን ለአርሶ አደሮቹ ተጨባጭ የሆነ መልስ መስጠት አለመቻሉን ይናገራሉ::

ከቦታው ላይ የተፈናቀለው የአርሶ አደር ብዛት 300 ይሆናል የሚሉት አቶ ሀሰን ፤ ይሁን እንጂ በተፈናቃይነት የተመዘገበው 250 የሚሆነው ሰው ብቻ መሆኑን አብራርተዋል::

አሁን ላይ ማህበረሰቡ ተስፋ እየቆረጠ ነው የሚሉት አቶ ሀሰን፤ ይህም አካባቢውን ወደ አላስፈላጊ ግጭት ሊያስገባው እንደሚችል ጠቁመዋል:: በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከመገፋፋት ወጥተው ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ አመላክተዋል::

ከሰነድ የተገኙ ማስረጃዎች

ሰነድ አንድ፡- ይህ የሰነድ ማስረጃ በዋናነት የሚዳስሰው የየኪ ወረዳ አርሶ አደሮች ያጋጠማቸው ችግር እንዲፈታላቸው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥትን በጠየቁ ጊዜ የክልሉ መንግሥት ስለጉዳዩ ለማጣራት እንቀስቃሴ ባደረገበት ወቅት የከፋ ዞን ስለጉዳዩ አጣርቶ ምላሽ እንዲሰጥ መጠየቁን ፤ ዞኑም የክልሉ መንግሥት ለጠየቀው ተገቢውን መለስ ለመስጠት ይችል ዘንድ የየኪ ወረዳን ስለጉዳዩ ምን ታውቃለችሁ ? ሰነዶች ምን ይላሉ? ሲል ጠይቆ ባገኘው ምላሽ ላይ ያተኮሩ ደብዳቤዎች ነው::

የየኪ ወረዳ ወረዳ በቁጥር ቡ2/11198/89 በቀን 26/8/1989 ለካፊቾ ሸካቾ ዞን በበጻፈው ድብዳቤ እንዳመላከተው የካፊቾ ሸካቾ ዞን ስለተፈጠረው አለመግባባት በቁጥር 01/1376/252/89 በቀን 17/7/89 በተጻፈ ደብዳቤ የየኪ ወረዳን ጠይቆ እንደነበር እና የየኪ ወረዳም በደርግ ዘመነ መንግሥት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በኢሰፓ ጽህፈት ቤት የተጻፉ ደብዳቤዎች በመጥቀስ እና ዋቢ በማድረግ የሚከተለውን ምላሽ በደብዳቤ መስጠቱን ያትታል::ዝግጅት ክፍላችንም የየኪ ወረዳ እንደመነሻት የተጠቀማቸውን በኢሰፓ ጽህፈት ቤት የተገኙ የሰነድ ማስረጃዎች የተወሰኑ የቃላት ማሻሻያዎችን በማድረግ ደብዳቤዎችን እንደወረደ አስቀምጠናል::

በየኪ ወረዳ በቀድሞ ስማቸው ዳሪሙ፣በቆ ልማት ፣ ሰላም ሰፈር እና ዳኑ በተባሉ ቀበሌዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች የቡና ማሳ ይዞታን የቴፒ ቡና ተክል ፕሮጀክት ያለአንዳች ጥያቄ እና የሚመለከተው አካል እውቅና በፈቃዱ በዶዘር ነቃቅሎ ከጣለባቸው በኋላ በገበሬው እና በፕሮጀክቱ መካከል ያለመግባባት በመፈጠሩ ሁኔታውን ለማርገብ በወቅቱ የየኪ ወረዳ ኢሰፓ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቁጥር ጃ/ዳ5.ፖ1-መመ23-3/42 በቀን 26/01/81 ለኢሊባቡር ክፍለ ሀገር ኢሰፓ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ጻፈ:: በተጻፈው ደብዳቤም እንደተመላከተው የቴፒ ቡና ተክል ፕሮጀክት በ04/13/80 በአርሶአደሮች ማሳ ላይ የፈጸመው ተግባር ትክክል አለመሆኑን እና ዳግመኛ የዚህን አይነት ድርጊት እንዳይፈጸም፤ ለወደመው ንብረት ክፍያ የበላይ አካልን ውሳኔ የሚጠይቅ በመሆኑ ውሳኔ ያስተላለፈባቸውን ነጥቦች በደብዳቤው በመዘርዘር አስቀምጧል::

በደብዳቤው ከተጠቀሱት ነጥቦች መካከል በዋነኝነት የቴፒ ቡና ተክል ፕሮጀክት በጥናት በቀረበው መረጃ መሰረት የፈጸመው ክፍያ ለአንድ ዓመት የምርት ግምት እንጂ ለዘላለሙ እንዳልሆነ እና አጠቃላይ ግምቱን በተመለከተ በአመራር አሰጣጥ በኩል ፕሮጀክቱን ለማዘዝ የክልሉ ስልጣን ስላልሆነ በሚኒስቴር ደረጃ ታይቶ ተገቢው ክፍያ መፈጸም እንዳለበት ተጠቁሟል::

ሌላው በኢሰፓ ሥራ አስፈጻሚ ደብዳቤ የተመላከተው ደግሞ ለአቅመ ደካማ አርሶ አደሮች የመኖሪያ ቤት ሰርቶ የመስጠት ፣ የቡና ችግኝ መስጠት እና በአርሶ አደሮች ለሚያደርጉት ቡና ተከላ የቴፒ ቡና ፕሮጀክት የዶዘር እርዳታ ትብብር ማድረግ ይልና በመጨረሻም የቴፒ የቡና ፕሮጀክት አርሶ አደሮችን የቡና ማሳ ከተረከበ በኋላ ከአንድ ዓመት የምርት ክፍያ ውጪ የፈጸመው ክፍያ እንደሌለ ፣ የግምት ክፍያም ቢሆን የበላይ አካል ለኮሚቴው የጥናት መረጃ በመነሳት ውሳኔ ሳይሰጥበት በጎን የተፈጸመ ነው የሚል ነው::

ከኢሰፓ ደብዳቤዎች በመነሳት ለሸካ ዞን መረጃ የሰጠው የየኪ ወረዳ ለምክር ቤት እንደጠቆመው፤በወረዳቸው ከጉዳዩ ጋር የሚገናኙ በኢሰፓ ጽህፈት ቤት የተደራጁ ሰነዶች መኖራቸውን ገልጾ፤ ነገር ግን አሁንም ጉዳዩ በበላይ አካል መታየት ስላለበት የበላይ አካል ጉዳዩን ተመልቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት በማመላከት በርካታ አባሪ የሰነድ ማስረጃዎችን ለሸካ ዞን መላካቸው ተመላክቷል:: ይህን ተከትሎ የሸካ ዞን ከወረዳ ያገኘውን ሰነድ ለክልል ላከ:: ይሁን እና የክልሉ መንግሥት ውሳኔ ከመወሰን ይልቅ ጉዳዩ የክልል መንግሥት ስልጣን አይደለም በሚል ለአርሶ አደሮች ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጥ ቀረ::

ሰነድ ሁለት፡- የሸካ ዞን በቁጥር አስ/01-03-7/80 በቀን 24/12/85 ለበደቡብ ብሔር ፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት በጻፈው ድብዳቤ እንዳመላከተው፤ በየኪ ወረዳ ጻኑ፣ዳርሙ፣በቆ ሰላም ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች የተፈጸመባቸውን ግፍ በተደጋጋሚ ለወረዳ ፣ለዞን እና ለክልሉ እንዲሁም ለፌዴራል መንግሥት የልማት ድርጅት ኤጀንሲ ቢያመለክቱም ከክልሉ መንግሥት እና ከኤጄንሲው ይህ ነው የሚል ምላሽ ባለማግኘታቸው በአርሶ አደሮች ላይ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሯል:: ጉዳዩም በዞኑ ትልቅ የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑ ታውቆ የክልሉ መንግሥት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለአርሶአደሮች ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥብት ሁኔታ እንዲመቻች የሚል ነው::

ሰነድ ሶስት፡- የበደቡብ ብሔር ፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ለፌዴራል የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ፕራይቬታዜሽን ኤጄንሲ በቁጥር ደአ/ርመ237/590 በቀን 2/12/99 በጻፈው ድብዳቤ እንደተጠቀሰው በደቡብ ክልል ሼካ ዞን የኪ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ 180 አርሶ አደሮች ይዞታ( የአትክልት እና ቤት ንብረት) በቴፒ ቡና ተክል ልማት ፕሮጀክት በ1980 ዓ.ም የወደመባቸው ስለሆነ አርሶ አደሮቹ በከፍተኛ ችግር ላይ ይገኛሉ::

ስለሆነም ንብረታቸው ለወደመባቸው አርሶ አደሮች ምንም አይነት ካሳ ስላልተሰጣቸው ጉዳዩ የሚመለከተው ፌዴራል የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ፕራይቬታዜሽን ኤጄንሲ ችግሩን ተመልክቶ አፋጠኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ከዚህ ቀደም በቁጥር ደኢ/መ2/53/259 በቀን 30/10/89 በተጻፈ ደብዳቤ የጠየቅን ቢሆንም ኤጄንሲው ግን ምን አይንት ምላሽ ባለመስጠቱ ችግሩ እንዲፈታ በድጋሚ በተጻፈ ደብዳቤ መሆኑን የሚያመላክት ነው ::

ሰነድ አራት፡- በቁጥር ዕንባ/ዘ2-ኢሀ/21/1 በቀን 01/05/2000 ዓ.ም የተጻፈ ደብዳቤ እንደሚጠቁመው፤ የፌዴራል እንባ ጠባቂ ተቋም በተለያዩ ጊዜያት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፕራይቬታይዜሽን እና የመንግሥት ልማት ድርጅት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በርካታ ድብዳቤዎችን መጻፉን ፤ይሁን እንጂ የፕራይቬታይዜሽን እና የመንግሥት ልማት ድርጅት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ምንም አይነት ምላሽ ባለመስጠቱ የፌዴራል እንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣን ጠቅሶ በኤጀንሲው ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድበት ያመላከተበት ነው::

ሰነድ አምስት፡- ይህ ሰነድ ሁለት ደብዳቤዎችን የያዘ ነው:: አንደኛው የሸካ ዞን በቁጥር የወ/ሀ2/93/99 በቀን 26/11/ 1999 ለደቡብ ክልል የተጻፈው ነው:: በዚህ ደብዳቤ እንደተመላከተው፤ የሸካ ዞን የደቡብ ክልልን የ180 ገበሬዎች ይዞታና የካሳ ግምት ምን ደረሰ ሲል የጠየቀበት ሲሆን ሌላኛው ደብዳቤ ደግሞ የደቡብ ብሔር ፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ለሸካ ዞን ደኢ02/መ92/1585/9 በቀን 23/7/95 ያጻፈው ነው::

በዚህ ደብዳቤ በሸካ ዞን በየኪ የሚኖሩ 180 የሚሆኑ አርሶ አደሮች በቴፒ ቡና ተክል ድርጅት 10 ጋሸ ማሳ መነጠቃቸውን እና ለተወሰደባቸው መሬት ምን አይነት ካሳ እንዳልተከፈላቸው ጠቅሶ፤ይሁን እንጂ የክልሉ መንግሥት ለአርሶ አደሮች ካሳ የመስጠትም ሆነ የማሰጠት ስልጣን እንደሌለው ፣ ይህ ስልጣን የፕራቬታይዜሸን እና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጠሪ ኤጄንሲ ስለመሆኑ የጠቆመበት ነው::

የጋዜጠኞች ትዝብት

ከላይ ማየት እንደተቻለው /ከጽሁፉ/ ከላይ እስከ ታች ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች (ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እስከ ወረዳ አስተዳደር) ተፈጠረ በተባለው ችግር ላይ አንድ አይነት አረዳድ እንዳላቸው፤ በዚህም በአርሶ አደሮች ላይ ከፍተኛ በደል ስለመፈፀሙ የተጠራጠረ የለም ::

ይሁንና የአርሶ አደሮችን ቅሬታ በመቀበል ችግራቸውን ለመፍታ በሚደረገው ሂደት ላይ ግን በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መካከል ከፍተኛ የሆነ መገፋፋት እንዳለ እና ኃላፊነት ወስዶ የተበዳይ ዜጎችን ችግር ከመፍታት አኳያ ከፍተኛ ውስንነት ስለመኖሩ ከሰዎች እና ከሰነድ ያገኘናቸው ማስረጃዎች ያሳያሉ:: ወድ አንባቢያን በቀጣይ በሚኖረን ክፍል፤ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ምላሽ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል! እስከዚያው መልካም ጊዜ እንዲሆንላችሁ ተመኘን! ቸር እንሰንብት ::

በሙሉቀን ታደገ እና መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን የካቲት 13/2016

Recommended For You