ኢትዮጵያ ጸንታ የኖረችው በሕዝቦቿ ክቡር መስዋዕትነት ነው !

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሉዓላዊነቱ ቀናኢ ነው:: በየዘመናቱም ከውስጥና ከውጭ የተቃጡ ሉዓላዊነትንና የግዛት አንድነትን የሚፈታተኑ ተግባራትን በጽኑ ታግሎ ሀገሪቱን ከነሙሉ ክብሯ ለአሁኑ ትውልድ አስረክቧል::

ከጥንት እስከ ዛሬ የቅርብ እና የሩቅ ጠላቶች ከሀገር ውስጥ ባንዳዎች ጋር ተባብረው ኢትዮጵያን ለመበታተን መሄድ እስከሚችሉት ድረስ ተጉዘዋል:: ሆኖም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገሩ ዳር ድንበር የሚዋደቅ፤ ከራሱ በፊት ሀገሩን የሚያስቀድም፤ ቅኝ ገዢዎችንና ሌሎች ወራሪ ኃይላትን አሳፍሮ የሚመልስ ጀግና ሕዝብ ነው ::

ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሀገራት ነፃነትና እኩልነት የሚታገሉ፤ በአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት የሆኑ ኩሩ ሕዝቦች ናቸው:: ይህም ጀግንነትና አይበገሬነት በተባበሩት መንግሥታት ጭምር እውቅና አግኝቶ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን በሩዋንዳ፤ በቡሪንዲ፤ በላይቤሪያና በሶማሊያ ተሰማርቶ ጀግንነቱን አስመስክሯል::

ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ እስከ ማይጨው፤ ዶጋሊና ሶማሊያ ወረራ ድረስ ሕይወታቸውን በመገበር፤ ደማቸውን በማፍሰስ እና አጥንታቸውን በመከስከስ በመስዋዕትነት ሀገራቸውን አጽንተዋል::

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ታሪክ የክቡር መስዋዕትነት ታሪክ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም:: አፍሪካን ብሎም ኢትዮጵያን እንደ ዳቦ ለመቀራመት የመጡ ቅኝ ገዢዎችን አሳፍሮ መመለስና ለአፍሪካ ብሎም በዓለም ላይ ላሉ ጥቁር ሕዝቦች ኩራት መሆን የተቻለው በመስዋዕትነት ነው::

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አሰቃቂና አሳዛኝ ከሆኑት ጭፍጨፋዎች መካከል አንዱ የሆነው የየካቲት 12 ጭፍጨፋም ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው የከፈሉት ከባድ የመስዋዕትነት መገለጫ ነው:: በጣሊያን ወራሪ ኃይል ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው ጭፍጨፋ በአዲስ አበባ ብቻ እስከ 30 ሺ ነዋሪዎች አልቀዋል:: ይህም ጭፍጨፋ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩ አስከፊ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው ።

በጊዜው ኢትዮጵያውያንን ለዚህ ሁሉ ግፍ እና በደል የዳረጋቸው የሠሩት ጥፋት ኖሮ ሳይሆን በአንገዛም ባይነታቸውና ለሉዓላዊነታቸው ባላቸው ቅናት ብቻ ነበር። ይህ አሰቃቂ ክስተት ሆነ ዘንድሮ ሰማንያ ሰባተኛ ዓመቱን ደፍኗል።

ለሀገር ሉዓላዊነትና ለግዛት አንድነት የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች ውለታ የሚመለሰው የሠላምና የልማት አርበኛ መሆን ስንችል ነው:: በተለይም ሠላም ለራቃት ሀገራችን የሠላም አምባሳደር በመሆን የአባቶቻችንን መስዋዕትነት ከንቱ እንዳይሆን የበኩላችንን ጥረት ልናደርግ ይገባል::

የግጭት፣ የጦርነት፤ ያለመግባባት ታሪካችን ተዘግቶ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የምንግባባ፤ ለጋራ ሀገራችን የምንተጋ፤ ለልጆቻችንም የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማውረስ የጋራ እሳቤ የጨበጥን አዲስ ትውልድ መሆን ይገባናል::

በአባቶቻችንና እናቶቻችን ተጋድሎ ያገኘነው ኩራትና ነፃነታችን ሙሉ እንዲሆን ሀገሪቱን በልማት ማበልፀግ ያስፈልጋል:: ይህ ትውልድ ታላቁን የዓባይ ግድብ ሠርቶ እያገባደደ ነው:: ይህን የሀገር ኩራት የሆነ ግድብ አጠናቆ ለሀገር ብሎም ለአፍሪካ ብርሃን ማጎናጸፍ የዚህ ትውልድ አንዱ አደራ ነው::

በግብርና ልማት በተለይም በስንዴ የተገኘውን አኩሪ እንቅስቃሴ ዘላቂ ማድረግና ከኢትዮጵያም አልፎ አፍሪካን መመገብ ሌላው የዚህ ትውልድ አሻራ ሊሆን ይገባል:: በርካታ የውጭ ኃይላት ኢትዮጵያ ስንዴ ማምረቷ ከተፅዕኖና ከተንበርካኪነት እንድትወጣና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ፈለጓን ይከተላሉ በሚል ስጋት ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ሲፈጥሩ ቆይተዋል:: ሆኖም ጫናዎችን መቋቋም በመቻሉ ዛሬ ኢትዮጵያ በስንዴ ዘርፍ ባሳየችው ውጤታማነት በዓለም መድረክ ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች::

አረንጓዴ አሻራ በማኖር ረገድ ኢትዮጵያውን ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ ታሪክ በመጻፍ ላይ ይገኛሉ:: ይህ አኩሪ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት የማይወዱ አካላት ሊያጣጥሉት ቢሞክሩም ተግባሩ የሚደበቅ አይደለምና ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው መድረኮች ሁሉ በውጤታማነቱ እየተወሳ ይገኛል:: ስለዚህም ትውልዱ ይህንን አንፀባራቂ እንቅስቃሴ ከዳር ማድረስና ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን አረንጓዴ ማልበስ ቀጣይ የቤት ሥራው ሊያደርግ ይገባል::

በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል የሀገርን ዳር ድንበር አላስደፍርም በማለት ደማቸውን በማፍሰስ፤ አጥንታቸውን በመከስከስ ውድ ሕይወታቸውን መስዋዕት ሲያደርጉ ኖረዋል:: የአሁኑ ትውልድም የሀገሩን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን በሠላም እና በልማቱም መስክ ሀገሪቱን ወደ ፊት ሊያራምዱ የሚያስችሉ ተግባራትን በመከወን መስዋዕት የከፈሉ ቀደም አባቶችን ፈለግ ሊከተል ይገባል!

አዲስ ዘመን የካቲት 13/2016

Recommended For You