ቴክኖሎጂ እያንዳንዱን የዓለምን እንቅስቃሴ በተቆጣጠረበት እና ምቹና ቀልጣፋ ኑሮንም ሆነ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገትን ከቴክኖሎጂው ዘርፍ እድገት ውጪ ማሰብ በማይቻልበት በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያም ከቴክኖሎጂ ዘርፍ እድገት ተቋዳሽ ለመሆን ትልልቅ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ምርትና አገልግሎትን በዘመናዊ አሰራር የሚያቀርቡ ቴክኖሎጂዎች በብዛት ወደ ሥራ እየገቡ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ አገልግሎት አቅራቢዎችንና ፈላጊዎችን በቀላሉ በማገናኘት ረገድ አሁንም በርካታ መሰናክሎች አሉ።
ለአብነት ያህል በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሞሎች (Malls) የት እና ምን ዓይነት ምርትና አገልግሎት አቅራቢዎችን እንደያዙ በቀላሉ ማወቅ ፈታኝ ተግባር ሆኖ ይስተዋላል። ለዚህ ችግር በቴክኖሎጂ የታገዘ መፍትሄ የሚሰጥ፣ ‹‹ሞል ኢን አዲስ›› (Mall in Addis) የተሰኘ ቴክኖሎጂ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለአገልግሎት በቅቷል። ቴክኖሎጂውን ለአገልግሎት ያበቃው ‹‹መልፋን ቴክ›› (Melfan Tech) የተባለ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ነው።
‹‹መልፋን ቴክ›› በቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ የተሰማራ ድርጅት ሲሆን፣ ሶፍትዌር በማልማት ሥራ (Software Development) ላይ የበለጠ አተኩሮ ይሰራል። ከአምስት ዓመታት በፊት፣ በ2012 ዓ.ም የተመሰረተው ድርጅቱ፣ የብዙ ተቋማትን የንብረት፣ የሰው ሀብት፣ የፋይናንስና ሌሎች የአገልግሎት አሰጣጥና አሰራር ሥርዓቶችን ያዘመኑና ተገልጋዮች (ምርትና አገልግሎት ፈላጊዎች) በፍጥነት እንዲስተናገዱ ያስቻሉ በርካታ ቴክኖሎጂዎችን ሰርቷል።
የ‹‹ሞል ኢን አዲስ›› ምንነትና ፋይዳዎቹ
የ‹‹መልፋን ቴክ›› መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወጣት መልካሙ ምትኩ እንደሚገልጸው፣ ‹‹ሞል ኢን አዲስ›› (Mall in Addis) በዕለት ከዕለት የስራ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ለሚገጥሙ ተግዳሮቶች በቴክኖሎጂ የታገዘ መፍትሄ ለመፈለግ እውን የሆነ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው። ምርትና አገልግሎት የሚፈልጉ ተገልጋዮች የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች ለማግኘት ብዙ መሰናክሎች ያገጥሟቸዋል። ችግሩ የትኞቹ አገልግሎቶች በምን ያህል ብዛት፣ ጥራትና አማራጭ በየትኞቹ ሞሎች ላይ እንደሚገኙ በትክክል ከማወቅ ይጀምራል። ተገልጋዮች የሚፈልጓቸውን ምርቶችንና አገልግሎቶችን የያዙ ሞሎች በተለያዩ የከተማው አካባቢዎች ተበታትነው የሚገኙ ናቸው። በከተማው ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም ሞሎች ተዘዋውሮ ለማዳረስ ደግሞ ብዙ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጭ ይጠይቃል።
ለአብነት ያህል ሰዎች የሚከራይ ቢሮ ሲፈልጉ የትኛው ህንፃ ላይ እንዳለ ለማወቅ ተለምዷዊ የሆኑትን ሌሎች ሰዎችን የመጠየቅ፣ ማስታወቂያዎችን የመመልከትና የህንፃ ባለቤቶችን እየዞሩ የመጠየቅ አሰራሮችን ይጠቀማሉ። እነዚህ አሰራሮች አድካሚ እንዲሁም ጊዜና ገንዘብ የሚያባክኑ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም አገልግሎት ፈላጊዎችና አቅራቢዎች ባለመገናኘታቸው ምክንያት ያለሥራ የተቀመጡ ቢሮዎች ይኖራሉ። ይህ ደግሞ አከራዮች ማግኘት የሚገባቸውን ዋጋ እንዲሁም ተከራዮችም የሚፈልጉትን ቢሮ ሳያገኙ ብዙ ጊዜያት እንዲያልፉ ምክንያት ይሆናል። በሌላ በኩል ተከራዮች ‹‹የስራ ቦታዬ አልታወቀልኝም፣ ብዙ ደንበኛ አላገኘሁም…›› በሚሉ ምክንያቶች በየጊዜው የሥራ ቦታቸውን ለመቀየር ይገደዳሉ። አሰሪዎችና ሥራ ፈላጊዎች ደግሞ የሥራ ማስታወቂያዎችን በተገቢው ቦታ የማስቀመጥና የመፈለግ ችግሮች ሲታዩባቸው ይስተዋላል። ስለዚህ ለዚህ ችግር ምላሽ የሚሰጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ መፍትሄ ያስፈልጋል። ‹‹ሞል ኢን አዲስ›› እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ታሳቢ ያደረገ መፍትሄ ለማቅረብ እውን የሆነ አዲስና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አማራጭ ነው።
የህንፃ/ክፍሎች ተከራዮች በተለያዩ አጋጣሚዎች የሥራ ቦታቸውን የሚቀይሩና ሞሎች የተከራዮች መረጃዎች የሚገኙባቸው መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቴክኖሎጂው ሞሎችን ታሳቢ (Target) አድርጎ የሚሰራ ነው። ይህም ቴክኖሎጂው ሞሎችን፣ ሞሎች ተከራዮቻቸውን እንዲሁም ተከራዮች ደግሞ ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲቆጣጠሩ አመቺ እድል ይፈጥራል። ይህ የሥራ ክፍፍል ቴክኖሎጂው ይበልጥ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆንና ተቀባይነት እንዲያገኝ ይረዳል።
በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እንዲሰጥ ይፋ የተደረገው የ‹‹ሞል ኢን አዲስ›› ገፅታ፣ ድረ-ገፅ (mallinaddis. com ዌብሳይት) ሲሆን፣ በቀጣይ ደግሞ ለአንድሮይድና ለአይፎን አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችሉ መተግበሪያዎች (Application/App) እየተሰሩ ይገኛሉ፤በቅርቡም ለአገልግሎት ይበቃሉ።
ቴክኖሎጂው የትኛው ሞል ላይ ምን ዓይነት ቢሮዎች፣ ምርቶችና አገልግሎቶች እንዲሁም የሥራ ማስታወቂያዎች እንደሚገኙ ዝርዝር መረጃ ይሰጣል። በዚህ መሰረት አገልግሎት ፈላጊው ሰው ወደ አካባቢው ይሄዳል። አገልግሎት ፈላጊው የአካባቢውን አቅጣጫ ካላወቀው ቴክኖሎጂው ለዚህ ችግር የሚሆን መፍትሄም አለው፤የቦታውን መገኛ የሚያሳይ አቅጣጫ አመልካች አካትቶ የያዘ በመሆኑ በዚሁ አቅጣጫ አመልካች በመመራት ወደ ስፍራው መድረስ ይችላል።
ተገልጋዮች ወደ ድረ-ገፁ (mallinaddis.com) ሲገቡ ሞሎቹ ምን ያህል ክፍሎች እንዳሏቸው፣ ያልተያዙት ክፍሎቻቸው የትኞቹና ምን ዓይነት እንደሆኑ፣ ምን ያህል የሥራ ማስታወቂያዎች እንዳሉ … መመልከት ይችላሉ። መረጃዎቹ በጽሑፍ፣ በፎቶና በቪዲዮ የታገዙ ናቸው። ቴክኖሎጂው ለሥራ ማስታወቂያዎች እዚያው ድረ-ገፁ ላይ ወዲያውኑ ማመልከት የሚቻልበትን አሰራርም ይዟል። በሌላ በኩል ለጊዜው ሞሉ ለኪራይ አገልግሎት የሚውል ክፍት ቦታ ከሌለውና ተገልጋዩ በቀጣይ ጊዜ ክፍት ቦታ ሲኖር እንዲያዝለት ከፈለገ፣ ተመዝግቦ እንዲጠብቅ የሚያስችል አሰራርም አለው። ከዚህ በተጨማሪም ቴክኖሎጂው ለአገልግሎት ፈላጊዎች በርካታ አማራጮችን የሚያቀርብ ሲሆን፣ ከእነዚህ አማራጮች መካከል አንዱ ተገልጋዮች የትኞቹ አካባቢዎች የሚገኙ ሞሎች ላይ አገልግሎት እንደሚፈልጉ ምርጫቸውን የሚያሳውቁበት ዘዴ ነው።
‹‹መልፋን ቴክ›› ከሞሎች ጋር በሚያደርገው ስምምነት መሰረት መረጃዎቻቸውን በከፍተኛ ጥራት ወደ ድረ-ገፁ ያስገባል። የሞል ባለቤቶች የሚሰጣቸውን የተጠቃሚነት መለያ ስም (User Name) እና የይለፍ ቃል (Password) ተጠቅመው ስለሞሎቻቸውና ስለተከራዮቻቸው መረጃዎችን ይመዘግባሉ። ተከራዮችም የሥራ ቦታ ተከራይተው በአከራዮቻቸው ሲመዘገቡ የተጠቃሚነት መለያ ስም እና የይለፍ ቃል ይሰጣቸዋል። ስለምርቶቻቸውና አገልግሎታቸው ዝርዝር መረጃዎችን ያስገባሉ። ከህንፃው ሲለቁ ደግሞ መረጃዎቻቸው ስፍራውን እንዲለቁ ይደረጋል። ወደ ሌሎች ሞሎች ሲዘዋወሩ መረጃዎቻቸውም ወደ አዲሱ የሥራ ቦታዎቻቸው ይዘዋወራሉ፤ይህም አድራሻ ስለመቀየራቸው ያሳውቃል። ምርቶቻቸውና አገልግሎቶቻቸው እንዲተዋወቁላቸው ስለሚፈልጉም መረጃዎቻቸውን አሻሽለው (Update) ለተገልጋዮች ያሳውቃሉ። አዲስ የሚተኩት ተከራዮችም በዚሁ አሰራር መሰረት ይቀጥላሉ።
‹‹መልፋን ቴክ›› ቴክኖሎጂው ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ይሆን ዘንድ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን አከናውኗል። ለአብነት ያህልም 130 የሞል ባለቤቶችን፣ ሥራ አስኪያጆችንና ተወካዮችን በመጋበዝ ስለቴክኖሎጂው ምንነትና ፋይዳዎች ሰፊ ገለፃዎችን አድርጓል። በዚህም በርካታ ሞሎች ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ከፍተኛ ፍላጎት ዐሳይተዋል። እስካሁን 24 ሞሎች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ለመሆን የተመዘገቡ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ለመመዝገብ ፍላጎታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።
የቴክኖሎጂው ልዩ ገጽታዎች
‹‹ሞል ኢን አዲስ›› የሞል አስተዳር ስራዎችን ከሚሰሩ ተቋማት ልዩ የሚያደርጉት በርካታ ባህርያትና ገጽታዎች እንዳሉት መልካሙ ያስረዳል። ‹‹ሞል ኢን አዲስ›› የሞሎች ዝርዝር መረጃዎች ላይ አተኩሮ የሚሰራ አዲስ ቴክኖሎጂ ነው። በተለምዶ ከሚታወቁት የመረጃ ዳይሬክቶሪዎች በእጅጉ የተለየ አማራጭ ነው። በድረ-ገፁ ላይ የሚመዘገቡት መረጃዎች ከጉዳዩ ባለቤቶች በቀጥታ የተገኙ ትክክለኛ መረጃዎች ናቸው። የሥራ ቦታቸውን የሚቀይሩ ተከራዮችን መረጃ በቀላሉ ለማግኘትም ያስችላል።
‹‹በዘርፉ የአሰራር ለውጥ እንዲኖር አድርገናል። የሞሎችን የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን አዘምነነዋል። የሞል አስተዳደር ስርዓቱ (Mall Management) የውስጥ ስራቸውን ያዘምንላቸዋል። በ‹ሞል ኢን አዲ› ቴክኖሎጂ በየጊዜው የታደሰ መረጃ ይቀርባል። ስለሆነም የሞሎቹ ድረ-ገፅ፣ ሞል አስተዳደር (Mall Management) እና ‹ሞል ኢን አዲስ› ተቀናጅተው እንዲሰሩ እድል ይፈጥራል›› በማለት ስለቴክኖሎጂው ልዩ ገፅታ ያስረዳል።
ቴክኖሎጂው ለአገልግሎት ፈላጊዎች በርካታ አማራጮችን ያቀርባል። ከእነዚህ አማራጮች መካከል አንዱ ተገልጋዮች የትኞቹ አካባቢዎች የሚገኙ ሞሎች ላይ አገልግሎት እንደሚፈልጉ ምርጫቸውን የሚያሳውቁበት ዘዴ ነው። ቴክኖሎጂው የሞል ባለቤቶችን፣ ተገልጋዮችንና ሌሎች የቴክኖሎጂ ተዋንያንንና ኅብረተሰብ ክፍሎችን አሳታፊና ተጠቃሚ ያደርጋል።
ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦው
የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለምጣኔ ሀብት እድገት እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው። ‹‹ሞል ኢን አዲስ››ም በሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ የራሱ አወንታዊ አሻራ ይኖረዋል። ተጠቃሚው በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ አገልግሎት እንዲያገኝ፣ ጊዜና ገንዘብ እንዲቆጥብ እንዲሁም ስራውን እንዲያቀላጥፍ ያስችለዋል። ተከራዮች የሥራ ቦታ ሲቀይሩ የሞል ሥራ አስኪያጆች በተለምዶ የሚታወቀውን አሰራር (ማስታወቂያ መለጠፍ) መከተል አይጠበቅባቸውም። ደላላዎች በመሐል ገብተው የኪራይን ዋጋ ያለአግባብ እንዳያስወድዱት እድል ይፈጥራል፤ይህ ደግሞ የዋጋ ንረት እንዳይባባስ የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል።
ቴክኖሎጂውን መጠቀም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚደረጉና የመንገድ መጨናነቅና የነዳጅ ብክነት የሚፈጥሩ አላስፈላጊ ጉዞዎችን ማስቀረት ይቻላል፤በዚህም የነዳጅ ፍጆታን በመቀነስ ለኢኮኖሚው ላይ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ማበርከት ይቻላል። ‹‹ሞል ኢን አዲስ›› ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረትም ይደግፋል።
የአገልግሎት ደህንነት ዋስትና
የዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እጅግ የረቀቁና ውስብስብ መሆናቸው፣ የተጠቃሚዎች ሁለገብ የመረጃ አገልግሎት ደህንነት ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ምክንያት ሆኗል። ‹‹ሞል ኢን አዲስ›› ለአገልግሎት ደህንነት ዋስትና የሚሰጡ አሰራሮችን ተግባራዊ ያደረገ ቴክኖሎጂ ነው።
‹‹መልፋን ቴክ›› ከዚህ ቀደም በሰናቸው ስራዎች ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) ጋር በጋራ እንደሰራ የድርጅቱ መስራችና ሥራ አስኪያጅ መልካሙ ይናገራል። የስራዎቹን ደህንነት በተቋሙ ያስፈትሻል። ለፕሮጀክቶች ደህንነት ዋስትና የሚሰጡ ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀማል። መረጃዎቹ በከፍተኛ ጥንቃቄና ደህንነት የተመዘገቡ (Encrypted) ስለሆኑ በሌላ ሰው ሊቀየሩና ሊነበቡ አይችሉም። በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን ይጨምራል፤የደህንነት ፍተሻዎችን ያደርጋል። ስለሆነም የቴክኖሎጂው ደህንነት አስተማማኝ ነው።
ያጋጠሙ ችግሮች
አዲስ ቴክኖሎጂዎችን አበልጽጎ ለአገልግሎት ማብቃት ብዙ ፈተናዎች አሉት። ከእነዚህ ፈተናዎች መካከል አንዱና ዋናው ቴክሎጂውን በብቃት መጠቀምና ተደራሽ ማድረግ የሚችል የሰው ኃይል እጥረት ነው። የብቁ ሰራተኞች ከሥራ መልቀቅም የዚሁ ችግር አካል ነው። ‹‹መልፋን ቴክ›› ለዚህ ችግር መፍትሄ አድርጎ የተገበረው ተተኪ ሰራተኞችን በትጋት የማፍራትና ተተኪዎችም የባለቤትነት ስሜት ተሰምቷቸው እንዲሰሩ የማድረግ አሰራርን ነው።
የወደፊት እቅዶች
‹‹ከድርጅቱ ምስረታ ጀምሮ በነበሩት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብዙዎቹ ስራዎቻችን ያተኮሩት ድርጅቱን በማስተዋወቅ፣ ለደንበኞቻችን ታማኝነትን በማሳየትና በመገንባት፣ በፋይናንስ ራሳችንን በማጠናከር ላይ ነበር›› የሚለው መልካሙ፤ በአሁኑ ወቅት ‹‹መልፋን ቴክ›› በተለያየ መልኩ ማደጉንና ብዙ ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል አቅም መፍጠሩን ይገልፃል። የድርጅቶችን አሰራር ከማዘመን ወደ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ማበልፀግ ተሸጋግሯል።
‹‹ሞል ኢን አዲስ የአንድ ድርጅት ብቻ አይደለም። ማኅበረሰቡን፣ ድርጅቶችንና ሞሎችን የሚያሳትፍ እንዲሁም በሀገር ደረጃ ትልቅ ፋይዳ ያለው ቴክኖሎጂ ነው። ለብዙ ማኅበረሰብ ተደራሽ መሆን የሚችል ቴክኖሎጂ ነው። ከደንበኞች ጋር በሚገባ ትስስር በመፍጠር ተከራዮች ምርቶቻቸውን በኦንላይን (Online) መሸጥ የሚችሉበትን አሰራር መፍጠር እንዲሁም ከቪዲዮና ፎቶ በተጨማሪ እጅግ ዘመናዊና የተሻሻሉ የቨርቹዋል ሪያሊቲ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence – AI) አሰራሮችን እንተገብራለን። ቴክኖሎጂውን ይበልጥ በማዘመንና በማስፋት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎችም ተደራሽ ለመሆን እናስባለን። ከዚህ በተጨማሪም እንደድርጅት ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በማበልፀግ ለአገልግሎት የማብቃት እቅድ አለን›› በማለት መልካሙ ስለድርጅቱ ቀጣይ እቅዶች ያብራራል። ‹‹ሞል ኢን አዲስ›› በሚቀጥሉት ስምንት ወራት ከ150 በላይ ሞሎችን ተደራሽ ለማድረግ ያቀደ ሲሆን፣ ደረጃ በደረጃ ሁሉንም የአዲስ አበባ ሞሎች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዷል።
ኢትዮጵያ በ2025 ‹‹ዲጂታል ኢትዮጵያ››ን እውን ለማድረግ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝና በተለያዩ ዘርፎች ላይ ውጤቶች እየተገኙ እንደሆነ የሚገልፀው የ‹‹መልፋን ቴክ›› መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ መልካሙ ምትኩ፣ ነው። ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረጉ ጥረት የሁሉንም ዜጋ ርብርብ የሚፈልግ በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡ እንደ‹‹ሞል ኢን አዲስ›› ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንዲጠቀም እድሎችን ማመቻቸት እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ በአፅንኦት ይመክራል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም