የኢትዮጵያ ሚና ከፓን አፍሪካኒዝም እስከ አፍሪካ ኅብረት እንዴት ይገለጻል ?

በቅኝ አገዛዝ ስር የነበሩ የአፍሪካ ሀገራትን ነጻ የማውጣት ዋና ዓላማን አንግቦ በ 32 ነጻ የአፍሪካ ሀገራት የተመሰረተው ድርጅቱ ዛሬ 55 ሀገራትን በአባልነት አቅፏል:: ድርጅቱ ከምስረታው ጀምሮ እንደ ደቡብ አፍሪካና ዚምባብዌ ያሉ በቅኝ ግዛት ይማቅቁ ለነበሩ የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊና የስልጠና ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱንም ታሪክ የሚያስታውሰው ነው::

እኤአ በ1960 በአህጉሪቱ 17 ተጨማሪ ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎም ድሉ በየዓመቱ ግንቦት 25 “የአፍሪካ የነጻነት ቀን” ተብሎ እንዲከበር ምክንያት ሆኗል:: አፍሪካን በፖለቲካ በንግድና በምጣኔ ሀብት በማዋሃድ አንድ የተባበረ ሀገረ መንግሥት የመመስረት ውጥንን ያለመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እነሆ 61 ዓመታትን አስቆጥሯል ::

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ከምዕራባውያን ቅኝ አገዛዝ ነጻነታቸውን ከተቀዳጁ በኋላ በተለይም “ለአፍሪቃ ነጻነትና ክብር እንቆማለን” ባሉ ሁለት የተለያየ ሃሳብን በሚያቀነቅኑ ቡድኖች የእርስ በእርስ ሽኩቻና ግጭት ሳቢያ አህጉሪቱ በተሻለ መልኩ ጥንካሬና አንድነቷን ጠብቃ ልትቆም አልቻለም ነበር:: እንደውም “አፍሪካውያን በፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ራሳቸውን ከመቻል ጀምሮ እስከ ኮንፌዴሬሽን አንድ ወደ መሆን ውህደት ሊያመሩ ይገባል” የሚል ዓላማን በሚያራምደው የጋናውን ኩዋሚ ኑኩሩማንና የጊኒውን ሴኩቱሬ የመሳሰሉ የነጻነት ታጋዮችን ያሳተፈው ስድስት ያህል ሀገራት በመሰረቱት የካዛብላንካ ቡድንና “ አፍሪቃውያን ራሳቸውን ችለው ለመቆም ምጣኔ ሀብታቸውን ለማሳደግና ጠንካራ እንዲሆኑ ለማስቻል በሌሎች ያደጉ ሀገራት መደገፍ አለባቸው” የሚለውን ሃሳብ በሚያቀነቅነው አብዛኛዎቹ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ የነበሩ 22 የአፍሪካ ሀገራትን ባካተተው የሞኖሮቪያው ቡድን መሃል የተፈጠረውን ቅራኔን አስወግዶ አንድነትን ፈጥሯል።

መላው አፍሪካውያን ልዩነታቸውን አስወግደው በጋራ የሚሰባሰቡበትንና ወደ ጠንካራ ውህደት የሚያመሩበትን አንድ ወጥ የሆነ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በመመስረቱ ሂደት በዓድዋው የጦርነት ድል ምክንያት በአፍሪካውያንና መላው ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተቀዳጀችው ኢትዮጵያ ያበረከተችው ሚና የላቀ መሆኑ በታሪክ ይጠቀሳል::

በ1930ዎቹ ዓ.ም ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ የወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብቸኛዋ አፍሪካዊት አባል ሀገር እንድትሆን ትልቅ ሚና የተጫወቱት የኢትዮጵያው ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት እንዲመሰረት ከሃሳብ ጀምሮ እስከ ተግባራዊ ምስረታው ዕውን መሆን ድረስ እንደ ጋናው ክዋሜ ንክሩማ የኬንያው የነፃነት ታጋይና አርበኛ ጆሞ ኬንያታ የጊኒው ሴኮ ቱሬ የሴኔጋሉ ሊኦፖልድ ሴዳር ሴንጎርና ሌሎችም የአፍሪካ ቀደምት መሪዎች የነጻነት ታጋዮችና የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና አቀንቃኞች ጋር በጋራ በመሆን ያበረከቱት አስተዋጽኦ ዛሬም ድረስ ሲወሳ የሚኖር ነው።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ግን ከላይ ከተገለጸውም በላይ የጎላና ታሪካዊ ነበር። ኢትዮጵያ በራስዋ ልጆች ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር ነች። ኢትዮጵያ ያለምንም የውጭ ኃይል ጥበቃ፣ በራስዋ ልጆች ነጻነቷን አስከብራ መኖሯ፣ ነጻነቷን ለማስከበር ልጆቿ የከፈሉት መስዋእትነት፣ በምእራብ አውሮፓ ሀገራት ቅኝ ግዛት ስር ወድቀው የነበሩ የአፍሪካ ሀገራት ሕዝቦች በራሳቸው አቅም ነጻነታቸውን ለማስመለስ እንዲነሳሱ አድርጓል።

ብዙ የተነገረለት ጥቁር ሕዝቦች የነጭ ወራሪ ኃይልን ያንበረከኩበት የዓድዋ ድል ለዚህ ማሳያነት ይጠቀሳል። የዓድዋ ድል በቅኝ ግዛት ስር ወድቀው የነበሩ የአፍሪካ፣ የኢሲያና የደቡብ አሜሪካ ሕዝቦች የነጻነት ትግል እንዲያቀጣጥሉ አነሳስቷል። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያበረከተችው አስተዋጽኦ በነጻነት ተምሳሌትነት ተነሳሽነትን በመፍጠር ብቻ የተገደበ አይደለም። በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የአፍሪካ ሀገራት ነጻነታቸውን እንዲቀዳጁ የማድረግ ዓላማ የነበረውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አ.አ.ድ) እንዲመሰረት የመሪነት ሚና ተጫውታለች።

ኢትዮጵያ የተባበረች አፍሪካን ለመመሰረት እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረችው ከ1950ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ሲሆን ፤ በወቅቱ የነበሩትን 30 ገደማ የሚሆኑ ነጻ ሀገራትን በማነሳሳትና የመሪነት ሚና በመጫወት በ1955 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ በአዲስ አበባ አፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት አድርጓል። የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመሰረቱት 32 ነጻ የአፍሪካ ሀገራት ነበሩ። ይህ ከሃያ በላይ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የአፍሪካ ሀገራትን ነጻ ማውጣትና የጥቂት ነጮች የበላይነት ሥርዓት ያለባቸውን ሀገራትም ከዚህ የዘር መድልዎ ሥርዓት ማላቀቅ ዋነኛ ዓላማው ያደረገው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በምስረታው ብቻ አላማውን አሳክቷል።

የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ኃይለስላሴ ግንቦት 15 ቀን 1955 ዓ.ም ዋናው የድርጅቱ ምስረታና የአፍሪካ መሪዎች የመክፈቻ ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ ሲካሄድ ባሰሙት ንግግር “የዚህ ታላቅ ጉባኤ መደረግና የመላው አፍሪካ መሪዎች ተካፋይ መሆን ለዚህች ክፍለ ዓለማችን በውስጧም ለሚገኙ ሕዝቦቻችን ላለን ጥልቅ አሳቢነት ዓይነተኛ ምስክር ነው፤ ተስፋና ራዕያችንንም በተግባር እናሳያለን” በማለት ነበር ጉባኤውን የከፈቱት።

በመጨረሻ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የተቀላቀለችው ሀገር ደቡብ አፍሪካ ስትሆን ደቡብ አፍሪካ የጥቂት ነጮች የዘረኝነት ሥርዓትን አስወግዳ አፍሪካ አንድነት ድርጅትን የተቀላቀለችው በ1986 ዓ.ም ነበር። ታዲያ ይህን የአፍሪካ ሀገራትን ነጻነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ዓላማው አድርጎ የተመሰረተና ዓላማውን ያሳካው አፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረትና ተልዕኮውን እንዲወጣ በማድረግ ረገድ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ እንዲሁም ድርጅቱ ዓላማውን በመወጣት ሂደት የጎላ ድርሻ እንዲኖራቸው ያደረጋቸው በቅድሚያ የነጻ ሀገር መሪ መሆናቸው ሲሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት ደግሞ በሕዝቧ መስዋዕትነት የተረጋገጠ ነው።

በ1990 ዎቹ ከግማሽ ክፍለ ዘመን ቆይታ በኋላ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ተልዕኮውን አድሶ በአዲስ መልክ መዋቀር ነበረበት። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምዕራፍ ተዘግቶ፣ በ1993 ዓ.ም ግንቦት ላይ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት የሚል ስያሜ ይዞ ዳግም ተመሰረተ። ታዲያ፤ የአፍሪካ ኅብረት በአዲስ የአፍሪካ መጻኢ ራዕይ እንዲፈጠርና ወደ ሥራ እንዲገባ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ ከአራት አስርት ዓመታት በፊት እንዳደረገችው ሁሉ የጎላ ድርሻ ነበራት።

በወቅቱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ በዚህ ረገድ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ኢትዮጵያውያንና ቀደምት የሀገሪቱ መሪዎች ለአፍሪካ ነጻነት ያበረከቱትን ታላቅ አስተዋጽኦ አስታውሰው፤ አዲስ የተመሰረተው የአፍሪካ ኅብረት ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ እንዲሆን ማድረጋቸውም አይዘነጋም። የአፍሪካ ኅብረት ጽህፈት ቤት፣ አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን መደረጉ ኢትዮጵያውያንና ቀደምት መሪዎቿ ለአፍሪካ ሀገራት ነጻነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የሚመጥን ተገቢ ዋጋ ነው። ይህንን መነሻ በማድረግ ለኢትዮጵያ መሪ ለኅብረቱ ምስረታ የጀርባ አጥንት ለነበሩት ነጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በኅብረቱ ጽህፈት ቤት ቅጥር ጊቢ መታሰቢያ ሃውልት እንዲቆምላቸው ወስኗል። ይህ ኢትዮጵያውያን በመሪዎቻቸው አማካኝነት ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጀምሮ እስካሁን አፍሪካ ኅብረት ድረስ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተሰጠ እውቅና ነው።

በወቅቱ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ያበረከተችው ተኪ የለሽ ሚና አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ እንዲህ ያስታውሱታል፤ “አፍሪካ ኅብረት ሲመሰረት ወጣት ዲፕሎማት ነበርኩኝ፤ ውጭ ጉዳይንም በሥራ ከተቀላቀልኩ የስምንት ወር እድሜ ብቻ ነበር ያስቆጠርኩት፤ በዚህ ወጣት እድሜዬ ከ32 ሀገራት መሪዎች ጋር መገናኘት ስሜቱ አስደሳች ነበር” ይላሉ።

እኤአ በ 1963 በግንቦት ወር ድርጅቱ ተመሰረተ እዚህ ላይ ለመድረስ ግን የኢትዮጵያ ሚና ላቅ ያለ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ ባትኖር ድርጅቱ አይቋቋምም ነበር ማለት ይቻላል የሚሉት አምባሳደር ቆንጂት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከንጉሥ ኃይለሥላሴ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ በሙሉ ኃይል የተነቃነቁበት እንደነበር ያስታውሳሉ።

ከታሪክ እንደምትረዱት በወቅቱ አፍሪካ ሞኖሮቪያና ካዛብላንካ በሚል በሁለት ተከፍላ የነበረ በመሆኑ ይህንን ሁለት ጎራ አስታርቆ ወደአንድ ማምጣት በጣም ከባድ ስራን ፣ትዕግስትና አልሸነፍ ባይነትን የሚጠየቅ ነበር። ኢትዮጵያውያን ግን በንጉሡ አማካይነት ከባዱን ውጣ ውረድ አልፈው ድርጅቱ እንዲመሰረት ቻርተሩም እንዲፈረም ማድረግ የቻሉበት ከዓድዋ ቀጥሎ ትልቅ ድል የተገኘበት ታሪካችን ነው ይላሉ።

በወቅቱ ከአጼ ኃይለሥላሴ ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ አቶ ከተማ ይፍሩ የነቃ ተሳትፎ በማድረግና ለድርጅቱ መመስረት ዋናዎቹ ተዋናይ ቢሆኑም ኢትዮጵያውያን እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሁሉ የተሳተፉበት ነበር ማለት እንደሚቻልም ነው የሚናገሩት።

በተለይም ንጉሡ አጼ ኃይለሥላሴ ስብሰባው እንዲካሄድ የአፍሪካ ኅብረት እንዲመሰረት በየሀገሩ በመዞር አልስማማ ያሉትን በማግባባት ደብዳቤዎችን በመጻፍ ብቻ በጣም በርካታ ሥራዎች ናቸው የተሠሩት፤ መጨረሻ ላይም ሁሉም በመስማማት ‹‹እሺ አዲስ አበባ ላይ እንገናኝ›› ብለው ወሰኑ በማለት ይናጋራሉ።

በሌላ በኩልም የኢትዮጵያን የሞኖሮቪያና የካዛብላንካውን ረቂቆች ማዋሃድ ነበረባት የሚሉት አምባሳደር ቆንጂት፤ ይህንን አስታርቆ እንደ ረቂቅ ለማውጣት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰራተኞች ዳይሬክተሮች ሚኒስትሮች ብቻ ሁሉም ሌት ተቀን ሰርተዋል። ስራውንም አጠናቀው አንድ ረቂቅ አዘጋጁ፤ ስምምነቱም የሚደረግበት ቀን ተቆረጠ ይላሉ ።

ወቅቱ እንደ አሁኑ ሁለ ነገር የተሟላበት ካለመሆኑ ጋር በተያያዘ ወረቀት የሚባዛው በእጅ ነበር። የ32 ሀገራት መሪዎችን ደህንነት የማስጠበቅ ጉዳይ እና መሪዎቹን በተመቻቹ ሆቴሎች ማሳረፍ ራሱን የቻለ ከባድ ኃላፊነት ነበር ። ከፍተኛ የገንዘብ አቅምን የሚጠይቅ ቢሆንም እኛ ኢትዮጵያውያን ላመንበት ነገር ወደኋላ የምንል ሕዝቦች ስላልሆንን ሁሉንም በአሸናፊነት ተወጥተን የዛሬውን የአፍሪካ አንድነትን እውን ማድረግ ተችሏል።

“ከሁሉም በላይ ከባድ የነበረው ቻርተሩን ማጽደቅ ነበር፤ ለሶስት ቀናት ከተወያዩበት በኋላ በመጨረሻው ቀን ቀኑን ሙሎ ያለእረፍት ዋሉበት፤ ምሽቱም መጣ በዚህን ጊዜ እራት እንብላና ተመልሰን እንምጣ ተባለ። በወቅቱ ግን አጼ ኃይለሥላሴ “እሺ መብላት አለብን ደክሞናል ግን ይችን ቋጭተን እንበላለን” ከማለታቸው ከቤተመንግሥት አስተናጋጆች መጥተው በእያንዳንዱ መሪ ፊት ሰሀን አስቀመጡ። ምግብ ደረደሩ ሃሳባችንን እየበላን እንሂድበት ብለው ንጉሡን አሳመኑ” ይላሉ አምባሳደር ቆንጂት።

ይህ አካሄድ እጅግ በጣም የረቀቀ የዲፕሎማሲ መንገድ ነው የሚሉት አምባሳደር ቆንጂት በወቅቱ እነዛ መሪዎች ለእራት እንውጣ እንዳሉት ቢወጡ አብዛኞቹ እንደማይመለሱ ንጉሱ ገብቷቸው ይህንን ማድረጋቸው የሚያስደንቃቸው ነው። በዛን ምሽትም ሌሊቱን ሙሉ የቀጠለው ስብሰባ ሊነጋጋ ሲል ቻርተሩን በማጽደቅ ተጠናቀቀ በማለት ይናገራሉ።

ኤሚሬት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ ሁሉም ሀገራት ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ስልቱ ላይ አለመስማማቶች ነበሩ። እንደ እነ ኑኩርማ ያሉት አሁኑኑ አንድ ሀገር እንሁን ሲሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ ናይጄሪያ ላይቤሪያ እና ሌሎች ደግሞ መጀመሪያ ኢኮኖሚያዊ አንድነት አግኝተን ነው ወደፖለቲካዊ አንድነት የምንሻገረው የሚል ሃሳብ ያቀነቅኑ ነበር።

እንደ ኤምሬት ፕረሮፌሰር ባህሩ ገላጸ የመጀመሪያው ጉባኤ ሲካሄድ የሞኖሮቪያና ካዛብላንከላ ሃሳቦች ተፋጠው ነበር የመጡት። አጼ ኃይለሥላሴም በተለይም ሴኩ ቱሬን በመጠቀም ኑኩርማ አቋማቸውን እንዲያለዝቡ በማድረግ የአፍሪካ እንድነት ድርጅት ቻርተር ሊፈረም መቻሉን ያስረዳሉ።

“……ሁኔታው አስገራሚ ብሎም ለማሰብ የሚከብድ ነገር ነበር። ሲመጡ ሁለት የተለያዩ ሃሳብ ያነገቡ ሰዎችን አንድ አድርጎ በመሸኘትም ኢትዮጵያና መሪዋ ላቅ ያለ ሚናን በመጫወት ታሪክ የማይዘነጋው ትልቅ ሥራ ሠርተዋል” ይላሉ።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን  የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You