ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ትልቅ ስትባል፤ የትልቅነቷ መሠረት የሆነው እና በትልቅነቷ እንድትገለጥ ያደረገው ሕዝቧ ነው። ትልቅ ሕዝብ ደግሞ ትልቅ ሀገር የሚሠራ እንደመሆኑ በትልቅነት ውስጥ ታላቅ ሆኖ መዝለቁ እሙን ነው። ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ይሄው የኅብር ገጻቸው የሆነው ትልቅነትና ታላቅነት ታዲያ፤ በሁሉም ቦታና በሁሉም ሁነትና ሁኔታ እየተገለጠ የዘለቀ ነው።
ትናንት በአልበገር ባይነቱ የነፃነትን ቀንዲል ለመላው አፍሪካውያን እና ጭቁን ሕዝቦች ያቀበለው ይሄ ኢትዮጵያዊነት ታዲያ፤ ዛሬም ከትናንት አባቶቹ በወረሰው የፓን አፍሪካኒዝም ልዕልናው አፍሪካውያንን በአንድ እያሰባሰበ ወደ ምሉዕ ሉዓላዊነታቸው እንዲሸጋገሩ እየተጋ ይገኛል።
ኢትዮጵያን የነፃነት ምልክትም፣ የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከልም እንድትሆን ያደረገው ይሄ ታላቅነት ታዲያ፤ አዲስ አበባም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ከተማነቷን የሚመጥን ኃላፊነቷን በብቃት እንድትወጣ እያደረጋት ይገኛል። በዚህም ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አኅጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ የመሪዎችም፣ የተቋማትም ጉባኤዎችን በስኬት የምታስተናግድ ከተማ ሆናለ ች።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይነት ጎልቶ የሚጠቀስ ተግባር ነው። ይሄ ሕዝባዊ እሴት ደግሞ እንግዶች በክብር ተቀብሎ ወደሚያስተናግዳቸው ሕዝብ ደጋግመው እንዲያማትሩም፣ እንዲመላለሱም የሚያደርግ ሲሆን፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተገነባ የመጣው የፀጥታና ደኅንነት ኃይሉ አቅም ደግሞ እንግዶች ስጋት እንዳያድርባቸው እያደረገ ይገኛል።
በዚህም ኢትዮጵያ በርካታ ዓለምአቀፍ ሁነቶችን ለማስተናገድ ተመራጭ ሀገር እየሆነች መጥታለች። በዛው ልክ የሕዝቦቿን ልዕልና፤ የዲፕሎማሲ መንገዷን ስኬታማነትም እየገለጠች ትገኛለች። የየትኛውም ዓለም መሪና ተቋም፣ አልያም ተወካይ ያለ ስጋት የሚጎበኛት፤ ያለ ችግር የሚስተናገድባት፤ ያለ መሳቀቅ ጉዳዩን ፈጽሞ የሚመለስባት ትልቅ ሀገርነቷንም እያስመሰከረች ነው።
የሰሞኑ 37ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤም የዚህ አንድ ማሳያ ሲሆን፤ በተለይ ብዙዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሠላም የለም በሚል ሂደቱን ለማደናቀፍ ሲውተረተሩ የነበረበትን ሁነት ቀዝቃዛ ውሃ የቸለሰበት ነበር። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የደረሰችበትን ደረጃ፤ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ ለአፍሪካውያን ወንድም ሕዝቦችና መሪዎቻቸው ያላቸውን ከፍ ያለ ቦታ በአደባባይ የገለጠ ሆኗል።
ምክንያቱም፣ ጉባኤው የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ፣ ኢትዮጵያ እንደ ኅብረቱ መቀመጫ ሀገርነቷ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጋለች። በተለይ ከሠላምና ፀጥታ፣ ከሆቴልና ሌሎችም የሎጀስቲክስ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተገቢው ዝግጅት ተደርጓል። በጥቅሉም መሪዎቹ ለጉባኤው መሳካት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ሙሉ ደህንነትና ምቾታቸው ተጠብቆ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል።
መሪዎቹ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጀምሮ ተገቢው አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፤ በሆቴል ቆይታቸው ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያደርጓቸው ዝግጅቶችም ነበሩ። በከተማዋ በሚኖራቸው ቆይታም የደህንነት ሥጋት እንዳይሰማቸው ያደረገው የፀጥታ ኃይሎች ዝግጅት በተግባር የተገለጠባቸው ሁነቶች ደግሞ ለጉባኤው በስኬት መጠናቀቅ የነበራቸው አበርክቶ ከፍ ያለ ድርሻ ነበረው።
በተለይ ቀደም ብሎ ሲራገብ ከነበረው አሉባልታ አኳያ የፀጥታና ደህንነት ኃይሉ ሲያከናውን የነበረው ከፍ ያለ ተግባር፤ ኢትዮጵያ ከትናንቱ በላቀ መልኩ ዛሬ በዘርፉ አቅም መገንባቷን፤ ነገም የትኛውንም አህጉራዊም ሆነ ዓለምአቀፋዊ ሁነት ያለምንም የፀጥታ ሥጋት ማካሄድ እንደምትችል አቅሟን የገለጠችበት ሆኗል።
የፀጥታና ደህንነት ኃይሉ ደጀን የነበረው እንግዳ ተቀባዩ ሕዝብም፣ ለኅብረቱ ጉባኤ መሳካት የነበረው አበርክቶ ተኪ የሌለው ነው። በጥቅሉ የኅብረቱ ጉባኤ በስኬት ለመጠናቀቁ፣ የፀጥታ ኃይሉ ትጋትና ቅንጅት፤ እንዲሁም የሕዝቡ ተባባሪነትና እንግዳ ተቀባይነት ወሳኝ ነበር።
ለዚህ አኩሪ ተግባርም ሁሉም አካል ሊመሰገንም፤ ተገቢውን እውቅና ሊቸርም የሚገባው ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ቤታቸው፣ ኢትዮጵያውያንንም ሕዝባችን ብለው በጉባኤው በመሳተፍ ለጉባኤው ስኬታማነት የድርሻቸውን ለተወጡ አፍሪካውያን ወንድም መሪዎችም ክብርም፣ ምስጋናም ይገባቸዋል። ምክንያቱም የዚህ ድምር ውጤት ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያን ትልቅነት፣ የኢትዮጵያውያንንም ታላቅነት አረጋግጧልና!
አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም