ልብ ብላችሁ ከሆነ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ይላሉ:: ‹‹ምናባቱ ደግሞ ለመንግሥት ገንዘብ!›› የራሴ አይደለም አይቆጨኝም እንደማለት ነው:: አንድ ሰው የግሉን ነገር ሲያባክን ሲያስተውሉ ‹‹የመንግሥት ንብረት አደረከው እኮ!›› ይላሉ:: በጥንቃቄ ያዘው ማለታቸው ነው፤ የመንግሥት ከሆነ ግን ቢባክንም ችግር የለውም እንደማለት ነው:: ብዙ ሰዎች በቤታቸው የማያደርጉትን ነገር የሚያደርጉት የመንግሥት ተቋም ውስጥ ነው:: ውሃ ሳይዘጉ መሄድ፣ የኤሌክትሪክ ገመዶችን እና ማከፋፈያዎችን ማበላሸት፣ በር በኃይል መወርወር፣ የበር እጀታ መገንጠል… እነዚህን እና የመሳሰሉት መረን የለቀቁ ግዴለሽነቶች የሚደረጉት በመንግሥት ተቋም ውስጥ ነው:: የቤቱን ዕቃዎች ግን በጥንቃቄ ይይዛቸዋል:: በዚህ ሁኔታ ብዙ የመንግሥት ንብረት ይባክናል፤ ሕዝብ ግን በአገልግሎት ይቸገራል::
የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር እንኳን ነዋሪው አዲስ አበባን የረገጠ ሁሉ የሚያውቀው ነው:: በትራንስፖርት ምክንያት ብዙ ጊዜ ይባክናል:: የአንድ የታክሲ ሰልፍ ርዝመት ከአንድ የታክሲ ፌርማታ አያንስም:: የመጨረሻው ሰልፍ ጋር ለመድረስ ታክሲ ያስፈልጋል እየተባለ ሁሉ ይቀለዳል::
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በትንሽ ብልሽት ምክንያት አገልግሎት አቁመው የሚባክኑ ብዙ ተሽከርካሪዎች አሉ:: በመንግሥት ተቋም ግቢ ውስጥ ብዙ ተሽከርካሪዎችን ታያላችሁ:: ከእነዚያ ውስጥ ግን ምናልባትም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አገልግሎት የማይሰጡ ናቸው:: በአንድ ትንሽ ብልሽት ምክንያት ቆመው ሙሉ ለሙሉ ለመበላሸት የተዘጋጁ ናቸው:: ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው በአቧራና ጭቃ የዛጉ ናቸው:: በትንሽ ብር ይስተካከል የነበረው ችግር ባለመስተካከሉ በሚሊዮን የተገዛ ተሽከርካሪ ከጥቅም ውጪ ይሆናል ማለት ነው::
ችግራቸው በጣም ቀላል መሆኑን የነገረኝ በተከራየሁበት ግቢ ውስጥ ያለ አንድ የአንበሳ አውቶቡስ አሽከርካሪ ነው:: ከከባድ ተሽከርካሪዎች እስከ ትንንሽ ተሽከርካሪዎች በትንሽ ብልሽት ምክንያት ሥራ ያቆሙ ብዙ ናቸው:: አሽከርካሪው እንደ ባለሙያ ስለሚያውቀው አንዳንዶቹ በቀላሉ ችግራቸው አንድ ሰዓት እንኳን የማይወስድ፣ አምስት ሺህ ብር እንኳን ወጪ የማያስወጣ መሆኑን ታዝቧል:: በትንሽ ችግር ምክንያት ሥራ ያቆመ ተሽከርካሪ እያለ ተቋሙ ግን ለአንዳንድ ሥራዎች ብዙ ወጪ አውጥቶ ኮንትራት ይዋዋላል:: ወይም በውድ ዋጋ ሌላ ተሽከርካሪ ይገዛል:: ወይም ከዛሬ ነገ በሚል ቸልተኝነት የሥራ መስተጓጎል ይፈጠራል:: የተሽከርካሪው ችግር ግን ምናልባትም ጎማ መቀየር ሊሆን ይችላል::
የትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ ተብሎ ብዙ አይነት አማራጮች ሲነገሩ እንሰማለን:: አሁን ባለው የምንዛሪ ውድነት ከፍተኛ ወጪ ወጥቶ ተሽከርካሪዎች ይገዛሉ:: ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በጥቂት ወጪ መስተካከል የሚችሉት ተሽከርካሪዎች ላይ ትኩረት አይደረግም:: የማሽን ዕቃ ነውና አገልግሎት ሳይሰጥ በቆየ ቁጥር እየዛገ እና የበለጠ እየተበላሸ ይሄዳል:: በዚህም ምክንያት ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ይሆናሉ::
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ከሦስት ዓመት በፊት በሠራው ዘገባ፤ ተበላሽተው የቆሙና መወገድ ያለባቸው ከሁለት ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች በመንግሥት ተቋማት ተገኝተዋል:: ሌሎች የንብረት አይነቶችም ተበላሽተው መወገድ እንደሚገባቸው የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በወቅቱ አስታውቋል:: በዚያው ዘገባ ውስጥ፤ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ በንብረት ምዝገባው በብልሽት ምክንያት የቆሙና ሊወገዱ የሚገባቸው 2 ሺህ ተሽከርካሪዎች ውስጥ በቀላል ጥገና የሚሰሩ አሉበት ብለዋል:: ይሄ ማለት እንግዲህ ብዙ ክትትል ቢደረግ በየመሥሪያ ቤቱ ሥራ አቁመው ፀሐይና ዝናብ ከሚፈራረቅባቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ በቀላል ጥገና አገልግሎት የሚሰጡ ነበሩ ማለት ነው::
በወቅቱ በተደረገው የምዝገባ ሂደት፤ 200 የሚጠጉ ማሽነሪዎች፣ 700 ሺህ ኪሎ ግራም ቁርጥራጭ ብረቶች፣ 40 ሞተር ብስክሌቶች እና ሌሎች ንብረቶች መገኘታቸው ይፋ ተደርጎ ነበር::
እንግዲህ ምን ያህል ንብረት እንደሚባክን ልብ በሉ:: ይህ በአንድ ሪፖርት ወይም በአንድ ቃለ መጠይቅ (ለዚያውም ከሦስት ዓመት በፊት) የተገኘ ብቻ ነው:: የተበላሹት ተሽከርካሪዎች ተሸጠው የሚያስገኙት ገቢ ይኖር ይሆናል:: ዳሩ ግን ተበላሽተው ሲሸጡ ከሚያስገኙት ገቢ ቀላሉን ብልሽት በማስተካከል የሚሰጡት አገልግሎት ይበልጥ ነበር:: ሲበላሹ ንብረትነታቸው ብቻ አይደለም መታየት ያለበት:: አንድ ተሽከርካሪ ሲበላሽ የተገዛበት ዋጋ ሳይሆን መታየት ያለበት ይሰጠው በነበረው አገልግሎት ያጣነውን ጥቅም ነው:: በትራንስፖርት ችግር ምክንያት የባከነውን ጊዜ እና የሰው ኃይል ነው ማሰብ ያለብን:: ሥራ ላይ ከሚውለው ጊዜ ይልቅ ለትራንስፖርት ሰልፍ የሚውለው ጊዜ ሊበልጥ ነው ማለት ነው::
ይህ በተሽከርካሪ ብቻ የታዘብነው ነው:: ሌሎች የመንግሥት ተቋም ንብረቶችን ልብ በሉ:: ከጠረጴዛ እና ወንበር እስከ ትልልቅ ንብረቶች በጥንቃቄ ጉድለት ይበላሻል፤ በዚያው ይባክናል:: የመንግሥት ንብረት ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ብዙ ሰው በግዴለሽነት ይጠቀምበታል:: ቤታችን ውስጥ ላለው ወንበር ወይም መስታወት የምናደርገውን ጥንቃቄ መሥሪያ ቤታችን ውስጥ ላለው ወንበር ወይም መስታወት ጥንቃቄ አናደርግም:: ይህ እጅግ ሲበዛ ኋላቀርነት ነው::
የመንግሥት ንብረት ሲባል ግን የማን ይሆን? ይህንን እንኳን ማሰብ የተሳነን ነን:: የመንግሥት ንብረት ሲባል የሕዝብ ንብረት ማለት ነው:: እነዚያ በግዴለሽነት የምናበላሻቸው መገልገያዎች በከፊል ግብር የተገዙ ናቸው:: ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚበጀተው በጀት የሕዝብ ገንዘብ ነው:: የመንግሥት ገንዘብ ሲባል ከየት የሚመጣ እየመሰለን ይሆን?
እንደ ሕዝብ ይህ የግንዛቤ ችግር አለ:: እንደ መንግሥት ደግሞ እጅግ ሲበዛ ግዴለሽነት ይታያል:: ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል የለም:: ለምሳሌ፤ አንድ የፌዴራል ተቋም ተበላሽተው የቆሙ ተሽከርካሪዎች አሉት እንበል:: የተቋሙ አመራሮች ምን ሆነው እንደቆሙ ለምን አይጠይቁም? እንደ ችግሩ መጠን ለምን እንዲስተካከል አያደርጉም? በአንዲት ትንሽ ችግር የቆመ መኪና ሲኖር እንዴት አይቆጫቸውም?
አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ወይም የመንግሥት ተቋም፤ ለሌላው ሕዝብና ተቋም አርዓያ ነው መሆን ያለበት:: የዝርክርክነት እና የብክነት ምሳሌ መሆን የለበትም:: የግዴለሽነት እና የምን አገባኝነት ስሜት የሚንፀባረቅበት መሆን የለበትም:: የተበላሹ እና የቆሸሹ ነገሮች የሚታዩበት መሆን የለበትም:: ለሀገርና ለሕዝብ ኃላፊነትን የመወጣት ተምሳሌት መሆን ነው የሚገባው:: ለዚህ ደግሞ ተራው ሠራተኛም ሆነ ከፍተኛ ኃላፊዎች በኃላፊነትና በተቆርቋሪነት ሊሠሩ ይገባል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም