ቀይ ባህር በአፍሪካ እና በእስያ መካከል የሚገኝ የውሃ አካል ሲሆን ትልቅ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦሎጂካል ጠቀሜታ አለው። ባህሩ በምዕራብ ከግብፅ፣ በምሥራቅ ሳውዲ አረቢያ እና በደቡባዊ ሱዳን ይዋሰናል ይህም ለንግድ እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ስትራቴጂካዊ ቦታ ያደርገዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን ያሉ ሀገራት በቀጣናው ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ስለሚፎካከሩ የቀይ ባህር የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ማዕከል ሆኗል። ባሕሩ በየቀኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የነዳጅ በርሜሎች ማስተላለፊያ መንገድም ነው።
ቀይ ባህር ከፖለቲካዊ ጠቀሜታው በተጨማሪ የተፈጥሮ ሀብትና የብዝሀ ህይወት ባለቤት ነው። ባህሩም ለዘመናት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ለኢትዮጵያ ወሳኝ የንግድ መስመር ሆኖ ከዓለም ጋር በማገናኘት ወደ ሀገር ውስጥ እንድታስገባ እና ወደ ውጭ እንድትልክ ለዘመናት ሲያስችላት ቆይቷል።
በወቅቱ ኢትዮጵያ የአክሱም መንግሥት በመባል ትታወቅ የነበረች ሲሆን በአካባቢው ትልቅ የንግድ ኃይል ነበራት:: ሀገሪቷም በቀይ ባህር አቅራቢያ በመገኘቷ በአፍሪካ፣ በአረብ እና በህንድ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለመቆጣጠር አስችሏት ቆይቷል::
በቀይ ባህር ላይ የአክሱም ስርወ መንግሥት የዝሆን ጥርስ፣ ወርቅ፣ ቅመማ ቅመም፣ ጨርቃጨርቅ እና የተለያዩ ሸቀጦችን ይገበያይ ነበር። በእስላማዊው ወርቃማ ዘመን (Islamic Golden Age) ቀይ ባህር ለሙስሊም ነጋዴዎች ጠቃሚ የንግድ መስመር ሆኖ ነበር። የኢትዮጵያ ነጋዴዎችም እንደ እጣንና ከርቤ ያሉ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ በንግዱ ተሳትፈዋል።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓ ኃያላን በቀይ ባህር አካባቢ ፍላጎት ማሳየት ጀመሩ:: ኢትዮጵያ ባላት ስልታዊ አቀማመጥ እና ቅኝ ካልተገዙ ሁለት የአፍሪካ ሀገራት አንዷ በመሆኗ የአውሮፓ ትኩረት ሆነች። እንደ እንግሊዝ እና ጣልያን ያሉ የአውሮፓ ኃያላን በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር እና የቀይ ባህርን ተደራሽነት ለመቆጣጠር ጥረት ማድረግ ጀመሩ።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ የቀይ ባህር መዳረሻ በኢትዮጵያና በኤርትራ ጦርነት ወቅት አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ነበር። የኢትዮጵያ ግዛት ስር የነበረችው ኤርትራ በሕዝበ ውሳኔ በግንቦት 16፣ 1985 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ነጻ መውጣቷን ተከትሎ፤ በቀይ ባህር የሚገኘውን የአሰብ ወደብን ተቆጣጠረች። ይህም ኢትዮጵያ በቀጥታ የባህር መዳረሻ እንዳትሆን አድርጓል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ጋር በምታደርገው የንግድ ልውውጥ የጅቡቲ ወደብ ትጠቀማለች። ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ቀጥተኛ መዳረሻ ባይኖራትም አሁንም የቀጣናው ጠቃሚ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አጋር ናት።
በፖለቲካው ኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች የባህር መዳረሻዋን ለማስፋት ስትፈልግ ቆይታለች። ከእነዚህ መንገዶች አንዱ እንደ ጅቡቲ እና ሶማሌላንድ ባሉ የጎረቤት ሀገራት ወደቦች ማልማት ነው። እነዚህ ወደቦች ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ተጠቃሚ እንድትሆን ከማድረጉም በላይ ሸቀጣ ሸቀጦችን ወደ ውጭ እንድትልክ እና እንድታስገባ አስችሏታል።
በኢኮኖሚ ዘርፍ ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ ጠቃሚ የንግድ መስመር ነው። ባህሩ በኢትዮጵያ እና በተቀረው ዓለም መካከል ወሳኝ የሆነ ትስስር በመፍጠር እቃዎቿን ወደ ውጭ እንድትልክ እና አስፈላጊ ግብዓቶችን እንድታስገባ ያስችላታል። በአሁኑ ሰአት ኢትዮጵያ ቀይ ባህር ታሪካዊ መዳረሻዋ ቢሆንም እንደቀደምት ተጠቃሚነቷ ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት አልቻለችም:: ለዚህም ማሳያው ኢትዮጵያ 95 በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን የንግድ ልውውጥ የምታስተናግደው በጅቡቲ ወደብ ላይ በእጅጉ ጥገኛ በመሆን ነው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ለ30 ዓመታት በቀይ ባህር ጉዳይ የበይ ተመልካች ሆና ቆይታለች::
አሁን ግን ሀገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምረውን የሕዝብ ቁጥርና የገቢ እና ወጪ ንግድ ለማሳለጥ በለውጡ መንግሥት በቀጣናው የባህር በር ጥያቄ ተነስቷል:: በዛሬው ወቅታዊ አምዳችን የቀይ ባህር እና የባህር በር ጥያቄን አስመልክቶ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ከሆኑት አቶ ሙሉአለም ኃይለማርያም ጋር ቆይታ አድርገናል::
አዲስ ዘመን፡- የባህር በርን አስመልክቶ ዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ ምን ይላል?
አቶ ሙሉአለም፡- ዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ ድንበር ተሻጋሪ ለሆኑ የውሃ አካላት የራሱ የሆነ ሕግ አስቀምጧል:: ነገር ግን ባህር ከአንድ ሀገር ወደሌላ ሀገር የሚፈስ ወይም የሚንቀሳቀስ አይደለም:: ቢሆንም ድንበር ተሻጋር ያልሆኑ የውሃ አካላትን የምንጠቀምበት መንገድ(ሜካኒዝም) አለው:: ለመጓጓዣ(ናቪጌሽን) እና ለምርምር(ለኤክስፕሎሬሽ) አገልግሎት ሲሆን የራሱ የሆነ በኪሎ ሜትር የተወሰነ የአጠቃቀም ሥርዓት አለው:: ነገር ግን ለባህር በር አገልግሎት ሲሆን ዩናይትድ ኔሽን ኮንቬንሽ ኦን ዘ ሎው ኦፍ ዘ ሲ(united nation convention on the law of the sea) በ1983 የወጣ እና እስካሁንም በአገልግሎት ላይ ያለ ስምምነት ተግባራዊ ይደረጋል:: ይህ ኮንቬንሽን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በምን አግባብ የባህር በር መጠቀም እንደሚችሉ ይደነግጋል:: ነገር ግን ይህ ሕግ ፍጹማዊ(አብሶሊዩት) የማይለወጥ ሕግ አይደለም::
ኢትዮጵያ እና ሌሎች እንደኢትዮጵያ ያሉ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የባህር በር ለማግኘት የሚያስችላቸው ሶስት መንገዶች አሉ::
የመጀመሪው፤ ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ በሰቶ መቀበል ሕግ ነው:: ይህም ሲባል ቀላል አይደለም ሰጥቶ ለመቀበል ኢትዮጵያ ካሏት ሀብቶች ውስጥ የህዳሴው ግድብን፤ የእርሻ መሬትን፤ ቴሌኮምን፤ አየር መንገድ የመሳሰሉ ሀብቶችን የተወሰነ ድርሻ ሰጥቶ በምትኩ ወደብ ማግኘት የሚል ነው::
ሁለተኛው፤ ከሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን ወደብን በማልማት መጠቀም ነው:: ለምሳሌ ብናነሳ የበርበራ ወደብ 19 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ አልምቶ የመጠቀም ስምምነትን ማንሳት እንችላለን:: ሶስተኛው እና የመጨረሻው አማራጭ በኃይል የወደብ ፍላጎትን ማሳካት የሚል ነው:: የዓለም አቀፍ ሕግም የሚለው ይህንን ነው ::
አዲስ ዘመን፡- ሀገራችን የባህር በር እንድታገኝ የሚደግፉ የሕግ ማእቀፎች አሉ?
አቶ ሙሉአለም፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዩናይትድ ኔሽን ኮንቬንሽ ኦን ዘ ሎው ኦፍ ዘ ሲ (united nation convention on the law of the sea) በኋላ ብዙም ስለወደብ የሚያወሩ የሕግ ማእቀፎች አልወጡም:: ሆኖም ግን በየቀጣናው የሚወጡ ሕጎች አሉ:: እነዚህ ሕጎችም ቢሆኑ ይህንን የባህር በር እከሌ ለሚባል ሀገር ስጡ የሚል አይደለም:: በትብብርና በጋራ በመሆን ወደብን በማልማት እንዲጠቀሙ የሚያደርግ ነው::
ለኢትዮጵያ ይህንን ያህል በመቶ ከቀይ ባህር ላይ ትውሰድ የሚል ሕግ የለም:: ነገር ግን ኢትዮጵያ በታሪክ የምታነሳቸው ጥያቄዎች አሉ:: ኢትዮጵያ እስከ የመን ድረስ ግዛቷ የነበረ ቢሆንም፤ ዓለማችን በየእለቱ ተቀያያሪ በመሆኗ አሁን የባህር በር የሌላት ሀገር ሆናለች:: ነገር ግን አሁንም ያበቃለት ነገር አይደለም በሚቀጥሉት ጊዜያት ልናገኝ የምንችልባቸው እድሎች አሉ፤ የተዘጋ ነገር አይደለም::
ሕጉ የሚደግፈው ከኤርትራ ߹ ከጅቡቲ ጋር በትብብር እንድንሰራ ነው:: ይህንን ለማድረግ ጠንከር ያሉ የዲፕሎማሲ ስራዎች ይጠይቃሉ:: ኢትዮጵያ በዚህኛው አካሄድ እንደ አዲስ ወደብ የምታገኝበት ሳይሆን ከዚህ ቀደም የነበራትን ወደብ የምትጠይቅበት ነው:: በኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ውስጥ የወደብ ባለቤት የነበረች ሀገር ናት::
ኢትዮጵያ በታሪኳ ወደብ ያጣችው ኤርትራ በጣሊያን ቀኝ ግዛት ውስጥ በነበረችበት ጊዜ እና ኢህአዴግ ወደ ስልጣን በመጣበት ወቅት ነበር:: ስለዚህ ያሉት ህጎች በግድ ወይም በሃይል የሚባለውን ነገር የሚደግፉ ሳይሆኑ በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ እና በሰቶ መቀበል መርህ ወደብ እንድታገኝ የሚደግፉ ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- የባህር በርን በሰላማዊ መንገድ እንድናገኝ ምን አይነት የዲፕሎማሲ ስራዎች መሰራት አለባቸው?
አቶ ሙሉአለም፡- ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝባቸው እድሎች አሉ:: ከ1890 እስከ 1940 ኤርትራ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ስር ነበረች:: ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት ኤርትራ በሪፈረንደም ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሃድ ማድረግ ችለዋል:: ይህ የዲፕሎማሲ ሥራም ኤርትራና ሕዝቦቿን ከመመለስ ባሻገር ኢትዮጵያ የባህር በር እንድናገኝ አድርጓታል:: በዚህ ሂደት ውስጥ ጦር አልተማዘዙም:: ሂደቱን ማሳካት የቻሉት በሁለት መንገድ ነበር:: አንደኛው ከኤርትራ ሕዝቦች ጋር ባለን የታሪክ እና የባህል ቁርኝት በመጠቀም ሲሆን፤ በዚህ ሂደት ውስጥ በዓድዋ ጦርነት ጊዜ አጼ ምኒልክ ኤርትራን ለጣሊያን ትቷታል በሚል ያኮረፉ አካላትን የማስማማት ሥራ ተሠርቷል:: በሌላ በኩል አንድ ሕዝቦች ነን በደም የተሳሰርን ነን የሚሉ ወገኖች በመኖራቸው ያንን ተጠቅመው ሪፈረንደሙን ማሳካት ችለው ነበር::
ሁለተኛው መንገድ ደግሞ በወቅቱ ከነበሩ ኃያላን ሀገራት ጋር ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጠንካራ የሆነ የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት ኤርትራን የኢትዮጵያ አንድ ግዛት ማድረግ ችለዋል:: በ1950ዎቹ እንግሊዝ ኢትዮጵያን በመርዳት ከጣሊያን ቅኝ ግዛት ማስለቀቅ ስለቻለች ኤርትራን ለመልቀቅ ለበርካታ ዓመታት ፍላጎት አልነበራትም:: ነገር ግን በመጨረሻ በጠንካራ ዲፕሎማሲ ኤርትራ የኢትዮጵያ አንድ አካል ሆነች:: በዚህም አጥታ የነበረውን የባህር በር ማስመለስ ችላ ነበር::
አሁንም ኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎቷን በሁለት መንገድ ማሳካት ትችላለች:: የመጀመሪያው ከሚመለከታቸው ሀገራት ጋር ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን በመሥራት ሲሆን፤ በተለይም በቀጣናው የባህር በር ካላቸው ሀገራት ጋር ማለትም ከኤርትራ፤ ከጅቡቲ እና ከሱማሊያ ጋር ጠንካራ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር መፍጠር አስፈላጊ ነው:: ጎረቤታችን ከሆነችው ኤርትራ ጋር የምጽዋን እና የአሰብን ወደብ ለመጠቀም ቅርብ በመሆኗ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራዎች መሥራት ይጠበቅብናል::
በኤርትራ በኩል የማይሳካ ከሆነ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ያስፈልጋል:: ለሰጥቶ መቀበል መርሁ መሳካት እጅግ አጓጊ ነገሮችን ይዞ መቅረብ ያስፈልጋል:: ይህ ዓይነቱ አካሄድ ዓመታትን ሊወስድ ይችላል:: ለምሳሌ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጊዜ የነበረው የባህር በር የማስመለስ ሂደት በአጠቃላይ ለ10 ዓመታት የቀረበ ጊዜን የወሰደ ነበር::
እንደበርበራ ያሉ ወደቦችን የማልማት ሂደትም ጠቃሚ ነው:: ይህንንም ለማሳካት ዲፕሎማቶች ብቻ ሳይሆኑ መንግሥታትም ጭምር ትኩረት ሰጥተው ሊጓዙበት ይገባል:: ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን እና ውይይቶችንም ማድረግ ጉዳዩን ሊያፈጥነው ይችላል:: በተጨማሪም ኃያላን ሀገራትን ማነጋገር ያስፈልጋል:: በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ ሀገራት የሆነ ነገር ሰጥተው በምትኩ ሌላ ነገር በመቀበል ነው የሚሰሩት፤ በመሆኑም ኃያላን ሀገራት በቀጣናው ላይ ያላቸውን ፍላጎት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ውይይቶች እና የዲፕሎማሲ ሥራዎችን መስራት ይኖርብናል::
ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገራት ጋር በትብብር መስራትና ሰጥቶ የመቀበል ፖሊሲን መከተል ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው:: ይህም አስፈላጊ የሆነው ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉላት ለማስቻል ነው:: ይህንን ማድረግ ከተቻለ ኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎቷን የማሟላቷ ነገር በሰላማዊ መንገድ እውን መሆን ይችላል::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የባህር በር ያላት ሀገር መሆኗ ይታወቃል:: በታሪክ አጋጣሚ የባህር በር ኖሯቸው የማያውቁ በመሬት የተከበቡ ሀገራት የባህር በር ካላቸው ሀገራት ጋር ያላቸው የግንኙነት ተሞክሮ ምን ይመስላል?
አቶ ሙሉአለም፡- በታሪክ አጋጣሚ የባህር በር ኖሯቸው የማያውቁ ሀገራት የባህር በር ካላቸው ሀገራት ጋር ያላቸው ግንኙነት ለወደብ በሚከፍሉት ዓመታዊ የገንዘብ ክፍያ ላይ የተመሰረተ ነው:: ልክ አሁን ኢትዮጵያ ለጅቡቲ እንደምትከፍለው ማለት ነው:: ነገር ግን በአፍሪካ እና በሳውዝ አሜሪካን ያሉ አንዳንድ ሀገራት በአቅራቢያቸው ከሚገኙ የባህር በር ካላቸው ሀገራት በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር ፍላጎታቸውን ሊያሳኩ የቻሉ አሉ::
ኢትዮጵያ የባህር በር ቢኖራት በቀይ ባህር ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራት ከማድረግ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷ እና የውጭ ኢንቨስተሮችን ቁጥር የመጨመር እድሏን እጅግ ከፍ ያደርገዋል:: ፖለቲካዊ ተሰሚነቷን እና የደህንነቷን(security) ጉዳይም ታጠናክራለች::
አዲስ ዘመን፡- አሁን ኢትዮጵያ ያነሳችው የባህር በር ጥያቄ ምን ያህል ተገቢ ነው?
አቶ ሙሉአለም፡– በአሁኑ ሰዓት አየሩን ከያዙ ነገሮች መካከል የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ዋጋ የሌለው አድርጎ የማየት ነገር ነው:: በየማህበራዊ ሚዲያው ብንመለከት የኢትዮጵያን የባህር በር ተገቢነት የሌለው አድርገው የሚመለከቱ በርካታ ሰዎችን እናያለን፤ ይህ ትክክል አይደለም:: የኢትዮጵያ የባህር በር ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከመጡ በኋላ የተነሳ ጥያቄ አድርጎ የሚያስብ ሰውም አለ:: መሬት ላይ ያለው ሀቅ ግን በመንግሥታት ለውጥ ውስጥ ኢትዮጵያ የባህር በር ባልነበራት ጊዜያት ውስጥ ሁሉ ሲጠየቅ የነበረ ጥያቄ መሆኑ ነው::
በተለይም 1890 በኋላ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በdomestic politics ትልቅ ቦታ አላቸው የሚባሉት አፄ ምኒልክ ወደ ደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅ እና ደቡብ ምዕራብ ያደረጉት ዘመቻ አላማው ሰዎችን ግብር አስገብሮ ለማዕከላዊ መንግሥት ገቢ እንዲያደርጉ አልነበረም:: አንዱ አላማቸው የዛን ጊዜዋን ዜይላ የአሁኗን ጅቡቲ መቆጣጠርና የኢትዮጵያ አካል ማድረግ ነበር፤ ባይሳካላቸውም:: ስለዚህ ምኒልክ ጦር ጭምር አዝምተው ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንድትሆን ጥረት አድርገዋል::
ቀጥሎ የመጣው ልጅ እያሱም ሕፃን ቢሆንም ስለሱ የተፃፉ ፅሁፎችን ብንመለከት ‘አንድ ቀን ግመሎቼ የቀይ ባህርን ውሃ ይጠጣሉ’ ይል እንደነበር እናያለን:: ንግግሩ ውስጥ ምኞት እንደነበረው መመልከት እንችላለን፤ የባህር በር ጥያቄ ነበረ ነው::
ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ከተቀላቀሉ በኋላ ከEPLF (Eritrean people liberation front) ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል ያደረጉት ለሁለት ምክንያቶች ነበር:: ግዛታዊ አንድነቱን ማስጠበቅ(ሉአላዊነትን ማስከበር) እና ኤርትራ ከተገነጠለች ወደብ እናጣለን የሚል ስጋትም ስለነበር ነው:: የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ሳይደረግ ይቆይ በሚል እንጂ ጉዳዩ አይነሳም ብለው አላሰቡም ነበር:: ቀጥለው የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም አንዱ አጀንዳቸው ይሄው የወደብ ጉዳይ ነበር:: እንዳሁኑ ጎልቶ በየሚዲያው አይወጣም እንጂ የባህር በር ጥያቄ ኢትዮጵያ የባህር በር ባጣችባቸው ጊዜያት ሁሉ በመንግሥታት ለውጥ ውስጥ የነበረ ትልቅ ጥያቄ ነው::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቴሌቪዥን መስኮቶች መጥተው ሃሳቡን ከማንሳታቸው በፊት የባህር በር ሳይኖረን የባህር ኃይል አደራጅተናል:: ይህ ተግባራቸው ወደፊት የባህር በር ሊኖረን ይችላል የሚል ነው::
አሁን ባለንበት ጊዜ ሊበራል የሆነው ዓለም ስለበዛ፣ ነጻ ገበያ የበላይነቱን ስለያዘ፣ ትልልቅ ኢንቨስተሮች ከሀገር ወደ ሀገር እየሄዱ ኢንቨስት የሚያደርጉበት ጊዜ ከመሆኑ የተነሳ የባህር በር ቢኖረን በኢኮኖሚው ጠቀሜታው ከፍተኛ በመሆኑ የወጣቱን የማህበረሰብ ክፍል ፍላጎትና የሥራ እድል ጥያቄ ሊያቀዘቅዝልን የሚችል ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል:: ስለዚህ የባህር በር ጥያቄው ተገቢ ነው ወይ? አዎ ተገቢ ነው:: ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካ እንዲሁም ከደህንነትም አንፃር ካየነው ጥያቄው ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ:: ምክንያቱም በባህር በር በኩል የራሳችን ድርሻ ሊኖረን ይገባል:: እድሉ ኖሮን የባህር በር ጥያቄያችን ቢመለስልን በዚህ ምክንያት ብቻ አብረውን ሊሰሩ የሚችሉ በርካታ ኃያላን ሀገራት እንደሚኖሩ አልጠራጠርም::
አዲስ ዘመን፡- ይህ የባሕር በር ጥያቄ በዚህ ወቅት መነሳቱ ተገቢ ነው?
አቶ ሙሉአለም፡- የግብርና፣ የትምህርት እና የጤና ፖሊሲ ብለን እንደምናወጣው የውጭ ፖሊሲም አንዱ የፐብሊክ ፖሊሲ አካል ነው:: ስለባህር በር ስናወራ ስለውጭ ፖሊሲ እያወራን ነው:: ሀገሪቱ የውስጥ ችግሮች ስላሉባት የግብርና፣ የትምህርት እና የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ መደረጉን አላቆመም::
በእርግጥ በውጭ ፖሊሲ ይሄ ተገቢ ጊዜ ነው፤ ይሄ ተገቢ ጊዜ አይደለም የሚባሉ ነገሮች አሉ:: በኔ እምነት ግን ጉዳዩን አነሳን ማለት በኃይል እናሳካለን ማለት አይደለም:: በኃይል እናሳካለን የሚል ነገር በሌለበት ዛሬም ነገም ጉዳዩን በየቀኑ ትኩረት ሰጥተን እያነሳን ብንሄድ ስህተት የለውም ባይ ነኝ::
የባህር በር ጥያቄው ጊዜው አይደለም ለሚሉ ሰዎች፤ ትምህርት አላቆምንም፤ ጤና አገልግሎት አላቆምንም፤ በግብርናው ዘርፍም ቢሆን ምርት ማምረት አላቆምንም:: ይሄም አንድ እንደ ውጭ ፖሊሲ መርህ የማናቆመው ዛሬም ነገም የምናነሳው ጉዳይ ስለሆነ ጥያቄው መነሳቱ ተገቢ ነው፤ ወቅታዊ ጉዳይም ነው::
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም ወደነበሩ ዘመናት እንመለስና ኢትዮጵያ የባህር በር በነበራት ወቅት የነበረችበት ከፍታና የባህር በር ካጣች በኋላ ያለችበትን ሁኔታ በንፅፅር እንዴት ልንገልፀው እንችላለን?
አቶ ሙሉአለም፡- የባህር በር በነበረን ጊዜ የሚያዳምጠን ብዙ ነው:: በቀጥታ ተሳትፎ የምናደርግባቸው ጉዳዮች ብዙ ነበሩ::
ቀይ ባህር የዓለማችን 10 በመቶ የንግድ የባህር ላይ ንግድ የሚካሄድበት ቦታ ነው:: ቀይ ባህር ላይ በዋናነት ንግድ የምናከናውነው እኛ አይደለንም:: በአብዛኛው ንግዱን የሚያከናውኑት ትልልቆቹ ሀገራት ናቸው:: ቀይ ባህር ኢዥያን ከአፍሪካ፤ አፍሪካን ከአውሮፓ የሚያገናኝ ትልቅ የውሃ አካል ነው:: ስለዚህ የቀይ ባህር ወደብ ባለቤት በሆንን ቁጥር እነዚህ ኃያላን ሀገራት ጭምር የየራሳቸው ፍላጎት ስላላቸው እና አካባቢው ሰላማዊ እንዲሆን ስለሚፈልጉ ከኛ ጋር ይሰራሉ::
የቀይ ባህር ባለቤት በነበርንባቸው ጊዜያት ሁሉ ካለን ሀብት ካለን ታሪክ በቅኝ ያልተገዛን ከመሆናችን የተነሳ በቅርብ ኢትዮጵያ ጋር የሚሰሩ የዓለም ሀገራት እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ቁጥር ከፍተኛ ነበር:: የቀይ ባህር ባለቤትነታችንን ካጣን በኋላስ የሚለውን ስንመለከት ግን በቀይ ባህር ጉዳይ ኢትዮጵያን የሚጋብዝ አካል የለም::
ከኢኮኖሚ አንፃር፤ በተለይ ቀዝቃዛው ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሊበራል አይዶሎጂ አብላጫውን ቦታ በመያዙ ሁሉም ሀገራትን የውጭ ኢንቨስትመንትን ወደ ሀገር መሳብ(come and invest) የሚለው ሃሳብ እየተስፋፋ መጣ:: ከዛ በፊት እኛ ሀገር የምትከተለው የሶሻሊዝም አይዶሎጂ ስለነበር የመንግሥት ሀብት እንጂ የግል ሀብት ማፍራት የሚደገፍ ባለመሆኑ መንገዶች ሁሉ ዝግ ነበሩ:: በመሆኑም ለኢንቨስትመት ምቹ አልነበረም:: ቢያስን ግን ለሌሎች ሀገራት የምሸጣቸው የተወሰኑ ምርቶቻችንን በጅቡቲ ወደብ በኩል የገንዘብ ክፍያ እየከፈልን እንልክ ነበር:: አሁንም በዚህ መልኩ በመጠቀም ላይ እንገኛለን::
የቀይ ባህር ባለቤት በነበርን ሰዓት ለጅቡቲ ወደብ የምንከፍለውን ገንዘብ ለልማት እናውለው ነበር:: አሁን የቀይ ባህር ባለቤት ባልሆንበት ወቅት ደግሞ ለጅቡቲ ወደብ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እየከፈልን እንገኛለን:: ይህ ብቻም አይደለም፤ ገጠር የሚኖረው አብዛኛው ሰው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ሳንችል ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል ሰጥተናል:: ይሄ ሁሉ የሚደረገው ጅቡቲ አኩርፋ የባህር በር እንዳትከለክለን ነው::
በፖለቲካው ዘርፍም ቢሆን የባህር በር ስለሌለን ተሳትፏችን ተገድቧል:: በሆነ ሳጥን ውስጥ የተገደብን እንድንሆን አድርጎናል:: ወደኋላ መለስ ብለን ብንመለከት የኢትዮጵያ ድንበር የት ድረስ ነበር አሁንስ የት ነው ያለው የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል:: የባህር በሮቻችንን የማንለቅባቸው እድሎች ነበሩን ግን አባክነናቸዋል:: ወደፊት እንደምንም ብለን መልሰን የምናገኝበትን እድል መፍጠር ያስፈልጋል ብዬ አስባለው::
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ግንኙነትን ከማጠናከር አንፃር አሁን ላይ ምን መሠራት አለበት?
አቶ ሙሉአለም፡- ቀይ ባህር ላይ ቀጥተኛ ድርሻ ካላቸው ጎረቤት ሀገራት ጋር ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት አለብን:: ወጃጅነታችንን እያጠናክርን መሄድ ያስፈልጋል:: ክፍተቶቻችንን እየሞላን መሄድ ይኖርብናል:: በአፍሪካ ካሉ ሀገራት በተጨማሪ ከአረብ ሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር አለብን:: ወደኋላ ተመልሰን ብንመለከት ከአረብ ሀገራት ጋር የነበረን ግንኙነት ባለመተማመን ላይ የተመሰረተ ነበር::
አረብ ሀገራት ፀረ-ኢትዮጵያ የሆኑ ቡድኖችን ይደግፋሉ የሚል ክስ ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ መንግሥታት ይነሳ ነበር:: ነገር ግን በተለይ የኢህአዴግ መንግሥት ከመጣ በኋላ፤ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከመጡ በኋላ ከአረብ ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት በአንፃራዊነት ወደመተማመን ደረጃ ከፍ እያለ በመሆኑ ከነሱ ጋር መሥራት ያስፈልጋል::
ይህንን የምልበት ምክንያት ለምሳሌ የኤርትራን መንግሥት ብንመለከት ወደ አሜሪካ ሀገራት ጉብኝት አያደርግም፤ ወደ አብዛኞች የአውሮፓ ሀገራት እንዳይገባ ተከልክሏል:: ቢሄድ ሊሄድ የሚችለው ወደ ሩሲያ ነው:: የአረብ ሀገራት ግን ብዙ ተመላልሶ የሚሄድባቸው ሀገራት ናቸው:: ስለዚህ ከነሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ባጠናከርን ቁጥር የኤርትራን መንግሥት የሚያሳምኑበት እድል ሰፊ ስለሆነ ከአረብ ሀገራትም ሆነ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- ይህን ሁሉ ርቀት ተሄዶ የወደብ ጥያቄው ባይሳካ ምን መደረግ አለበት?
አቶ ሙሉአለም፡- ለወደብ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ የማግኘት እድል ሃምሳ ሃምሳ ነው:: የወደብ ጥያቄው ስለተነሳ ብቻ ይሳካል ማለት አይደለም:: ለዚህ ጥያቄ በአዎንታዊ ምላሽ ለማግኘት ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድሮ የወደብ ጥያቄ ስላነሱ ዘንድሮ ይሳካል ማለት አይደለም:: ለሚቀጥሉት 10 ዓመታትም ላይሳካ ይችላል:: ምክንያቱም ጠንካራ የሆነ ዲፕሎማሲና እርስ በእርስ መተማመን ከሚጠይቁ ዘርፎች መካከል አንዱ ነው::
ጥያቄያችን ባይሳካ አሁን እየተከተልን ያለነውን መንገድ አጠናክረን መቀጠል አለብን የሚል እምነት አለኝ:: ነገር ግን አይሳካም መንገዱ ዝግ ነው የሚባል ነገር ስለሌለ ጥያቄያችንን በተገቢው መልኩ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል:: ባይሳካም ለጊዜው አልተሳካም ብሎ ማለፍና እንደአዲስ መሞከር እንጂ እስከመጨረሻው ተስፋ ቆርጦ መተው መፍትሄ አይሆንም::
ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደተናገሩት፤ እንደሀገር ወደብ ማግኘት ለኛ እጅግ ወሳኝ ነው:: ተሳክቶልን በሰጥቶ መቀበል መርህ ወደብ ማግኘት ብንችል ስኬታማ እንሆናለን:: 30 በመቶ የህዳሴ ግድብን እንዲያስተዳድሩ ተደርጎ ወደብ ማግኘት ቢቻል ጥቅሙ ያመዝናል:: መለያችን የሆነውን አየር መንገድ የተወሰነውን ፐርሰንት ቢጋሩና ለኛ የባህር በር ቢሰጡን ይሄም አዋጭ ነው:: ያለምንም ግጭት ምንም አይነት የህይወት ዋጋ ሳንከፍል የባህር በር ለማግኘት ከመሞከር ለኛ በምንም ያዋጣናል:: የእርሻ መሬት ሰጥተን የባህር በር ማግኘት በራሱ ለኛ አዋጭ ነው::
ወደ ጦርነት መጥተን በጉልበት የባህር በር እናግኘው ብንል ግን ብዙ ዋጋ ሊያስከፍለን የሚችል ነገር ነው:: እንደመጨረሻ አማራጭ ልንከተለው እንችላለን፤ ነገር ግን ያዋጣናል ወይ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል:: በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አጥተን የባህር በር ብናገኝ ለቀጣዩ ትውልድ ሊጠቅም ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ነገር ምን ያህል ያዋጣል? በጦርነት ተሸንፎ የባህር በር የሰጠው አካልስ ነገ ኃይሉን አደራጅቶ ተመልሶ ለመልስ ምት አለመምጣቱን እርግጠኛ ነን ወይ? ለቀጣዩ ትውልድስ ያለው የዲፕሎማሲ ሥራ ከባድ አይሆንበትም ወይ የሚሉትን ጉዳዮች ማሰብ አስፈላጊ ነው::
በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ ሁልጊዜ በቋሚነት ኃይል ይዞ መቆየት ላይኖር ይችላል:: ዛሬ ከፍተኛ ኃይል ያለው ሀገር ነገ በሌላ ጉልበተኛ ኃይሉን ሊነጠቅ የሚችልባቸው እድሎች ሰፊ ናቸው:: በመሆኑም በኃይል የሚገኝ የትኛውንም ነገር ዘላቂነቱን መተማመን አንችልም:: በጊዜውም አንፃር በኃይል ነገሮችን ማድረግ እኛን የሚመጥነን ተግባር አይደለም:: ጊዜው ነገሮች በንግግር ተግባብቶ የሚከናወኑበት ነው::
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ እና መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም