ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሁሉም የዜግነት ግዴታውን ሊወጣ ይገባልḷ

ኢትዮጵያ በረጅም ዘመናት የታሪክ ጉዞዋ ጥሩም ሆነ መጥፎ ታሪኮችን አሳልፋለች፡፡ የነጻነትና የአይበገሬነት ተምሳሌት የመሆኗን ያህል በጦርነት፤ በርሃብ፤ በዜጎች መፈናቀልና የጥላቻ ትርክት አላስፈላጊ ዋጋዎችንም ከፍላለች፡፡

አብዛኛውን የኢትዮጵያን የውስጥ ታሪክ መለስ ብሎ ላየው የውስጥ አለመግባባት፤ግጭትና ጦርነት የበዛበት ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ መግባባት ካለመቻላችንም በላይ የግጭትና የጦርነት መንስኤ እስከ መሆን ደርሷል፡፡

ይህ ደግሞ ሀገሪቱን በማያባራ ግጭትና ጦርነት ውስጥ ከቷል፤ ለበርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራም ዳርጓል፡፡ ለሀገሪቱ ዕድገትም ፈተና ሆኗል፡፡ በአንድ ሀገር ላይ ቆመን የጋራ አሰባሳቢ ትርክት መገንባት አቅቶንም ረጅም ዘመን አሳልፈናል፡፡ ትናንትናችን የአሁንና የነገ ተግዳሮታችን ሆኖ ኖሯልም፡፡

ይህ የታሪካችን ጠባሳ ግን አንድ ቦታ መቆም አለበት ተብሎ እንቅስቃሴ ከተጀመረም ዋል አደር ብሏል፡፡ የግጭት፣የጦርነት፣ያለመግባባት ታሪካችን ተዘግቶ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የምንግባባ፤ ለጋራ ሀገራችን የምንተጋ፤ ለልጆቻችንም የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማውረስ የጋራ ዕሳቤ የጨበጥን አዲስ ትውልድ መሆን ይገባናል በሚል እሳቤ እንደሀገር የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባን ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

በእነዚህ ጊዜያትም ምክክሩ የሚመራበትን አቅጣጫ ከመቀየስ ጀምሮ የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮዎችን የመቀመርና በምክክሩ የሚሳተፉ ዜጎችን የመለየት ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በቀጣይም የምክክሩን አጀንዳዎችን ከኅብረተሰቡ የመቀበልና ምክክሩን ወደ መሬት የማውረድ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡

ስለሆነም ሀገራዊ ምክክሩ የቀድሞ ችግሮቻችን፤ አሁን ያሉት ችግሮቻችን መፍቻና በቀጣይም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳያጋጥሙን የመፍትሄ አቅጣጫን የሚጠቁመን መድህን መሆኑን አምኖ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት መታገል ይጠበቅብናል፡፡ በሀገሪቱም መተማመን የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት ለመመስረትም እርሾ ሆኖ እንደሚያግዝ እምነት መጣል አለብን፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ሲችል ነው፡፡ የምክክር ሂደቱ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ የሚጠይቅና ውጤታማነቱም በእያንዳንዳችን አበርክቶ ላይ የሚወሰን ነውና፡፡

እያንዳንዱ ዜጋ በቅድሚያ ሁሉም ነገር በንግግር እና በምክክር ይፈታል የሚል እምነት መጨበጥና ይህኑ ባህል ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ዘመናትን የተሻገሩ ጥያቄዎችም ሆኑ እነሱን ተከትለው የመጡ አለመግባባቶች በምክክር እና በውይይት እንደሚፈቱ አምኖ መስራት ዘመኑ የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

የወሰንም ሆነ የማንነት ጥያቄ እንዲሁም ራስን በራስ ማስተዳደር እና የፍትህ ጥያቄዎች በአጠቃላይ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በሙሉ በሀገራዊ ምክክር ሊፈቱ የማይችሉበት ምክንያት አይኖርም፡፡

አሁን ያሉት አለመግባባቶች ተወግደው በፍቃደኝነት እና በመግባባት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ምክክሩ የማይተካ ሚና አለው፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ ከዘመን ወደ ዘመን ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታትና የመወያየትና የመነጋገር ባህልንም ለማዳበር ይረዳል፡፡ በመወቃቀስ ላይ የሚያተኩረውንም የፖለቲካ ባህላችንንም ወደ መነጋገር፤ መተባበርና መደጋገፍ እንዲመጣ ያደርጋል፡፡

ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን በርካታ ችግሮችን አስከትሎብናል፡፡ ከመነጋገር ይልቅ በር ዘግቶ መወቃቀስና አልፎ ተርፎም ነፍጥ እስከ ማንሳትና መገዳደል ድረስ አድርሶናል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ግጭት፤ ጦርነትና መወነጃጀል ሳይሆን ውይይትና ምክክር ብቻ ነው፡፡

ስለዚህም ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልም እንደሀገር ሊጎለብት ይገባል፡፡ የስልጣኔም አንዱ መለኪያም ይኸው ነውና፡፡ በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ወገኖች፣ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው፡፡ ሀገራዊ ምክክሩን እንደ ዕድል ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

እንደ ሕዝብም የታሪካችን አንዱ ክፋይ ሆኖ ዘመናትን የተሻገረውን ጦርነትና ግጭትን ለማስወገድና የተረጋጋች፤ ሰላሟ የተጠበቀ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማውረስ ሀገራዊ ምክክሩ ይዞ የመጣውን ዕድል መጠቀም ሀገርን የማሻገር አንዱ ተልዕኮ ነው፡፡

ስለዚህም በየትኛውም ጫፍ ያለ ኢትዮጵያዊ በዚህ የምክክር ሂደት መሳተፍና የመፍትሄው አካል መሆን ሀገርን ማዳን መሆኑን ሊረዳ ይገባል!

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You