የእንስሳት ሀብት ልማቱ ተስፋና ፈተናዎች

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከዓለም አምስተኛ መሆኗ ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ ለመሆኑ ሀገራችን ይህን ሀብቷን ምን ያህል እየተጠቀመችበት ነው?

በእንስሳት ሀብት ፖሊሲና በመዋቅራዊ ሂደቱ ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት ያካሄዱት የእንስሳት ፖሊሲ ጥናት ተመራማሪው ደሳለኝ ቤኛ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ የኢትዮጵያ የእንስሳት ምርትና ምርታማነት እያደገ አይደለም። በዘርፉ በተፈለገው ፍጥነት ልማት ማምጣት እንዳይቻል ያደረገ የፖሊሲ ክፍተት አለ ያሉት ዶክተር ደሳለኝ፤ የእንስሳት ልማቱ አልፎ አልፎ የአቅርቦት እጥረት በሚያጋጥምበት ጊዜ ወይም ከፍተኛ ምርት ለውጭ ገበያ በሚያስፈልግበት ወቅት በዘመቻ መልኩ ስትራቴጂዎች የሚቀረጹለት ነው ብለዋል።

የዶክተር ደሳለኝ ጥናት ግኝት እንደሚያሳየው የእንስሳት ልማት ዘርፉ በዘልማድ ከሚከናወነው የተሻለ ደረጃ ላይ አልደረሰም። በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚደረጉ ሙከራዎችና ጥረቶች እንዳሉ ሆነው ዘርፉ በፖሊሲ ባለመደገፉ ውጤት ሊመጣ አልቻለም። ጥሩ ፖሊሲ ቢኖር እንኳን ትግበራውን ለማከናወን የሚያስችል መዋቅር አልተዘረጋም።

የእንስሳት ምርቱ ከሀገሪቱ ሕዝብ ብዛት እኩል እያደገ ባለመሆኑ ለወደፊቱ ከእንስሳት የሚገኙ አልሚ የሚባሉት ምግቦች እየጠፉ ይሄዳሉ። በዚህም ኢትዮጵያ ብዙ ችግር ውስጥ ልትገባ ትችላለች ሲሉ የጠቆሙት ዶክተሩ፤ በተጨማሪም ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬም እየቀነሰ ሲሄድ የሀገር ኢኮኖሚን ይጎዳል ሲሉ አመላክተዋል። በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ጥናት ማዕከል ተመራማሪው ታደሰ ኩማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የእንስሳት ዘርፉ ለሀገራዊ ልማት ተኪ የሌለውና በምግብ ዋስትና፣ በውጭ ምንዛሬና በሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ቦታ የሚይዝ ነው።

ባለንበት ወቅት የእንስሳት ዘርፍ በርከት ያሉ ፈተናዎች እየገጠሙት ይገኛል ያሉት ዶክተር ታደሰ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የመኖ እና ውሃ ሀብት እጥረትና ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዞ የእንስሳት ዕድገትና ምርታማነት ውስን ሆኗል ይላሉ። ተመራማሪው እንደሚናገሩት፤ ለዘርፉ ወደኋላ መቅረት የመጀመሪያውና ትልቁ ማነቆ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚመራ እውቀትን ማዕከል ያደረገ አለመሆኑ ነው። አብዛኛው የእንስሳት ዘርፍ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ በሚመሩ አነስተኛ አርሶ አደሮች እጅ የሚመራ ነው። በፖሊሲና ስትራቴጂ ደረጃ ያለው የመንግሥት ድጋፍም ቢሆን ወደ ሰብል ልማት ያዘነበለ ነው። የእንስሳት ዘርፉን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች ቢኖሩም መሬት የመርገጥ ውስንነት አለባቸው።

ሌላኛው የእንስሳት ዘርፉ ፈተና ከተቋም ጋር የሚያያዝ መሆኑን አመላክተው፤ አንድ ሀገር የሚለማው ጠንካራ ተቋም ሲኖር መሆኑን በመጥቀስ፣ የእንስሳት ዘርፉ አንድ ጊዜ ሲደራጅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲፈርስ እንደ ተቋም ተረጋግቶ የመሥራት ዕድል እንዳላገኘ ይገልጻሉ። ዘርፉ እንዲያድግ መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች በጠቆሙበት ንግግራቸው፤ የእንስሳት ልማትን መንግሥትና አነስተኛ አርብቶ አደሮች ብቻ ሊደግፉ አይችሉም፤ የግል ባለሀብቶች በብዛት መሳተፍ አለባቸው። ከፍተኛ ሀብት እንዲሁም በዘርፉ ከፍ ያለ እውቀትና ልምድ ያላቸው ብዙ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ባለሀብቶች መኖር አለባቸው። ጅምሩ ቢኖርም አንዳንዶቹ ከገቡበትም ሲወጡ ይታያል ብለዋል።

በተለይም ከአካባቢ መራቆት የተነሳ አቅርቦቱ ቀንሶ ፍላጎቱ በጨመረው የእንስሳት መኖ ላይ ባለሀብቶች ለዘለቄታው የሚሰማሩበትን መንገድ መቀየስ ያስፈልጋልም ብለዋል። የኢትዮጵያ እንስሳት ምርታማነት ከሌሎች ጋር ሲነጻጻር ከ25 በመቶ እንኳን የዘለለ አይደለም። አንድ አላስፈላጊ አካላቱ የወጡለት የበሬ ስጋ ብንመዝን 110 ኪሎ አካባቢ ነው። በሌሎች ሀገራት 400 እና 500 ኪሎ ይመዝናል የሚሉት ታደሰ ኩማ (ዶ/ር)፤ የእንስሳትን ምርታማነት በተለያየ ደረጃ መቀየር እንደሚያስፈልግና፤ ሳይንስና ቴክኖሎጂን የተከተለ አመራርት ዘዴን ይፈልጋል ብለዋል።

አብዛኞቹ የቀንድ ከብቶች የሀገር ውስጥ ናቸው፤ ከውጭ ያመጣናቸው ይበልጥ ምርታማ የሆኑ ዝርያዎች ሁለት በመቶ ብቻ ናቸው። ከውጭ መጥቶ የተዳቀለ ዝርያው ከፍ ያለው ዶሮ ብቻ ነው፤ የተቀሩት ሁሉ ትንንሽ ናቸው። የራሳችንን ዝርያዎች ይዘን ከዓለም የተሻለ ምርት ከሚሰጡ ዝርያዎች ጋር በማዳቀል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አለብን ሲሉ መክረዋል።  በሁለቱ ተመራማሪዎች በቀረበው ሃሳብ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ፤ በግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ውስጥ የእንስሳት ዘርፉን ለማሳደግ የሚረዱ ሰፋ ያሉ የፖሊሲ አቅጣጫዎች አሉ ብለዋል።

በመዋቅር ደረጃም ከዚህ በፊት በብዙ መልኩ ትኩረት ያልተሰጠው የአርብቶ አደር አካባቢ በተቋም ደረጃ እውቅና አግኝቶ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር እንዲቋቋም ተደርጓል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተቀመጡ ስትራቴጂዎችን ወደተግባር ቀይሮ እየሠራ በመሆኑ ከዘርፉ መጠቀም ከሚገባን አንጻር ይጎድሉ የነበሩ ነገሮችን ለመድረስ ጥረት እየተደረገ ነው ያለው ይላሉ።

ከዚህ ቀደም የግብርና ሚኒስትር የሆነ ሰው እንኳን ግብርና ሲባል የተወሰነውን ክፍል ይዞ የሚሮጥ እንደነበር ያወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አሁን በሚገርም ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የሌማት ቱርፋት ኢኒሼቲቭ ከተጀመረ አንድ አመት አልፎታል። እንደየ ክልሉ አውድ በክልል መንግሥታት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንስሳት እርባታ ቦታዎች በመገኘት እንስሳት የሚያረቡትን ባለሙያዎች በማበረታታትና ለዘርፉ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሬ በማቅረብ ዘርፉን እየደገፉ ይገኛሉ። በዚህም ከነበረው ሁኔታ አንጻር በምርትና ምርታማነትና በግብዓት አቅርቦት ትላልቅ መሻሻሎች እያየን ነው ብለዋል። አክለውም፤ አዲስ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ቀረጻ ተጠናቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ የሚጸድቅበት ደረጃ ላይ ይገኛል ሲሉም የእንስሳት ዘርፉን ችግሮች ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተመራማሪዎቹ ያሉትን ክፍተቶች ዳስሰው ወደፊት መስተካከል የሚገባቸውን ነገሮች እንደ ግብአት እንድንወስድ ያቀረቡት ምክረ ሃሳብ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረንና ወደፊትም ምን ዓይነት ክፍተቶችን ማስተካከል እንዳለብን ግንዛቤ የጨበጥንበት ነውም ብለዋል።

ተስፋ ፈሩ

 አዲስ ዘመን የካቲት 11/2016

Recommended For You