ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ቀደምት፤ የመንግሥት ሥርዓቷም ያልተቆራረጠ ሀገረ መንግሥት ባለቤት ናት። ይሄ የቀደምትነትና ያልተቆራረጠ ሥርዓተ መንግሥት ባለቤትነቷ ደግሞ ነፃ እና ጠንካራ ሆና እንድትዘልቅ አድርጓታል። ይሄ ነፃነትና ጥንካሬዋ ደግሞ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ፤ ከአፍሪካም ከፍ ብላ ለመላው የዓለም ጭቁን ሕዝቦች ምልክት እንድትሆን አስችሏታል፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ እንደ አንድ ነፃ እና በቅኝ ያልተገዛች ሀገር ብሎም እንደ አንድ አፍሪካዊት ሀገር፤ ለአፍሪካውያን ነፃነትና ሉዓላዊነት ከፍ ያለ ዋጋ ከፍላለች። በዚህም አፍሪካውያን ከቅኝ ተገዥነት በተግባርም በእሳቤም ነፃ እንዲወጡ የሚያስችላቸውን የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ በመያዝ፤ አፍሪካውያን በአንድ ተሰባስበው ለነፃነትና ሉዓላዊነታቸው እንዲታገሉ በማድረግ ገረድ ከፍ ያለ ሚናን ተወጥታለች፡፡
ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት) እውን መሆን ከፍ ያለና እልህ አስጨራሽ ዲፕሎማሲያዊ ሥራን ሠርታለች። ለዚህ ደግሞ የነፃነት ምድር መሆኗ ትልቅ ሚና የነበረው ሲሆን፤ በወቅቱ የነበሩ መሪዎችና ዲፕሎማቶቿም ሚናቸው ጉልህ ነበር፡፡
ይሄ ጥረቷም፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እውን ያደረገ ሲሆን፤ አፍሪካውያንም በአንድ መድረክ ተሰባስበው ለነፃነትና ብልጽግናቸው በጋራ እንዲሠሩ፤ ነፃነታቸውንም እንዲጎናጸፉ አስችሏል። በኋላም ለአፍሪካ ኅብረት መመስረት መንገድ አደላድሏል፤ ኢትዮጵያም በተቋሙ ታግዛ ለአፍሪካውያን ነፃነት የድርሻዋን እንድትወጣ አቅም ፈጥሮላታል፡፡
ይህ እንዲሆን ጥንስሱ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እውን መሆን ነው። ይሁን እንጂ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመመስረት ሂደቱ ቀላል አልነበረም። ይልቁንም አፍሪካውያን በቅኝ ገዥዎቻቸው በተፈጠረባቸው የባህል ተጽዕኖ ምክንያት ርስ በርሳቸው በቋንቋ ሳይቀር ተከፋፍለው ነበር። ኢትዮጵያም በወቅቱ መሪዋ በአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት አመራር ታግዛ ይሄንን ለማስታረቅ ከፍ ያለ የዲፕሎማሲ ሥራን ከውና በተለይ የካዛብላንካ እና የሞኖሮቪያ ቡድኖችን ለማቀራረብ ችላለች፡፡
ይሄም በአህጉሪቱ ታሪክ አንድነትን፣ ልማትን፣ ሰላምን እና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እጅግ መሠረታዊ የሆነ ታሪካዊ ምዕራፍ ሲሆን፤ በወቅቱም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ በወርቃማ ፓን-አፍሪካዊ ቀለም የተፃፈ የዲፕሎማሲ ዘመን ሆኖም ይታወሳል።
በወቅቱ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን የመረጡ 32 አባል ሀገራት በተገኙበት ግንቦት 1963 ዓ.ም የመሪዎቹ ስብሰባ በአዲስ አበባ ተጀመረ። በወቅቱም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የስብሰባው ሊቀመንበር እንዲሆኑ በሙሉ ድምፅ ተመረጡ። ከቀናት ምክክር በኋላም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር በመሪዎች ተፈርሞ «አህጉሩን ከቅኝ እና ከአፓርታይድ አገዛዞች ፈጽሞ ማላቀቅ፤ በአፍሪካ ሀገራት መካከል አንድነትን እና ወዳጅነትን ማጠናከር፤ ለልማት የሚደረገውን ትብብር ማጠናከር፤ የአባል ሀገራትን ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ትብብር ማጠናከር፤» የሚሉ ዓላማዎችን ይዞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመሰረተ።
የድርጅቱን እውን መሆን ተከትሎም፣ አፍሪካውያን ጉዳዮቻቸውና ችግሮቻቸው ከእነሱ ውጪ በሆኑ አካላት ይታይ የነበረበት አካሄድ መታረም እንዳለበት አቅጣጫ ተቀመጠ። አፍሪካውያን የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው መክረው የመፍታት አቅምም መብትም እንዳላቸው በግልጽ ተቀመጠ። «ከጥቂት ዓመታት በፊት የአፍሪካ ችግሮች ከአፍሪካ ውጪ አፍሪካውያን ባልሆኑ ወገኖች ውሳኔ ይሰጠበት ነበር፣ ዛሬ አፍሪካውያን ጉዳያቸውን በራሳቸው የሚመክሩበት ዕድል በዚህ ኮንፈረንስ ተፈጥሯል፡፡” የሚለው የወቅቱ የአፄ ኃ/ሥላሴ ንግግርም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነበር፡፡
በዚህ መልኩ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ሂደት የታየው የኢትዮጵያ ሚና፤ በኋላም አፍሪካውያን በዓለም መድረክ ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው እንዲጨምር የሚያስችሉ በርካታ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ስትከውን ቆይታለች። በኋላም ድርጅቱ ወደ ሕብረት (የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት) ሲለወጥ የድርሻዋን የተወጣች፤ የኅብረቱ ልዕልና እንዲጠበቅም የተጋች ሀገር ናት፡፡
ለአብነትም፣ ኅብረቱ አፍሪካዊ ተቋም ሆኖ እንዲገለጽ ከሚያስችሉት ጉዳዮች መካከል አንዱ ፋይናንስ ነው። ይሄን የፋይናንስ ፍላጎቱን ለማሟላት ደግሞ አባል ሀገራቱ መዋጮ አንዱ መንገድ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የኅብረቱን መዋጮ ከሚያዋጡ በጣት ከሚቆጠሩ ሀገራት ቀዳሚዋ ናት። በተመሳሳይ ኅብረቱ በዓለም መድረኮችና ዓለምአቀፍ ተቋማት ቋሚ ውክልና እና ድምጽ እንዲኖረው ለማስቻል ያልተቆራረጠ ሥራ እየሠራች ትገኛለች፡፡
በዚህ ሁሉ ጉዞ ከውስጧ ባላወጣችው የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ መሰረትም፤ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም የአፍሪካ ጉዳዮችና ችግሮች በራሳቸው አፍሪካውያን እንዲሁም የራሳቸው ተቋም በሆነው የአፍሪካ ኅብረት አቅምና ዐውድ ውስጥ ሆነው መታየትና መፈታት እንዳለባቸው አጽንዖት ሰጥታ እየሰራችም ነው። አፍሪካውያን ነጻነታቸው ምሉዕ ሆኖ እንዲገለጽ የማኅበራዊ መሰረታቸው እንዲጠናከር፤ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እንዲጎለብት፤ የመሰረተ ልማት ትስስራቸው በጋራ ተጠቃሚነትና አብሮ በመበልጸግ መርህ እንዲቃኝ አበክራ እየለፋች ያለች ናት። ይሄው እሳቤና ጥረቷ ከትናትን የቀጠለ፤ ዛሬም ያለ፤ ወደፊትም የሚዘልቅ ስለመሆኑም የታመነ ነው!
አዲስ ዘመን የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም