ወረፋ – ወረፋ – ወረፋ …

በወጉ ፈገግ ያላለው ዕለተ ቅዳሜ አሁንም እንዳኮረፈ ነው፡፡ የሰሞኑ አየር ደግሞ እንዲህ ሆኗል፡፡ ከፀሐይ የተጣላ ይመስል ማለዳው እንደጨፈገገው ይረፍድበታል። እኔ ግን ለዛሬ ይህን የማስተውልበት ቀልብ የለኝም። ሌቱን ጭምር ሲያሳስበኝ ላደረው ጉዳይ መፍትሔ ለመሻት ከቤት የወጣሁት በጠዋቱ ሆኗል፡፡

ጉዳዩ የተገላቢጦሽ የሆነብኝ እግሬ ልክ ቦታውን ሲረግጥ ነበር፡፡ በእኔ ቤት በጠዋት ወጥቻለሁ፡፡ ካሰብኩት ስደርሰ ግን ራሴን አጥብቄ ወቀስኩት፡፡ እንደኔው የመብራት ካርድ የሚያስሞሉ በርካታ ደንበኞች ዙሪያገባውን ይዘው ሰልፉን አርዝመውታል፡፡ በዚህ ሁኔታ እነዚህ ሰዎች በስፍራው የደረሱት ገና ወፍ ሳይንጫጫ መሆኑ ነው፡፡

የረጅሙን ሰልፍ ጫፍ በድካም ፈልጌ አገኘሁት፡፡ እየተሰላቸሁ ከአንዱ ጀርባ ለመቆም ሳወላዳ አንዷ ኮስተር እንዳለች ብቅ አለችና ‹‹ ከእሱ ኋላ እኔ ነኝ፣ ‹ከእነሱ ፊት ደግሞ ሌሎች አራት ሰዎች አሉ› አለችኝ›› ለምንና እንዴት አላልኩም፡፡ መጨረሻው ላይ ይህን ያህል ሰው አለ ከተባለ ከፊትና ከመሀል የሚሰገሰገውን ሰልፈኛ አስብኩትና ዝም አልኩ፡፡ ልናገርስ ብል ምን ላመጣ አዎ ! ዝም ከማለት ውጪ ምርጫ አልነበረኝም፡፡

ወዲያው ተቆጥሮ ከተነገረኝ የመጨረሻው ረድፍ ጫፍ ሌሎችን ለመምሰል ወረፋ ያዝኩኝ፡፡ በተስፋ መቁረጥ ዓይኖቼ አሻግረው አስተዋሉ፡፡ ከፊቴ የተጥመለመለው ሰልፍ ለነገም የሚያልቅ አይመስልም፡፡ ቀስ በቀስ እንደዋዛ ደቂቃዎች ተቆጠሩ፡፡ አሁንም ሰልፉ ንቅንቅ እያለ አይደለም።

ጥቂት ቆይቶ ወገቤ ሲንቃቃ ተሰማኝ፡፡ የሚገርመው በስፍራው በስህተት እንኳን የተቀመጠ ማረፊያ የለም። ዓይኖቼ ከወዲያ ወዲህ ቃበዙ፡፡ እዚህም እዚያም ተበታትነው የተቀመጡ ድንጋዮች ባዷቸውን አይታዩም፡፡

 

በነፍስ ወከፍ ባለ ወረፋዎቹ ተቀምጠውባቸዋል፡፡ ሰዎቹ ሰልፋቸው ርቆ ቢያልፍ እንኳን የሚነሱ አይደሉም፡፡ ድንጋዮቹን ልክ እንደ ርስት አጥብቀው ይዘዋቸዋል፡፡

ከወዲያ ወዲህ ማለቱ ቢሰለቸኝ ከቆምኩበት ጫፍ በተቃራኒው ወደፊተኞቹ አቅጣጫ ተራመድኩ፡፡ በዚህኛው ረድፍ ያለው ሰልፈኛ ቁጥር ይብሳል፡፡ ከየጎኑ የቆመው ደግሞ ቀዳዳ ፈላጊ እንደሆነ ነጋሪ አያሻም፡፡ የመብራት ካርዱን ከሚሞሉት ወገን አንዳች ነገር እየተሰማ አይደለም። ቁጥሩ የማይጎድለው ሰልፈኛ ግን አሁንም ከፊት ከኋላው እየተቀጣጠለ ነው፡፡

ሰዓታትን የቆመው የመብራት ተስፈኛ እርስ በርሱ እያወራ ነው፡፡ ስለ ኑሮ መወደድ፣ ስለመብራት መጥፋትና ፍጆታው፣ ስለሽንኩርት ዋጋ መናርና ተያያዥ ጉዳዮች ፡፡ ዕለቱ ቅዳሜ ነውና አብዛኞቻችን ሠራተኞቹ ‹‹በቃ! ሰዓት ደርሷል›› ብለውን እንዳይሄዱ ሰግተናል፡፡

ይህ ስሜት ቀስ በቀስ በሁሉም ዘንድ ተጋብቷል። እውነትም አጋጣሚው እንዲህ ካስከተለ ሁኔታውን ያሰጋዋል፡፡ ቀጥሎ ያለው ቀን ዕሁድ ነውና መብራቱ ካልተሞላ ችግሩ ቀላል አይሆንም፡፡ የመብራትና ውሃ ነገር በተለይ ለጋራ መኖሪያዎች ፈተናው የበዛ ነው፡፡ አንዴ ከጠፋ ጠፋ ነው፡፡ በቀላሉ መፍትሔ ለመሻት ደግሞ የሚቻል አይደለም፡፡

ከፊት ከኋላዬ የቆሙትን ሰልፈኞች ቃኘኋቸው። አብዛኞቹ በዕድሜ የገፉ እናት አባቶች ናቸው፡፡ ከጠዋት ጀምሮ ያለፋታ መቆማቸውን አሰብኩና ከልቤ አዘንኩ። ለእነሱ ሲባል እንኳን በቂ መረጃ የሚሰጥ ባለሙያ ቢኖር መልካም ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ወገብ እግራቸው እስኪንቀጠቀጥ ለሚቆሙበት ማረፊያ ቢጤ ቢዘጋጅ ዕድሜያቸውን ማክበር ይሆናል፡፡

አሁን አብዛኛውን ሰው እያሳሰበው ያለው የመብራት ካርዱ የአሞላል ሂደት ሆኗል፡፡ ዛሬ ተደጋግሞ እንደሚስተዋለው የመጡበትን ጉዳይ በቀላሉ ገባ ብለው አይጨርሱም፡፡ ወረፋ ቢደርስዎ እንኳን ‹‹ሲስተም›› ይሉት ቴክኖሎጂ ከጊዜዎ ጊዜ መስረቅ ማሰልቸቱ አይቀሬ ይሆናል፡፡

ለዛሬው የወረፋ መበራከት አንዱ ሰበብ የሆነውም ይኸው ምክንያት ነበር፡፡ ገና በማለዳው ወረፋ ይዘው መብራት ለመሙላት የቆሙ ሰዎች እንዳሰቡት አልሆነላቸውም፡፡ ገንዘቡ የሚከፈለው በቴሌብር ነው በመባሉ ድካም ተርፏቸዋል፡፡ ወረፋ ጠባቂው ሥርዓቱን ይዞ አገልግሎት ቢጠብቅም እንዳሻው የሚስተናገድ አልሆነም፡፡

ማንም እንደሚረዳው ቴክኖሎጂን ለተጠቃሚው ተደራሽ ማድረግ ጠቀሜታው የጋራ ይሆናል፡፡ ችግር ሊሆን የሚችለው ግን በአግባቡ ጉዳዩን ሳናውቅና ዝግጁ ሳንሆን ለሌሎች እናስተላልፍ ያልን እንደሆን ነው፡፡ በዕለቱ በቆምንበት ስፍራ ማወቅ የቻልኩት እውነታም ከዚሁ ጥግ ያደርሰናል፡፡

አገልግሎት ሽቶ በደጅ የተኮለከለውን ተጠቃሚ እያስተናግዱ የነበሩት ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም ቢሆኑ ከቴክኖሎጂው በወጉ ያልተግባቡና በየምክንያቱ ብስጭት ውል የሚላቸው ነበሩ፡፡ ከውጭ ቆሞ በወረፋ እየተንገላታ ያለው ደግሞ አሠራሩን ፈጽሞ የማያውቅና ተፈጥሯል ለተባለው ሲስተም ሙከራው የሌለው ደንበኛ ነው፡፡

በጣም አስገራሚው ጉዳይ አብዛኛው ተጠቃሚ መብራት ለማስሞላት መቆሙን እንጂ ምን እየተካሄደ ስለመሆኑ የሚያውቅ እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ምናልባትም በዕድሜ ከገፉት አረጋውያን እጅ ሞባይል ይሉት ላይገኝ ይችላል፡፡ ይህን በሚመለከት ሊፈጠር የሚችለውን ግራ መጋባት መገመቱም ቀላል ነው፡፡

እውነት እንነጋገር ከተባለ ምን ያህሉ ሰው በሞባይሉ ገንዘብ አስተላልፎ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል? የሚለው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች ችግሮች በወጉ ባልተመቻቹበት አግባብ ፈጥኖ ወደሥራ መግባትም ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

በእርግጥ ዘመኑን የሚዋጅ ቴክኖሎጂን መጋራቱ መልካም ነው፡፡ ይህ ሲሆን ግን አስቀድሞ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ በመስጠት ቢሆን ይመረጣል፡፡ እስከዛሬ ካሉ ተሞክሮዎች ለመረዳት እንደሚቻለው አብዛኛው ተጠቃሚ ለሕግና ደንቦች ለመገዛት ዝግጁነት አለው፡፡ ሁሌም ቢሆን አድርግ የተባለውን ለመፈጸም ወደኋላ የሚል አይደለም፡፡

አገልግሎት ፈልጎ በመጣ ጊዜ ደግሞ በተባለው ልክ ጊዜና ጉልበቱን የማይሻማ ተግባራት እንዲተገበርለት ይፈልጋል፡፡ እንዲህ ካልሆነ ሰዓታትን ለሚፈጅ እንግልት ይዳረጋል፣ በአሰልቺና አድካሚ ወረፋ ጊዜና ጉልበቱን ይበላል፣ እግረመንገድ ለሚያጋጥሙ የዘረፋና ማጭበርበር ወንጀሎችም ይጋለጣል፡፡

ነገርን ነገር ያነሳዋል ሆኖ የመብራት ካርድ ወረፋው ጉዳይ ከሌላው ትውስታ ወሰደኝ፡፡ የዛሬ ዓመት አካባቢ በግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ ላይ የደረሰው እንግልት፡፡ ግብር ማለት ማንኛውም ዜጋ በሕግና ደንብ ተመስርቶ ለሀገሩ መክፈል የሚገባው ግዴታ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ግብር ከፋዩ ይህን ባደረገ ጊዜ ከሀገሪቱ በተዘዋዋሪ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም አያጣም፡፡ ይህ የውዴታ ግዴታም ከጥንት እስከዛሬ የታመነ ሕግ ሆኖ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይህ አሠራር የራሱ ሥርዓትና አካሄድ አለውና ማንኛውም ግብር ከፋይ ስለመብቱ ሲል ግዴታውን በአግባቡ ይወጣል፡፡

ዓምና ላይ የሆነው አጋጣሚ ግን በአሠራር ሂደቱ ብዙኃንን ያንገላታና ያሳዘነ ነበር፡፡ በድንገት የወጣውን የጋራ መኖሪያቤቶች የግብር አዋጅ ተከትሎ የተከሰተው የአሠራር ዝርክርክነት በርካቶች ቀናትን ለፈጀ አሰልቺ ወረፋና እንግልት እንዲዳረጉ አስገድዷል፡፡

ይህ ሁሉ የሆነው አስቀድሞ ለሥራዎች ዝግጁ ባለመሆን ነበር፡፡ ዘንድሮም ከመብራት ካርድ መሙላት ጋር ተያይዞ እየተከሰተ ያለው ክፍተት በወጉ መፈታት ካልቻለ አገልግሎት ሰጪውን ለድካም፣ ተጠቃሚውን ለሚያሰለች ወረፋና እንግልት መዳረጉን ይቀጥላል፡፡ አንድን ጉዳይ ከመጀመር በፊት ቆም ብሎ ማሰብ ጠቀሜታው ለሁሉም ይበጃልና አስቀድሞ ይታሰብበት መልዕክታችን ይሁን፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You