አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ዘመን አንስቶ የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን ለመቀራመት በተደረገ የአደባባይ ሴራ ብዙ ዋጋ ለመክፈል የተገደዱ፤ ከነፃነት ዋዜማ ጀምሮም በተመሳሳይ ሴራ ሰላማቸውን አጥተው የግጭትና የሁከት፤ የድህነትና የኋላቀርነት ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱ ሕዝቦች ናቸው።
አፍሪካ 30∙3 ሚሊዮን ኪሎሜትር ስኩዬር ስፋት ያላት/ ከእሲያ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ሰፊ አህጉር፣ ከ1∙4 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ የያዘች / ከዓለም ሕዝብ 18 በመቶው የሚኖርባት፣ ከ1250–3000 የሚደርሱ የራሷ ቋንቋዎች ያሏት፣ እኤአ በ2022 2.96 ትሪሊዮን ዶላር የጠቅላላ ምርት ገቢ የነበራት አህጉር ናት።
አህጉሪቱ በተፈጥሮ ከታደሉ የዓለም አካባቢዎች አንዱ ተደርጋ ብትወሰድም ይህን ሀብት በአግባቡ አውቆ በማልማት የአህጉሪቱን ሕዝቦች ተጠቃሚ ማድረግ ባለመቻሉ፤ ሕዝቦቿ ለከፋ ድህነትና ኋላ ቀርነት፤ ከዚህ ለሚመነጭ ስደትና ጠባቂነት ተዳርገዋል። ለግጭቶችና ጦርነቶች ሰለባ ሆነዋል።
በየወቅቱ ከዚህ ነባራዊ እውነታ ለመውጣት ያደረጓቸው የተናጠል ጥረቶች፤ ስኬታማ ከመሆን ይልቅ ተጨማሪ ፈተናዎች በመውለድ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነውባቸዋል። ለአህጉሪቱ ተስፋ ያደረጓቸውን ብሩህ ነገዎች እውን ማድረግ አቅቷቸው ለልብ ስብራትና ቁዘማ ተዳርገው ኖረዋል።
ከትናንት የነፃነት ወቅት የትግል ተሞክሮ ቆም ብለው መማር ባለመቻላቸው፤ ዛሬም በተሳሳተ የትግል ስትራቴጂ ያልተገባ ዋጋ በመክፈል ፤ የሕዝቦቻቸው ተስፋ እንዲርቅ ሆኗል፡፡
ግለኝነት፣ የሥልጣን ጥማት፣ ራስወዳድነት፣ ባንዳነት፣ ለሕዝብ የማይጠቅም ትርክት ናፋቂነት፣ በሴራ እርሾ የተቦካ ጥላቻ … ወዘተ በነፃነት ትግሉ ወቅት የነበረውን የትግል ግለት አቀዝቅዞት ፤ አፍሪካውያን በተናጠል ጉዟቸው ለአዲስ የቅኝ ግዛት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል።
በዚህም የብዙ አቅም ባለቤት የመሆናቸው እውነታ «የተረት ተረት ያህል» እየተቆጠረ አፍሪካውያን ዛሬን ማሸነፍ አቅቷቸው ጠባቂነት ዋነኛ መለያቸው ሆኗል። በጠባቂነት ውስጥ ያለው ታዛዥነት በብዙ ያገኙትን የፖለቲካ ነፃነታቸውን ሳይቀር ጥያቄ ውስጥ የሚከትበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል።
አፍሪካውያን አባቶቻችን ከነፃነት ዋዜማ ጀምሮ ከሁሉም በላይ ስለ ኅብረታቸው እና አንድነታቸው ቅድሚያ ሰጥተው የተንቀሳቀሱት፣ የሚጠብቁት ድል በኅብረት እና አንድነታቸው ውስጥ ስለመኖሩ መረዳት በመቻላቸው ነው። ይህን እውን እንዳያደርጉ በወቅቱ ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶችም ስለ አንድነት የበለጠ እንዲተጉ አድርጓቸዋል።
አባቶቻችን ብዙ ፈተናዎችን ተሻግረው የአፍሪካ ኅብረትን መፍጠር መቻላቸው፣ በወቅቱ በቅኝ ግዛት ባርነት ውስጥ ለነበሩ ወንድሞቻቸው የቱን ያህል የነፃነት ትግላቸው ጉልበት፤ የድላቸው አቅም እንደነበር ትውልድ ይማሩበት ዘንድ በደማቅ ቀለም ጽፎ ያስቀመጠው የገድላቸው አንድ ምዕራፍ ነው።
ይህ ትውልድ በብዙ መስዋዕትነት የተጀመረውንና ገና ብዙ ምዕራፎች የሚቀሩትን የነፃነት ትግል ምሉዕ ለማድረግ ከሁሉም በላይ እንደቀደሙት አባቶቹ በመማር ቀጣይ ድሎቹ በአንድነቱ እና በኅብረቱ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን በአግባቡ ሊረዳ ይገባል፤ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መፍጠርም ይጠበቅበታል።
ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የመጣንባቸው መንገዶች፤ ቀጣይ አፍሪካዊ ትግሉ የሚጠብቀውን ኅብረትና አንድነት መፍጠር ያላስቻለ፤ ልዩነቶችን ለጋራ ተጠቃሚነት አቅም አድርጎ ከመውሰድ ላለመግባባቶች መነሻ አድርጎ መውሰድን፤ በዚህም አህጉሪቱን የግጭትና የሁከት ማዕከል ያደረገ ነው።
እንደ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ የሚያጋጥሙ ዕድሎችን ለአህጉራዊ ተጠቃሚነት ከማዋል ይልቅ በተናጠል ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረጉ ጥረቶች፤ የውጭ ኃይሎች በአህጉራዊ ጉዳዮቻችን ጣልቃ እንዲገቡ ከማስቻል ባለፈ የዕድሉ ተጠቃሚ የምንሆንበትን ሰፊ አማራጮች ሲያሳጡን ቆይተዋል።
ሰፊ ሕዝብ፣ ትልቅ መልክዓ-ምድርና የኢኮኖሚ ባለቤት ሆነን በጉዳዮቻችን ድምጽ መስጠት የሚያስችለን ውክልና በዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይኖረን፤ ውክልና መጠየቅ እንደ ቅንጦት እየታየ፣ ስለ ነፃነትና ሉአላዊነት እየዘመርን ለዓመታት ስለእኛ ጉዳይ ሌሎች ሲወስኑልን ቆይተዋል፤ ዛሬም እየወሰኑልን ነው ።
በዚህም የከፈልነውና እየከፈልን ያለው ዋጋ ቀለል ብሎ የሚታይ አይደለም፣ ለመጪዎቹ ትውልዶችም አስቀምጠን የምናልፈው ዕዳ ከትውልዶቹ የመሸከም አቅም በላይ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ብዙ የሚከብድ አይሆንም። ለዚህ ዛሬ ላይ ቀና ብለን እንዳንሄድ ያጎበጡንን ሸክሞቻችንን በተረጋጋ መንፈስና አእምሮ ማየት ብቻ በቂ ነው።
የቀደሙት አባቶቻችን ለእኛ ለልጆቻቸው ካለሙልን ህልም አኳያ አሁን ላይ እየኖርነው ያለው አይመጣጠንም። ከእነሱ የተቀበልነውን የትግል እና የአሸናፊነት ችቦ ይዘን ብዙ መጓዝም አልቻልንም። በትውልዶች ቅብብሎሽ የትግሉ ግለት እየተቀዛቀዘ መጥቷል ።
አሁን ከሁሉም በላይ ባልተገባ የልዩነት ትርክት እና ሴራ እየተፈተነ ያለውን፤ ለቀደሙት አባቶቻችን ድል መሠረት የሆነውን ፣ ኅብረታችንን በጸና መሠረት ላይ ማዋቀር የሚያስችል የታደሰ አእምሮ ያስፈልገናል። ይህን መሰል አስተሳሰብና አዕምሮ አባቶቻችን ተስፋ ላደረጓት አህጉር አፍሪካ አልፋ እና ኦሜጋ ነው!
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም