«የዓድዋ ድል ፓንአፍሪካኒዝም እንደሚተገበር ማረጋገጫ ሠጥቷል» ወይዘሮ ሕይወት አዳነ ፓንአፍሪካኒስት

የዛሬው የዘመን እንግዳችን ወይዘሮ ሕይወት አዳነ ይባላሉ፡፡ አፍሪካውያን ሃብታም ሆነው በግጭት ማለቅ የለባቸውም የሚል ሃሳብ ይዘው 19 ሺ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ በ14 የአፍሪካ አገራት ቅስቀሳ አካሂደዋል፡፡ አዲስ አበባ ተወልደው አዋሬ አካባቢ ያደጉት ወይዘሮ ሕይወት፤ ስለአፍሪካ ማሰብ የጀመሩት ገና በዘጠኝ ዓመታቸው ነው፡፡ አባታቸው አቶ አዳነ «ማንዴላ መች ተፈታና» የሚሉ በራሪ ፅሁፎችን ሲያነቡ፤ «ማንዴላ ማን ነው? ምንድን ነው?» የሚል ጥያቄ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ አባታቸው አቶ አዳነ፣ ምላሽ ቢሰጡም፤ እርሳቸው ይበልጥ ስለኔልሰን ማንዴላ ማንበብ ጀመሩ፡፡ አያይዘውም የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄን በተመለከተ የተለያዩ ፅሁፎችን ማሰሳቸውን ቀጠሉ፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በስላሴ ካቴድራል ትምህርት ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ፒያሳ በሚገኘው የልደታ ካቴድራል ካቶሊክ ትምህርት ቤት የተከታተሉት ወይዘሮ ሕይወት፣ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይካሄድ በነበረ የመድረክ ክርክር ላይ «አፍሪካ ወደ ኋላ የቀረችው በራሳቸው በጥቁሮች ድክመት ምክንያት ነው ወይስ በነጮች ሴራ ሳቢያ?» የሚል ክርክር ላይ ተሳትፈው አድናቆት ማግኘት ችለዋል፡፡ በተጨባጭ አፍሪካን በተመለከተ ሁሉም አፍሪካዊ ማሰብ አለበት ሲሉም ጉዳዩን ማጠናከሩን ተያይዘዋል፤ በዚህም የበለጠ እውቅና ማግኘት ጀምረዋል፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወይዘሮ ሕይወት እና አፍሪካኒዝም በእጅጉ የተሣሠሩ መሆናቸውን ሰዎች ማወቅ ጀመሩ፡፡ የመጀመሪያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስነልሳን እና ኮሙኒኬሽን ላይ አተኩረው የሠሩት ወይዘሮ ሒሩት፤ በዩኒቨርሲቲ ውስጥም የባሕላዊ የራስ ተፈሪያን በተመለከተ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠሩ እና ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ካሉ አፍሪካ አንድ መሆን አለባት ብለው ከሚያቀነቅኑት ጋር በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በሚካሔዱ ስብሰባዎች ላይ በስፋት ተሳትፈዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በነበሩ የጥቁር እንቅስቃሴዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ «አፍሪካውያን ዓለምን የሚመግብ በቂ መሬት እና ሃብት እያለን እርስ በእርሳችን መጠፋፋት የለብንም” የሚል ሃሳብ ይዘው አፍሪካን ሲዞሩ ራሳቸው ሃሳቡን አንስተው ዕቅድ አውጥተው ሌሎች ተከትለዋቸው ሃሳቡን እንዲያስተጋቡ ማድረግ ችለዋል፡፡ የተለያዩ ሃሳቦችን በማመንጨት ለተባበሩት መንግስታትም ሆነ ለአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም ለኢትዮጵያ መንግስት ሥራዎችን ለማከናወን የ”ይፈቀድልኝ” ጥያቄዎችን በማቅረብ ክፍተቶችን ለመሙላት የተለያዩ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ ከእኚሁ የአፍሪካዊነት አቀንቃኝ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

 

 አዲስ ዘመን፡- ቆይታችንን አፍሪካን የዞሩት ለምንድን ነው? ከሚለው ጥያቄ እንጀምር?

ወ/ሮ ሕይወት፡- 13 የአውሮፓ አገራት 14ኛ አሜሪካን ጨምረው ጀርመን በርሊን ላይ አፍሪካን እንዴት እንከፋፍላት ብለው 104 ቀን የፈጀ ውይይት አካሂደዋል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ከአፍሪካ ሰዎችን ወስደናል፤ ነገር ግን አፍሪካ ከሌላው ዓለም የተለየ ብዙ ሃብት ስላላት ይህንን ሃብቷን እንዴት እንውሰድ? ብለው ተወያይተዋል፡፡ ያንን ሳውቅ አሁንም እያደረጉት ያለውን ስታዘብ እነርሱ ተግባብተው ለመቀራመት ሲሞክሩ፤ እኛ ተግባብተን መኖር እንዴት ያቅተናል!? የሚል ቁጭት አደረብኝ፡፡

አፍሪካውያን የሚታይ እና የሚጨበጥ ሃብት አለን። የአፍሪካን ያህል ሃብት የሌላቸው ሌሎች አህጉሮች ውስጥ ያሉ አገሮች የአፍሪካን ወርቅ እና ማዕድን እየዘረፉ ለአፍሪካ ገንዘብ ብቻ በማበደር በወለዱ ሲኖሩ እያየን ነው። ሰዎቻችንን ከመውሰድ፣ በባርነት ከመግዛት አልፈው ሃብታችንን በመውሰድ እነርሱ ጠግበው እየኖሩ ነው፡፡ ይህንን በደንብ በመረዳት ለሌሎች ለማስገንዘብ ስል ‹‹አፍሪካውያን በሰላም ተግባብተን እንኑር ›› የሚል ፕሮጀክት በመቅረፅ በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለነበሩ አቶ መለስ ዜናዊ እና በጊዜው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ለነበሩት አቶ ስዩም መስፍን ደብዳቤ ፃፍኩኝ፡፡

ይህ ለእኔ የተለመደ አካሔድ ነው፡፡ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት መላቀቃቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም አንዳንድ የሚያስቆጩ ነገሮች አሉ፡፡ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ሔጃለሁ፡፡ አሁንም በቅኝ ገዢዎቻቸው ተፅዕኖ ውስጥ ናቸው። ከስማቸው ጀምሮ በራሳቸው ቋንቋ እና ባሕል ላይ የተመሠረቱ አይደለም፡፡ እኔ ስሜ ሕይወት አዳነ ነው፡፡ ስሜ በአማርኛ ትርጉም ያለው ነው። እነርሱ ግን ጆን፣ ቶም እያሉ በቅኝ ገዢዎቻቸው ቋንቋ ባሕላቸውን በማያሳይ እና ለእነርሱ ትርጉም በማይሰጥ መልኩ የሚጠሩ ናቸው፡፡ ይህ ተራ ይመስላል፤ ነገር ግን ትልቅ ነገር ነው፡፡ ጉዳዩ ከዚህ ይጀምራል፡፡ እቅዴን ለኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ሕብረትም አስገባሁ፤ በሁለቱም በኩል ተቀባይነትን አገኘ፡፡

በእርግጥ አፍሪካ ሕብረት ላይ ይኸው ተመሳሳይ ሃሳብ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ይህንን የመሳሰሉ  ፕሮጀክቶችን ለመስራት ፊርማ ይካሄዳል፡፡ ነገር ግን ጭብጦቹን ወደ ተግባር የሚለውጥ አካል ብዙ ጊዜ አይገኝም፡፡ ስለዚህ ፕሮግራሞች የሚካሄዱት ስብሰባ በማካሄድ፣ የሙዚቃ ወይም የፋሽን ኮንሰርት በማዘጋጀት ወይም ቀለል ባሉ ፕሮግራሞችን በመተግበር ነው፡፡

እኔ ግን ሌሎችንም ጨምሬ አንድ አገር ሔዶ ስብሰባ ወይም ኤግዚቢሽን ማካሔድ ሳይሆን፤ አፍሪካን በመዞር “አፍሪካ ሰላም እንደሆነች እናሳይ” ብዬ ተነሳሁ። በተጨማሪ ታች ያለው ማኅበረሰብ ስለእርስ በእርስ ግጭት እና ስለሰላም ምን ያውቃል? የሚለውን እንቃኘ አልኩ፡፡ በጉዟችን በጎሳዎች መካከል ግጭት ሲከሰት አፍሪካውያን የሚፈቱት እንዴት እንደሆነ ተመለከትን፡፡ ከላይ ሚዲያው እንደሚያራግበው ሳይሆን አፍሪካውያን ሰላም እንዲመጣ ምን ያህል በራሳቸው መንገድ እየሠሩ ነው የሚለውን ለማየት እንደምንፈልግ የሚያሳይ ፕሮጀክት ይዘን ሔድን፤ በየአገሩም ተቀባይነት አገኘን። በሰዓቱ የ30 ሺህ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አደረጉልን፡፡ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ስንሔድ የየአገሩ መንግስታት ሲቀበሉን ነበር፡፡

19 ሺህ ኪሎ ሜትር የተጓዝን ሲሆን፤ የዑጋንዳን ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒን አግኝተናቸው ነበር፡፡ የቀድሞውን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪን አግኝተን ነበር፡፡ በእኔ በኩል ብዙ ነገር ታዝቤያለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን ራሳችንን አልሸጥንም፡፡ ኬኒያ ውስጥ ሳይቀር ‹‹ኢትዮጵያዊ ነን›› ስንል የተገዛችሁት በማን ነው? በስፔን ነው? ወይስ በሌላ? እያሉ ይጠይቁ ነበር። ያ ማለት እኛ ኢትዮጵያውያን ለአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያ ማለት በቅኝ ግዛት ያልተገዛች እንደሆነች አልገለፅንም፡፡

ሌላው ቡድኑ የሚመራው በእኔ በኢትዮጵያዊቷ ሴት ነው፡፡ በጉዟችን እየተጥመዘመዝን 14 አገራትን አዳርሰናል፡፡ ከኢትዮጵያ ሶስት ሆነን የተነሳን ሲሆን፤ ሁለት ወንድ እና አንድ ሴት ነበርን፡፡ ኬኒያ ስንገባ ፍላጎት ያላቸው ኬኒያውያን አብረውን ጉዞ ጀመሩ። ዑጋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ሞዛምቢክ እያልን ስንቀጥል ብዙዎች ተቀላቀሉን። መጨረሻ ላይ ደቡብ አፍሪካ ገብተን ኬፕታዎን እስከምንደርስ የተቀላቀሉን ብዙ ሰዎች አሉ።

ጉዟችን 30 ቀን የፈጀብን ሲሆን፤ በየአገሩ በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት ወጣቶች፣ ምክር ቤቶች እና የአገር መሪዎች ሳይቀሩ ተዘጋጅተው ይጠብቁን ነበር፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተዘጋጅተው ይጠብቁን ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን የመጀመሪ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሳይቀር ሔደን ስለሰላም ስንወያይ ነበር፡፡ ጫካ ውስጥ ስንሔድ የአገር ሽማግሌዎችን እናገኛለን፡፡ በገጠር ስናልፍ እርሻ ውስጥ ሰዎች ተሰብስበው ይጠብቁን ነበር። በየአገሩ ችግኝ እየተከልን መልዕክታችንን እያስተላለፍን ነበር፡፡ በተጨማሪ የአፍሪካ ሕብረት ያዘጋጀውን በራሪ ወረቀትም በየአገሩ እንበትን ነበር፡፡ አንደኛው የአፍሪካ ሕብረት ከመሪዎች ጋር የለኮሰው ችቦ ሲሆን፤ ሁለተኛውን የሰላም ችቦ በየአገሩ እየሄድን ያበራነው እኛ ነን፡፡

በየአገሩ ስንዞር የአፍሪካ ሕብረት ለአፍሪካውያን ምን ማለት እንደሆነ፤ እኛ አፍሪካውያን ሰላምን እንዴት እናስፍን፤ የሚያጋጨን ነገር ምን እንደሆነ እንነጋገር፤ በተጨማሪ እርስ በእርስ የሚያጋጨን ምንድን ነው? እያልን አወያይተናል፡፡ ለምሳሌ እኛ የተነሳነው ከአፍሪካ ሕብረት ካለባት አዲስ አበባ ነው። መነሻችንም “ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም ይስፈን!” የሚል ነበር፡፡ የጦር መሳሪያ ማከማቻ መሆን የለብንም፤ የሰው ልጅ በመጨረሻ መስማማቱ አይቀርም፤ ስለዚህ በአህጉር ደረጃ የታወጀ የሠላም ጥሪ ስለመኖሩ እንናገር ነበር። እኛ እንደተመለከትነው አፍሪካውያን ጦርነት አይፈልጉም። የአፍሪካ ሕብረት የሠላም እና መረጋጋት ክፍል ደግፎናል፡፡ ስለሰላም በመኪና እና በእግራችንም ብዙ በመጓዝ ቅስቀሳ አድርገናል፡፡ እኛ አፍሪካውያን ነፃ ከወጣን በኋላ የጎዳን ዘረኝነት እና የሰላም እጦት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ፓና አፍሪካኒዝም እና የአፍሪካ ሕብረት አመሰራረትን በተመለከተ ምን ይላሉ?

ወ/ሮ ሕይወት፡- አፍሪካኒዝም ብቻ ሳይሆን በ18ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያኒዝም የሚል ንቅናቄ በስፋት ሲካሔድ ነበር፡፡ የመጀመሪያው የጥቁር ምሁር ዱ ቦንሲ፣ አፍሪካ ለአፍሪካውያን የአፍሪካ ነፃነት የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ አፍሪካውያን ዘር ላላቸው ሁሉ።›› የሚለው ሃሳብ በጣም የተንሰራፋበት ሁኔታ ነበር፡፡ ያንን ሃሳብ ከፍ አድርገው የሚናገሩ በተለይም የባሪያ ንግድ መቆም አለበት፤ በሚል ትልቅ ቅስቀሳ የሚያደርጉ የበዙበት ጊዜ ነበር፡፡ በዛ እንቅስቃሴ ላይ እ.አ.አ በ1896 የኢትዮጵያ የዓድዋ ድል መጣ፡፡

የዓድዋ ድልንም ሆነ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን አሸናፊነት በጣም ከፍ ከሚያደርገው መካከል አንዱን ለመግለፅ ያህል፤ ከአጼ ምኒልክ ጋር ሊዋጉ የመጡ ወራሪዎች ዋሻ ውስጥ ተደብቀው በረሃብ እና በጥም ሊያልቁ ነበር፡፡ ሶስት ጥይት በአንድ ብርጭቆ ውሃ ሲሸጡ ከአጼ ምኒልክ ሰሙ። ለጠላት የጦር መሪ “ወታደሮችህን በርሃብ እና በጥም ከምትጨርሳቸው ውጣ እና እንዋጋ” ብለዋል፡፡ ወደ ሌላ አዝማች ለመሔድ ወይም ሜዳ ላይ ውጊያ ለመግጠም እቃዎቻችንን መጫኛ አጥተናል ሲሉ፤ ከአጼ ምኒልክ 500 አጋሰስ ለጠላት አዝማች በመላክ ከሌሎች ጋር ተቀላቅሎ እንዲዋጋ አድርገዋል፡፡

ውጊያ ክብርን ጠብቆ መግጠም እንጂ መጎዳዳት እንዳልሆነ የሚያውቁ ናቸው። የጠላት ጦር ከሌላ ወገኑ ጋር ተገናኝቶ ውጊያ ሲገጥማቸው አሸንፈውታል። ጦርነት ጉልበት መፈታተን እንጂ ሰውን መግደል እንዳልሆነ አሳይተዋል፡፡ ጥቁር ሕዝብ በዚህ ያህል ጥልቀት ባለው መንገድ እንደሚያስብ አሳይተዋል። ነጮች ጥቁር ሕዝብ ከኖህ ጊዜ ጀምሮ ተረግሟል ብለው ያሰቡ ነበር፡፡ ነገር ግን “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚያብሔር ትዘረጋለች” የሚለው መለኮታዊ ሃሳብ ስለኢትዮጵያ በቅዱስ ቁርዓንም ሆነ በቅዱስ መፅሐፍ የተፃፈ ነው፤ በመሆኑ ጥቁሮች ኢትዮጵያኒዝም የሚል ንቅናቄ ጀመሩ፡፡ ይህንኑ ባስነሱበት ጊዜ እና እንደገና የፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄን አንዱ ቦንሲ ባመጡበት ወቅት የኢትዮጵያ ጥቁር ሕዝቦች እንደገና አድዋ ላይ ነጮችን አሸነፉ፡፡ ይህ ትልቅ ንቅናቄን ፈጥሯል፡፡

በዚያ ምክንያት እኤአ 1899 ላይ የፓን አፍሪካኒዝም አያት የሚባለው የሔቲ ዜግነት ያለው ሄነር ሲልቨስተር ዊሊያም፤ ለይተን ጥቁር ብቻ ማለት የለብንም አጠቃላይ አፍሪካውያን ነፃነት እና ከቅኝ ግዛት ለመውጣት የሰዎችን ሰብዓዊ መብት ለማክበር ይህንን ማድረግ አለብን በሚል እኤአ በ1900 ለንደን ላይ ስብሰባ አዘጋጁ። በእርግጥ ስብሰባውን  ከማካሔዳቸው ከአንድ ዓመት በፊት እኤአ በ1899 ኢትዮጵያ ተጋብዛ ነበር። በዚያ ስብሰባ ላይ ምን ነገሮች መነሳት አለባቸው የሚለውን ለመነጋገር ኢትዮጵያ ተጋበዘች፤ ከኢትዮጵያ ጋር የተገኙት ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያ እና ጋና ነበሩ። ከደቡብ አሜሪካ ብዙ አገሮች፣ ከምዕራብ ሕንድ፣ ከለንደንም ተሳትፈው ውይይት አካሂደዋል፡፡

በኋላም የእነ ማርክስ እንቅስቃሴ መጣ፤ ዓለምን የማሻሻል ንቅናቄ መጣ፡፡ ይህ ደግሞ “ኔግሮ” በሚል ሰብ ሰሃራ ላይ የተጠናከረ ሆኖ እናያለን፡፡ እንግዲህ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ላይ እነ ኩዋሜ ኑኩሩማ የመሳሰሉ መሪዎች እና እነ ጋናን የመሳሰሉ አገሮች ይህንን በስፋት ማቀንቀን ጀመሩ፡፡

በኋላም ጣሊያኖች ኢትዮጵያ ለመግዛት በሚሞክሩበት ጊዜ በሊግኦፍኖሼን ውስጥ ቀዳማይ ኃይለስላሴ የተናገሩት ኢትዮጵያ ስለራሷ ብቻ ሳይሆን ስለመላ ስለተጨቆኑ ሕዝቦች ብቻዋን ጮሃለች፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም የአፍሪካ ሕብረት ከኢትዮጵያ ይነሳል ሲባል ይህንኑ አስታውሰው ተናግረዋል። ብቻችንን በሊግኦፍኔሽን ቆመን ስለተጨቆኑ ሕዝቦች ጥያቄ አቅርበናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት አባል በምትሆንበት ጊዜ አባቶቻችን በጣም ንቁ ሆነው ይሳተፉ ነበር፡፡ ፍትሕ የለም ብለው በሚያስቡበት ጊዜ ቀዳሚ ሆነው ይቆሙ ነበር። ስለዚህ በተባበሩት መንግስታት በኢኮኖሚው ረገድም ሆነ በጭቆና በኩል ዓለም የገባውን ቃል ኪዳን እንዲያከብር የጥቁር እና የተጨቆኑ ሕዝቦች መብታቸው እንዲከበር ብለዋል፡፡

የኢኮኖሚ ጉዳይ ከፖለቲካ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፤ የኢኮኖሚ ጥንካሬ ከሌለ የፖለቲካው ነፃነት የሚያመጣው ነገር የለም ብለው አቀንቅነዋል። በዚያ ምክንያት ቀደም ብለው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እኤአ በ1954 እንዲቋቋም አድርገዋል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽንን ያቋቋመችበት የራሷ ምክንያት አላት፡፡ አፍሪካውያን እራሳቸውን በኢኮኖሚ መቻል አለባቸው ብላ 26 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ሠጥታ እና አምስት ሚሊየን 30 ሺህ ብር አውጥታ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እንዲቋቋም አድርጋለች፡፡

እኤአ ከ1951 በኋላ የፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በተለይ የጋናው ኩዋሜ ንኩሩማ እና የጊኒው መሪ እነሴኮ ቱሬም አባል የነበሩበት ትልቅ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ የእነርሱ ንቅናቄ ግን አፍሪካ በአንድ ሰንደቅ ዓላማ፣ አንድ አገር መሆን አለባት ብለው በካዛብላንካ ሥር ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡ እንደነታፌዋ ባሌዋ ያሉ የናይጄሪያውን መሪ ያጠቃለለው ደግሞ የሞኖሮቪያ ቡድን ትልቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነበር። ይህ ቡድን የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢዎችን ያጠቃለለ ሲሆን፤ በተለያየ ጎራ መበታተን በሚጀምርበት ጊዜ ኢትዮጵያ በነበራት ክብር እና ልዕልና ከሁለቱም ቡድን ጥሪ ደርሷታል፡፡

በወቅቱ አገርን ሲያስተዳድሩ የነበሩት መሪዎች ብልሆች ስለነበሩ ትኩረታቸው የተከፋፈለች አፍሪካ ወደ አንድ የምትመጣበትን ሁኔታ በማሰብ ለሁለቱም ቡድኖች በግልፅ ሃሳባቸውን አስረድተዋል፡፡ በማህበር የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት በቀጣይ ዓመት ስብሰባው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲካሔድ አሳምነዋል፡፡

የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና የሰዎችን ሰብዓዊ መብት ማክበር፤ ፍትህ ማስፈን፤ ሃብትን በተገቢው መልኩ ለሁሉም ማዳረስ የሚል ነው። ፓናአፍሪካኒዝም የፍትህ የሰላም የዲሞክራሲ ጥያቄን ያነገበ ነው፡፡ እኩልነት ወንድማማችነት እና አንድነትን የሰነቀ ነው። ይህ የሚመጣው በመበታተን ሳይሆን በመሰብሰብ ነው፡፡ እኩልነት እና ፍትህ የሚመጣው በመተባበር እርስ በእርስ በመተዋወቅ እና በመደናነቅ ነው፡፡ ይሔ ነገር ገብቷቸው በዚህ መልኩ በኢትዮጵያ ሁለቱም ቡድኖች ወደ አንድ እንዲመጡ በመስራት የጋራ ስምምነት ላይ እንዲደርስ ሚናቸውን ተወጥተዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የዓድዋ ድል የአፍሪካ ሕብረት እንዲመሰረት የነበረው ሚና ምን ያህል ነው?

ወ/ሮ ሕይወት፡- የአድዋ ድል ውጊያ ብቻ ሳይሆን የማንነት እና የስብዕና መለኪያም ጭምር ነው። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሃፊ የነበሩት ዳክ ሃመር ሾዎን እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያውያን በታላቅ መንፈሳዊ ታሪክ ውስጥ ጥልቅ ስር የሰደደ ጥበብ እና መንግስት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው ብለው ነበር፡፡ ጦርነትም ቢሆን የሚካሔደው የሰውን ልጅ ክብር በሚያሳይ መልኩ የሚካሔድ መሆኑን የሚያሳይ ስብዕና ያላቸው መሪዎች እንደነበሩ ዓለም ያውቃል። ሲዋጉ የሰውን መብት በሚያከብር መልኩ የሚያካሒዱ፤ በብዙ መልኩ አርቀው የሚያስቡ፤ ችግር ባዩበት ሁሉ መፍትሔ ለማመላከት የሚጥሩ ነበሩ፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያውያን አድዋ የሕዝባቸውን ክብር ማንነታቸውን ያስመለሱበት መሆኑን ያውቃሉ። በዚያ ጊዜ የእኛ አገር መሪዎች ዓለምን ያውቁ እና ከዓለም ጋር ይገናኙ ነበር፡፡ ሲልቪያን በነቶ ሲሊቪያን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ እውቅና የነበራቸው ሰዎችም ከንጉሱ ጋር ይሠሩ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በአድዋ ድል ስታሸንፍ እኛ ብቻ ሳንሆን አፍሪካውያን ቀና ብለው እንዲሔዱ ሆኗል፡፡

የዓድዋ ድል የፓንአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ በትክክል ሊተገበር እንደሚችል ማረጋገጫ የሠጠ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥቁር ሕዝብ ነጭን አንበርክኳል፤ ስለዚህ ሌሎችም የሚታሰቡ ነገሮች ሊሳኩ ይችላሉ የሚል እምነት እንዲያድር አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ያ አስተሳሰብ እና ልዕልና በውስጣቸው ስለነበር፤ እነርሱ የወሬ ወኪሎች የሚሏቸው የሚዲያ አካላት በሙሉ ‹‹አፍሪካ አንድ ልትሆን አትችልም›› በሚሉበት ጊዜ ንጉሱን ሳይቀር ‹‹የማይቻለውን ሞክረው ይዋረዳሉ ›› ሲሏቸው፤ ‹‹ግድ የለም፤ ይቻላል! ባይቻል እንኳ እኛ ኢትዮጵያውያን ከመበታተን መሰባሰብ ይሻላል ብለው ነበር የሚል ታሪክ ትተን እናልፋለን እንጂ አንተወውም›› ብለው ያንን የድል ልዕልና ተጠቅመው አስቀጥለውታል።

አዲስ ዘመን፡- የዓድዋ ድልን በእርግጥ ምን ያህል ተግባብተን ተጠቀምንበት?

ወ/ሮ ሕይወት፡- በዓድዋ ድል በብዙ ተግባብተን በጥቂቱ ተጣልተንበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የጥላችን ምክንያት ብዙ ጊዜ ከጀርባችን እንድንጣላ የሚሠሩ በመኖራቸው ነው፡፡ ጥቁር ነጭን ማሸነፉ የሚያናድዳቸው አሉ ፡፡ አፍሪካዊ ሆነን ከሆድ ይልቅ ማንነታችን ጠንቅቀን አውቀን ስንንቀሳቀስ እኛን ለማጣላት ብዙ ይሠራሉ፡፡ አሁንም ለማጣላት በሥፋት እየሠሩ ነው፡፡ ያ የፈጠረው ችግር በተፈለገው እና ባሰብነው ልክ መሔድ እንዳንችል አድርጎናል። ግን ደግሞ በሌላ በኩል የሠራነውን ስንመለከት፤ ኢጋድን አቋቁመናል፤ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማትን መምራት የሚችሉ ሰዎችን አፍርተናል። እስከ አሁን ያለንን አለቀቅንም።በጣም ደክመን ቢሆን ኖሮ የአፍሪካ ሕብረት ከዚህ ተነስቶ ይሔድ ነበር፡፡

መሪዎቻችንም ቢሆን በዚህ ላይ የተለያየ አቋም የላቸውም፡፡ ይህ ነገር ሲነሳ ሁሉም ቢያንስ የነበረውን ለማስቀጠል ችለዋል፡፡ በሌላ በኩል ከዓለም ፍጥነት አኳያ ሲታይ ግን፤ ምንም እንኳ ተፅዕኖ ቢደረግብንም መሔድ ባለብን ልክ ያልሔድንበት ሁኔታ መኖሩ አይካድም፡፡ ነገር ግን ቢያንስ አስቀጥለነዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አዎ አስቀጥለነዋል፤ ነገር ግን አድዋ ነጭ ከጥቁር እኩል መሆኑን ያረጋገጥንበት የድል ታሪክን በልኩ ለዓለም እያስተዋወቅን ዘክረነዋል ማለት ይቻላል?

 

 ወ/ሮ ሕይወት፡- ትክክል ነው አልዘከ ርነውም። እኛ ራሳችንን ለማወቅ የምንሽኮረመም ነን፡፡ የነበረውን እንኳ ስንናገር አጋንነን እንደተናገርን እያሰብን እውነታውን በልኩ አናስተዋውቅም፡፡ ለሌሎችም በዚህ ልክ አልተናገርነውም፡፡ የግድ መንግስት እንዲሠራ እና እንዲናገር መጠበቅ የለብንም፡፡ ለቀጣዩ ትውልድ ታሪኩን የማሳወቅ እና ድሉ ምን ማለት እንደሆነ ማስገንዘብ የእኛም ኃላፊነት ነው። አስተያየት መስጠት ብቻ ሳይሆን ጉዳዩን እንደራስ ጉዳይ በመውሰድ፤ በሚገባው ልክ ታሪኩ ለአገር ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ጭምር ትልቅ ጉዳይ መሆኑን አላስተዋወቅነውም፡፡

አዲስ ዘመን፡- የዓድዋ ድል ነጭ በጥቁር እንደሚሸነፍ በማሳየቱ ኢትዮጵያውያን ተጎድተ ውበታል ይባላል፡፡ በእርግጥ በድሉ ተጎድተናል?

ወ/ሮ ሕይወት፡- በትክክል! ምክንያቱም ፀጥ ለጥ ብሎ ይገዛ በነበረ አህጉር ላይ ኢትዮጵያ አመፅን እንዳስነሳች ተቆጥራለች፡፡ ይህም ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ በሰዓቱ የነበሩ ገዢዎች ጅቡቲን እንድናጣ አድርገውናል። ኤርትራን እና የሶማሊያ ወደቦቻችንን እንድናጣ ማድረግ ችለዋል፡፡ በኢኮኖሚ እንድንደቆስ አድርገውናል፡፡ አሁንም ኢትዮጵያውያን ትንሽ ነገር ካገኙ አፈትልከው እንደሚወጡ ስለሚያውቁ እንደዛ እንዳይሆን ሴራ እየተሠራብን ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ደግነቱ ጠላታቸውን አውቀው ጠላትን እንዴት ወዳጅ ማድረግ እንደሚቻል የሚገነዘቡ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ የአፍሪካ አንድነትም ሆነ በኋላ የአፍሪካ ሕብረት መመሥረቱ ያስገኘው ትሩፋት ምንድን ነው?

ወ/ሮ ሕይወት፡– አፍሪካ አንድነት መጀመሪያ ሲመሠረት 32 አገራት ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ ነፃ ሆና የተባበሩት መንግስታት ዓባል አገር ነበረች። ከዛ ደግሞ የነበሩት ሁኔታዎች ሲታዩ አዲስ አበባ ላይ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሲቋቋም ኢትዮጵያ፣ ላይቤሪያ፣ ጋና፣ ሱዳን፣ ጊኒ ፣ ሞሮኮ እና ቱኒዚያ ብቻ ነበሩ። ከዛ አፍሪካ ሕብረት መቋቋሙ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በእርግጥ የአፍሪካ ሕብረት የተቋቋመው የአውሮፓ ሕብረት በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ነገር ግን እነርሱ ገንዘባቸውን አንድ ማድረግ ችለዋል፡፡ እርስ በእርሳቸው በነፃ በሻንጋይ ቪዛ መዘዋወር የሚችሉበትን ሁኔታዎች ፈጥረዋል፡፡

አፍሪካ ጥቅም ያለባት የምትቦረቦር አህጉር ስለሆነች፤ አንዳንድ ጊዜ ልጆቿም ቢሆኑ ባንዳ የሚሆኑባት አገር ስለሆነች፤ በአጠቃላይ የአፍሪካ ሕብረት ተፅዕኖ ስላለባት እንጂ የተቋቋመበት ጊዜ እንደአውሮፓ ሕብረት የጋራ የመገበያያ ገንዘብን ጨምሮ ብዙ ውጤቶችን ማምጣት ይቻል ነበር፡፡ ያም ቢሆን ግን ሕብረቱ ሲቋቋም የተቋቋመበትን ዓላማ ሁለት ነው፡፡ አንደኛ በቅኝ እየተገዙ ያሉ አፍሪካውያን ነፃ መውጣታቸው እንዲፋጠን ለመሥራት ነው፡፡ በዚህ ውጤታማ መሆን ተችሏል፡፡

ሁለተኛ ደቡብ አፍሪካን የመሰሉ አገራት ከአፓርታይድ ነፃ እንዲወጡ ለማድረግ ተችሏል። አንድ ጥቁር 10ኛ ክፍል ካልደረሰ መደመር እና መቀነስ መማር አይችልም የሚባልበት አገር ነበር። ጥቁር ሆኖ ማወቅ መማር የለበትም የሚባልበት አገር፤ የሰዎች ስብዕና በዛ ልክ መውረድ የለበትም ብሎ እነርሱን ነፃ ማውጣት ነበር፤ ያንን ማድረግ ተችሏል፡፡

ሌላው ነገር ቢያንስ በአፍሪካ ሕብረት በብዙ መልኩ ሃብታም የሆኑ የአፍሪካ አገሮችን የሚመሩ በአንድ ላይ የሚሰበሰቡበት ተቋም መፍጠር በራሱ በጣም ትልቅ ውጤታማ የሆነ ነገር ነው። ይህንን እነርሱ ፈፅመውታል፡፡ አሁን ዛሬ ላይ ስንመለከት ቀዳማይ ኃይለስላሴ በሕብረቱ መክፈቻ ላይ ያደረጉትን ንግግር አንቀፅ በአንቀፅ ያነሷቸው ጉዳዮች አሁን ላይ አጀንዳ 2063 ተብሎ የአፍሪካ ሕብረት 60ኛ ዓመት ላይ እንዲተዋወቅ እየተደረገው አጀንዳ ሆኖ እየቀረበ ነው፡፡

የተወሰኑትን ለማንሳት ያህል የነገዋ አፍሪካ ምን መምሰል እንዳለባት የሚያመላክተው አንቀፅ፤ በሌላ በኩል አፍሪካውያን ቂም በቀል ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው የሚያመላክተው አንቀፅ፤ ቀዳማይ ኃይለስላሴ ቃል በቃል ብለውታል፡፡ ‹‹ አፍሪካ በሙሉ ነፃ እንድትሆን የገባነውን ቃልኪዳን እንደገና ስናድስ ባለፈው ጊዜ የደረሰብንን በደል ቂም መያዝ አይገባም። ቀኝ ገዢዎች በጭቆና ያስተዳድሩ በነበረ ጊዜ፤ የሠሩት ሥራ ሁሉ ለራሳቸው መጠቀሚያ ቢሆንም አሁን ለአፍሪካውያን መገልገያነት ስለዋለ ያለፈውን ወደ ጎን ትተን ለወደፊቱ እንድከም፡፡ ባለፈው ከበደሉን ጋር በሰላም በስምምነት ለመኖር እንሞክር ብለዋል፡፡

አሁንም አፍሪካ ውስጥ ጦርነት እየተካሔደ ያለው ይህ ስለጠፋ ነው፡፡ ኒልሰን ማንዴላ ይህን በማድረጋቸው ዓለም ላይ ከፍ ብለዋል፡፡ በተግባር ቂም እና በቀልን በመተዋቸው ተሞግሰዋል፡፡ በተቃራኒው ግን እኛ እንደዛ መሆን ስላልቻልን በጎሳ በባህል መለያየታችን ለአፍሪካውያን ምን ያህል እንቅፋት እንደሆነ አይተናል፡፡

በአጠቃላይ ስናያቸው ቀዳማይ ኃይለ ስላሴ ትምህርት እንደሚያስፈልግ፤ ድንቁርና መወገድ እንዳለበት፤ አፍሪካውያን አንድ ዩኒቨርሲቲ እንደሚስፈልጋቸው፤ አፍሪካውያን የብሔር ልዩነት የሚመጣውን ችግር ማስወ ገድ እንዳለባቸው፤ የጦር መሳሪያ ቅነሳ እንደሚያስፈልግ በጊዜው አሳስበዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ላይም አሳስበዋል፡፡

በኢኮኖሚ በኩልም በአንድ ጊዜ አንድ ልንሆን ባንችልም፤ የቀጣናው ማኅበረሰብ የንግድ ትስስር ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በየቀጣናው አንድ እየሆንን በሒደት እንደምንቀጥል፤ ባንኮች እንደሚያስፈልጉን፣ የኢኮኖሚ ነፃነት ከሌለ ከገንዘብ ጋር የሚመጡ አጀንዳዎች ስለሚኖሩ እና ይህም የፖለቲካ ነፃነትን ስለሚያሳጣ ከዛ ለመዳን የገንዘብ ተቋማትን ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፈንድን፣ የአፍሪካ ሞኒተሪንግ ፈንድን እና ባንኮችን መፍጠር አለብን ብለው አጀንዳ አስቀምጠው ነበር፡፡

አባቶቻችን ቀደም ሲል የአፍሪካ ሕብረትን መመስረት ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ሊሠሩ የሚገባቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ ሕብረት መፈጠሩ ብዙ ትሩፋቶች አሉት ማለት ይቻላል፡፡ በዛ ላይ እንዳለፉት አባቶች ባንሠራም ምንም ቢሆን ካለመኖር መኖር በብዙ መልኩ ይሻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የአፍሪካ ሕብረት ከዚህ በኋላ በምን መልኩ መቀጠል አለበት? አፍሪካውያንስ ምን ማድረግ አለባቸው?

ወ/ሮ ሕይወት፡- በዋናነት በተማርነው እና ባስቀመጡልን ልክ መቀጠል አለብን፡፡ አፍሪካውያን ወደ ውስጣችን ማየት አለብን፡፡ ሁሉ ነገር አለን። ልጆቻችን ዓለምን እያገለገሉ ነው፡፡ አፍሪካ በጣም የበለፀገች ነበረች፡፡ ያ ዕድገቷ በባሪያ ንግድ ታውኳል። በቅኝ አገዛዝ አሁንም የሚሠሩ ጭንቅላቶቻችን ባክነዋል፤ ወድቀዋል፡፡ ብዙ ነገር መፍጠር የሚችሉ ጭንቅላቶቻችን ታስረዋል፡፡ የሚሠራ ጉልበት ያለው አቅም ያለው የሰው ኃይል ባክኖብናል፡፡ አህጉራችንን ከፍ አድርጎ ማስቀጠል የሚችል ብዙ የባከነብን ነገር አለ፡፡

ስለዚህ ወደ ኋላ ዞረን ችግሮቻችን ምንድን ናቸው? ያሰረን ምንድን ነው? መፍትሔውስ ምንድን ነው? ብለን በእርሻው፣ በግንባታው፣ በሕክምናው ከሆነ በብዙ ዙሪያ በልማቱም ሆነ በዕድገቱ በቴክኖሎጂው ክፍተታችንን ሊሞሉልን የሚችሉ ልጆቻችንን እየሸኘን ዝም ብለን መኖር የለብንም፡፡ ይህንን የሚያስቡ መሪዎች ያስፈልጉናል። መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ይህንን የሚያሳስቡ የመገናኛ ብዙሃን ያስፈልጉናል፡፡ ዞሮ ዞሮ የሁላችንም ሥራ ነው፡፡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሲቪል ማኅበራትም መንግስት የረሳውን ነገር ሊያስታውሱ ይችላሉ፡፡ ብዙ ነገር ከማኅበረሰቡ ሲመጣ በሕዝቡም ተቀባይነት ያገኛል፡፡ መጣላት፣ መጋጨት የለብንም። የጎደለውን የመሙላት ደግሞ የሁላችንም ግዴታ ነው።

ያደሩ ሥራዎች ለምን አደሩ? ብሎ የሚጠይቅ ማኅበረሰብ ያስፈልጋል፡፡ የተፈረሙ ስምምነቶች ለምን አይተገበሩም? መባል አለበት፡፡ መንግስታትም ሕዝብን ማዳመጥ፤ ከሕዝብ ጋር አብሮ የመስራት ባህልን ማዳበር አለባቸው፡፡ ያለበለዚያ እንደተለመደው የእኛን ሃብት ሌሎች እያጌጡበት ይቀጥላሉ፡፡ ይህንን ቅኝት መቀየር አለብን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ፡፡

ወ/ሮ ሕይወት፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን  የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You