ትምህርትን በአፍሪካውያን የዕለት ተዕለት ሕይወት የተሟላ ትርጓሜ እንዲኖረው መሥራት ወሳኝ ነው!

አፍሪካውያን የበለጸገች አኅጉር ለመፍጠር የሰነቁትን ራዕይ እውን ማድረግ የሚችሉት ራሱን የሚያውቅ እና በራሱ የሚተማመን ትውልድ መፍጠር ሲችሉ ብቻ እንደሆነ ይታመናል። ለዚህ ደግሞ ትምህርት ሊኖረው የሚችለው በሁለንተናዊ ጠቀሜታ የጎላ እና መተኪያ የሌለው ነው።

ትምህርት ያደጉ ሀገሮች የአሁናዊ ዕድገታቸው ሆነ የቀጣይ ዘመናቸው ተስፋ ዋነኛ መሰረት ነው። ለዚህም ትናንትም ሆነ ዛሬ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ነው። ትውልዶችን ዘመን የሚዋጅ እውቀት በማስታጠቅ ለአንቱታ ያበቃቸው ስልጣኔ ቀጣይ እንዲሆን ባላቸው አቅም ሁሉ እየተንቀሳቀሱ ነው።

ይህ ለትምህርት የሰጡት ትኩረት ከትናንት ዛሬ፤ ከዛሬ ነገ ለሚያልሟቸው ህልሞች እውን መሆን አቅም ከመሆን ባለፈ፤ ዓለም አሁን ላይ ላለችበት ዕድገት ባለውለታ አድርጓቸዋል፤ ከዚህም ባለፈ የተቀረው ዓለም ከእነርሱ ጋር እኩል ለመሄድ የስልጣኔያቸው ጠባቂ እየሆነ ያለበትን ሁኔታ መፍጠርም ችለዋል።

አፍሪካውያን በቀደሙት ዘመናት/በቅኝ ግዛት ዘመን ከነበሩበት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ባርነት አንጻር፤ ከትምህርትና ትምህርት ሊፈጥረው ከሚችለው የአእምሮ ልዕልና /እውቀት ተገልለው እንዲኖሩ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ከዚህ የተነሳም ላልተገባ የጭለማ ሕይወት ተዳርገዋል።

የአህጉሪቱ ሕዝቦች፣ የነጻነት ትግሉ የአህጉሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ በትምህርት የመቀየር የዳበረ ራዕይ ቢኖረውም፤ ከነጻነት ማግስት በአህጉሪቱ የተፈጠረው ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ምስቅልቅልና ከዚህ የመነጨው የዕርስ በዕርስ ግጭት እና ጦርነት አህጉሪቱ ለትምህርት ተገቢውን ትኩረት እንዳትሰጥ ተግዳሮት ሆኖባት ቆይቷል።

ይህም ዛሬ ጭምር አፍሪካ እና ሕዝቦቿ የብዙ የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት፤ ከራሳቸው ተርፈው ለለሌሎች የሚተርፍ ሀብት ባለቤቶች ቢሆኑም የድህነትና የሀዋላ ቀርነት ተምሳሌት ከመሆን አልተሻገሩም። አንገታቸውን ደፍተው ከጠባቂነት ሕይወት አልተላቀቁም ።

አፍሪካውያን ካሉበት የድህነት፤ የኋላ ቀርነት እና የጠባቂነት ሕይወት ወጥተው፤ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን ከሁሉም በላይ ዘመኑን የሚዋጅ ትምህርት ያስፈልጋቸዋል። ከነጻነት ማግስት ጀምሮ ካሉበት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ወጥተው የተረጋጋች ሰላማዊ እና የበለጸገች አኅጉር ለመፍጠር ትምህርት ወሳኝ አቅማቸው ነው፡፡

ለዚህም ከሁሉም በላይ ራሳቸውን በተገቢው መንገድ ማወቅ የሚያስችል፤ የቀደሙት ቅኝ ገዥዎቻቸው እንደሚያስቧቸው ሳይሆን ፍጥረታዊም ሆነ አሁንዊ ማንነታቸው የራሳቸውን ብሩህ እጣ ፈንታ መስራት የሚያስችል የተሟላ ስብዕና ባለቤት መሆናቸውን ሊያረጋግጥላቸው የሚችል ትምህርትና የትምህርት ስርዓት ያስፈልጋቸዋል።

ያላቸውን የተፈጥሮ ጸጋዎች አውቆ ማልማት፣ መነጋገርን ፣ ተነጋግሮ መደማመጥን ፣ ተደማምጦ መስማማትን መፍጠር የሚያስችል፣ በዚህም አህጉሪቱን ከግጭት አዙሪት በማውጣት ሕዝቦቿን ብዙ ዋጋ ወደ ከፈሉበት የተሟላ ነጻነታቸው የሚመራ በዕውቀት የተገራ አእምሮ ያስፈልጋቸዋል፤ ለዚህ ደግሞ ዘመኑን የሚዋጅ ከራሳቸው ትናንቶች የተቀዱ እውቀቶች ወሳኝ ናቸው።

በወንድማማችነት፤ በጋራ ተጠቃሚነታቸው ላይ ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ባልተገባ ትርክት የጠቆረውን የቀደመ ታሪካቸውን በመለወጥ፤ በብዙ ሴራ የተተበተበውን አብሮ የማደግ አቅማቸውን ተጨባጭ አቅም ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ ለዚህ ደግሞ ለሴራ ያልተገዛ አእምሮ መፍጠር ይኖርባቸዋል።

በዓለም አቀፍ መድረኮች እንደ አንድ ትልቅ ማኅበረሰብ እራሳቸውን ወክለው የሕዝቦቻቸውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እውን በማድረግ ቀጣይነት ያለው የትውልዶች መነቃቃት መፍጠር፤ በመነቃቃጥ ውስጥ ቀጣይነት ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገቶችን አስጠብቆ ማስቀጠል የሚያስችል የትምህርት ስርዓት ያስፈልጋቸዋል።

ይህን ለመፍጠር ከሁሉም በላይ እንደ አህጉር ለትምህርት ትኩረት መስጠት፣ የትምህርት ስርዓቶችም ይህንኑ እውነታ ተጨባጭ ማድረግ የሚያስችል አቅም እንዲኖራቸው በኃላፊነት መንፈስ መስራት ያስፈልጋል። የትምህርትን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ከአካዳሚክ ትርጓም ባለፈ በአፍሪካውያን የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የተሟላ ትርጓሜ እንዲኖረው በቁርጠኝነት መሥራት ወሳኝ ነው።

ትውልዱ ነገዎቹን በባዕድ ሀገር ተስፋ ከማድረግ አውጥቶ ፣ ቁጭት በሚፈጥረው የመሥራት መነቃቃት የራሱን ዕጣ ፈንታ ብሩህ ማድረግ፣ ከጠባቂነት ወጥቶ ተራፊ ሊሆን እንደሚችል፤ የሚያስተውልበትና በተግባር በቁጥ የሚንቀሳቀስበትን የትምህርት መነቃቃት መፍጠር ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ የሀገራት መሪዎች ኃላፊነት ትልቅ እና ታሪካዊ ጭምር ነው!

አዲስ ዘመን የካቲት 8 /2016

 

Recommended For You