በተለምዶ የምንጠቀማቸው ብዙ ቃላት አሉ፤ ዳሩ ግን በሕጋዊ አገባባቸው ሲታዩ ደግሞ ትክክል ያልሆኑ (እንዲያውም ይባስ ብሎ ሕገ ወጥ የሆኑ) ናቸው። ከእነዚህም አንዱ ‹‹ስደተኛ›› የሚለው ቃል ነው። የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ባለፈው ሳምንት (ከጥር 28 እስከ 30) ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በስደተኞች አዋጅና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና ሰጥቶ ነበር። ሥልጠናውን የሰጡት የተቋሙ ባለሙያዎች ገጠመኞቻቸውን ሲናገሩ፤ ብዙ ሰዎች ከስደተኝነት ጋር በተያያዘ ግንዛቤው የላቸውም። ሊያሳውቁ የሚገባቸው ጋዜጠኞች ራሱ አግባብ ባልሆነ መንገድ ሲጠቀሙ እና ተቋሙ ኃላፊነቱ ያልሆነውን ነገር ሁሉ ሲጠይቁ ይስተዋላል። ይህ የሆነው አዋጁን በሚገባ ካለማወቅ እና የቃላት አገባባቸውን ባለመገንዘብ ነው።
ወደ ልማዳዊ አገላለጾች እንመለስ። በልማዳዊ አገላለጽ ‹‹ስደተኛ›› የሚባለው ማንኛውም አካባቢውን ለቆ የሄደ ሰው ነው። ይባስ ብሎ በሀገሩ ውስጥ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የሄደውንም ‹‹ስደተኛ›› ሲባል ይሰማል። አካባቢውን ለቆ የሄደው ሰውም ‹‹ተሰድጄ›› ሲል ይሰማል። ልክ አንዳንድ ሰዎች (በተለይም በገጠር አካባቢ) አካባቢያቸውን ‹‹ሀገሬ›› ብለው እንደሚጠሩት ማለት ነው። ራቅ ካለ አካባቢ የመጣን ሰው ‹‹ሀገርህ የት ነው?›› ብለው ይጠይቁታል። መላሹ ‹‹ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ….›› ብሎ አይደለም የሚመልስ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አንድ አካባቢ (የመጣበትን) ይናገራል። ይህ በልማዳዊ አገላለጽ ነው፤ ሕጋዊና አግባባዊ አገባቦችን ባለማወቅ ነው።
ልክ እንደዚህ ሁሉ፤ ስደተኛ የሚለውን ቃል ሕጋዊ ባልሆነ አገባቡ እንጠቀመዋለን። ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ያለ ችግር አይደለም። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዚሁ ጉዳይ ባወጣው አንድ ሐተታ፤ ስደተኛ፣ ፍልሰተኛ እና ጥገኝነት ጠያቂ የሚሉትን ቃላት ሰዎች በተተካኪነት ሲጠቀሟቸው ይስተዋላል። ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚጠቀሟቸው በእንግሊዘኛ ቃላት ስለሆነ የተሰጣቸው ትርጓሜ ዓለም አቀፍ ይሆናል። ወደ አማርኛ ስናመጣው ግን ምናልባትም አንዳንዶቹ ላይ አከራካሪ ሊሆን ይችላል። እስኪ የተሰጣቸውን ትርጓሜ እንመልከት።
ስደተኛ (refugee) ማለት በአንዲት ሀገር ለመኖር ሕጋዊ ዕውቅና ያገኘ ከሌላ ሀገር የመጣ ማለት ነው። ለምሳሌ፤ ከኤርትራ ወይም ሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ፣ የስደተኝነት ዕውቅና አግኝቶ በኢትዮጵያ የሚኖር ማለት ነው። ይህን ዕውቅና የሚያገኘው ከዜግነት ሀገሩ በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ለመሰደድ የበቃ ሲሆን ነው። የሚሰደድበት ምክንያት ጦርነት፣ የዘር ወይም የሃይማኖት ጥቃት ሊሆን ይችላል። በአጭሩ ስደተኛ ማለት ጥገኝነት በጠየቀበት ሀገር ውስጥ ዕውቅና ያገኘ ማለት ነው።
ጥገኝነት ጠያቂ (asylum seeker) ማለት ደግሞ በድንበር ወይም ጠረፍ ላይ ሆኖ የስደተኝነት ዕውቅና ለማግኘት የሚጠይቅ ማለት ነው። የስደተኝነት ዕውቅና ለመስጠት ሥልጣን ላለው አካል አመልክቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሚጠባበቅ ማለት ነው። ፍልሰተኛ (Migrant) ማለት ቃሉ እንደሚገልጸው ከሀገራቸው ፈልሰው ወደ ሌላ ሀገር መሄድ ማለት ነው። የአማርኛውም ሆነ የእንግሊዘኛው ቃል ሕጋዊ ትርጉም አልተሰጣቸውም። ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የላቸውም። እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ ተቋማት ግን ያውቋቸዋል። ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) የሚባል የተባበሩት መንግሥታት ተቋም በዚሁ ጉዳይ ላይ የሚሠራ ነው። ፍልሰተኞች ላይ የሚሠራ ተቋም ቢሆንም ፍልሰተኞች (Migrants) ግን ዓለም አቀፋዊ ሕጋዊ ዕውቅና የላቸውም። ፍልሰተኞች በፈለጉ ጊዜ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ናቸው።
በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ምሳሌ ከወሰድን በሊቢያ በኩል አድርገው ወደ አውሮፓና ሌሎች ሀገራት የሚሄዱት የሀገራችን ዜጎች ማለት ነው። ፍልሰተኞች የሚሄዱት የተሻለ ኑሮ ወይም ትምህርት ፍለጋ ነው። በሀገራቸው ምቹ ኑሮ አላገኘንም በሚል ሠርቶ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ነው። እነዚህን ሰዎች በተለምዶ ‹‹ስደተኞች›› ስንላቸው ይሰማል። በሕጋዊ አግባብ ግን ስደተኞች ሳይሆኑ (ዕውቅና ስላላገኙ) ፍልሰተኞች ይባላሉ። ተፈናቃይ (Internally displaced people) የሚባለው ደግሞ ቃሉ እንደሚገልጸው ከአካባቢው የተፈናቀለ ማለት ነው። እነዚህ ሰዎች ከሀገራቸው አይወጡም። የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ እንደ ማሳያ ብንወስድ፤ ከአንድ የኢትዮጵያ አካባቢ በጦርነት ወይም በድርቅ፣ ወይም በሌላ ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋ አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ሌላ የኢትዮጵያ አካባቢ ተፈናቅለው የሄዱ ማለት ነው።
አንዳንድ ጊዜ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን እንደ ስደተኛ የማየት አጋጣሚ እንዳለ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ባለሙያዎች ገጠመኞቻቸውን ተናግረዋል። የተቋሙ ስያሜ ‹‹ስደተኞችና ተመላሾች›› ስለሚል ተፈናቃዮችን ‹‹መቼ ነው ወደ ቀያቸው የሚመለሱ?›› የሚል ጥያቄዎች ይቀርቡላቸዋል። የስደተኞችና ተመላሾች ጉዳይ ግን ዓለም አቀፍ ጉዳይ ነው፤ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚያገናኝ ነው። በዚህ አጋጣሚ ተመላሾች ማለት በስደት ከቆዩበት አገር ወደ ትውልድ ወይም የዜግነት ሀገራቸው የሚመለሱ ማለት ነው። የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ባለሙያዎች የዳሰሳ ጥናት መረጃ እንደሚያሳየው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ120 ሰዎች አንዱ ስደተኛ ነው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ደግሞ ከ26 ሀገራት የተቀበለቻቸውን ስደተኞች ታስተናግዳለች።
በነገራችን ላይ ይህ የኢትዮጵያ ስደተኞችን የማስተናገድ ባሕል ለሺህ ዘመናት የኖረ ነው። የዓለም ሀገራት አስገዳጅ የሆነ ሕግ አውጥተው በቁጥጥር ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ባሕል ነው። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ ሕግ ተገዢ ሆና ሕጋዊ ስምምነቶችን የፈጸመች እና የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ያወጀች ቢሆንም ስደተኛን መቀበል የጀመረችው ግን ዓለም ሕግ የሚባል ነገር ከማወቁ በፊት ነው። ዛሬ ላይ ያለውን ትውልድ ባሕል ብናስተውል እንኳን አልጋውን ለእንግዳ ለቆ መሬት ላይ የሚተኛ ዜጋ ያለባት አገር ናት። ‹‹ቤት ለእንግዳ ነው›› በሚል የሃይማኖት፣ የባሕልና ሞራል ተገዢ የሆነ ዜጋ ያለባት አገር ናት። የሥልጣኔ እና የሞራል ማማ ላይ ነን የሚሉ የነጭ ሀገራት አፍሪካ አገር ውስጥ የሚደረግን ነገር የማመስገን ልማድ ባይኖራቸውም ስደተኞች ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያስተዋሉትን በጎ ነገር በተለያየ አጋጣሚ ሲናገሩ ይሰማል።
አንዳንድ ጊዜ መንገድ ላይ ከሀገር ውስጥ የኔ ቢጤዎች ይልቅ ለውጭ ሀገር ዜጎች ሳንቲም ሲሰጥ ልታስተውሉ ትችላላችሁ። አንዳንድ ሰዎች ምናልባትም ‹‹ለነጭ ማሽቃበጥ›› ሊሉ ይችላሉ። ግን አይደለም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሞራል ባለቤት ስለሆነ ነው። ለልመና ጎዳና ላይ የወጣ የውጭ አገር ዜጋ ምን እንዳደርግለት ነው የሚሽቃበጥለት? መቼ ውለታ ይመልስልኛል ብሎ ነው?
ለውጭ ሀገር ዜጎች ድጋፍ የሚሰጠው በቁሳዊ ውለታ ሳይሆን ‹‹ነግ በኔ›› በሚለው ብሂል ለሕሊና ተገዢ በመሆን ነው። ያ የውጭ አገር ዜጋ የገንዘብ ችግር ብቻ አይደለም ያለበት፤ የሥነ ልቦና መጎዳትም አለበት። በሰው ሀገር ነው ያለው፤ የሀገሩን አየር ይናፍቃል። ከሀገሩ የወጣበትን ችግር ያስባል። የኢትዮጵያ ሰዎች ለዚህ ሰው ገንዘብ የሚሰጡት በሰው ሀገር ውስጥ ሲኖር በገንዘብም በሞራልም እንደሚጎዳ ስለሚያስቡ ነው። በአጠቃላይ ስደተኛን መቀበል ለኢትዮጵያ ሕጋዊ አስገዳጅ ሳይሆን (ሕጉ እንዳለ ሆኖ) ባሕል ነው ማለት ይቻላል። ይህ ባሕል ደግሞ ዲፕሎማሲ ሆኗል ማለት ይቻላል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ገጽታ በበጎ እንዲነሳ ያደርጋል። ይህ ባሕላችን ይቀጥል እያልን ከስደት ጋር የተያያዙ ሌሎች መረጃዎችን በሌላ ክፍል ይዘን እንመለሳለን።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2016