ኢትዮጵያውያን አንድነት መለያቸው፤ ማሸነፍ ታሪካቸው ነው። ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ የማይደረምሱት ተራራ፤ የማያሸንፉት ጠላት፤ የማይወጡት አቀበት አይኖርም። ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስከብራና የጥቁር ሕዝቦች መከታ ሆና የዘለቀችው በሕዝቦቿ ትብብርና አንድነት ነው።
ትላንት ኢትዮጵያውያን አድዋ ላይ ቅኝ ገዢዎችን አሳፍረው መልስዋል። በወቅቱ በመሪው አጼ ሚኒሊክና በተለያዩ ሀገረ ገዢዎች መካከል አለመግባባትና ቅራኔ ቢኖርም ሁሉም ነገር ከሀገር በታች ነውና ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው ወራሪውን የጣሊያን ጦር በአንድነት ድል ነስተዋል። በዚህም ኢትዮጵያን ከፍ አድርገዋል፤ ከዛም አልፎ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ሆነዋል። አንድት ኃይልም እንደሆነ ለቀሪው ዓለም የማይፋቅ ታሪክ ጽፈዋል።
በአጼ ሚኒሊክና በተለያዩ ገዢዎች መካከል ያለውን ልዩነት ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ለመውረር የተነሳው የፋሺሽት ኃይል በኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ ተደቁሶ ወደ መጣበት ከመመለሱም ባሻገር ኢትዮጵያውያን በውስጣቸው ልዩነት ቢኖርም ኢትዮጵያን ለማዋረድና ለመበታተን ለሚመጣ ኃይል ክፍተት እንደማይሰጡ ትምህርት ሆኗል።
የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተመው በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክና በእቴጌ ጣይቱ አመራር ስር በአንድ ጥላ ተሰባስበው ባደረጉት ተጋድሎ የተመዘገበ ታሪካዊ ክስተት ነው። በአጠቃላይ አድዋ ከኢትዮጵያ አልፎ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ነው።
ሆኖም እኛ የአሁን ትውልዶች ድሉን የምንረዳው በዛ ልክ ነው ወይ የሚለው መጠየቅ ያለበት ጉዳይ ነው። እኔ እንደታዘብኩት ግን አድዋን የተረዳነው አይመስለኝም። ወይንም አንዳንድ ፖለቲከኞች ሆን ብለው ከጊዜያዊ ጥቅም ከማሰብ ድሉን ወደ ብሄርና ጎሳ አውርደው ለማሳነስ ሲጥሩ ታዝቤያለሁ። ይህንኑ ተከትሎም እንደፋሽን ይህንን ግዙፍ ታሪክ መንደር ውስጥ ለመወሸቅ የሚደረግ መውተርተር ጎልቶ ይታያል።
የአፍሪካን ድል ከጥቁር ሕዝቦችና ከአፍሪካ ድልነት አውርደን ወደ ብሄርና ሰፈር ለማሳነስ የምናደርገው ግብግብ እውን እኛ አድዋ መንፈስ ገብቶናል ወይ የሚያስብል ነው። ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው የመከሩበትና በጋራ ሆነው ልዩነታቸውን ሁሉ በመተው በመካከላቸው ቅሬታ ያለባቸው ሁሉ “ይቅር ለእግዚአብሄር” ተባብለው በአንድነት በመትመም በግማሽ ቀን ወራሪውን ኃይል ድባቅ የመቱበት ድል ነው። ታዲያ እኛስ ከዚህ ድል ምን እንማራለን።
የዛሬዎቹ ትውልዶች ከመተባበር ይልቅ መከፋፈልን፤ ከአንድት ይልቅ ልየነትን፤ በጋራ ከመቆም ይልቅ መነጣጠልን አጥብቀን እንወዳለን። በዚህ ደግሞ ድል እንደማይገኝ ከአድዋ በላይ ምስክር የለም። ጦርነቱን ለማስተባበር፣ ወረኢሉ ለመክተትና ከመላው ኢትዮጵያ ሰራዊቱ አድዋ ላይ እስኪገኝ በጥቅሉ አስር ወራትን መፍጀቱን የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ። በመካከል ልዩነት ቢኖር፣ ንጉሰ ነገስት አፄ ሚኒሊክ የጠሩት ክተት ላይ መተማመን ቢጠፋና በአንድ ኢትዮጵያ መፅናት የጋራ ዓላማ ባይኖር ኖሮ አድዋን የሚያክል ግዙፍ ታሪክ ማስመዘግብ የሚታሰብ አልነበረም። ዛሬ ታዲያ በዚህ መልኩ ልዩነት ላይ አተኩረን ሀገራችንን አሸናፊ ማድረግ የምንችለው ? እንዴት ነው የእኛን ማደግ ማይፈልጉ የውጪ ጠላቶችን መርታት የምንችለው? እንዴት ነው ሊከፋፍሉንና ሊነጣጥሉን ሰርክ የሚሰሩ አካላትን ማሳፈር የምንችለው ?
የዛሬው ትውልድ መሪውን ምን ያህል ያዳምጣል?፤ በጎደለ ለመሙላት ራሱን ምን ያህል አዘጋጅቷል?፤ እሱ ወድቆ ወንድሙ እንዲያሸንፍ ምን ያህል ጨብጧል ? የተሰጠውንስ አደራ ምን ያህል ይጠብቃል ? ከስልጣን ይልቅ ሀገራችንን ምን ያህል እናስበልጣለን የሚለውን ከአድዋ ታሪክ አንጻር መመልከቱ በቂ ነው። ንጉሰ ነገስቱ ለአስር ወራት ግንባር ላይ ሲቆዩ ራስ ዳርጌ የኢትዮጵያን መንግስት ሲመሩ እንደነበር፤ ይህም አንድ የጋራ አገርና ሕብረት እንደነበር ትልቅ ምሳሌ የሚወሰድ ነው። አጼ ሚኒሊክ ስልጣናቸው ሳያሳሳቸው ለራስ ዳርጌ አሳልፈው ሰጥዋል፤ ራስ ዳርጌም ስልጣን ሳያጓጓቸው አደራቸውን ጠብቀው ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።
አድዋ የአሸናፊነት ብቻ ሳይሆን የርህራሄም መገለጫ ነው። የሰው ልጅ ክብር የተገለጠበት ነው። ጣሊያኖች ብዙ ጀነራሎች፣ የጦር መሪዎችና ወታደሮች ሞተውባቸው ጦርነቱን ሲያሸነፉ ጭፈራና የድል ፈንጠዝያ በኢትዮጵያውያን ዘንድ አልነበረም። እቴጌ ጣይቱ “የሞተው የሰው ልጅ ነው፤ ምንም ጭፈራ አያስፈልግም” በሚል አስክሬናቸው ፍትሃት ተደርጎለት እንዲቀበር አድርገዋል።
እኛስ ምን ያህል ይቅር ባዮች ነን ? ምን ያህል ሰብአዊነት ይሰማናል ? ወይስ የራሳችንን ወገን ዘቅዝቀን ምንሰቅል፤ የምናፈናቅል፤ የምንገድል፤ ሰዎች ሆነን ነው የምንቀጥለው። እስኪ እራሳችንን መለስ ብለን እንይ። በአድዋ ዙሪያ የተጻፉ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት፤ ‹እምቢ ለነፃነቴና ለሀገሬ ክብር› ብሎ ወደ ፍልሚያው የገባው ኢትዮጵያዊ ለእግሩ ጫማ አልነበረውም፤ ጥሻና ገደሉን በባዶ እግሩ በመውጣትና በመውረድ ነው የተዋጋው።
በእጁ የያዘው መሣሪያም የጠላትን ጦር ይመክታል ብሎ የሚገመትም አልነበረም። ኢትዮጵያውያን ኋላቀር የሚባለውን መሣሪያ ሊያውም በበቂ ሁኔታ ሳያገኙ፣ ጦርና ጋሻ ይዘው፣ ታላቅ ወኔ ተላብሰው፣ የንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጼ ምኒሊክና የእቴጌ ጣይቱን የጦርነት ስልት ተጠቅመው በመዋጋት ጠላትን መግቢያና መውጫ አሳጥተው ነው አድዋን ያህል ታላቅ ድል መቀዳጀት ችለዋል።
የዛሬውስ ትውልድ ቅድሚያ የሚሰጠው ለምቾቱ ነው ወይስ ለሀገሩ ? ለሀገሬ ልስጥ ነው ወይስ ሀገሬ ትስጠኝ የሚለው ? ይህ እያንዳንዳችንን የሚመለከትና ምላሹም ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ነው። የዓድዋ ድል የትብብርንና የአንድነትን ውጤታማነት እንዲሁም ለነፃነት መስዋዕትነት መክፈል ታላቅ ክብር እንደሆነ ያሳየ፣ የነጮች የበላይነት ማክተም እንደሚችልም የጠቆመና መንገድ የከፈተ አንፀባራቂ ክስተትም ነው። ይህን ክብርና መንገድ በጀግንነትና በመስዋዕትነት በታጀበ ተግባር ያሳዩትና የመሩት ኢትዮጵያውያን ደግሞ የጭቁኖች መመኪያ መሆናቸውን አስመስክረዋል።
ከዚህስ አንጻር የአሁኑ ትውልድ ከራሱ አልፎ ለሌሎች ጥቁር ሕዝቦች ምን ያህል መመኪያ ሆኗል ? እራሱን ነጻ አውጥቶ ሌሎችን ነጻ ለማውጣት ምን ያህል ዝግጁ ነው ? በተለይም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አማካኝነት የተፈጠረውን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ተገንዝቦ እራሱን እና ሀገሩን ምን ያህል እየተከላከለ ነው ? በየቀኑ በሶሻል ሚዲያ አማካይነት እየተሰራጩ ከሚገኙ ትውልድ አምካኝና ሀገር አጥፊ መልዕክቶች እራሱን ሀገሩን ምን ያህል እየጠበቀ ነው ?
የዓድዋ ድል ፋይዳዎች በርካታ ናቸው። የመጀመሪያው ኢትዮጵያን ከወራሪ ኃይል ጠብቆ ማቆየት ቢሆንም በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ ልዩነቶችን አስማምታ አንድነቷን የጠበቀች በአጠቃላይ ኃያል የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠርና መገንባት ነበር። ይህ የተቀደሰ ዓላማ ምን ያህል ተሳክቷል ? ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ነፃነት፣ ክብርና አንድነት ሲሉ በዓድዋና በሌሎች ስፍራዎች ለማመን የሚከብዱ ከባድ ተጋድሎዎችን አድርገው ነፃ አገር ለ‹‹ተተኪው ትውልድ›› ቢያስረክቡም፣ ተተኪው ትውልድ ከአንድት ይልቅ ልዩነት በመምረጥ እርስ በራሱ ሲገዳደል ማየት የተለመደ ሆኗል። ይህ አስከፊ ሁኔታም ዛሬ ድረስ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ በዘር፣ በኃይማኖትና በአመለካከት ሳይከፋፈሉ ዓድዋ ላይ ጠላትን ድል ያደረጉ ልጆች እናት መሆኗን ማሰብና ከዓድዋ ድል በኋላ ባፈራቻቸው ‹‹ልጆቿ›› ምክንያት በአስከፊ የዘር ፖለቲካ ስትታመስ መመልከት እጅግ አሳዛኝና አስገራሚ ተቃርኖ ነው። ይህ ውድቀት ደግሞ በእውነት እኛ የአድዋ ልጆች ነን የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል።
አድዋ የአንድነትና ተባብሮ የመስራት ውጤት ነው። በወቅቱ ኢትዮጵያም ልክ እንደሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች በኃይማኖት፣ በዘርና በቋንቋ የተለያዩ ሕዝቦች ያሉባት ሀገር ነበረች” የሚሉት ምሁሩ፣ ኢትዮጵያውያን በዘር፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ ቢለያዩም፣ ከነበረው ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የተነሳ፣ ለነጻነታቸውና ለሀገራቸው ባላቸው ቀናኢነት ሁሉም በአንድነት ተሰልፈው የሀገርን ሉአላዊነት ሊዳፈር የመጣውን ጠላት በመመከት ማሸነፍ መቻላቸውን ያመለክታሉ። ያ የጣሊያን ጦር ዘመናዊ በሆነ አደረጃጀት የተዋቀረ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያውያን፣ በመሪዎችና በጦር አመራሮች መካከል የነበረውን አንድነትና በሕዝቦች መካከል የታየውን ጠንካራ የተሳሰረ የአንድነት መንፈስ ፈጽሞ ሊሰብረው እንዳልቻለ ያስረዳሉ።
በአድዋ ያ ታላቅ ድል የተመዘገበው በኢትዮጵ ያውያን መካከል ቀደም ሲል ምንም አይነት ልዩነቶች ስለሌሉ የሆነ አይደለም። ጠላት ሲመጣ ግን ኢትዮጵያውያኑ ልዩነቶቻቸውን ወደጎን በመተው ለሀገራቸው ሉአላዊነት፣ ለነጻነት ያሳዩት እጅግ በጣም የሚደንቅ አንድነትና ቆራጥነት ለድል አብቅቷቸዋል። ለድሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ባለው የኅብረተሰብ ክፍል መካከል የታየው አንድነት፣ የአመራር ብቃት፣ ችሎታና ጠንካራ የሆነ ቁርጠኝነት መሆኑን ይጠቅሳሉ። የኢትዮጵያ ሉዕላዊነት የተጠበቀው ኢትዮጵያውያን ባሳዩት አንድነትና የዓላማ ጽናት ነው ማለት ይቻላል።
አድዋ ላይ የተገኘው ለጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነው ድል በሁሉም ነገር አንድ ስለሆንን የተገኘ አይደለም፤ ሆኖም ግን ልዩነቶችን ወደ አንድነት በማምጣት ተባብሮ መሥራት ለድል እንደሚያበቃ መመልከት ችለናል ይላሉ። ከአድዋ ድል የምናገኘው ትልቅ ትምህርት አንድነታችንን ብንጠብቅ ልክ እንደ አድዋ ሉዕላዊነታችንን የሚዳፈር አንዳች ጠላት በሚመጣበት ጊዜ ሉአላዊነታችን አስጠብቀን ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚቻል ያሳየ ነው።
ከጣሊያኖች ስትራቴጂ አንደኛው የኢትዮጵያውያንን አንድነት ሊቦረቡር በሚችል መልኩ የተለያዩ ሀገር ገዢዎችን በጥቅማጥቅም ማማለል አንዱ እንደነበር ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያውያኑ በሀገር ጉዳይ ምንም አይነት ድርድር አያውቁምና ይህን ስትራቴጂም አክሽፈዋል። አባቶቻችን በጣም በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆነው ታሪክ ሠርተው የአድዋን ድል አስመዝግበዋል ያሉት ምሁሩ፣ በሚመች ሁኔታ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጣም በማይመች ሁኔታ ውስጥም ሆነን ለመጪው ትውልድ ሊተርፍ የሚችል ታሪክ መሥራት አለብን ፡
ዛሬም የአድዋን ድል መሰል የጀግንነት ስራ ልንሰራባቸው የሚገቡ በርካታ የቤት ስራዎች ያሉን ሕዝቦች ነን። አገራችን እንደ አደዋው ዘመን በቀጥታ ቅኝ ሊገዟት ባይመጡም በእጅ አዙር ሊያንበረክኳት የእነሱ ተላላኪ የሆነ መንግስት ሾመው እንደፈለጉ ሊፈልጧት ሊቆርጧት የሚቋምጡ በርካታ የዓለም አገራት መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ስለዚህም እኛ ልክ እንደ አድዋ ጀግኖች የውጭ ወራሪዎችን እና ተንኮለኞችን ሴራ ለማክሸፍ ምን ያህል ዝግጁዎች ነን ? የሚለው መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2016