‹‹የተፋሰስ ልማት ለአካባቢው አማራጭ የሌለው እንደሆነ አርሶአደሩም ሆነ አርብቶአደሩ ተገንዝቧል››  ወይዘሮ ኢክራም ጠሐ የምዕራብ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ

በኦሮሚያ ከሚገኙ 23 ዞኖች መካከል አንዱ ምዕራብ ሐረርጌ ነው። 15 ወረዳዎች እና 512 ቀበሌዎች አሉት። አዋሳኞቹም ምሥራቅ ሸዋ፣ ምሥራቅ አርሲ፣ ባሌ፣ ሶማሌና አፋር ክልሎች ናቸው። ምዕራብ ሐረርጌ በመካከል ላይ የምትገኝ የወጪ ንግድ ማዕክል (ኢምፖርት ኤክስፖርት ኮሪዶር) ናት። በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋም ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ጫት ነው። የህዝቧ የኑሮ እንቅስቃሴም የተመሰረተው በዚሁ የጫት ንግድ ገቢ ነው። የቡና ልማትም ሌላው የአካባቢው የኢኮኖሚ ምንጭ ነው። የተለያዩ የሰብል ልማቶችም ይከናወናሉ። ከነዚህ የሰብል ልማቶች ደግሞ የበጋ ቆላ ስንዴ መስኖ ልማት ለዞኑ ተጨማሪ መሆኑም እንደ አንድ ትልቅ እመርታ ተወስዷል።

በነዚህ የልማት እንቅስቃሴዎች፣ በማኅበራዊ አገልግሎቶችና ከወቅታዊ ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በተለይም የአካባቢ ሰላምንና ደህንነትን በማስጠበቅ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት የምዕራብ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ ከወይዘሮ ኢክራም ጠሐ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል።

አዲስ ዘመን፦ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የግብርና እና አጠቃላይ የልማት ሥራ እንቅስቃሴና ውጤታማ የሚባሉ ተግባራትን ቢገልጹልን፤

ወይዘሮ ኢክራም፦ በዞኑ በግብርናው በአረንጓዴ አሻራ ተፋሰስ ልማት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ተደርጓል። በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት፤ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ልዩ ትኩረት በመስጠት፤ የተቀናጀና የተናበበ ሥራ በመሥራት ስኬት ማስመዝገብ ተችሏል። በዚህ የተፋሰስ ልማት ሥራም ተራቁተው የነበሩ የዞኑ ተራራማ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ማድረግ ተችሏል። የደን ሽፋናቸውም እየተሻሻለ መጥቷል። ደርቀው የነበሩ ምንጮች አሁን ላይ ወደነበሩበት ተመልሰዋል። ለአብነትም ባሮጨርጨር ደርቆ ነበር። አሁን ላይ ተመልሶ በብዛት የአሣ ምርት ማግኘት ተችሏል። ይህ አካባቢም በክልሉ መንግሥት በኢኮ ቱሪዝም እውቅና ስለተሰጠው የማልማቱ ሥራ ተጠናክሯል። የተሰራው ሥራም ተጨባጭ ለውጥ ያስገኘ በመሆኑ በጥሩ ተሞክሮ ተወስዷል። እንዲህ ያሉ በጎ ተሞክሮዎች መቀጠል እንዳለባቸውም ከተሰሩት የሥራ ውጤቶች ግንዛቤ መያዝ ተችሏል።

ምዕራብ ሐረርጌ ዝናብ አጠር ከሚባሉ አካባቢዎች አንዱ ሆኖ ሲሆን በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በተከታታይ ዓመታት የዛፍ ችግኞች በመተከላቸው አካባቢው ላይ የሚስተዋለው የዝናብ እጥረት እንዲሚሻሻል ተስፋ ያሳደረ ሥራ ሆኗል ። የዝናብ መጠን መጨመር ለግብርናው ብቻ ሳይሆን፣ የአካባቢውን የመጠጥ ውሃ ችግርንም ስለሚፈታ የተፋሰስ ልማት ለአካባቢው አማራጭ የሌለው እንደሆነም አርሶአደሩም ሆነ አርብቶአደሩ ተገንዝቧል።

የተፋሰስ ልማት ስራ እንደሀገር የተቀመጠውን አቅጣጫ ለመተግበር እኛ በዞናችን ቀድመን ነው ሥራ የጀመርን ሲሆን በየዓመቱም በተራራማ አካባቢዎች የተፋሰስ ልማት ስራዎች ይሰራሉ። ከዛፍ ችግኝ ተከላዎች በተጨማሪ የተለያዩ የፍራፍሬ ልማት ሥራዎችም ጎን ለጎን እየተከናወነ ይገኛል። እነዚህ ተጨማሪ የልማት ሥራዎች ገቢ ማስገኛዎች ወይንም የአካባቢ ስነምህዳርን ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን፤ ማህበረሰቡ አመጋገቡ የተመጣጠነ እንዲሆን የሚያስችሉ ጭምር ናቸው።

በግብርናው ዘርፍ፤ በአካባቢው የተለያዩ የሰብል ልማቶች ቢከናወኑም እስከ አሁን በስንዴ ልማት አካባቢው አይታወቅም ነበር፤ ስንዴ ባለመመረቱም በተለይም በቆላማው የዞኑ ወረዳዎች ለሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ስንዴ በእርዳታ ነበር እንዲያገኙ ሲደረግ የነበረው። አሁን ላይ ግን እንደ ሀገር ታቅዶ ወደ ትግበራ የተገባው የበጋ ቆላ ስንዴ መስኖ ልማት በዞናችንም ለመተግበር መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ ላይ አመራሩ፣ ባለሙያው፣ አርሶአደሩም ሁሉም በጋራ ተወያይተው መግባባት ላይ በመድረስ ወደ ሥራ የተገባው በመሆኑ በረሀ ውስጥ ስንዴ እንዲለማ እያስቻለ ነው።

በተለይም በዘንድሮ በጀት ዓመት በዞኑ ወደ 40 ሺ 500 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ልማት እንዲከናወን ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን እቅዱን ከግብ ለማድረስ የልማት ሥራው ከዓመት ዓመት እየጨመረ በመምጣቱ አሁን ላይ ውጤት ማየት ተጀምሯል። በ2014 በጀት ዓመት በ17ሺ ሄክታር መሬት ላይ፣ በ2015 በጀት ዓመት ደግሞ 34ሺ ሄክታር ላይ ነበር ልማቱ የተከናወነው። በዚህ በጀት ዓመት የልማቱ ሥራ ቀድሞ ነው የተጀመረው። ስንዴውም ቀድሞ መድረስ ችሏል። በአሁኑ ጊዜም አርሶአደሩ የአጨዳ ሥራ ላይ ይገኛል።

ሌላው በግብርናው ዘርፍ በሌማት ትሩፋት የሚከናወነው ሥራ ሲሆን ከብት ማድለብ፣ በንብ ማነብ የማር ልማትና በሌሎችም በሰፊው እየተከናወነ ይገኛል። አጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ እየተሰራ ያለው ሥራ ተስፋ ሰጪና የሚያበረታታ እንደሆነ ነው የሥራ ግምገማችን የሚያሳየው። ግምገማችን በዚህ መልኩ ቢያስቀምጥም ክፍተቶች መኖራቸውንና አሁን እየተሰራ ካለው በላይ ስኬት ለማስመዝገብ በልማቱ ላይ ያለውንም በማስተባበር የተጠናከረ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል።

አዲስዘመን፦ በማኅበራዊ ዘርፍ በትምህርት፣ በጤና እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራትና ተደራሽነቱን እንዴት ይገልጹታል?

ወይዘሮ ኢክራም፦ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ሰፊ የትምህርት ቤት ግንባታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡ በዞኑ ከዚህ ቀደም የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤቶች አልነበሩ በመሆኑና አስፈላጊነቱም ስለታመነበት የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበር ወደ 999 መዋዕ ሕፃናት ትምህርት ቤቶች በመገንባትና ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ እድሉ ያልነበራቸው ከከተማ ራቅ ያሉ አካባቢዎች እየተጠቀሙበት ነው።

እንደ ሀገር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በመንግሥት የተያዘውን አቅጣጫ ተግባራዊ በማድረግ የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤቶች ቅድሚያ እንዲያገኙ የተሰራ ሲሆን በዚህም የትምህርት ጥራትን ከታች ጀምሮ ለማስጠበቅ ዞኑም የድርሻውን ለመወጣት ችሏል። ወደላይ ያሉት ተማሪዎች በትምህርታቸው ጠንካራ እንዲሆኑም የተለያዩ ማበረታቻዎች እዲደረጉም ጥረት እየተደረገ ነው። በትምህርታቸው የተሻሉ ተማሪዎችና ሴቶች ተለይተው የተለየ እገዛ ለማግኘት እንዲችሉ ልዩ ትምህርት ቤት (ስፔሻል ክላስ) በማዘጋጀት ሥራዎች እየተሰሩ ነው። እንደ ሀገር የትምህርት ጥራት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ያለ ቢሆንም በ 2015 ዓ.ም በተሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ያለፉ 4 ነጥብ 9 በመቶ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲገቡ ሆኗል። በነገራችን ላይ ይህ ውጤት እንደ ዞናችን አበረታች የሚባል ነው።

የትምህርት ጥራት መጓደል የተማሪው፣ የቤተሰብ ችግር ብቻ ተደርጎ መውሰድ የለበትም። የአመራር ቁርጠኝነት ማነስ ጭምርም ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ አመራር በትምህርት የሚመዘገበውን ስኬትም ሆነ ውድቀትን ኃላፊነት እንዲወሰድ አቅጣጫ ተቀምጧል። የትምህርት ጉዳይ የበለጠ ትኩረት እንደሚስፈልግ ካለፉ ተሞክሮዎችም ትምህርት መውሰድ ይቻላል። የትምህርት ጉዳይ የመንግሥትም ትኩረት በመሆኑ አንጻር ዞናችንም የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ ትምህርት ቤቶችን ከታች ጀምሮ ገንብቶ ተደራሽ በማድረግና በመማር ማስተማሩም ትኩረት ሰጥቶ ለመንቀሳቀስ በአመራሩ በኩል ቁርጠኛ አቋም ይዟል።

በጤናው ዘርፍም በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተሰሩት ሥራዎች ውጤት አስገኝተዋል። በተለይም ማኅበረሰቡ የጤና መድን ተጠቃሚ እንዲሆን ከፍተኛ ሥራ በመሰራቱ ብዙዎች አገልግሎቱ ለቤተሰባቸው ዋስትና እንደሆነ ግንዛቤ በመያዝ አባል ሆነዋል። በዚህም በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ 23 ዞኖች መካከል ምዕራብ ሐረርጌ በተሻለ አፈፃፀም ተጠቅሷል። ተጠቃሚው በአገልግሎት አሰጣጥ የሚያነሳውን ቅሬታም ለማስተካከል ያሉ ክፍተቶችን በውይይት ለመፍታት ጥረት ተደርጓል። ከጤና አገልግሎት ጋር በተያያዘ ትልቁ ችግር በሚፈለገው መጠንና አይነት የመድኃኒት አቅርቦት አለመኖር በመሆኑ ማኅበረሰቡ የጤና መድን አባል በመሆን ግዴታውን ተወጥቶ ግን በሆስፒታሎች ውስጥ መድኃኒት እየቀረበለት አይደለም። መድኃኒት ፍለጋ የግል አቅራቢዎች ጋር እንዲሄድ እየተገደደ ነው፡፤ ይህም ቅሬታ እየፈጠረ በመሆኑ አስተዳደሩ አጀንዳ አድርጎ በተለያየ ጊዜ እየመከረበት አቅርቦቱ የሚሻሻልበት መንገድ እንዲፈጠር ጥረት ቢያደርግም ካለው ፍላጎት አንጻር አቅርቦቱ ሊመጣጠን አልቻለም። በመድኃኒት አቅርቦት በኩል የሚሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አይደለም። በግንባታ በኩልም በተከናወኑ የተለያዩ ተግባራት፤ በወረዳዎች ተደራሽ ለማድረግ የጤና ኬላዎች ተሰርተዋል።

በማኅበራዊ አገልግሎትም እንዲሁ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል። በዚህ በኩል ረዳትና የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ነዋሪዎች ማኅበረሰቡን በማስተባበር የቤት እድሳትና ግንባታ ተከናውኗል። በቤተሰብ አቅም ማነስ የትምህርት ቁሳቁስ ላልተሟ ላላቸው ተማሪዎችም በዞኑ በሚገኙ 15 ወረዳዎችና አምስት ከተሞች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። ማኅበራዊ አገልግሎቱ በተቀናጀና በተደራጀ ሁኔታ በመከናወኑ ውጤት ተገኝቶበታል። ብዙ የአካባቢው ማኅበረሰብም ተጠቃሚ ሆኗል። በመንግሥት በጀት መሸፈን የማይቻል ሥራ ነው በማኅበረሰብ ተሳትፎ የተከናወነው። የበጎ አድራጎት ሥራ በኦሮሚያ ክልል ሕግ ሆኖ በመጽደቁም የበለጠ ተጠናክሯል።

ማኅበረሰቡ እንደክፍተት ከሚያነሳቸውና ከሚያማርራቸው የፍትህ መጓደል አንዱ ነው። የማኅበረሰብ ቅሬታን መሰረት በማድረግ ሰዎች ፍትህ ለማግኘት ፍርድቤት ተመላልሰው ረጅም ጊዜ የወሰደባቸውን ጉዳይ በማኅበራዊ ፍርድቤት በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ በማግኘት እንዲችሉ ተደርጎ ውጤትም እየታየበት ሲሆን ይህ አሰራር ደግሞ ሰዎች ትክክለኛ ፍትህም እንዲያገኙ፣የገንዘብ ወጪና ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ አስችሏል። በማኅበራዊ ፍርድ ቤት ውስጥ የዳኝነቱን ሥራ የሚሰሩትም በአካባቢያቸው ያለውን የማኅበረሰቡን ችግር ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው በቀላሉ መፍትሄ የሚሰጡ ናቸው። በተለይም በሀሰት ምስክርነት በዳዩ ተጠቃሚ፣ ተበዳዩ ደግሞ ተጎጂ የሚሆንበት በስፋት የሚስተዋልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ማኅበራዊ ፍርድቤቱ ይሄን ክፍተት በማስቀረት የተሻለ አገልግሎት የሚሰጥ ሆኖ ተገኝቷል።

ሰዎች ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙ ማኅበራዊ ፍርድቤቱ ሰዎች በሀሰት ሊምሉ በማይችሉባቸው ነገሮች መሀላ እንዲፈጽሙ ነው የሚያደርጓቸው። እነዛ መሀላ በማይፈጽሙባቸው ነገሮች ማንም ደፍሮ ለመማል አይሞክርም። የባህል ፍርድ ቤቱ በዚህ መንገድ በመጠቀም መደበኛ ፍርድ ቤት ሊፈታ ያልቻለውን ፍትህ በመስጠት ለማኅበረሰቡ በተለይም ለተበዳይ እፎይታን ሰጥቷል። የዚህ ማኅበራዊ ፍርድቤት ሌላው በጎ ተግባር ወይም እንደ መልካም ነገር የሚወሰደው በትክክለኛው ፍርድ በዳይ ቅጣት ሲበየንበት ተበዳይ ደግሞ ትክክለኛውን ፍትህ ሲያገኝ፤ የበዳይና የተበዳይነት ስሜት ተፈጥሮ አይሸኙም። ተቀያይመው እንዳይሄዱ ነው የሚደረገው። ማኅበራዊ ፍርድቤቱ ሁለቱንም አስታርቆ ነው የሚሸኛቸው።

እንዲህ ያለው አሰራር በመደበኛው ፍርድቤት የተለመደ አይደለም። ፍትህ ፈላጊዎች በማኅበራዊ ፍርድቤት መዳኘት ከጀመሩ ወዲህ በሀሰት መመስከርን ወይንም ውሸትን አስቀርቷል። የመደበኛ ፍርድቤት ሥራንም በማቃለል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። እንዲህ ዘርፈብዙ ጥቅም እየሰጠ ያለው ማኅበራዊ ፍርድቤት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስፈልጋል። ማኅበራዊ ፍርድቤቶቹ ተልእኮአቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ፀሐፊ ተቀጥሮላቸዋል። የሚሰሩበት ቢሮም ተሰጥቷቸዋል። ለተገልጋዩ የሚሰጡት ደረሰኝም ተዘጋጅቶ እየቀረበላቸው ነው። ማኅበራዊ ፍርድቤቶች የሕዝቡን የፍትህ ጥያቄ እንዲመልሱ፣ የማኅበረሰብ የበጎ አገልግሎት ተግባርም ተጠናክሮ ዘላቂ እንዲሆን እውቅና ተሰጥቷቸዋል። የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ሕግ ሆኖ ሥራ ላይ እንዲውል በአዋጅ አጽድቆታል። እስካሁን በተከናወኑት ሥራዎችም የሕዝብ እርካታ መኖሩን ለመገንዘብ ተችሏል።

የመደጋገፍ ባህልን ለማሳደግም” ቡሳጎኖፋ” የሚባል አሰራር በክልሉ መንግሥት በአዋጅ ፀድቆ እየተሰራበት ሲሆን ቡሳጎኖፋ እንደቀይም መስቀል ማህበር አይነት ነው። አርሶአደሩ፣ አርብቶአደሩ፣ ነጋዴው፣ በየደረጃው ያለው ሕብረተሰብ ሁሉ አባል ሆነው በጋራ የመደጋገፍ ሕብረት ይፈጥራሉ። ለዚህም አባላት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ መፈጸም ይኖርባቸዋል። በአይነት ደግሞ ከእያንዳንዱ አባል እህል ይሰበሰባል። በግለሰብ ወይንም በወረዳ ደረጃ የኢኮኖሚ ችግር ቢያጋጥም መንግሥት አይጠበቅም። ቀድሞ ከአባላት ከተሰበሰበው ገንዘብና እህል ለተቸገረው ወይንም ለሌላው ድጋፍ ይደረጋል። ችግሮች ሲያጋጥሙ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የተቀመጠ ዘዴ በመሆኑ ሰዎች ብዙ ጉዳት ሳይደርስባቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ። በዞኑ በትምህርትቤቶች የተተገበረው ምገባም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው።

ሌላው”” ጋቸናሲርና የሚባለው ነው። ይህ ማለት ከሕብረተሰቡ ውስጥ ተመልምሎ ስልጠና ወስዶ የወረዳውን፣ የቀበሌውን፣ አጠቃላይ የማኅበረሰቡን ሰላምና ደህንነት የሚጠብቅ ማለት ነው። ጋቸናሲርና ለሰላሙ እራሱ ባለቤት የሚሆንበት አሰራር ነው። ሰላሙን የሚያደፈርሰውን ተባብሮ በአንድነት ከውስጡ የሚያስወግድበት ነው። ምዕራብ ሐረርጌ ዞን በሰላም ዙሪያ፤ ከፀጥታውም ሆነ ከፖለቲካ አመራሩ ጋር በተቀናጀ እየተሰራ ሲሆን፣ በየጊዜው ሥራዎች እየተገመገሙና አቅጣጫም እየተቀመጠ የጥበቃ፣ የፍተሻ፣ የኦፕሬሽን ሥራዎች ተጠናክረው እየተከናወኑ ነው።

በዚህ ረገድ አስፈላጊው መስዋዕትነት እየተከፈለ ነጋዴውም ንግዱን እንዲያከናውን፣ ተማሪውም ተምሮ እንዲገባ በአጠቃላይ ሕዝባችን ከስጋት ነፃ ሆኖ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ እየተሰራ ነው። ይህም በመሆኑ ሕዝቡ ያለአንዳች ስጋት 24 ሰዓት በመንቀሳቀስ የእለት ተእለት ተግባሩን እየተወጣ ይገኛል። ይህም የጠንካራ የፖለቲካ ሥራ ውጤት ነው። ሕዝቡም ከፀረሰላም ኃይሎች ጋር የሚያብሩትንና ለመቀላቀል የሚንቀሳቀሱትን ለመንግሥት አካል መረጃ በመስጠትና በማጋለጥ እያደረገ ያለው እገዛም ከግምት ውስጥ የሚገባ በመሆኑ ሕዝቡም የራሱን ድርሻ በመውሰዱ ምስጋና ይገባዋል።

ዞናችን የወጪ ንግድ (ኢምፖርት ኤክስፖርት) ኮሪደር በመሆኑ፤ በፀጥታ በኩል ልዩ ትኩረት ነው የተሰጠው። ፀጥታ በማደፍረስ የሚፈታተኑ ስላሉ አጎራባች ከሆኑት ሶማሌና አፋር ክልሎችና ከሌሎችም ጋር ምክክር በማድረግ በጋራ እየሰራን እንገኛለን። በዞናችን ውስጥም ቢሆን በክላስተር ወረዳዎች እርስበርስ በሰላም ዙሪያ መረጃ በመለዋወጥ፣ በገንዘብ፣ በሰው ኃይል እየተረዳዱ ይረባረባሉ። በልማት ደግሞ እየተፎካከሩ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ነው ያለው።

ጠንካራ የሆኑ ሚሊሻዎችንም በስልጠና በማብቃትና በማስታጠቅ ጭምር የአካባቢው ሰላም የበለጠ እንዲረጋገጥ እየሰራን እንገኛለን። ይህ ሁሉ ሥራ ለሰላም የተሰጠውን ቅድሚያ የሚያሳይ ነው። ምክንያቱም ሰላም ከሌለ ስለ ልማትና እድገት ማሰብም መስራትም አይቻልም። ውሎ መግባትም ስጋት ነው ። በያዝነው በጀት ዓመት የስድስት ወር ግምገማችን የሚያሳየው ምዕራብ ሐረርጌ፤ በሰላምና በልማት ሥራ በተለይም ተነሳሽነት በመውሰድ በገጠርና በከተማ ክላስተር፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ዘርፍ ክላስተርና በገቢ ማሰባሰብ በዞን ደረጃ በሶስተኛ ደረጃ ነው የሚገኘው።

እስካሁን የሰራነው ስራ የሚያበረታታ ቢሆንም በቂ አይደለም። የበለጠ አቅማችንን መፈተሸ አለብን። ሰፊ የሆነ የሰው ኃይል፣ በሀብት በኩል እንዲሁ የተፈጥሮ ሀብቶች አሉን። ይህን ፀጋ ይዘን ወደ ሥራ በመቀየር ሕዝባችን ከድህነት ውስጥ እንዲወጣ ማድረግ ይኖርብናል። በተለይም በበጋ ቆላ ስንዴ ልማት በዞኑ እየተመዘገበ ያለው ውጤት እጅግ አበረታች ነው። መንግሥት ለውጭ ገበያ ስንዴ ለማቅረብ በያዘው እቅድ እንደምዕራብ ሐረርጌ ኮታ ተሰጥቶን ተሳትፈናል። እንዲህ ያለው ነገር በጣም የሚያበረታታና የሚያነቃቃ በመሆኑ ሕዝባችንን እያወያየን በጋራ እንቀሳቀሳለን። ለልማቱ ትልቁ አቅም ሕዝቡ ነው። ጠንካራ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ከተቻለ ልማትን ማፋጠንና እድገት ማምጣት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፦ ዞኑ የምድር በረከት ፀጋዎችም እንዳሉት ይታወቃል። በዚህ በኩልስ ምን ተግባራት ተከናወኑ?

ወይዘሮ ኢክራም፦ በዞኑ ለጌጣጌጥ እና ለኢንደስትሪ ግብአት የሚውሉ የማዕድን ሀብት ክምችት አለ። ሆኖም ግን ለማዕድን ሥራ የሚያስፈልጉ ማሽኖች ባለመኖራቸው ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ የለም። ማሽን ለማቅረብ አቅም አለመኖሩ ደግሞ ክፍተቱን አስፍቶታል። ስራው ቢኖር ሰፊ የሰው ኃይል በመያዝ ያግዝ ነበር። ወደፊት ግን በማዕድን ልማት ላይ 60 በመቶውን ባለሀብቱ ቀሪውን ደግሞ ወጣቶች የሚጠቀሙበት አሰራር ኖሮ ልማቱ እንዲከናወን ከማዕድን ቢሮ ጋር ተነጋግረናል።

አዲስ ዘመን፦ ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ዞኑ ምን አይነት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው?

ወይዘሮ ኢክራም፦ ሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ በስፋት እየተሰራ ያለው በቆላማው የዞኑ አካባቢዎች ነው። መሬት በስፋት ያለው በቆላማ አካባቢ በመሆኑ ነው በአካባቢው ላይ ትኩረት የተደረገው። በዞናችን ወጣቶች ተደራጅተው በበርበሬ ልማት ላይ እንዲሰማሩ እየተደረገ ሲሆን አሁን ላይ ያመረቱት በርበሬ ለጅቡቲ ገበያ እየቀረበ ነው። በከተማ ግብርናም በከብት ማድለብ፣ ዶሮ በማርባት፣ ንብ ማነብና በሌሎችም የልማት ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩም ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሮላቸዋል።

በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሥራ ፈላጊ ወጣት እስካሁን የተሰሩት ስራዎች አመርቂ ናቸው ብሎ ለመናገርም አያስደፍርም። በመሆኑም በማኅበር በማደራጀት ሥራ እንዲፈጠርላቸው ማድረግ ላይ ሰፊ ሥራ ይጠይቃል። ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ፣ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሥራ ፈላጊዎች ወጣቶችን እንዲሁም በዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ውጤት ያልመጣላቸውን የሥራ እድል ሊፈጥሩ የሚችሉ እንደ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ያሉ አምራች ኢንደስትሪዎች ምዕራብ ሐረርጌ ውስጥ አለመኖራቸውም ሰፊ የሥራ እድል እንዳይኖር አድርጓል።

አዲስ ዘመን፦ ዞኑ ላይ ምን አይነት የኢንቨስ ትመንት እድሎች አሉ? ባለሀብቶችን ለመሳብ የተከናወኑ ተግባራትስ ምን ይመስላሉ?

ወይዘሮ ኢክራም፦ በዞኑ በግብርና ሥራ ግንባር ቀደም የሆኑ አርሶ አደሮችንና በማይክሮ የተደራጁትን ወደ ኢንቨስትመንት እንዲሸጋገሩ የማድረግ ሥራ ተጀምሯል። በክልል ደረጃም ተቀባይነት አግኝቷል። በቁጥር ወደ 60 የሚሆኑ ተለይተው ፍላጎታቸው ታይቶ የመስሪያ ቦታ ከማቅረብ ጀምሮ አስፈላጊው ነገር ተመቻችቶላቸው ወደ ሥራ ገብተዋል። ይህ በቂ ባለመሆኑ የተጀመረው ሥራ የበለጠ ተጠናከሮ የሚቀጥልበት ሁኔታም አቅጣጫ በመቀመጡ እንቅስቃሴው ይቀጥላል።

አዲስ ዘመን፦ በቱሪዝም ኢንደስትሪው በኩል ያለው እንቅስቃሴስ እንዴት ይገለፃል?

ወይዘሮ ኢክራም፦ በዞኑ ዋሻዎች ፣ የተለያዩ የዱር እንስሳት፣ የመስህብ ስፍራዎች፣ እድሜ ጠገብ የሆኑ ከቤተክርስቲያን ጋር የተያያዙ ታሪኮች፣ ቢታወቁና ቢወጡ የቱሪዝም መዳረሻ የሚሆኑ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች አሉ። ሆኖም ግን በሚፈለገው ልክ በዚህ ዘርፍ እንቅስቃሴ አልተደረገም። በቱሪዝም ዘርፍ መስራት እንዳለብን ግን እንገነዘባለን።

አዲስ ዘመን፦ መሠረተ ልማትን ከማሟላት አንጻር የተሰሩ ሥራዎች ምን መልክ አላቸው?

ወይዘሮ ኢክራም፦ በመብራት ኃይል አቅርቦት በኩል ከፍተኛ የሆነ ችግር አለ። ከ40 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ማሰራጫ (ሰብስቴሽን) አለው። በቂ የሆነ አቅም ስለሌለው የሚገኘው ኃይል ደካማ ነው። አደራጅተን ወደ ሥራ ያስገባናቸው አብዛኞቹ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈልጉ ናቸው። በዚህ ረገድ የኃይል መቆራረጡ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው። አስተዳደሩ ለሚመለከተው አካል በየጊዜው አቅርቦ ምላሽ በመጠበቅ ላይ ይገኛል። በመንገድ መሰረተ ልማት በኩልም ደረጃዎች የማሳደግ ስራ የሚፈልጉ ናቸው። ሆኖም በመንግሥት በኩል አዲስ በጀት ባለመያዙ የመንገድ ሥራው ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ድልድዮች ግን ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ነው ያለው።

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ እጅግ እናመሰግናለን።

ወይዘሮ ኢክራም፦ እኔም አመሰግናለሁ።

ለምለም ምንግሥቱ

 

አዲስ ዘመን የካቲት 7/2016

 

Recommended For You