ከመሪዎቹ ስብሰባ አፍሪካውያን ብዙ ይጠብቃሉ!

አፍሪካውያን በቀደሙት ዘመናት የተመኙትን የተሟላ ነፃነት እውን በማድረግ ነገዎቻቸውን ብሩህ ለማድረግ ከነፃነት ትግሉ ያልተናነሰ የትግል ቁርጠኝነትና መስዋዕትነት እንደሚያስፈልጋቸው ይታመናል። ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠርም አሁን ያለው አፍሪካዊ ትውልድ ዋነኛ ኃላፊነት ነው።

አፍሪካውያን አባቶቻችን በቀደመው ዘመን የተጫናቸውን የቅኝ ግዛት ቀንበር፤ ከላያቸው ላይ ለመጣል እዚህ እዚያም የጀመሩት የእምቢተኝነት ንቅናቄ የትግል ዘር እየሆነ፤ በብዙ መስዋዕትነት ነፃነታቸውን በደማቸው መቀዳጀት ችለዋል። ነፃነት ምን ያህል ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችልም ለመጪዎቹ ትውልዶች ተጨባጭ ተሞክሮዎችን ጥለው አልፈዋል ።

በአንድ በኩል ለነፃነታቸው መሠረት የሆነውን አንድነታቸውን ማጽናት እንዳይችሉ የሚፈጠሩ የልዩነት ትርክቶችንና ሴራዎችን መቋቋም የሚያስችሉ እልህ አስጨራሽ ሥራዎችን እየሠሩ፤ በሌላ በኩል ትግሉ በራሱ የፈጠረውን የእምቢተኝነት ግለት እንዳይቀዛቀዝ የአስተሳሰብ መሠረት እንዲኖረው ብዙ ርቀት ተጉዘዋል።

ኢትዮጵያኒዝምን ጨምሮ የፓን አፍሪካኒዝምን እሳቤ፤ የትግል ርዕዮተ ዓለም አድርጎ በመውሰድ፤ የነፃነት ትግሉ የቅኝ ግዛትን ቀንበር ከመስበር ባለፈ አፍሪካዊ የተስፋ ራዕይ እንዲኖረው፤ የትግሉ ስኬት መለኪያም የአህጉሪቱን ሕዝቦች የተሟላ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ነፃነትን ታሳቢ ያደረገ ሆኗል ።

በዚህም ትግሉ በአንድ ወቅትና በአንድ ትውልድ ተጀምሮ የሚያበቃ ሳይሆን በትውልዶች ቅብብሎሽ የሚከወን፤ ለስኬታማነቱም የእያንዳንዱን ትውልድ የነቃ ተሳትፎ፤ ከፍ ያለ ቁርጠኝነት ከሁሉም በላይ ደግሞ የአፍሪካውያኑን መስከንና መደማመጥ የሚጠይቅ ሆኗል ።

የትናንቱ ከቅኝ ግዛት ነፃ የመውጣት ትግላቸው ስኬት ከሁሉም በላይ አንድነታቸው የፈጠረው አቅም መሆኑን በአግባቡ በመረዳት፤ ይህን አቅማቸውን ማጠናከር፤ ልዩነቶቻቸውን ከማጥበብ ጀምሮ ልዩነት ፈጣሪ ሴራዎችን እና ትርክቶችን መታገል ለነገ ድላቸው ዋነኛ መሠረት ነው ።

ይህንን እውነታ በአግባቡ በመረዳት፤ ለአፍሪካውያን የተሟላ ነፃነት ለማቀናጀት ትናንት በብዙ መስዋዕትነት የተጀመረው ትግል የሚጨበጥ ፍሬ እንዲያፈራ አሁን ላይ ያሉ የአህጉሪቱ መሪዎች ኃላፊነት ከትናንቱ አፍሪካውያን የነፃነት ታጋዮች የበለጠ እንጂ ያነሰ እንደማይሆን ይታመናል ።

የአሁኑ ትግል የተሟላ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ነፃነትን በመቀዳጀት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን የሚያጎናጽፍ ከመሆኑ አንጻር፤ አሁን ባለው ተለዋዋጭ፣ ውስብስብ እና በብዙ ፍላጎቶች የተሞላ ዓለም ውስጥ በቀላሉ ማሳካት የሚቻል አይሆንም። በብዙ መስከን መደማመጥን የሚፈልግ ነው ።

አጠቃላይ የሆነው የአህጉሪቱን ሕዝቦች የቀደመ ትግል፣ ትግሉ የፈጠረውን መነቃቃት፣ መነቃቃቱ የፈጠረውን መሻት፣ መሻቱን ተጨባጭ ለማድረግ የተቀመጡ የትግል መርሆዎችን በአግባቡ ማስተዋል፣ ክፍተታቸውን መገምገምና ዘመኑን በሚዋጅ መንገድ ማጥበብ ያስፈልጋል ።

በተለይም የአህጉሪቱ መሪዎች የአህጉሪቱን ሕዝቦች በማስተባበር፣ ከተባበረው ማንነታቸው የሚፈጠረውን አቅም በማቀናጀት፣ በቀደመው ዘመን በብዙ መስዋዕትነት አንድ ምዕራፍ መጓዝ የቻለውን የአህጉሪቱን ሕዝቦች ራስን የመሆን ትግል ተጨማሪ ርምጃ እንዲራመዱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ለዚህም በየትኛውም ሁኔታና መንገድ የሚያደርጓቸው መሰባሰቦች፣ አፍሪካውያኑን ዛሬ ላይ ካሉባቸው ተደራራቢ ችግሮች መታደግ የሚያስችሉ፣ የራሳቸውን ብሩህ ነገዎች ተጨባጭ በማድረግ የታሪክ ሂደት ውስጥ ተጠቃሽ ሊያደርጓቸው የተገቡ ሊሆኑ ይገባል። መሰባሰባቸውም ይህን ታሳቢ ማድረግም ይኖርበታል።

በዚህ ሳምንት ማብቂያ ላይ የሚደረገው የአህጉሪቱ የመሪዎች ስብሰባ ከዚህ አኳያ ብዙ የሚጠበቅበት ነው። በተለይም የአህጉሪቱን ሕዝቦች ካሉባቸው ውስብስብ ችግሮች ወጥተው፣ ብሩህ ነገዎቻቸውን እውን ለማድረግ ከሁሉም በላይ በአንድነት መቆማቸው ወሳኝ ስለመሆኑ አፅንዖት ሰጥቶ እንደሚነጋገር ይጠበቃል።

አፍሪካውያን ያላቸውን የተፈጥሮ ፀጋዎች አቀናጅተው፣ በተናጠል ሊገፉት የማይችሉትን ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ መሻገር እንዲችሉ፣ የኢትዮጵያን አዲስ የትብብር እሳቤ እንደ አንድ ማሳያ በመውሰድ፣ እሳቤውን የሚያበረታቱበት አጋጣሚ እንደሚሆንም ይታመናል።

ይህ እሳቤ ከፓን አፍሪካኒዝም የተቀዳ፣ የአፍሪካን ወንድማማች ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ማስፈን የሚያስችል፣ እስከ ዛሬ በተናጠል ሲታገሉት የነበረውን፣ አቅማቸውን ሲከፋፍል የኖረውን፣ የጠባቂነት መንፈስ በማስወገድ፣ ሁለንተናዊ አህጉራዊ አቅም መገንባት የሚያስችል፤ ዓለም አቀፍ ተደማጭነትን የሚያሳድግ ጭምር ነው!

አዲስ ዘመን የካቲት 7/2016

Recommended For You