ሁለቱን የአዲስ አበባ ታላላቅ ክለቦች የሚያገናኘው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሀገር ውጪ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ ይካሄዳል። ጨዋታው ከሀገር ውጪ ሲካሄድ ክለቦቹ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን እንዲቀስሙና ከባህር ማዶ ደጋፊዎቻቸው ጋር እንዲገናኙ እንዲሁም ገቢ እንዲሰበስቡ ታስቦ እንደሆነ ተጠቁማል። ጨዋታው መጋቢት 17 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንደሚካሄድ አዘጋጆቹና ሁለቱ ክለቦች ከትናንት በስቲያ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
ጨዋታውን ከሀገር ውጪ ለማካሄድ በርካታ ምክንያቶ እንዳሉ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ክለቦቹ የሀገሪቱ ታላላቅና የበርካታ ደጋፊ ባለቤት መሆናቸው ጨዋታውን ባዘጋጁት አካላት ቅድሚያ ተሰጥቶ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንድያገኙ እንዳስመረጣቸው ተገልጿል።
የፊፋ የጨዋታ አዘጋጅ አቶ ፍጹም አድዕኖ ከመጋቢት 14-17 በዱባይ በተዘጋጀው መርሃግብር የሁለቱን ክለቦች የወዳጅነት ጨዋታ ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶች መሰናዳታቸውን ተናግረዋል፡፡ የጨዋታውን ዋና አላማ ሲያስረዱም የኢትዮጵያ ክለቦች ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንዲያገኙና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና የኢትዮጵያን እግር ካስ ግንኙነት ለማጠናከር መሆኑን ገልፀዋል። ይህ የመጀመርያ እንጂ የመጨረሻ እንዳልሆነ ጠቁመውም፣ ለኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሰጠው ባለቸዉ የደጋፊ ብዛት፣ እርስ በርስ ባለዉ ፉክክር እንዲሁም ስምና ዝናቸው መሆኑን አብራርተዋል።
ክለቦቹ በዳባይ በሚኖራቸው ቆይታ ከተለያዩ ሀገራት ክለቦች ጋር የልምድ ልዉዉጥ የሚያደርጉ ሲሆን የራሺያውን ክለብ ሎኮሞቲቭ ሞስኮን ጨምሮ የሌሎች ሁለት ሀገራት ክለቦች እንደሚገኙበት ተገልፃል፡፡ ከእነዚህ ክለቦች ጋር የጊዜ ማጣር በማጋጠሙ እንጂ የወዳጅነት ጨዋታም ለማድረግ ታስቦ እንደነበር ተጠቁሟል። ፈረሰኞቹና ቡናማዎች ወደ ዱባይ ሲያቀኑ በከተማዋ የሚገኙና ከተለያዩ የአረብ ኤምሬቶች የተወጣጡ የሁለቱም ክለቦች ደጋፊዎች አቀባበል የሚያደርጉላቸዉ ይሆናል።
በሚዘጋጅ የእራት ግብዣ ላይ የገቢ ማሰባሰብ መርሀ ግብር እንደሚኖር የተጠቆመ ሲሆን፣ በዚህም የጊዮርጊስና የቡና የቀድሞ ታዋቂ ተጫዋቾች ማለያዎች ለጨረታ ይቀርባሉ። ጨረታው የተዘጋጀው የሁለቱም ክለቦች ደጋፊዎች የራሳቸው የሆነ ጥሩ ጊዜ ኖሮአቸው ከክለባቸዉ ጋር እንዲያሳልፉ ታስቦ እንደሆነ ተጠቅሷል። ይህም የዳያስፖራዉ ማህበረሰብ የናፈቀዉን ደርቢ በቅርቡ አግኝቶ የመመልከት እድል እንዲኖረው ያደርጋል ተብላል።
ሁለቱ ክለቦች በቦለርስ አካዳሚ ልምምዳቸዉን በሚያደርጉበት እለት የክለቦቹ አመራርሮች የሚሳተፉበት ሴሚናር እንደሚኖር ታውቋል። ይህም ለክለቦቹ የአካዳሚ ግንባታ ማማከርና አጋርነትን ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
ወደ ስፍራው አቅንተው በስቴድየም የሁለቱን ክለቦች የደርቢ ጨዋታ የመመልከት ዕድል ለማይኖራቸዉ ደጋፊዎች ከተባባሪ የሀገር ዉስጥ የሚድያ ተቋም ጋር በመሆን የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንደሚኖርም ተጠቁሟል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን በቀለ፣ የማህበሩ ቦርድ ሁኔታውን በሚገባ እንደተመለከተና በክለቡ ስም አዘጋጁን አመስግኖ የፕሮግራሙ መዘጋጀት የክለቡንና የሀገርን ግንኙነት በማጠናከር ፋይዳዉ ብዙ መሆኑን ጠቀሰዋል። የፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ተጠናቀው ሁለተኛ ዙር የሚጀምርበት ወቅት በመሆኑ ለክለቡ ትልቅ ተሞክሮ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል። ይሄም በዱባይ የሚገኙ የቀድሞ ደጋፊዎችን ለማግኘትና አዳዲስ ደጋፊዎችን ለማፍራት የፕሮግራሙ መዘጋጀት መልካም አጋጣሚ በመሆኑ የክለቡን ማልያዎችና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማጓጓዝ ለማቅረብም ታስቦ እየተሰራ ነው። የሁለቱ ክለቦች የደርቢ ጨዋታዎች ለሶስት ዓመታት በአዲስ አበባ ባለመካሄዳቸው ክለቦቹ ብዙ ተግዳራቶችን ማሳለፋቸውን ያስታወሱት አቶ ሰለሞን፣ ይሄን እንደመንደርደርያ በመጠቀም ወደፊት የሚፈጠሩ ዕድሎችን ለማመቻት ብርቱ ጥረት እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ፣ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊ ለሶስት ዓመት በአዲስ አበባ ላይ መመልከት እንዳልቻሉ ገልጸው፣ ከቦለርስ አካዳሚ ጋር በዙም ውይይት እንደተካሄደና በአካል በአካዳሚና ስቴድየም ግንባታ የልምድ ልውውጥና የማማከር ዕድል እንደሚኖርም ጠቁመዋል።
በደጋፊዎች ዘንድ ሁሌም በጉጉት የሚጠበቀው የሸገር ደርቢ ጨዋታ የአዲስ አበባ ስቴድየም እድሳት ባለመጠናቁ ባለፉት ሶስት ዓመታት በላይ በመዲናዋ መካሄድ አልቻለም፡፡ በዚህም ደጋፊው በለመደው ከተማ ተናፋቂውን የደርቢ ጨዋታ መመልከት ካለመቻሉ ባሻገር ክለቦቹም ከስቴድየም የሚያገኙት ገቢ ቀርቶባቸዋል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2016