የእናት አፍሪካ ተስፋና ተግዳሮቶች

የአፍሪካ ሕብረት ለ37ኛ የመሪዎች ጉባኤው እየተንደረደረ ነው። ባለፉት 36 ጉባኤዎቹ ሲያደርግ እንደ ነበረው ሁሉ በዚህኛውም በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተነጋግሮ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል። የተወሰኑትን ውሳኔዎች ወደ መሬት ማውረዱ ላይ አባል አገራቱም ተመሳሳይ ርምጃ ስለ መውሰዳቸውም እንደዛው።

ለዛሬ ግን ስለ አንዳንድ አፍሪካዊ ማንነቶች የአፍሪካን ማንነቶች ትንሽ እንድንጨዋወት ወደድኩ። እንደሚታወቀው አፍሪካ የጥቁር አፈርና የጥቁር ሕዝብ ምድር ነች። በመሆኗም በብዙዎች “እናት አፍሪካ” (ማዘር አፍሪካ) በመባል ስትጠራ ይሰማል። ድምፃውያኑም “አፍሪካ ማማ”፤ “ማማ አፍሪካ” ወዘተ እያሉ ሲያዜሙ መስማት የተለመደ ነው። እዚህ ጋ አህጉሪቱ ለዚህ ማኅበራዊ ማዕረግ ያበቃት ምንድን ነው? ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው።

በመሰረቱ አፍሪካ “ልዩ ምድር ነች” ሲባል ከራስነት ጋር በተያያዘ ለማንቆለጳጰስ በማሰብ አይደለም። አፍሪካን ልዩ አድርጎ የመግለፁም ሆነ በ“እናት አፍሪካ ነት” ማዕረግ የመጥራት ምንጩ አህጉሪቱ በተሰጣት ፀጋ እና በታቀፈችው ተዝቆ የማያልቅ ሀብት ብቻ አይደለም፤ በርግጥ ተዘርፎ እንኳን የማያልቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ (ወይም/እና፣ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ) ሀብት ባለቤት ናት። በመሰረቱ አፍሪካ ጥቅጥቅ ያለ ሀብት ባለቤት ነች። ይህ የሀብት ጥቅጥቅታ ደግሞ በሁሉም እንጂ በተፈጥሮውና በሰው ሰራሹ ብቻ አይደለም። በመሆኑም፣ “ማማ አፍሪካ” ልዩ ነች ስንል በባዶ አይደለም።

የኮምቦኒ ሚስዮናውያን ካህን እና የአፍሪካ ሊቅ የሆኑት አባ ጁሊዮ አልባኔዝ የአፍሪካ ቀን (ግንቦት 17)ን በማስመልከት ከቫቲካን ራዲዮ ጋር አድርገውት በነበረ ቃለ-ምልልስ (ቫቲካንኒውስ እንዳሰራጨው)፣ ስለ አፍሪካ በረከቶች፣ ስለ ሰው ልጅ ትስስር እና የሰው ልጅ የጋራ እጣ ፈንታ እንደ ተናገሩት “አፍሪካ በእውነት ለሰው ልጅ በረከት እንደሆነች በፅኑ አምናለሁ፥ አፍሪካ በርካታ አቅም ያላት አህጉር እና የአያት ቅድመ አያቶች ጥበብ መገኛ አህጉርም ጭምር፤ በጭራሽ ድሃ አይደለችም፥ ደሃ አህጉር አይደለችም፥ ነገር ግን በብዙ ሴራ ሰዎች ያደኸዩዋት አህጉር ነች።”ብለዋል

“የውጭ ኃይሎች ‘የጨዋታውን ሕግ መቀየር በሚፈልጉ’ በሲቪል ማኅበራት፣ በንቅናቄ አራማጆች፣ በተራው ሕዝብና እና በተለያዩ ኃይላት ላይ ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ሲሉ ኢንቨስት ማድረግ አለባቸው” ፤“በሌላ አነጋገር አፍሪካን በአዎንታዊ መልኩ ማየት አለብን” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

እናት አፍሪካ (ማማ አፍሪካ) ለእሷ፣ ለራሷ ይሆኗት ዘንድ አልታደሉም እንጂ የሳይንቲስቶች ምድር ነች። የነጩን ምድር እያበለፀጉ ያሉትን ጥቁር ሳይንቲስቶች “ቤቱ ይቁጠራቸው” ከማለት ያለፈ ምንም ማለት አይቻልም። ከዚህ አኳያ ናይጄሪያ እየከፈሉ ያሉትን ዋጋ ብቻ ማስታወሱ ይበቃል።

እርግጥ ነው፣ ከአጠቃላይ መሬት 20 በመቶውን የምትሸፍነው፣ 30∙3 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ስኴር ስፋት ያላት፣ ከ1∙4 ቢሊዮን (የ2021 ጥናት እንደሚያሳየው) በላይ ሕዝብ የያዘችው (ከዓለም 2ኛዋ)፣ ከዓለም ሕዝብ 18 በመቶው በእጇ ያለ፣ ከእሲያ ቀጥሎ 2ኛዋ ሰፊ አህጉር፣ ከ1250–3000 የሚደርሱ የራሷ ቋንቋዎች (native languages) ያሏት፣ በ2022 ጂዲፒዋ 2.96 ትሪሊዮን ዶላር የነበራት ዛሬም አፍሪካ ደሀ ነች።

ነገር ግን፣ በአንድ የአፍሪካ ሕብረት  የመሪዎች ጉባኤ ላይ የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ እንደ ተናገሩት፤ ከአፍሪካ የሚጋዘው የአትክልት ምርት እንግሊዞችን ሲያንበሸብሽ መንግስታቱን አቶጁሯል። አሜሪካ ከአፍሪካ በሚሄዱ ኦርጋኒክ ምርቶች ሁሌም ጥግብ እንዳለች ነው። ወዘተርፈ ∙ ∙ ∙ የዚህ ሁሉ ችግር መነሻው የአፍሪካ ምርቶች ፕሮሰስ ሳይደረጉ እንዳለ መሄዳቸው ነው፣ ፕሮሰስ ተደርገው (አልቆላቸው) ላለ መሄዳቸው ደግሞ ሆን ተብሎ የተሰራ ሴራ በመኖሩ ነው፤ በቃ ይሄው ነው።

አፍሪካ እንድትሆን የምትፈለገው ምርቷን እንደ ያዘች እንድትቆይና የሚፈልገው አካል በፈለገ ጊዜ እንዲዝቀው እንጂ ሌላ አይደለም። አንድ ነጭ የስነሰብ ምሁር (ፕሮፌሰር ናቸው) በአንድ አውሮፓ ውስጥ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ እንደ ተሰማው፤ የነጩ ዓለም ያለ አፍሪካ ምንም ዋጋ የለውም። ለነጩ ዓለም መበልፀግ መነሻው የአፍሪካ ሀብት ነው። በመሆኑም፣ የነጩ ምድር (አውሮፓና በውስጠ ታዋቂ አሜሪካንን ጨምሮ) ብልፅግና እንዲቀጥልና የበለጠም እየበለፀገ እንዲሄድ ከተፈለገ አፍሪካ ወሳኝነት አላት። በአፍሪካ ውስጥ ያሉት ተቋሞቻችን የተቋቋሙበት ዋና ዓላማ ይሄንን ለማስጠበቅ በመሆኑ በዚሁ መስመር ሊንቀሳቀሱ ይገባል። የአፍሪካ እምቅ ሀብት ስለ አውሮፓ ብልፅግና ሲባል በእምቅነቱ ተጠብቆ ሊቆይ ይገባል።

አሁን አሁን ከየጓዳው እየወጣ በአደባባይ የሚነገረው እውነታ ይኸው ነው፣ የሙሴቬኒ የአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ቁጭትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ አይደለም ለማለት የመከራከሪያ አቅም የለም። እናት አፍሪካ ዛሬ ያለችበትን ሁኔታና ይዞታ በቅርብ ለተከታተለ እውነትም ከላይ ያልነውን የማስጠበቅ ሁኔታ ያለ ይመስላል። አህጉሪቷ ከዳር እስከዳር እየተናጠች ነው። የቱ ጋ ሰላም እንዳለ እና እንደ ሌለ እንኳን ለመለየት በማያስችል ደረጃ ትርምስ አለ።

ግድያ፣ ሞት፣ ረሀብ፣ ጉስቁልና፣ በሽታ፣ የመልማት ጥያቄዎች፣ የከፋ የምግብና ንፁህ የመጠጥ ውሀ እጥረት፣ ስራ አጥነት ∙ ∙ ∙ የአህጉሪቱ ቁልፍ ችግሮች ናቸው፤ የዘንድሮው  (ከፌብሯሪ 17 እስከ 18 2024 የሚካሄደው) የአህጉሪቱ መሪዎች ጉባኤ ቀዳሚ የመወያያ አጀንዳዎችም peace and security, regional integration, እና development ተብለው ተቀምጠዋል። እንደ አህጉር፣ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄን ለመሻት ደግሞ ከአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተሻለ መድረክ የለም።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አሁን የአፍሪካ ሕብረት) የተመሰረተበትን ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም ለማሰብ፤ አፍሪካ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተሻግራ የመጣች መሆኗን፤ ለሁሉም ልጆቿ ፍትህ እና ሰላም ለማረጋገጥ ምን ያህል ተጨማሪ ሥራ መሰራት እንዳለበት ለመገንዘብና ለማስገንዘብ በማሰብ “የአፍሪካ ቀን ን” የምታከብረው እናት አፍሪካ በአህጉሪቱ ውስጥ፤ እንዲሁም በዓለም ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ወሳኝ ሚና ያላት መሆኑ በሚገባ ተረጋግጧል።

የአፍሪካ ቀንድ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከባሕረ ሰላጤው አገራት ነዳጅ እና ከእስያ ደግሞ ወሳኝ የኢንዱስትሪ ምርቶች ሰፊ ተጠቃሚ ወዳለባቸው የአውሮፓ እንዲሁም የአሜሪካ አህጉር የሚተላለፍበት ቁልፉ የቀይ ባሕር መተላለፊያ ስፍራን ለመቆጣጠር ካለፉት ዘመናት ጀምሮ፣ ኃያላን አገራቱ ተጽእኗቸውን እና ቁጥጥራቸውን ለማጠናከር በስፋት እየተንቀሳቀሱ ነው።

ምንም እንኳን አሁን ላይ “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” ቢባልም የአፍሪካን ችግሮች ለመፍታት እንደ ውሀ ቀጂ የሚመላለሱት እነ እንቶኔ እንጂ ሌሎች አይደሉም። ከአፍሪካ ሕብረት ይልቅ የአውሮፓ ሕብረት ነው “በአፍሪካ ላይ ያገባኛል” ሲል የሚሰማው። ይህ ደግሞ የእናት አፍሪካ አንዱና ቁልፍ ችግር ነው።

የዚህ ቀጣና ችግር ሁሌም ሲነሳና ሲጣል ይኑር እንጂ “የችግሩ ምንጭ ምንድን ነው፣ የግጭቶቹ ዘዋሪስ ማን ነው፤ ከግጭቶቹስ አትራፊው የሚል ማን ነው?” ለሚለው እስካሁን ደፍሮ መልስ የሰጠ ማንም የለም። “አለ” ከተባለም እርስ በእርስ ጣት ከመጠቋቆም ያለፈ አይደለም። በመሆኑም፣ ሁሉም እንደ ቀጠለ ነው።

የኃያላኑ ዐይን በአፍሪካ ቀንድ ላይ ማፍጠጡን በተመለከተ ዘገባዎች ለንባብ ያልበቁበት ጊዜ አለ ለማለት የሚደፍር የለም። ያልተደረጉ ጥናቶች አሉ ለማለት ወኔው አይኖርም። ውይይት ያልተካሄደባቸው የሆቴልና ህንፃዎች አዳራሾች አሉ ከተባለ ገና ያልተሰሩት ብቻ ናቸው። በመሆኑም ችግሩ ዘመን ተሻጋሪ ነው ማለት ነው።

እንደ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኙ አሰይድ አብዱራህማን አቡሃሺም ሙያዊ ማብራሪያ (ባለፈው ዓመት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደ ገለፁት)፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአፍሪካ ቀንድ አገራት እንዲሁም ምዕራባውያኑ፣ ቱጃሮቹ የአረብ አገራት፣ ቱርክ፣ ሩሲያ እና ቻይና በአካባቢው በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የተጽእኖ ስፍራ ለመያዝ የቻሉትን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ግጭት እና የፀጥታ ስጋት የማይለየው የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ እና በዓለም አቀፋዊ ተጽእኖዎች እየተናጠ ነው፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ወገኖች እየተካሄዱ ያሉት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች ለዚህ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። በተለይ በኤርትራ፣ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በሶማሊያ በኩል የሚካሄዱ ተደጋጋሚ ቀጠናዊ ግንኙነቶች እንዲሁም የአሜሪካ፣ የቻይና እና የሩሲያ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች እንዲሁም ባለሥልጣናት ወደ አፍሪካ ቀንድ አገራት በተደጋጋሚ መመላለሳቸውም እንደዛው።

ቀጣናው እንደ አሜሪካ፣ ሩሲያ እና ቻይና ካሉ ታላላቅ ኃያላን አገሮች ትኩረት ነጻ ሆኖ አያውቅም። የሩሲያ፣ የቻይና እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ በተደጋጋሚ ጉብኝት ማድረጋቸውም የዚሁ ቀጣናውን በትኩረት የመከታተላቸው እንቅስቃሴ አካል ነው።

ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ በአፍሪካ ውስጥ ያላት ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ተጽእኖ ሰፍቶ የቆየው አሜሪካ “በአሁኑ ወቅት በተለይ በቻይና እና በሩሲያ እየተፈተነ” መሆኑን ለጣቢያው የተናገሩት አቶ አሰይድ፤ በተለይ ባለፉት ጥቂት አስርታት ውስጥ በዓለም መድረክ ኃያልነቷ እየጎላ የመጣው ቻይና ከወታደራዊ እና ከፀጥታ ጉዳዮች በተለየ፣ የአፍሪካ አገራት በዋናነት በሚሹት የመሠረተ ልማት ግንባታ እና የምጣኔ ሃብት ልማት በኩል ትስስሯን እያጠናከረች ነው፤ ይህም ለአሜሪካ ስጋት ሆኗል።

ቻይና ምጣኔ ሃብታዊውን ትስስር ቅድሚያ ሰጥታ ትጀምረው እንጂ፤ ውሎ አድሮ ወደ ወታደራዊው መስክ መሸጋገሩ ስለማይቀር ለአሜሪካ ትልቅ ስጋት ነው ”እንደምትሆንም፤ አሜሪካ በአፍሪካ፣ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ እያደረገችው ያለው ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ደግሞ እየጨመረ የመጣውን የሩሲያ እና የቻይናን ተፅዕኖ ለማክሸፍ ያለመ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልም ይናገራሉ።

አፍሪካ ቀንድ አገራት ካለባቸው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የምጣኔ ሃብት ቀውስ፣ የጦርነት እና የፀጥታ ችግር አንጻር በተለያዩ ጊዜያት ትስስራቸውን ለማጠናከር ሲሞክሩ ይታያል። ኢጋድን የመሳሰሉ ተቋማትንም በማቋቋም ተፅእኖዎችን ለመግታት መጣራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ከወቅታዊ ተግዳሮቶቻቸው እና ፍላጎቶቻቸው አንጻር የአካባቢው አገራት የሁለትዮሽ እና ከዚያም በላይ የሆኑ ጥምረቶችን ሲመሠርቱም ታይተዋል።

“አገራቱ አንድ ላይ በመሆን በጋራ መቆም ካልቻሉ በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ መድረክ ደካማ ይሆናሉ” የሚለውን የምሁራን አስተያየት በመረዳትም ይሁን፤ ወይም፣ ከላይ እንደ ጠቀስነው የሕብረቱ ኮሚሽን ሙሳ ፋኪ “አንድነት እና ሕብረት የግድ“ መሆኑን በመገንዘብ ሁሌም መፍትሄ ያሉትን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ ብለው አያውቁም።

ከላይ የጠቀስናቸው ተመራማሪ እንደሚነግሩን ከሆነ አገራቱ ሁሌም (በጋራም፤ በግልም) ለመፍትሄ ቢፍጨረጨሩም ከተግዳሮት ሲፀዱ አይታዩም። በመሆኑም፣ የአሁኑ የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ (Moussa Faki Mahamat) ጠበቅ ያለ ንግግር አፍሪካ እንደ አህጉር ለመቀጠል ያሏት ሀብቶች ሁለት ናቸው፣ እነሱም አንድነት እና ሕብረት (Unity and Solidarity) ብለዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የየራሳቸው ተግዳሮት ያለባቸው ናቸው የሚሉት አሰይድ “አገራት ውስጣዊ ችግሮቻቸውን ሳይፈቱ እና ሳይጠናከሩ የሚፈጥሩት ማንኛውም ጥምረት ጊዚያዊ ካልሆነ በስተቀር ጠንካራ፣ ዘላቂ እና ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ስለዚህም የቀጠናዊ ጥምረት ኃይል ከውስጣዊ ጥንካሬ የሚመነጭ ነው” ሲሉም ነው የሚገልፁት። “ቢሆንም ግን በአፍሪካ ቀንድ አገራት መካከል ቢያንስ ግንኙነት፤ ውይይት እና ትብብር ለመፍጠር ፍላጎት መኖሩ እንደ አንድ አዎንታዊ ነጥብ ሊወሰድ ይችላል በማለትም ተስፋቸውን ያካፍሉናል።

ጉባኤው “ይኹን አንጂ፣ የአፍሪካ ቀንድ አገራት በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ እና በወታደራዊ መስኩ በተናጠል ከሚቀራረቡት ጋር ሲደጋገፉ እና አብረው ሲቆሙ ቢታዩም ጠንካራ እና ዘላቂ የትብብር ማዕቀፍ ግን ለማዳበር አልቻሉም። የሚለውን ከዓመት ዓመት የሚገላበጥ አስተያየት ከልቡ መርምሮና “ለምን?” ብሎ ለዘላቂ ሰላምና ለችግሩ መፍትሄ የሚሆን ውሳኔን ያሳልፍ ዘንድ ቀጣናው ያለበት ሁኔታ ራሱ ግድ ይላል። መሪዎቹም በዚሁ ማእቀፍ ውስጥ ሆነው ጥቂት ሊቆዝሙና ወደ ጋራ መፍትሄም ለመጡ ይገባል።

እ.ኤ.አ. በ1963፣ 32 ነፃ መንግሥታት “የአፍሪካ አንድነት ድርጅት“ በማለት ያቋቋሙትና በ2002 (እ.ኤ.አ) ወደ “የአፍሪካ ሕብረት የተሸጋገረው ሕብረትና በዚሁ ሕብረት አማካኝነት የሚካሄደው ጉባኤ የአህጉሪቱ የሁሉም ነገር የስበት ማእከል እንደ መሆኑ መጠን ከቃላት ባለፈ “እውን ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ባሉትና ባለሙት መሰረት እየሄደ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን መፈተሽ ግዴታ ይሆናል።

”ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለው መርህ መስራች እና አራማጆች፤ የአሁኖቹን፣ የአህጉሪቱ ቁልፍ ችግሮች መፍቻ ይሆናል የተባለው የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባላት፤ እንዲሁም፣ በአህጉሪቱ የሚስተዋሉት ችግሮች ተቀርፈው የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የጸና አቋም ያላት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአህጉሪቱ ሀገሮችን የሚካያትት ነው። ለዚህም የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባላትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የጋራ ስብሰባ እዚህ አዲስ አበባ፣ ባለፈው ህዳር ወር መካሄዱ ይታወሳል።

የአፍሪካ ሀገራት የራሳቸውን ችግሮች በራሳቸው መፍታት እና በአህጉራዊ ጉዳዮች ውስጥ የውጭ ተዋንያንን ጣልቃ ገብነትና ተጽዕኖ መቀነስ ስለ ሆነው፤ ስለ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች” ገፋና ሰፋ አድርጎ ለመረዳት፣ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ቴሪ ሜይስ “African Solutions for African Problems: The Changing Face of African-Mandated Peace Operations” በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቁትን ጥልቅ ስራ ማየቱ ተገቢ ነው፤ እንዲሁም፣ የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን እንዲፈቱ ጽኑ አቋም ካላቸው ግንባር ቀደም ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ጠቅሶ ማለፍ ተገቢ ይሆናልና አድርገነው እንለፍ።

በድፍን “አህጉሪቱ እየተስተዋሉ ያሉት ችግሮች ማለትም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የከፋ ሙስና፣ ኢ-እኩልነት፣ ድህነት፣ የጤናና ትምህርት ተደራሽነት፣ የእርስ በእርስ ግጭት ወዘተ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዴት ነው ሊቆሙ የሚገባቸው?“ የሚለው ላይ መሪዎቹ አፍ ለአፍ ገጥመው ሊመክሩና ሊመካከሩ፤ ሊወስኑና ወደ ተግባርም ሊገቡ ይገባል። ጉባኤው የ“አጀንዳ 2063 አፈፃፀምን በመገምገምም ቀጣይ አቅጣጫን ሊያስቀምጥ እናት አፍሪካ ብቻ ሳትሆን የተቀመጠበት ወንበር ራሱ ግድ ይለዋል።

መልካም ጉባኤ!!!

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን የካቲት 6/2016

 

Recommended For You