ለትምህርት መሰረተ ልማቱ እድሳትና ግንባታ ውጤታማነት!

መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በጥናት ላይ ተመስርቶ ለማከናወን ከያዛቸው ተግባራት መካከል የትምህርት መሰረተ ልማቶች እድሳትና ግንባታ ይጠቀሳል፡፡ ለትምህርት ቤቶቹ የሚያስፈልጉ እንደ ውሃ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ፣ ወዘተ ያሉት የትምህርት መሰረተ ልማቶች አለመኖር በተማሪዎች ትምህርት አቀባበል ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳርፍ ይታመናል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶች ሊኖራቸው የሚገባ መሰረተ ልማቶችን መፈተሻ ቅጽ አዘጋጅቶ ባደረገው ጥናትም ይህንኑ አረጋግጧል፡፡ በጥናቱ ከመንግስት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ 49 ሺ የሚሆኑት ተካተዋል፡፡ በጥናቱ መሰረትም ስድስት ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው የተሟላ መሰረተ ልማት ያላቸው ሆነው የተገኙትና ከደረጃ አራት ትምህርት ቤቶች ተርታ መሰለፍ የቻሉት፡፡

አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውሃ፣ ጥሩ የመጫወቻ ስፍራ ፣ ንጽህናቸው የተጠበቀ ፣ የተማሪ ክፍል ጥምርታቸውም 40 ተማሪ በክፍል የሆነ ናቸው፡፡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ደግሞ መጥፎ የሚባሉ አይደለም፤ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያሉት ትምህርት ቤት ሊባሉ የማይችሉ ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት ከትምህርት ቤቶቹ በአጠቃላይ ደረጃን የሚያሟሉት የሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች ዜሮ ነጥብ ዜሮ ሁለት በመቶ አካባቢዎቹ ብቻ ናቸው፡፡ ይህ እጅግ ትልቅ ጉድለት ነው፡፡

በመንግስት በኩልም ይህን አስከፊ ሁኔታ መቀየር እንደሚያስፈልግ በጽኑ ታምኖበት ባለፈው ሰኔ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በትምህርት መሰረተ ልማት ላይ ለውጥ የማምጣቱ ዘመቻ በይፋ ተጀምሯል፡፡ ይህ ሥራ በመንግስት አቅም ብቻ ሊከወን እንደሚይችል ታምኖበትም ለመላው ሕዝብም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ሥራ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ተደርጎለታል፡፡

ባለፉት ወራት በተደረገው ርብርብም ውጤት መመዝገቡን የትምህርት ሚኒስቴር ሰሞኑን አስታውቋል፡፡ እስከ አሁን 11 ሺ611 ትምህርት ቤቶች ታድሰዋል፡፡ በአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታም ሦስት ሺ 180 ቅድመ አንደኛ ደረጃ፣ አንድ ሺ 390 አንደኛ ደረጃ እንዲሁም 295 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ ወደ አራት ሺ 871 ትምህርት ቤቶች በሕዝብ መዋጮ ተገንብተዋል፡፡ የፌዴራል መንግስት አዳዲስ 50 ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ያቀደ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ከርዳታ ድርጅቶች ጋር በመሆ ን የ16ቱ ግንባታ ተጀም ሯል፡፡ በዚህ ዓመት ደ ግሞ የአራቱ ግንባታ ይጀመ ራል፡፡

እስከ አሁን የተከናወነው ተግባር በአምስት ዓመት በትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ግንባታ በኩል ለመድረስ የታሰበውን ዕቅድ ማሳካት እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ተጠቁሟል፡፡ እነዚህ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሳደግ ስራ ውጤቶች ባለፉት ሁለት ዓመታት በሚኒስቴሩ ከተከናወኑ የተሳኩ ተግባራት መካከል መጠቀስ ችለዋል፡፡ መንግስት መውሰድ የጀመረው ርምጃ ከጅምሩ ለውጥ ማምጣት የሚያስችለው ውጤት ማሳየቱ ርብርቡን ከነግለቱ አንዲቀጥል በማድረግ የታሰበው ላይ መድረስ አንደሚቻል ያመላክታል፡፡

እንደሚታወቀው፤ ሀገሪቱ ለሁሉም መሰረተ ልማት ሊሆን የሚችል ሀብት የላትም፤ ያላትን ሀብት ቅድሚያ ለሚሰጠው ጉዳይ ነው የምታውለው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቀደም ሲል የተጀመሩትን ለማጠናቀቅ እንጂ ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች ሊውል የሚችል ብዙም ሀብት የላትም፡፡ ለፕሮጀክቶች ግንባታ የውጭ ብድርና ርዳታ ማማተሩም አዋጭ አይደለም፡፡

ስለሆነም ኢትዮጵያ ያላት ትልቅ አቅም ሕዝቧ ነው፤ ሕዝቧን ይዛ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ገንብታለች፤ እየገነባችም ትገኛለች። መንግስት ለትምህርት መሰረተ ልማት ግንባታና ማደሱ ሥራም መላውን ሕዝብና ባለሀብቶች.ወዘተ እያስተባበረ ያለውም ለዚሁ ነው፡፡ በትምህርት ዘርፍ ጥራትን ለማምጣት ወሳኝ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነውን የዘርፉን መሰረተ ልማት ለማሟላትም ይህን መንገድ መጠቀሙ ትክክለኛ አቅጣጫ ነው፤ ኅብረተሰቡ የትምህርት ሥራውን በባለቤትነት እንዲከታተለው ለማድረግም ያስችላል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ለጋሾችን በማስተባበር ጭምር ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የጀመረው ጥረት እንዲሁም መላውን ሕዝብ፣ ባለሀብቶችንና ሌሎች የልማት አጋሮችን በማስተባበር መሰረተ ልማቶቹን ለማሟላት እንዲሁም መሰረተ ልማቶቹ የተሟላላቸውን ትምህርት ቤቶች ለመገንባት የጀመረው ርብርብ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ሕዝቡን በተለይም በውጭ ሀገሮች ጭምር ያለውን ኢትዮጵያዊ በልማቱ ለማሳተፍ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ብዙ ተሰርቷል፤ ይህም ለተገኘው ለውጥ የራሱን ሚና ተጫውቷል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ይህን ውጤታማ ተግባር የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ አሁንም ከተለመደው መንገድ ወጣ ያሉ አቀራረቦችን መከተልን ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን፣ ታዋቂ ሰዎችንና አንቂዎችን፣ ወዘተ ለመጠቀም የበለጠ ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡

በዚህ ዘመን እነዚህ መንገዶች ርዳታ በፍጥነት ለማሰባሰብ ያላቸው አቅም ከፍተኛ ስለመሆኑ ባለፉት ዓመታት በዚህ መንገድ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ የተገኘበት ሁኔታ ያመላክታል፡፡ በተለይ በውጭ ሀገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተማሩባቸውን ትምህርት ቤቶች እንዲያድሱ፣ ባደጉባቸው አካባቢዎች አዳዲስ ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ ለማድረግ ወሳኝ እንደመሆኑ ለዚህ ስራ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ከእስካሁኑም በላይ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ለዚህ ታላቅ ሀገራዊ ጥሪ ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጥ መሠራት ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓለምም በአፍሪካም ታላቅ የተሰኘውን የዓባይ ግድብ የገነባ ነው፡፡ ይህን ማድረግ የቻለ ሕዝብ የትምህርት ጥራት አንዱ ችግር ተደርጎ የተለየውን የትምህርት ቤት መሰረተ ልማት ችግር መፍታት አይሳነውም!

ዋናው ነገር ሁሉንም የሕብረተሰብ ከፍል በልማቱ ማሳተፍ ነው፣ ዘመኑ ደግሞ ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ባለጸጋ የሆነበት እንደመሆኑ ይህን በመጠቀም ርቡርቡ እንዲጠናከር ማድረግ ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን የካቲት 6/2016

Recommended For You