ከጅማሬው እስከ ፍፃሜው በልብ አንጠልጣይ ክስተቶችና ባልተጠበቁ ውጤቶች የታጀበው የ2023 አፍሪካ ዋንጫ ከትናንት በስቲያ እኩለ ሌሊት ፍፃሜውን አግኝቷል:: ውድድሩን አንድ ቢሊየን ዶላር አውጥታ የደገሰችው አስተናጋጇ ኮትዲቯርም ከወደቀችበት ተነስታ ለ3ኛ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ነግሳለች::
የአፍሪካን የእግር ኳስ ደረጃ ከ1-5 የያዙ አገራት ባልተጠበቀ መልኩ በጊዜ ከውድድሩ በተሰናበቱበት የዘንድሮ አፍሪካ ዋንጫ በ2006 በግብፅ ከተካሄደው ውድድር ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የውድድሩ አዘጋጅ አገር ዋንጫ ማንሳት ችሏል:: ኮትዲቯር ዋንጫውን ከማንሳቷ በላይ ያነሳችበት መንገድም የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ ይበልጥ አስደናቂ እንዲሆን አድርጓል:: በዝሆኖቹ የቻምፒዮንነት ጉዞ ሁለት አስደናቂ ክስተቶች ለሌሎችም ከውድቀት በኋላ መነሳት እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ሆኗል::
አንደኛው ዝሆኖቹ ከምድብ ጨዋታዎች ጀምሮ ዋንጫውን እስካነሱበት ድረስ በእያንዳንዱ ጨዋታ የገጠማቸው ጉዳይ ነው:: ኮትዲቯር በመክፈቻውና በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ጊኒ ቢሳውን 2ለ0 አሸንፋ አጀማመሯ ያማረ ቢሆንም በተከታዮቹ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች የገጠሟት አስደንጋጭ ሽንፈቶች የዝሆኖቹን ቅስም የሰበረ ነበር:: በናይጄሪያ 1ለ0 እንዲሁም በኢኳቶሪያል ጊኒ 4 ለምንም በሆነ ውጤት አስደንጋጭ ሽንፈት የገጠማት ኮትዲቯር አበቃላት ሲባል ወደ ጥሎ ማለፍ ዙር ያለፈችው በተአምር ተንጠልጥላ ነበር::
በተለይም ዝሆኖቹ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታቸው በሜዳና በደጋፊያቸው ፊት በኢኳቶሪያል ጊኒ የደረሰባቸው የ4ለ0 ሽንፈት አስደንጋጭና ተስፋ የሚያስቆርጥ ነበር። ከዚህ ውጤት በኋላም የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአሰልጣኝ ጂን ሉዊስ ጋሴት የስንብት ደብዳቤ ለመፃፍ ጊዜ አልፈጀም። በዚህም የቀድሞው የዝሆኖች ኮከብ ኢመርስ ፋኤ በጊዚያዊ አሰልጣኝነት ዝሆኖቹን ተረከበ::
ዝሆኖቹ በጥሎ ማለፍ ዙሩም የ2021 ቻምፒዮኗን ሁሉንም የምድብ ጨዋታዎች ያሸነፈችውን ሴኔጋልን በመጋፈጣቸው የትም አይደርሱም የሚሉ ግምቶችን ከፍ አድርጎ ነበር:: ያም ሆኖ ዝሆኖቹ ለጥቂት በውድድሩ የቆዩበትን እድል ተጠቅመው የቴራንጋ አናብስትን ማንበርከክ ቻሉ:: ከዚያ በኋላም የሚያቆማቸው አልተገኘም:: ዝሆኖቹ በሩብ ፍፃሜ፣ ግማሽ ፍፃሜና የፍፃሜ ወሳኝ ጨዋታዎች ከመመራት ተነስተው ተስፋ ሳይቆርጡ እስከ መጨረሻው ደቂቃ በመፋለም ዋንጫውን በሜዳቸው ማስቀረት ቻሉ::
በዝሆኖቹ ልብ አንጠልጣይ ጉዞ የኮከባቸው ሴባስቲያን ሀለር አስደናቂ ታሪክም ለብዙዎች ፅናትንና አልሸነፍ ባይነት ያስተማረ ነው:: ሀለር ሐምሌ 2022 ሲሰቃይበት የነበረውን የካንሰር ህመሙን አሸንፎ በጥር 2023 ዳግም ወደ እግር ኳስ ተመለሰ። መስከረም 2024 ሀገሩን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ያሳለፈችውን ብቸኛ ግብም አስቆጠረ። ከአራት ቀናት በኋላም ዝሆኖቹ በፍፃሜው ፍልሚያ ናይጄሪያን 2ለ1 አሸንፈው ዋንጫውን ሲያነሱ የማሸነፊያዋን ግብ ከመረብ ያሳረፈው ይሄው ከጥቂት ዓመት በፊት በካንሰር ህመም ሲሰቃይ የነበረ ኮከብ ነው::
ኮትዲቯር ከአርባ ዓመታት በፊት 1984 ላይ አዘጋጅታ በነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ቻምፒዮን ባለመሆኗ በርካታ የዝሆኖቹ ደጋፊዎች ቁጭት ቢያድርባቸውም አሁን በሜዳቸው የአህጉሪቱን ትልቅ ዋንጫ የማስቀረት ህልማቸው እውን ሆኗል:: ኮትዲቯራውያን በበርካቶች ዘንድ ልዩና ምርጡ የአፍሪካ ዋንጫ እንደሆነ የተመሰከረለትን ድግሳቸውን ከድል ጋር ሲያጣጥሙ በውድድሩ ታሪክ የማይረሱ ክብረወሰኖችና ክስተቶች ታይተዋል:: በ52 ጨዋታዎች 119 ግቦች ተቆጥረው አዲስ የአፍሪካ ዋንጫ ክብረወሰንም ተሻሽሏል:: 24 አገራት በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ ከጀመሩ ወዲህ በርካታ ግብ የተቆጠረው በግብፁ 2017 ዋንጫ ሲሆን 102 ግቦች ብቻ ነበሩ ከመረብ ያረፉት::
የአፍሪካ ዋንጫውን ፍፃሜ ተከትሎ እስከ ሩብ ፍፃሜው ፍልሚያ አስደናቂ ጉዞ የነበራት ኢኳቶሪያል ጊኒ ኮከቧ ኤሚሊዮ ሱይ አምስት ግቦች ከመረብ በማሳረፍ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የወርቅ ጫማውን ወስዷል:: በተመሳሳይ የውድድሩ ክስተት በመሆን ሦስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ደቡብ አፍሪካ ግብ ጠባቂ ሮንዌን ዊሊያምስ የውድድሩ ኮከብ በረኛ በመባል የወርቅ ጓንት አሸናፊ መሆን ችሏል። ከ7 ጨዎታዎች በአምስቱ መረቡን ያላስደፈረው ይህ ግብ ጠባቂ ከአምስት የመለያ ምት አራቱን በማዳን በአፍሪካ ዋንጫ አዲስ ታሪክ መስራቱ ይታወቃል:: በፍፃሜ ተፋላሚዋ ናይጄሪያ አስደናቂ ጉዞ ንስሮቹን በአምበልነት የመራው ዊሊያም ትሮስት ኢኮንግ ደግሞ የውድድሩ ኮከብ በመሆን የወርቅ ኳሱን ወስዷል::
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2016