ግብርናን በዲጂታል ቴክኖሎጂ

ግብርና የኢትዮጵያ ትልቁ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው:: ከሀገሪቱ ሕዝብ አብላጫውን ቁጥር የሚይዘው በዚሁ ዘርፍ ይተዳደራል:: ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ገቢ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው::

ዘርፉ የሀገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ እንደመሆኑ የሚጠበቅበትን አስተዋፆ እንዲያበረክት ይጠበቃል:: ለዚህም ነው በመንግስት በኩል ዘርፉን በማዘመን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ያለው:: ከእነዚህ ሥራዎች መካከል አንዱ ግብርናውን በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ ማሳደግ ነው::

ኢትዮጵያ በ2025 የዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ነድፋ በተለያዩ ዘርፎች እየተገበረች ትገኛለች:: በዚሁ የዲጂታል ኢኮኖሚ ትራስፎርሜሽን ስትራቴጂ ውስጥ አራት ዋና ዋና ዘርፎች የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የግብርናው ዘርፍ ይገኝበታል::

የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ቴክኖሎጂ ወሳኝ መሆኑን በመረዳት በመንግስት በኩል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን፣ ግብርናውን በቴክኖሎጂ በማዘመንና በማሳደግ ረገድ የግሉ ሴክተር ተሳትፎም ወሳኝ መሆኑ ይነገራል:: በግብርና ቴክኖሎጂ ተሳትፎ እያደረጉ ከሚገኙ የግል ድርጅቶችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥቷል:: ከእነዚህ ውስጥ ‹‹ግሪን አግሮ ሶሊዩሽን›› የተሰኘው ሀገር በቀል ድርጅት ይገኝበታል::

የድርጅቱ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አብርሃም እንድሪያስ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ በሥራ እድል ፈጠራም፤ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ትልቁን ድርሻ በማበርከትም ይጠቀሳል:: በዚህ የግብርና ሥራ ዋነኛዎቹ ተሳታፊዎች ደግሞ መሬታቸው አነስተኛ የሆነና በአማካይ ከአንድ ሄክታር በታች መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች ናቸው:: ድርጅቱ ከአስር ዓመት በፊት ወደ ግብርናው ዘርፍ ሲሰማራ ከእነዚህ አርሶ አደሮች ጋር የተለያዩ ሥራዎች ለመሥራት ነው::

ድርጅቱ የግል ዘርፍ እንደመሆኑ የግብርና ሥራውን ለማሳደግ ሲሞክር በቅድሚያ ምን አይነት አማራጮች እንዳሉ ለማየት ሞክሯል:: በተለይ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ለእነርሱ መብዛት አገልግሎት ሊሰጡ የሚያስችሉ የተለመዱ አሰራሮች እንዳሉ መረዳት ችሏል:: ለዚህም የዲጂታል ቴክኖሎጂው አንዱ በርካታ አርሶ አደሮች ዘንድ በስፋት ተደራሽ ለመሆን የሚያስችል መንገድ መሆኑ ሥራውን ለመጀመር እንደ መነሻ ሆኖታል::

በተጨማሪም የዲጂታል ግብርና አገልግሎቱን ለመጀመር ድርጅቱ ከዚህ በፊት የነበረውን የሜካናይዜሽን፣ የግብርና ግብአት አቅርቦትና ለአርሶ አደሮች ስልጠና የመስጠት የረጅም ጊዜ ልምድ ተጠቅሟል:: እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ ድርጅቱ ምን አይነት ቴክኖሎጂ ይበልጥ አርሶ አደሩ ዘንድ ለማድረስ በተለይ ደግሞ ለማስፋት እንደሚያስችል የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎችን በማየት ጥናት ማድረግ ጀመረ:: በመቀጠል ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ጥናት ሰርቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ግብርናውን ለማሳደግና በዘርፉ ውጤት ለማምጣት ምን አይነት ሞዴል እንደሚያዋጣ በመገምገም የሞባይል መተግበሪያን እንደ አንድ አማራጭ በመውሰድ ‹‹ለእርሻ›› የተሰኘና ለአርሶ አደሮች የዲጂታል ግብርና አገልግሎት የሚሰጥ የቴክኖሎጂ ምህዳር /platform/ ፈጥሯል::

አቶ አብርሃም እንደሚሉት፤ በዚህ ‹‹ለእርሻ›› የተሰኘው የአርሶ አደሮች የዲጂታል ግብርና አገልግሎት ምህዳር በሞባይል መተግበሪያ አማካኝነት ያለ ኢንተርኔት አርሶ አደሮች ከግብርና ሥራ ጋር የተያያዘ አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት ያስችላቸዋል:: በተጨማሪም በ7860 አጭር መልእክት በመጠቀም ተመሳሳይ የግብርና መረጃዎችን ለማግኘት ይረዳቸዋል:: የሞባይል መተግበሪያውንና በአጭር መልእክት አገልግሎቱ በግብርና ሞያ የተመረቁ ባለሞያዎች ለእርሻ በተሰኙ ኤጀንት /ወኪሎች/ አማካኝነት አጣምረው ይሰራሉ:: በዚህ ፕላትፎርም አማካኝነት ባለሞያዎቹ ለአርሶ አደሮች የሜካናይዜሽን፣ የግብርና ግብአት፣ የምክር አገልግሎትና የፋይናንስ አገልግሎት አቅርቦት እንዲያገኙ ያደርጋሉ:: ለዚህ ምክንያት የሆነው ደግሞ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች አንድ አገልግሎት ብቻ አግኝተው ውጤታማ የመሆናቸው እድል ዝቅተኛ በመሆኑ ነው::

ስለዚህ አርሶ አደሮች የተሟላ የግብርና አገልግሎት ለእርሻ ወኪሎች /ኤጀንቶች/ አማካኝነት ማግኘት ቢችሉ የግብርናውን ሥራ ቀላል ማድረግ ይችላሉ:: በዚህ ውስጥ እንደ ትልቅ ውጤት የሚታየው የአርሶ አደሮች ምርት መጨመርና ገቢ ማደግ ነው:: ምርት ጨምሮ ገቢያቸው ካላደገ ዘላቂነት ያለው የግብርና ቢዝነስ ሊኖር አይችልም:: ከዚህ አኳያ አርሶ አደሮቹ ምርታቸው ጨምሮ ጥሩ የገበያ ትስስር ኖሯቸው መሸጥ እንዲችሉ ዲጃታል ቴክኖሎጂው ያግዛቸዋል::

አቶ አብርሃም እንደሚያብራሩት፤ አርሶ አደሩ የግብርና ግብዓቶችን ለማግኘት በአማካይ ከ20 እስከ 30 ኪሎ ሜትር ይጓዛል:: አርሶ አደሮቹ በግብርና ግብዓት መሸጫ መደብሮች ውስጥ ምን አይነት ግብአቶች እንዳሉና አጠቃቀማቸው እንዴት እንደሆነ የመረዳት እድላቸውም በጣም ዝቅተኛ ነው:: ግብአት ፍለጋ ለመጓዝ የትራስፖርት አገልግሎት የማግኘት እድሉም የጠበበ ነው:: ስለዚህ አርሶ አደሮች የሚፈልጉትን የግብርና ግብአት ወዲያውኑ ማግኘት አይችሉም::

ይሁንና በዚህ የዲጂታል ምህዳር አማካኝነት በተለያዩ የአርሶ አደር አጎራባች አካባቢዎች ላይ የተከፈቱ ለእርሻ ኤጀንቶች /ወኪሎች/ አማካኝነት የተለያዩ የአርሶ አደር ፍላጎቶችን ሰብስበው አርሶ አደሩ ወደ ከተማ መሄድ ሳያስፈልገው በከተማ ካሉ የግብርና ግብአት አቅራቢ መደብሮች ጋር በማስተሳሰር ግብአቱ ለአርሶ አደሮቹ እንዲመጣ ያደርጋሉ:: ይህም የአርሶ አደሮችን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ይቆጥባል:: አርሶ አደሮቹ በአጭር መልእክት አማካኝነት የሚያገኙት መረጃ ደግሞ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል::

በተመሳሳይ ሜካናይዜሽንም ላይ የግብርና ማሽን ባለቤቶች በሚያውቋቸው አካባቢዎች ላይ ከአንድና ከሁለት ወር በላይ የሜካናይዜሽን አገልግሎት ላይኖር ይችላል:: በዚህም የግብርና ማሽናቸው ያለ ሥራ ይቀመጣል:: ነገር ግን ለእርሻ ኤጀንቶች /ወኪሎች/ ባሉባቸው አካባቢዎች ላይ የግብርና ማሽኖቹን አገልግሎቱን ከሚፈልጉ አርሶ አደሮች ጋር መገናኘት የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ካሉባቸው አካባቢዎች ውጪ ሌሎች ቦታዎች ላይም ጭምር ማሽናቸውን አንቀሳቅሰው መስራትና ገቢ ማግኘት ችለዋል:: በዚህም አንድና ሁለት ወር ይሰራ የነበረ ማሽን በዓመት ውስጥ እስከ ስምንት ወር የመስራት እድልም አግኝቷል:: በዚህም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆን ችሏል::

ከዚህም በላይ አርሶ አደሩ የግብርና ማሽኖችን ሲፈልግ ወደ ደላሎች ከመሄድ ይልቅ በእነዚህ ወኪሎች አማካኝነት መረጃ አግኝቶ በቀላሉ ማሽኖቹን መጠቀም ይችላል:: የማሽኖቹን አገልግሎት ፍለጋ ሲሉ ለደላሎች ሲያወጡ ከነበረው አላስፈላጊ ወጪዎች ድነዋል:: ከሜካናይዜሽን የሚያገኙት አገልግሎት ጥራትም ጨምሯል::

የአርሶ አደሩ ችግሮች የግብአት አቅርቦትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት አለማግኘት ብቻ አይደሉም የሚሉት አቶ አብርሃም፤ መቼ ሰብላቸውን መዝራት እንዳለባቸውና የአየር ንብረቱን ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለማወቅም መረጃ ያስፈልጋቸዋል ይላሉ:: ለዚህ ደግሞ ሳይንሳዊ መረጃ ሊሰጡ የሚችሉ በርካታ ተቋማት በሀገሪቱ ይገኛሉ ሲሉ ጠቅሰው፣ አርሶ አደሩ ደጅ የሚደርሱ በሬዲዮና በቴሌቪዥን አማካኝነት የሚቀርቡ አማራጭ የግብርና መረጃ ማድረሻ መንገዶች እንዳሉም ይጠቁማሉ::

እሳቸው እንዳሉት፤ ይህ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ግብርና ላይ ብቻ ያተኮሩና የወቅቱ የአየር ንብረት ምን እንደሚመስል የሚጠቁሙ መረጃዎችና ምክረ ሀሳቦች በዚሁ የዲጂታል ምህዳር አማካኝነት በሞባይል መተግበሪያና በአጭር መልእክት ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ ይደረጋል:: እንዲህ አይነት አሰራር በአርሶ አደሩ በኩል እምነት እንዲያሳድር ያስችላል::

‹‹ለእርሻ›› የተሰኘው የዲጂታል የግብርና አገልግሎት ምህዳር /ፕላትፎርም/ በተለይ ደግሞ አርሶ አደሩ ላይ ያመጣውን በጎ ለውጥ ለማወቅ በሶስተኛ ወገን ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ድርጅቱ ራሱ በሰራው የእርካታ መለኪያ ደረጃ መሰረት ሁለት ዓመት ያህል አገልግሎቱን የተጠቀሙ አርሶ አደሮች ምርታቸው እስከ 20 ከመቶ እንዳደገ ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል:: የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በትክክለኛው ጊዜ እንዲያርሱ የሚያገኙት መረጃ፣ የግብርና ግብአቶችን በሚፈልጉት ጊዜ ማግኘትና የሜካናይዜሽን ግብርና መጠቀማቸው ለዚህ አስተዋፅኦ አድርገዋል ሲሉም አብራርተዋል::

አቶ አብርሃም እንደሚናገሩት፤ በአሁኑ ጊዜ አንድ ሺ 490 የሚሆኑ በ‹‹ለእርሻ›› ኤጀንት /ወኪል/ ውስጥ የሚሰሩ የግብርና ምሩቅ ባለሞያዎች አሉ:: እ.ኤ.አ እስከ 2028 እነዚህን ባለሞያዎች ወደ ዘጠኝ ሺ የማድረስና እስከ ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ያህል አርሶ አደሮች ደግሞ ተጠቃሚ የማድረግ እቅድ ተይዟል:: ስለዚህ የተጠቃሚ አርሶ አደሮች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ የኤጀንቶቹ ተመራቂ ወጣቶችም ተሳትፎ እያደገ ይመጣል:: በዚያው ልክ ቴክኖሎጂውን ማላመድና ማሳደግ ይገባል:: ይህ እንዲሆን ደግሞ የፋይናንስ አገልግሎት በተለይ የብድር አገልግሎትን ማሳደግ የግድ ይላል::

የግብርናው ሴክተር የሀገሪቱ ትልቁ የኢኮኖሚ ዘርፍ እንደመሆኑ በዚህ ላይ የሚደረግ ማንኛውም የዲጂታላይዜሽን ሥራ ለ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረጊያ ስትራቴጂ ወሳኝ ነው:: በገጠር የሚኖሩና በብዛት የባንክ አገልግሎት የማያገኙ አርሶ አደሮች በድርጅቱ በኩል ተመዝግበው በባንኮችና በቴሌኮም ኩባንያዎች የሞባይል ዋሌት ይከፈትላቸዋል፤ ይህም ለአካታችነት እንደ አንድ ግብአት ሆኖ ያገለግላል::

ሌላው ደግሞ ሴቶችን ከማካተት አንፃር የሚታይ ነው፤ አብዛኛው የግብርና ሥራ በሴቶች ጉልበት የሚሰራ ቢሆንም፣ ብድር ወይም የግብርና አገልግሎቱን በማግኘት በኩል ግን ሴቶች ተጠቃሚ ሲሆኑ አይታይም:: ስለዚህ እንደ ለእርሻ አይነት የዲጂታል ምህዳሮች ከመጀመሪያውኑም ሴቶችንም ለማካተት ታሳቢ ተደርገው ከተቀረፁ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ነው::

ቴክኖሎጂን ለማላመድ ተከታታይ ስልጠና እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ አብርሃም፤ ድርጅቱም ለአርሶ አደሮችና ኤጀንቶች ጥልቀት ያለው ስልጠና እየሰጠ ይገኛል ይላሉ:: በመሆኑም በዚህ ዓመት ብቻ 350 ሺ አርሶ አደሮችን በስልጠና ለመድረስ እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ እ.ኤ.አ በ2024 በተመሳሳይ 350 ሺ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የምክር አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል:: ይህም ሰባት ሺ አርሶ አደሮችንና 12 ሺ 500 የሚሆኑ የልማት ጣቢያ ሰራተኞችን ማሰልጠን ያካትታል ሲሉ አብራርተው፣ በቀጣዮቹ ዓመታት ደግሞ አንድ ሺ 750 ለሚሆኑ የ ‹‹ለእርሻ›› ኤጀንቶች ስልጠና ለመስጠት መታቀዱን አመልክተዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ ድርጅቱ በዚሁ የዲጂታል ግብርና አገልግሎት ምህዳር በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ /የቀድሞው/፣ ሶማሌ፣ ሲዳማ ክልል እየሰራ ሲሆን በትግራይና ጋምቤላ ክልሎች ይህን አገልግሎቱን ለማስፋት በአሁኑ ወቅት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል::

ድርጅቱ ወደዚህ የዲጂታል ግብርና አገልግሎት ሥራ የገባው ገበያው በመኖሩና አርሶ አደሩም ስልክ እየያዘ ስለመጣ አይደለም የሚሉት አቶ አብርሃም፤ ከሥራው ባልተናነሰ ቴክኖሎጂውን ማላመዱና ስልጠና መስጠቱ ወሳኝ መሆኑን በመረዳትና ችግሩን ለመጋፈጥ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እየሰራ በመሆኑ ነው ሲሉ አብራርተዋል::

አቶ አብርሃም እንዳስታወቁት፤ እንዲህ አይነቱን የዲጂታል ግብርና አገልግሎት መጠቀም ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ተለዋዋጭ የሆኑና ወቅታዊ መረጃዎችን በሚገባ ለማሰባሰብና ለመያዝ ይረዳል:: የግብርና አገልግሎት ሰፊና የተለያየ እንደመሆኑ ማን ምን አይነት አገልግሎት መቼ ይፈልጋል የሚለውን በትክክል አውቆ አገልግሎቱን ለማቅረብም ያግዛል:: በሌላ በኩል ደግሞ በግብርናው ዘርፍ የፋይናንስ አገልግሎቱን ለማቅለል ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል:: ይህም በጥቅሉ የግብርና ምርት እንዲያድግና አርሶ አደሮች ጥሩ ገቢ እንዲያገኙ ያስችላል::

ሁሌም ቢሆን በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ዓለም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲመጡ ወዲያው የመቀበል ችግሮች ይገጥማሉ:: ስለዚህ ቴክኖሎጂውን ቀስ ብለው መልመድና ወዲያው መቀበል የሚፈልጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ በመረዳት በዚህ መንገድ መስራት ተገቢ ነው:: አዲስ ቴክኖሎጂ ሲመጣ የመጀመሪያው አማራጭ ቴክኖሎጂውን በትእግስት ማላመድ ነው:: ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ቴክኖሎጂውን ለማላመድ ማሳወቅ፣ ግንዛቤ ማስጨበጥና ስልጠና በመስጠት ወደ ትግበራው መግባት ይሆናል::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን የካቲት 5/2016

 

 

 

Recommended For You