ትውልድ እንደ ጊዜ ነው፤ ይመጣል፣ ይሄዳል:: ነገ ዛሬ እንደመሆኑ፣ ዛሬም ትናንት እንደመባሉ ሁሉ፤ ዛሬ ያለው ትውልድ ነበር መባሉ፤ በአዲስ ትውልድም መተካቱ አይቀሬ ነው:: በዚህ በዘመንና ትውልድ ጉድኝት ውስጥ ግን አንድ ነገር አለ፤ ተግባር:: ይሄ ተግባር ጊዜ እና ትውልዶች የሚገለጡበት፤ ምን ነበሩ? ምን ሠሩ? ተብሎ ሲጠየቅ መልስ ሆኖ የሚቀርብ፤ በተረክ ሳይሆን በታሪክ የሚነገር ሁነት ነው::
እናም በትናንቱ ጊዜ የነበሩ ትውልዶች፤ ጊዜና ትውልድ የሚገለጥበትን ተግባር ይከውናሉ:: ይሄ ተግባር ደግሞ ጊዜና ትውልዱ በታሪክ መዝገብ ላይ በመልካም ግብራቸው፣ አልያም በእኩይ ሥራቸው አጎዳኝቶ ይከትባቸዋል:: ኢትዮጵያውያንም በየዘመንና የኑሮ ምዕራፎቻቸው በእነዚሁ መልካቸው የሚገለጹበት አያሌ ሁነቶች አሏቸው:: ከእነዚህ አንዱና ቀዳሚው ደግሞ፣ ትውልድና ጊዜ ተስማምቶ የተገለጠበት የዓድዋ ድል ገድል ነው::
ዓድዋ፣ ለኢትዮጵያውያን የሰው ልጆች እኩልነትን የገለጡበት የማሸነፍ ሰብዕናቸው አውድ ነው:: ለጥቁሮችና ለጭቁኖች ደግሞ የቅኝ ተገዥነት ተግባርና እሳቤት ከላያቸው እንዲያወርዱ መንገድ ያሳየ የነጻነት መብራት ነው:: ለመላው የዓለም ጭቁኖች ደግሞ ሰው በሰውነቱ ከማንም የማይበልጥ አልያም የማያንስ ስለመሆኑ በተግባር ያረጋገጡበት ሁነት ነው:: እናም ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ድል፤ የጥቁሮች ነጻነት፤ የጭቁኖች መብራት ሆኗል::
ይሄ ታዲያ የትናንት ተግባር፤ የቀደምቶች ገድል፤ የወቅቱ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የከፍታና ልዕልናቸው ማንጸሪያ ነው:: ለዛሬዎቹ እኛ ደግሞ የኩራታችን ምንጭ፣ የማድረግ አቅም መፍጠሪያ ስንቅ ነው:: እዚህጋ ልብ ሊባል የሚገባው ግን፤ ቀደምቶቻችን ትናንት የራሳቸውን ገድል ጽፈው ደምቀው አድምቀውናል:: እኛም በእነርሱ ሥራ ኮርተን፤ ታሪካቸውንም ተርከናል:: ለመታሰቢያቸውም ሐውልት አቁመን፣ ሙዚየም ገንብተናል::
በዚህም ታሪክን ማክበራችን፤ ቀደምቶቻችንን ማሰባችን ያስመሰግነናል:: ነገር ግን ታሪክ አሳቢነትን እንጂ ታሪክ ሠሪነትን አያጎናጽፈንም:: እናም ከታሪክ ነጋሪነት ወደ ታሪክ ሠሪነት መሸጋገር ይጠበቅብናል:: ለዚህ ደግሞ ብልጽግናችንን እውን በማድረግ ዳግም የዓድዋን የነጻነት ተምሳሌትነታችንን ልናረጋግጥ ይገባል:: ምክንያቱም የዓድዋው ነጻነት ለጭቁኖች የድል ችቦን ያቀበልንበት የዓለም ጭቁን ሕዝቦች ተምሳሌት የሆንንበት ዓርማችን ነውና:: እናም እኛ የዛሬዎቹ ይሄን ታሪክ ከመዘከር ያለፈ የራሳችን ዐሻራ ማኖር ይጠበቅብናል:: ይሄ ዐሻራ ደግሞ ዘመኑን የመጠነ፤ ጊዜውን የዋጀ፤ ኢትዮጵያዊ ነጻነትን ወደ ምሉዕነት የሚያሸጋግር ሊሆን ይገባል::
ይሄም ድህነትን የማሸነፍ፤ ከስንዴ ልመና ነጻ የመውጣት፤ ኢኮኖሚያዊ ልዕልናን የመጎናጸፍ፤ በጥቅሉ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ዕውን ማድረግ ነው:: ምክንያቱም የትናንቱ የቅኝ አገዛዝን እንቢኝ የማለት የነጻነትና የድል መንገድ፤ በኢኮኖሚ ነጻነትና ድል ካልታጀበ ምሉዕ ሊሆን አይችልም:: በልቶ ያላደረ ሕዝብ መራቡ ስለማይቀር፤ የተራበ ደግሞ ለልመና እጁን መዘርጋቱ ግድ ስለሚሆን፤ ለልመና የተዘረጋ እጅም ለሌሎች ለመታዘዝ ስለሚገደድ፤ ይሄ መገደድ ደግሞ የነጻነት መንገዱን ስለሚያደበዝዘው፤ እኛ የዛሬዎቹ ነጻነታችንን ምሉዕ ለማድረግ ከድህነት ለመውጣት መትጋት ይጠበቅብናል::
ይሄን ስናደርግ የትናንቶቻችንን እናከብራለን፤ ዛሬያችንን እናቀናለን፤ ነጋችንን ብሩህ እናደርጋለን:: ከዚህም ባሻገር በሌላ የነጻነት አብዮት ለሌሎች የመልማትና ከኢኮኖሚ ጥገኝነት የመላቀቅ የመቻል አቅምን፣ የማድረግ ሰብዕናን፣ ድህነትን የማሸነፍ ቁርጠኝነትን መጎናጸፊያ የድል ችቦን እናበራላቸዋለን:: ይሄም ችቦ የልማት፤ የብልጽግና መስመር ማመላከቻ፤ የድህነት ማስወገጃ እና የተረጂነት እሳቤን መግቻ ብርሃን ነው::
ይሄ የዘመኑን አሸናፊነት የሚያጎናጽፈን የድል መንገድ ታዲያ ዝም ብሎ ስላወራን የምናገኘው፤ ታሪክ ስላወቅን የምንቸረው፤ አልያም የውጪውን እሳቤና ሃሳብ አመንጪዎችን አምነን ስለተከተልን የሚከናወንልን አይደለም:: ይልቁንም የእኛን መሻት፤ መሻታችንን ለመፈጸም መነሳትን፤ መነሳታችንን ለማዝለቅ መጽናትን፤ መጽናታችንን ለማጠንከር መተባበርን፤ መተባበራችንን ለማደርጀት ፍቅርና ሰላምን ገንዘብ ማድረግን አብዝቶ ይጠይቃል::
ዛሬ እኛ ኢትዮጵያውያንም የቅድሚያ ቅድሚያ አድርገን የራሳችን ሀብት ልናደርግ የሚገባውም ይሄው ነው:: የፍቅርን ኃያልነት፤ የአብሮነትን አለትነት፤ የሰላምን የሁሉ ነገር ማዕከልና መሠረትነት በልካቸው መገንዘብ ይጠበቅብናል:: ተገንዝበንም እንዳይርቁን አድርገን ከራሳችን ልናዋህዳቸው ይገባል:: ምክንያቱም ፍቅር ከራስ ይጀምራል:: ራሱን ያፈቀረ በዙሪያው ያሉትን ያፈቅራል፤ ማኅበረሰቡን ያፈቅራል፤ ሀገርና ሕዝቡን ያፈቅራል::
ፍቅር የተሞላው ግለሰብና ማኅበረሰብ ደግሞ በፍቅር ይተሳሰራል፤ ይተባበራል፤ ይደረጃል:: ፍቅር አስተሳስሮ ያደረጀው ማህበረሰብ ደግሞ ለመገፋፋት ሳይሆን ለመተባበር ይቀድማል:: ለጸብና ጦርነት ሳይሆን በችግሮቹ ላይ ተነጋግሮ ለመግባባት ይፈጥናል:: ለቂምና በቀል ሳይሆን፣ ለይቅርታና እርቅ ሳይታክት ይተጋል:: በስሜት ተገፍቶ ነፍጥ ለማንሳት ሳይሆን፤ በማስተዋል ተሞልቶ ጦርነትን ለማስቀረት ትዕግስትን ይላበሳል::
በፍቅር የተባበረ፣ ተባብሮም ሰላምን ገንዘቡ ያደረገ ማህበረሰብ ታዲያ፤ ሃሳብና መንገዱ የቀና ይሆናል:: ቀናው መንገድ ደግሞ ልማት ነው:: ቀናው መንገድ ድህነትን ማሸነፍ ነው:: ቀናው መንገድ እጅን ለልመና ከመዘርጋት ይልቅ ስንዴን አምርቶ ጎተራን መሙላትና መጠቀም ነው:: ቀናው መንገድ አጠቃላይ ብልጽግናን እውን አድርጎ፣ የብልጽግና ተምሳሌት መሆን ነው:: ለዚህም ነው ዛሬ እኛ ኢትዮጵያውያን የትናንቱ ልዕልናችንን ለዛሬው ሰላም ማጽኛ፤ ለነገውም ብልጽግና እውን ማድረጊያ አቅም ልናውለው የሚገባን!
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2016