በሃዋሳ ሐይቅ የግማሽ ማራቶን ሩጫ በግላቸው የተሳተፉ አትሌቶች በበላይነት አጠናቀዋል። ውድድሩ በርካታ አትሌቶች፣ የውጪ ሀገር ዜጎች፣ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም ሕጻናትን በማሳተፍ ትናንት ለ12ኛ ጊዜ ተካሂዷል።
በዓመት ውስጥ በርካታ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሚያካሂዳቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ይህ ሁለተኛው ነው። ውቢቷና ለአትሌቲክስ ስፖርት ምቹ የሆነችው ሀዋሳ በየዓመቱ በርካቶች የሚሳተፉበትን ይህንን ውድድር ስታስተናግድ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባለፈ የቱሪዝም ፍሠቱን ከመጨመር አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደምታገኝበት ይጠበቃል።
ሃያ አንድ ኪሎ ሜትር በሚፈጀው ውድድር ላይ ከክለቦች የተወጣጡ አንዲሁም በግላቸው 150 የሚሆኑ አትሌቶች ተሳትፈውበታል። ከ400 በላይ የሚሆኑ የጤና ሯጮችም የውድድሩ አካል ሲሆኑ፤ 35 የሚሆኑት ከእንግሊዝ ሀገር የመጡና አንዱ ደግሞ የዊልቸር ተሳታፊ ናቸው። ሕዝባዊው ሩጫ ደግሞ በ8 ኪሎ ሜትር 3ሺ500 ነዋሪዎችን እንዲሁም ሕጻናትን አሳትፏል። በሩጫው ዋዜማም የታቦር ተራራን የመውጣት መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በሀዋሳ ሐይቅ የግማሽ ማራቶን ውድድር የኦሪገን ዓለም የማራቶን ቻምፒዮናውን ታምራት ቶላን የመሳሰሉ ስመጥር አትሌቶች አፍርቷል። ዘንድሮም በርካታ ልምድ ያላቸውን አትሌቶች በማሳተፍ ጠንካራ ፉክክር አስተናግዷል። በዚህም በሴቶች የግል ተሳታፊዎቹ አትሌት ሙላት ተክሉ 1:15:05፣ ክለልቱ ካያሞ 1:15 :19 እንዲሁም ጽግነሽ መኮንን 1:15:24 በሆነ ሰዓት ተከታትለው በመግባት ከወርቅ እስከ ነሐስ ያለውን ሜዳሊያ ወስደዋል።
ርቀቱን ከአንድ ሰዓት በታች በመሸፈን የ100 ሺ ብር ጉርሻ ለማግኘት በወንድ አትሌቶች መካከል በተደረገው ጠንካራ ፉክክር እንየው ንጋት በግል አሸንፏል። አትሌቱ ክብረወሰኑን መስበር ባይችልም የገባበት ሰዓት 1:02:40 ሆኖ ተመዝግቧል። ከግሎባል ከተማና ከጎላዞ አትሌቲክስ ክለብ ተከትለውት የገቡት አትሌት አሰፋ ተፈራ እና ደበበ ተካ ደግሞ 1:02:47 እንዲሁም 1:03:04 ማጠናቀቅ ችለዋል።
ውድድሩን ተከትሎም የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ መኩሪያ መርሻዬ ይህን መሠል ስፖርታዊ ኩነቶች ለከተማዋ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል። በቱሪስቶች ዘንድ ተመራጭ የሆነችው ሀዋሳ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊና መሠል ሕዝባዊ ኩነቶችን በማዘጋጀት ትታወቃለች። የከተማዋ ነዋሪም ስፖርትን ባሕሉ ያደረገ ብቁ ማኅበረሰብ እንዲሆን ጠቃሚ ልምድ እንዲሆነውና ጤናውን እንዲጠብቅ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም ተናግረዋል።
ከስፖርት ቱሪዝም ጋር በተያያዘ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ የሚገኘው የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር የዚህ ውድድር አጋር ነው። ይህንንም ተከትሎ ሚኒስትር ዴኤታዋ ሌንሳ መኮንን ሩጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የታወቀችበትና ሰንደቋን ከፍ ያደረጉ ትልልቅ አትሌቶች የተገኙበት ስፖርት መሆኑን በማስታወስ፣ ፉክክር ባሕሪው ለሆነው የሰው ልጅ የጤናማ ፉክክር መገለጫ የሆነው ስፖርት ነው ብለዋል። በመሆኑም የሩጫ ውድድር የሚያዘጋጀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከውድድሩ ባለፈ ቱሪዝም ላይ የሚያከናውነው ተግባር ሊበረታታ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም