የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በከፍተኛ ሁኔታ የቡና እና የጫት ልማት የሚካሄድባትና ለልማትም ምቹ የሆነ ሥነምህዳርና የአየርፀባይ እንዳላት ይታወቃል። ልማቷም በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ሲሆን፤ በግብርና ዘርፍ የተለያዩ የሰብል ልማቶች ይከናወናሉ፡፡ እንደሀገር የበጋ ቆላ መስኖ የስንዴ ልማት ከተጀመረ ወዲህ ደግሞ፤ ከዚህ ቀደም በአካባቢው ባልተለመደ ሁኔታ የስንዴ ልማቱ ተጠናክሯል፡፡
በማዕድን ሀብትም የምድር ፀጋ እንዳላት የሚነገርላት ምሥራቅ ሐረርጌ፤ በቱሪዝም ኢንዱስትሪውም እንዲሁ የቱሪስት መስህብ የሚሆኑ ሀብቶችን በውስጧ ይዛለች። ይህን ሀብት ወደ በለጠ የኢኮኖሚ ጥቅም ለማሸጋገር በማኅበራዊ ዘርፍ በጤና፣ በትምህርት ተደራሽነት ላይ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት እንዲሁም የአካባቢ ሰላምን ማረጋገጥ በፀጥታ ዙሪያ እየተሠሩ ስላሉ ሥራዎች የምሥራቅ ሐረርጌ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አያሌው ታከለ ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- ምሥራቅ ሐረርጌ በስፋት በምትታወቅባቸው የቡና እና የጫት ልማትን በተመለከተ ቀድመው ማብራሪያ ቢሰጡን?
አቶ አያሌው፡– እርግጥ ነው፤ በምሥራቅ ሐረርጌ ቡና በስፋት ይለማል፡፡ የሐረር ቡና በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፤ በዓለም ላይ ይታወቃል፡፡ የአካባቢው አርሶ አደር የኢኮኖሚ ምንጭም ነው። በመሆኑም በቡና ልማት ላይ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል፡፡ በተለይም ሐረርጌ ቡና የሚባለውን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው፡፡ ለአብነት ያረጁ የቡና ተክሎችን በአዲስ እንዲተኩ የማድረግ፣ የቡና ችግኞችንም የማፍላት ሥራ ከተግባራቶቹ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ምርታማነትን ለመጨመር እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች የአካባቢው የቡና ምርታማነትም ከአመት አመት እንዲጨምር አስችሏል፡፡
በአካባቢው ከቡና ልማት ቀጥሎ በስፋት የሚለማው ጫት ነው፡፡ ለሀገር የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘትም በምጣኔያዊ እድገት ላይ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። በሌላ በኩል የጫት ንግድ ሕገወጥነት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ሕገወጥ ንግድን ለመከላከል አንድ አካል ብቻ የሚወጣው አይደለም፡፡ ሥራዎች መሠራት ያለባቸው በቀጥታ ልማቱ ላይ ያለው አርሶአደር፣ አርብቶአደር፣ ዞኑ፣ አልፎም የኦሮሚያ ክልልና የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይል አካላት በጋራ የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ በመፍጠር ነው ፡፡
በዚህ መንገድ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ አባላት የተካተቱበት ዐብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተገብቷል። በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ሕገወጥ ንግድን መከላከል ካልተቻለ ለሀገር እድገት ጠንቅ እንደሚሆን አረጋግጠናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሰብል ልማት በኩል ያለውን እንቅስቃሴ ደግሞ ቢገልጹልን?
አቶ አያሌው፡– በሰብል ልማትም እንዲሁ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በዞኑ ከሚመረቱት የሰብል ምርቶች መካከልም ስንዴ፣ በቆሎ፣ ከቅባት እህል ደግሞ ለውዝ፣ ሰሊጥ ይጠቀሳሉ፡፡ በአካባቢው በተጨማሪ እንደ አዲስ የተጀመረው የሩዝ ልማት ነው። ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የቆላ በጋ መስኖ ልማት ሥራ እንደ ተሞክሮ ተወስዶ ልማቱ በዞኑ ተጠናክሯል፡፡
በስንዴ ልማቱ በ2013 ዓ.ም በስድስት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረ ሲሆን፤ በየአመቱ ግን በስንዴ ልማት የሚሸፈነው መሬት እየጨመረ ነው፡፡ በ2014 ዓ.ም ወደ 14 ሺህ ሄክታር መሬት፣ በ2015ዓ.ም 30 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በማልማት ሽፋኑን መጨመር ተችሏል። በተያዘው በጀት አመት በ2016 ዓ.ም ደግሞ ወደ ልማቱ የገባነው ሽፋኑን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፤ ፈጠራም የታከለበት መሆን አለበት ብለን ነው፡፡ በዚሁ መሠረት 93 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ልማት ተከናውኗል፡፡
በምርታማነት በኩልም ውጤት ተመዝግቧል። በ2013 ዓ.ም በሄክታር የተገኘው ወደ 13 ሺህ ኩንታል ምርት ነበር፡፡ በተያዘው በጀት አመት በተከናወነው ልማት ደግሞ በሄክታር ወደ 85 ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅደናል፡፡ በአጠቃላይ ወደ ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡ ይህን ያህል ምርት የሚጠበቀው በ2015 በጀት አመት በሄክታር ወደ 58ሺ ኩንታል ማግኘት በመቻሉ ነው፡፡ በየአመቱ ያለው ውጤትም አበረታች በመሆኑ ጭምር ነው፡፡
የምሥራቅ ሐረርጌ ነዋሪ ስንዴን የሚያውቀው ወይም የሚያገኘው በልማት ሳይሆን፣ በእርዳታና በተለያየ መንገድ ነበር፡፡ አሁን ግን የአካባቢው አርሶአደር እራሱ አልምቶ ተጠቃሚ ለመሆንና የሀገርንም ኢኮኖሚ ለማሳደግ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ ታጥቆ ተነስቷል፡፡ ጥቅሙንም በተግባር እያረጋገጠ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ከልማቱ ወደኋላ የሚመልሰው አይኖርም፡፡ አርሶ አደሩ ዝናብ ካናዳ ሀገር ከሚዘንብ ምሥራቅ ሐረርጌ በተለይም ቁምቢ ወረዳ ውስጥ ይዝነብልን እስከማለት ደርሷል። ይህም ለልማቱ ያለውን ፍላጎትና ተነሳሽነት ያሳያል፡፡
አርሶ አደሩ ከእርዳታ ወጥቶ የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ ብሎም ለውጭ ገበያ በማቅረብ በሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ የድርሻውን ለመወጣት በሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡ ልማቱንም በሙሉ ፍቃደኝነት እያከናወነ ይገኛል፡፡ አርሶአደሩ በቁርጠኝነት የልማቱ ተሳታፊ በመሆኑም ምሥጋና ይገባዋል፡፡
ሌላው በግብርና ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ እየተከናወነ ያለው የተፋሰስና የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ሥራ ነው። በዚህም ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በአፈር መሸርሸርና በመሬት መጎዳት የተራቆተው ተራራማው አካባቢ ሁሉ መልሶ እንዲያገግም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
በ2016 በጀት አመት ብቻ የምሥራቅ ሐረርጌ ነዋሪ በአንድ ጀንበር ወደ 45 ሚሊዮን የተለያዩ የዛፍ ችግኞችን ተክሏል፡፡ የተፋሰስ ሥራ ወይም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፤ የአካባቢ ሥነምህዳር እንዲመለስ፣ በአካባቢ ገጽታ ላይም ካበረከተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን አስገኝቷል። አርሶ አደሩም የምግብ ዋስትናው እንዲያረጋግጥ መልካም የሆነ ዕድል ፈጥሯል፡፡
የተጠናከረ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ መሠራቱ ሌላው ያስገኘው ጥቅም፤ ለ17 አመታት መሬቱ ደርቆ ሜዳ ሆኖ የነበረው የሃሮማያ ሐይቅ መልሶ ማገገም መቻሉ ነው፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ሥራው በየአመቱ እየተጠናከረ በመሆኑ፤ ከዚህ በኋላ የሃሮማያ ሐይቅ ይደርቃል የሚል ስጋት አይኖርም። ሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ በበላይነት ይዞ ክትትል እያደረገ የሚገኝ በመሆኑ ዘላቂነቱን የሚያረጋግጡ በምርምርና ጥናት የታገዘ ተግባራት በዩኒቨርሲቲው በኩል እየተሠራ ይገኛል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ሥራው ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ ተራራማ አካባቢዎችም በደን ተሸፍነዋል። የአካባቢው የደን ሽፋን ከነበረበት በ14 ነጥብ 5 በመቶ ጨምሯል። ይህ ሁሉ ውጤት የተመዘገበው በምሥራቅ ሐረርጌ አርሶአደር፣ አርብቶአደር፣ እንዲሁም የልማት ሠራተኞችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ያደረጉት የጋራ ጥረት ነው፡፡ መንግሥት ለተፋሰስ ልማት የሰጠው ትኩረትም ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን፡- የበጋ ቆላ የመስኖ ልማት በቂ የውሃ አቅርቦት እንደሚያስፈልገው ይታወቃል። ከዚህ አንጻር ልማቱን ለማረጋገጥ በአካባቢው ያለው የውሃ ሀብት ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ አያሌው፡– በምሥራቅ ሐረርጌ ውስጥ የተለያዩ የውሃ ሀብቶች ያሉ ሲሆን፣ ከከርሰ ምድርና ከወንዞች የሚገኙ ናቸው፡፡ በቂ የውሃ ሀብት አካባቢው ላይ እንዳለም በተለያየ ጊዜ በተደረጉ የጥናት ሥራዎች ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ አሁን ላይ ሥራዎች መሠራት ያለባቸው ያለውን ሀብት በአግባቡ በማስተዳደር ጥቅም ላይ በማዋል ነው። ለዚህም ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምሥራቅ ሐረርጌ ውስጥ ያለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና በማኅበራዊ ዘርፍ በተለይ በትምህርት እና ጤና ዙሪያ ስላለው ተደራሽነት ቢያብራሩልን?
አቶ አያሌው፡– ምሥራቅ ሐረርጌ ውስጥ ሰፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አለ፡፡ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅሱትም በአካባቢው ላይ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ናቸው፡፡ በአካባቢው ላይ እየኖረ ያለው አንድ የሆነ የተጋመደ ማኅበረሰብ ነው። አካባቢያቸውን ለመለወጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉት እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡
በልማት፣ በንግድና በተለያየ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን፤ የዜግነት አገልግሎት በመሥጠትም ለውጥ ለማምጣት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ከ2012 ዓ.ም እስከ 2016 ግማሽ አመት ድረስ በተሰጠው የዜግነት አገልግሎት ወደ 53 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሥራ ተሠርቷል፡፡
በዚህ የዜግነት አገልግሎት 1ሺህ 533 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ ለአቅመ ደካሞችም 11ሺህ 972 ቤቶች ተሠርተዋል፡፡ እነዚህ የልማት ሥራዎች ዘርና ኃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ በአካባቢው ለሚኖር ማኅበረሰብ የተሠራ ሥራ ነው፡፡ ተጠቃሚውም ሆነ በልማቱ የተሳተፈው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎ በተለያየ መንገድ ይገለጻል፡፡
ለታላቁ የኢትዮያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ቦንድ በመግዛት በተሠራው ሥራም አበረታች ውጤት ታይቷል፡፡ በያዝነው በጀት አመት ብቻ በ53ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ ተከናውኗል፡፡ ለሀገር መከላከያ ሰራዊትም ከሕዘቡ ወደ 42ሚሊዮን ብር ተሰብስቦ ድጋፍ ተደርጓል። በአጠቃላይ በአካባቢና በሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ አስተዋጽኦ ያላቸው ሥራዎች ተሠርተዋል ማለት ይቻላል፡፡ በተለያየ መንገድ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ሲታይ፤ የዞኑ ሕዝብ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የቆመ ማኅበረሰብ ነው ማለት ይቻላል፡፡
የጤና እና የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በተሠራው ሥራም በተለይም ኅብረተሰቡ የጤና መድን ፈንድ ተጠቃሚ እንዲሆን ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ የጤና አገልግሎት መስጫዎችን በመገንባት፣ ያሉትንም በማጠናከር፣ ተጠቃሚ ለመሆን የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ሆስፒታሎችና የጤና ኬላዎች ተናብበው የሚሠሩበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍም አካባቢው ላይ ሊያሠሩ የሚችሉ ምቹ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑና መዳረሻዎቹንም ቢገልጹልን?
አቶ አያሌው፡– በዞኑ በትላልቅ ደረጃ ሊጠቀሱ የሚችሉ ሦስት የቱሪዝም መዳረሻዎች አሉ፡፡ አንዱ የባቢሌ ዝሆን ሲሆን፣ ሁለተኛው ጋራቁንዱዶ፣ ሦስተኛ ሁልቃ የሚባል ዋሻ ነው፡፡ ከእነዚህ ሦስቱ በተለይም የዱር ፈረስ በሚገኝበት በጋራቁንዱዶ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። ፈረሱ የሚገኘው ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ጃርሶና ጉሩሱም ወረዳ መካከል ነው፡፡ ከሦስት አመት በፊት የነበሩት ዘጠኝ ፈረሶች ብቻ ናቸው፡፡ አሁን ላይ ቁጥራቸው ወደ 33 ከፍ ብሏል፡፡
የዱር ፈረሶቹ የሚገኝበት ስፍራ ወደ ኢኮ ቱሪዝም እንዲቀየር፣ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት እውቅና ተሰጥቶታል፡፡ በመሆኑም ሰፊ የሥራ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ የባቢሌ ዝሆኖችም ብዛታቸው ከ300 በላይ ሆኗል፡፡ እነዚህ ሀብቶች የቱሪዝም መስህብ ሆነው የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲያስገኙ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በምሥራቅ ሐረርጌ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚያስችል ምን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል? ከዚህ ቀደም በአካባቢው በኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ካሉም ቢገልጹልን?
አቶ አያሌው፡– በአካባቢው ላይ ኢንቨስተሮችን ሊስቡ የሚችሉ ሀብቶች ይገኛሉ። ለኢንቨስትመንት የሚሆኑ በተለይም በግብርና ላይ ለመሰማራት ለሚፈልግ ሰፋፊ የእርሻ መሬት አለ፡፡ በምድር ውስጥ ፀጋም በማድን ላይ መሰማራት የሚችሉበት ዕድል አለ፡፡ ኢንቨስተሩ በአካባቢው ላይ ለመሰማራት ቢፈልግ በጥሩ ሁኔታ ለመቀበል ፍላጎት መኖሩን ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡
በዞኑ የሚኖረው ማኅበረሰብ አካባቢው ላይ ልማት ለማከናወን ፍላጎት ያለውን ለመቀበል ዝግጁ ነው፡፡ ኢንቨስተሩ ፍጹም ሰላምና የተረጋጋ አካባቢ እንደሚፈልግም ይታወቃል፡፡ በዚህ በኩልም በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም ስላለ ስጋት እንዳይገባችሁ ስል መልዕክቴን አቀርባለሁ። በዞኑ ቀደም ብለው በተለያየ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች አሉ፡፡ አብዛኞቹም የተሰማሩት በግብርና ሥራ ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ምን ያህል ሥራዎች ተከናውነዋል?
አቶ አያሌው፡- በዞኑ በተለያየ የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ፣ የትምህርት ዕድልም ያላገኙ ወጣቶች አሉ፡፡ እንዲህ በተለያየ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወጣቶች እንደየችሎታቸው የሥራ ዕድል ለመፍጠር በዞኑ በኩል የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል። በተለይም ላለፉት ሦስት አመታት በልዩ ትኩረት ተሠርቷል፡፡
ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥረው የግብርናው ዘርፍ በመሆኑ በግብርና ከፍተኛ ቁጥር ላለው ወጣት የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ በማር ልማት፣ በከብት ማድለብና በሌሎችም የግብርና ሥራዎች ላይ ተሰማርተው እያደረጉት ባለው እንቅስቃሴ ብዙዎች ውጤታማ መሆን ችለዋል። የአካባቢው የኢኮኖሚ ምንጭ ቡና፣ ጫትና ሌሎችም የግብርና ውጤቶች በመሆናቸው በእነዚህ ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡
በአሁኑ ጊዜም ወጣቱ በበጋ ቆላ መስኖ ልማት በስፋት ተሰማርቶ እያለማ ይገኛል። አንዳንዶችም ያለሙትን ስንዴ ለገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ለተለያየ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡ ሌላው የሥራ ዕድል ደግሞ የግንባታው ዘርፍ ነው፡፡ በሌሎችም የሥራ ዘርፎች እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡
አሁን ላይ የአካባቢው ወጣት ሥነልቦናም ሆነ የአስተሳሰብ ሁኔታ ተቀይሯል፡፡ ወይም እየተሻሻለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሰው ጠባቂ ወይንም የቅጥር ሥራ ፈላጊ ከመሆን ይልቅ የራስን ሥራ ፈጥሮ የተሻለ ገቢ አግኝቶ ለራስም ለሀገርም ጥቅም የሚያስገኝ ሥራ መሥራት የሚለው ፍላጎት በወጣቱ በኩል እየተፈጠረ ነው፡፡ ይህን ለማለት የሚያስችለው አሁን ወጣቱ እያቀረበ ካለው ጥያቄ በመነሳት ነው፡፡ አሁን ወጣቱ እየጠየቀን ያለው በተፋሰስ ልማት ሥራ የለማ ተራራ እንድንሰጠው እንጂ ቅጥር አይደለም። ይሄ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ወጣቶች የበለጠ እንዲበረታቱ ለማድረግ ከተከናወኑት ተግባራት መካከልም ኑሯቸውን በተለያዩ የውጭ ሀገራት ያደረጉ የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ተወላጆች በገንዘባቸው ያደረጉት ድጋፍ ፤ የዞኑና የወረዳው መዋቅር ደግሞ ለሥራ የሚሆን የመሬት አቅርቦትን ምቹ ማድረግ፣ እንዲሁም የመሥሪያ ሼዶችን ሠርቶ ማቅረብ ይጠቀሳሉ፡፡
በዚህ መልኩ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ሥራዎች ቢሠሩም ሁሉንም ወጣት ተደራሽ አድርገናል፣ ችግሮችም ተቀርፈዋል ብለን አፋችንን ሞልተን ለመናገር አንደፍርም። የበለጠ መሥራት ይጠበቅብናል። ወጣቱ በትምህርት ላይ ካልሆነ ወይንም ሥራ ካልሠራ ወዳልተፈለገ ነገር ውስጥ እንደሚገባ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ወጣቱ ወደ መጥፎ ድርጊት እንዳያመራ መታደግ ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፡-በምሥራቅ ሐረርጌ ያለውን ተጨባጭ የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ ጋር አያይዘው ምን ይላሉ?
አቶ አያሌው፡- በልማቱ እንደተደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ የአካባቢ ፀጥታን በመጠበቅ ረገድም ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ በሰላም በፀጥታ ዙሪያ ላረጋግጥ የምፈልገው በምሥራቅ ሐረርጌ የሚገኙ 583 ቀበሌዎችና 23 ወረዳዎች ውስጥ ነዋሪው ቀርቶ ነዋሪ ያልሆነው ሁሉ ያለስጋት ሊንቀሳቀስ ይችላል። እንደፈለገውም እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ነዋሪው የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅና የፀጥታ መደፍረስና ስጋት እንዳይኖር ቀድሞ የመከላከል ሥራ በነዋሪው በኩል ሌትከቀን እየተሠራ ይገኛል፡፡
ማኅበረሰቡ በፀጥታ ዙሪያ እየሠራ ያለው ጠብቀኝ፤ እጠብቅሀለሁ የሚል መርህ ይዞ ነው። እንቅስቃሴ እየተደረገ ያለው ሁሉንም ኅብረተሰብ ባካተተ መልኩ በጋራ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የፀጥታ ኃይሎችን በመያዝ ነው፡፡
የዞኑ ነዋሪ እጅና ጓንት ሆኖ ለአካባቢው ደህንነት እየሠራ ያለው ‹‹ይሄ መንግሥት የእኔ መንግሥት ነው፡፡ በራሴ ድምጽ የመረጥኩት መንግሥት ነው፡፡ እየተሠራ ያለው የልማት ሥራም የእኔ ነው፡፡›› እያለ ነው፡፡ ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን 23 ወረዳዎችና 583 ቀበሌዎች ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ ሁሉ አካባቢዎች የሚኖሩትም ሆኑ በአካባቢዎቹ ለተለያየ ምክንያት የሚንቀሳቀሱ እና ገብተው የሚወጡ ሰዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ በመሆኑ ምንም ዓይነት ሥጋት የለም፡፡ በዚህ በኩል እየተሠራ ያለው ሥራ እንደሀገርም ቢሆን ለሌሎች አካባቢዎችም ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ነው። እንዲህ ያለው የተሳካ ሥራ ያለ ማኅበረሰብ ተሳትፎ የሚመጣ ባለመሆኑ አሁንም ምስጋናውን መውሰድ ያለበት የአካባቢው ነዋሪ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት ?
አቶ አያሌው፡- የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪ አንተ ማነህ ሳይል ሰው፣ ሰው በመሆኑ ብቻ በፍቅር፣ በመከባበርና በመረዳዳት አብሮ የሚኖር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንደአዲስ የምንነግረው አይደለም። አሁንም ቢሆን ሀገራችን በገጠማት የውስጥ አለመረጋጋትና ግጭት ምክንያት በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች እያጋጠመ ያለው አለመረጋጋት፣ የሰላም እጦትና ስጋት በአካባቢው በተመሳሳይ እንዳይፈጠር በሰላም ዙሪያ አንድነቱን አጠናክሮ እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
በልማቱ በኩል አጠናክሮ በመቀጠል በተለይም የተጀመረውን የበጋ ቆላ መስኖ ስንዴ ልማት በተሻለ ሁኔታ በማምረት ከዚህ ቀደም ከሌሎች ይጠብቅ የነበረውን እርዳታ እንደሚያስቀርም እምነቴ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እናመሰግናለን፡፡
አቶ አያሌው፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም