በፍትሐዊነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የተቃኘው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ውጤታማ ጉዞ ተጠናክሮ ይቀጥል!

ኢትዮጵያ የቀደምትነቷ አንድ ማሳያ ከሚሆኗት ጉዳዮች መካከል አንዱ የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ተግባሯ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ጉዞ ጅማሮው ከንግሥተ ሳባ የእሥራኤል ጉዞ ታሪክ ጋር የተቆራኘ ስለመሆኑም የተለያዩ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ይሄ ማለት ዛሬ ላይ ኃያል፣ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲውም ፊታውራሪ ነን የሚሉ አንዳንድ ሀገራት እንኳን እንደ ሀገር ከመፈጠራቸው በፊት ማለት ነው፡፡

ይሄ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ጉዞዋ ታዲያ እንደየዘመኑ እና እንደ ሀገሪቱ የሥርዓተ መንግሥታት እሳቤ በልኩ እየተመራ እና በውጤት እየታገዘ ዘልቋል፡፡ ይሄ ጉዞም በአንድ በኩል ኢትዮጵያ በተናጠል ከሀገራት ጋር ተባብራ የምትሠራበትን አቅም ሲሰጣት፤ በሌላ በኩል ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ከተናጠል ይልቅ በባለ ብዙ ወገን ትብብር ታግዛ መሥራት የሚያስችላትን ዕድል ሰጥቷታል፡፡

ለዚህ ደግሞ ከኢጋድ እስከ ተመድ ያሉ የባለ ብዙ የትብብር መድረክን የሚሰጡ ተቋማት እንዲፈጠሩ በማድረግ ሂደት ውስጥ የላቀ አበርክቶን ያደረገች ሲሆን፤ በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት የሚከወኑ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊም ሆኑ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ፍትሐዊነትን የተላበሱ፤ የጋራ ተጠቃሚነትን ያሰፈኑ እንዲሆኑም የበኩሏን ተወጥታለች። በተለይ ገለልተኛ የሆነው የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ አካሄዷ ከነባሮቹ ባለፈ እንደነ ብሪክስ ካሉ አዳዲስና ሚዛን አስጠባቂ ኃይሎች ጋር በትብብር የምትሠራበትን የተፈላጊነት ገጽ ፈጥሮላታል፡፡

በባለብዙ መድረክነቱም፣ በሁለትዮሽ የትብብር መድረክም ሆኖ ከሚገለጸው የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ አውድ ደግሞ፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካውያን ጋር የሚኖራት አሕጉራዊ፣ ቀጣናዊ እና ተናጠላዊ (ከሀገራት ጋር በተናጥል የምታደርገው) የትብብር ግንኙነቷ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ከአፍሪካውያን ጋር በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ብሎም ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራትን፤ በሌላ በኩል አፍሪካውያን በአንድ ተደምረው በሚፈጥሩት ኃይል ዓለምአቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውን ማሳደግን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች፡፡

ለምሳሌ፣ አፍሪካውያን አጀንዳ 2063ትን ተልመው እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ሰላምን፣ ልማትንና ሰብዓዊ ልማትን፣ በጥቅሉ ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን የማድረግ ዓላማን የያዘ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ይሄንን ታሳቢ ያደረጉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች፡፡ ለምሳሌ፣ አፍሪካን በሁሉም መልክ በመሠረተ ልማት የማስተሳሰር ተግባሯ አንዱ ሲሆን፤ ይሄ ትስስርም የአህጉሪቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን እውን በሚያደርግ መልኩ እየተፈጸመ ያለ ነው፡፡

የዚህ ተግባሯ ማሳያ ሆነው ከሚገለጹት መካከል፣ የትራንስፖርት (የመንገድ፣ የባቡር፣ የአየርና ሌሎችም)፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመጠጥ ውሃና መሰል ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው መሠረተ ልማቶች ተጠቃሽ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው እንደተናገሩት ታዲያ፣ ይሄ ከጎረቤት ሀገራት ጀምሮ ቀጣናዊም ሆነ አህጉራዊ ትስስር፣ ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጠው ጉዞዋ ቀጥሎ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ስምምነት ከታንዛኒያም ጋር በቅርቡ ይፈረማል። ይሄ ደግሞ ቀጣይ ወደ ደቡቡ አፍሪካ ቀጣና ለመራመድ ዕድል ይሰጣል። በዚህ መልኩም የአፍሪካውያንን ልማትና የጋራ ጥቅም ለማሳደግ ያግዛል።

ከዚህ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ አፍሪካውያንም ሆኑ ሌሎች በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት አህጉር ዘለልና ዓለምአቀፋዊ በሆነው የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያቸው ፍትሐዊነት የሰፈነበት፣ የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን የማይተካ ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች፡፡ በዚህም የራሷን የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት መሥመር ከወገንተኝነት የጸዳ ሆኖ እንዲጓዝ ከማድረጓ ባሻገር፤ አፍሪካ ዓለምአቀፍ ተደማጭነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ እንዲያድግ፤ ሌሎች አዳጊ ሀገራትም እንደ ሀገር የራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ተከብሮላቸው እንዲጓዙ ከፍ ያለ ሥራን ስታከናውን ቆይታለች፤ እያከናወነችም ትገኛለች፡፡

ይሄ ገለልተኛ ሆኖ የመሥራት አቋሟ እና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተው የዲፕሎማሲ መሥመሯ ታዲያ፤ ለራሷ ዘርፈ ብዙ ጥቅምን፤ ለአፍሪካም መልካም ዕድልን፤ ለታዳጊ ሀገራትም በጎ እይታን ፈጥሯል፡፡ ምክንያቱም፣ ይሄ አካሄዷ ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ችግሯቿን የምትሻገርበት የዲፕሎማሲ አቅም ሲሰጣት፤ ለአፍሪካ እንደ አህጉር ሊጠበቅላት የሚገባው ጥቅም እንዲከበር የሚያስችል መንገድ አስጀምሯል፡፡ አዳጊ ሀገራትም የራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት የሚከበርበትን የዲፕሎማሲ መንገድ እንዲመለከቱ አስችሏቸዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር ያላት የሁለትዮሽ ትብብር ከዕለት ዕለት ከፍ እያለ እና በላቀ የወዳጅነትና የተባባሪነት መንፈስ እንዲቃኝ ሆኗል፡፡ ከኢጋድ እስከ ተመድ፤ ከአፍሪካ ልማት ባንክ እስከ የዓለም ባንክ፤ ከዓለም የምግብ ድርጅት እስከ የዓለም የገንዘብ ድርጅት፣… ሁሉም ኢፍትሐዊነት እየታገሉና እየቀረፉ ከሁሉም ለሁሉም የሚሆኑበትን መንገድ እንዲመለከቱ ለማድረግ እየሠራች ትገኛለች፡፡ የዚህ ሥራዋን ፍሬም ማጣጣም ጀምራለች፡፡

እነዚህና መሰል በትብብር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተቃኙ፣ የተቋማት አሠራር ፍትሐዊነትን ለመፍጠር የሚደረጉ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ፍሬዎች ከትናንት የቀጠሉ፤ ዛሬም በውጤት የታጀቡ ሆነው ተገልጠዋል። በመሆኑም ይሄ የትናንት ወረት፤ የዛሬ ውጤት የሆነው ጉዞ፤ ለነገው መንገድ ወረቱንም ውጤቱንም አቅም አድርጎ ሊጠቀም፤ ለውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲው የፍትሐዊነትና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ መጠናከር መትጋት ከሁሉም ይጠበቃል!

አዲስ ዘመን የካቲት 4 / 2016

 

Recommended For You