በውንሽፍሩና በዝናቡ መሀል አልፎ አልፎ ንፋስ ያፏጫል፡፡ መጣሁ ቀረሁ ሲል የነበረው ዝናብ በሰማዩ አዥጎድጓጅ የመብረቅ ድምፅ እየታጀበ ማስገምገሙን ቀጥሏል፡፡ ሰዓቱ ከትምህርት ቤት፤ ከሥራ መውጪያ ወደቤት መመለሻም በመሆኑ ከዝናቡና ከጎርፉ ለመሸሽ የሚደረገው የሕዝቡ ሩጫ የክረምቱን መግባት ያበስራል።
እነሆ ክረምቱ ገባ፡፡ እንግዲህ ዝናቡን ውሽንፍሩን የመብረቁን ጩኸት የወንዞችን ሙላትና ግሳት እያዩ መክረም ነው፡፡ የክረምቱ ዝናብ አዛዥ የለውም፡፡ አያ እንደልቡ፡፡ ያሻውን ያፈርሳል፡፡ ያሻውን ይንዳል። በል ሲለውም ይደረምሳል፡፡ ክረምቱ ጠፍተው ተደብቀው የነበሩ እፅዋትንም ያሳድጋል። ክረምት ገብቶ ዝናብ ከነጠፈ ችግር ይገባል፡፡ ውሃ የለም፤ሕይወት የለም፡፡ ክረምት ለዘለዓለም ይኑር እንበል እንዴ?
አባ ሙላት ክረምት፤አባ አደፍርስ ክረምት ባሻው አዳሪ ባሻው ፈሳሽና ተንጎማላይ ነው። ሰማዩ ጨለማ መስሎ ሲዳምን በሙሉ ግርማ ሞገስ በመብረቅ እየታገዘ ሲያስገመግም ሁሉም በያለበት ይመሽጋል።ክረምቱ ሲወድቅ (ሲገባ) ትርው ዝርው የለም ይሉ ነበር በጎጆ ቤታቸው ውስጥ የወይራ ፍልጦችን ማግደው የተጋጋመን እሳት እየሞቁ ዙሪያቸውን የመንደሩን ውሪ ሰብስበው እየተጫወቱ ይሞቁ የነበሩት እማማ ዲንጎ፡፡
እማማ ዲንጎ ባላቸው በኢጣሊያን ጦርነት ከመዝመታቸው በፊት ስድስት ልጆች ነበራቸው። የደረሱት ጎረምሶች ከአባታቸው ጋር ዘምተው ሁሉም ሳይመለሱ በዚያው ቀርተዋል፡፡ የተቀሩት ሴቶች ደግሞ አግብተው ወልደው ይኖሩ ነበር። ዛሬ ማንም አጠገባቸው የለም፡፡ ልጆቻቸው የመንደሩ ልጆች ናቸው፡፡ ይላላኳቸዋል፡፡ የሚረዷቸውና ከእሳቸው ጋር የሚኖሩም አሉ፡፡ ታዲያ አንዳንዴ በሃሳብ ይቆዝማሉ፡፡
‹‹ምነው እማማ›› ሲሉ ልጆቹ እሳቸው ደግሞ ‹‹ምንም ልጆቼ ምንም›› ይሉና ያንጎራጉራሉ። ከቤታቸው የአበሻ አረቄ አይጠፋም፡፡ ከሌለም ያስገዛሉ። ይሄ እኮ ዋናው የብርድ መድሀኒት ነው ይላሉ። ስለሚያሞቃቸው ይሆናል፡፡ እማማ ዲንጎ ጨዋታና ቀልድ አዋቂ በመሆናቸው በመንደሩ ነዋሪ በትንሹም በትልቁም የተወደዱ፤በሰፈሩ የተከበሩ አንቱ የተባሉ አዛውንት ናቸው፡፡
የባሕል ሕክምና አዋቂ በመሆናቸው የታመመ ሰው ሁሉ ሀገር አቋርጦ ቦታቸውን ጠይቆ እሳቸው ጋር ይመጣል፡፡ በባሕላዊው ኬሚስትሪ እሳቸው የሚያውቁትን ሥራ ሥሩን ቅጠላ ቅጠሉን ቀጣጥፈው ቀምመው ለታመመው ይሰጡታል፡፡ የሩቅ ሀገር ሰው ከሆነ ለሕክምና የመጣው እዚያው ጎጆ ቤታቸው መደብ ላይ ተኝቶ ቤት ያፈራውን መግበውት ድኖ ይሄዳል፡፡
ዙሪያ ገባውን በቅርብና በሩቅ ያለው ሕዝብ ‹‹እማማ ዲንጎ እጃቸው መድሀኒት ነው›› ብሎ ስለሚያምን የታመመ ሁሉ ወደሳቸው መሮጡ አዲስ አይደለም፡፡ በኢጣሊያ ወረራ ጊዜ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የሀኪም ስም ‹ዶክቶራ› ነው የሚባለው ብለው ለሕዝቡ ወሬ ስለነዙ እማማ ዲንጎን ዶክቶራ ብለው የሚጠሯቸውም ነበሩ፡፡
‹‹ምነው እኔ በፈረንጅኛ ጥሩኝ መቼ አልኩ›› ብለው ይቆጣሉ፡፡ ጥሎባቸው ፈረንጅ የሚባል አይወዱም፡፡ ምናልባት በጦርነቱ ለሀገራቸው ክብር ሲዋደቁ የሞቱትን ልጆቻቸውንና ባላቸውን እያስታወሱ ይሆናል፡፡ አይፈረድባቸውም፡፡ ‹‹ፈረንጆች ሰላቢዎች፤ መተተኞች ናቸው›› ይላሉ እማማ ዲንጎ፡፡ ‹አረ ተው እማማ ዲንጎ አይባልም›› ቢሏቸውም በጄ አይሉም፡፡
‹‹ሰላቢ፣ መተተኛ ፈረንጅ ነው›› ሲሉ አባ ሻቃ የተባሉ አዛውንት ለጠቅ አድርገው ‹‹አይ ዲንጎ፤ አሁን ከእኛ ደብተራዎች በላይ መተተኛ አለ ብለው ነው›› ቢሏቸው ‹‹እሱማ እውነት ነው የእኛንማ ማን ያህል መተተኛ ደብተራ ሁላ›› በማለታቸውም ይጠቀሳሉ። ፈረንጅ ደግሞ ምን ያውቃል ከእኛው እውቀትና ጥበብ እየወሰዱ አይደለም እንዴ የሚኩራሩት ይላሉ።
የውጭው ስልጣኔ እምብዛም ባልታወቀበት ዘመን በራሳችን የቀደመ ስልጣኔ ኩሩዎች ነበሩ አባቶች፤ እናቶችና አያቶቻችን።እነ እማማ ዲንጎ፡፡ እንደዚህ እንደ አሁኑ ዘመን ከማንነታቸው ተፋተው ነጭ አምላኪ አልነበሩም፡፡ የእኛን የባሕል መድሀኒት ጠይቆ እየወሰደ አይደለም እንዴ ፈረንጅ በሌብነት የከበረው ብለው ይቆጣሉ። እማማ ዲንጎ አንዳንዴ የበዛ ነጭ አምላኪ ሰው ሲገጥማቸው፡፡ እናንተ ልጆች እስቲ በቅጡ ሁኑ፡፡ ወደ ቀልባችሁ ተመለሱ፡፡
ኢትዮጵያ ብዙ ሊቃውንት የእውቀት አውራ የሆኑ አባቶች የነበሯት ያሏት ሀገር ነች፡፡ ጠጋ ብላችሁ አክብራችሁ ብትይዟቸው ብትጠይቋቸው ብዙ መላ ታገኙ እውቀትም ትጨብጡ ነበር። ይላሉ እማማ ዲንጎ፡፡ ሰሚ ቢገኝ፡፡ የራሳችሁን ባህል እውቀት ጠብቃችሁ ብትይዙት ትከበሩበት ነበር፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል፡፡ ‹‹መቼ ሰሚ አለና›› በማለት ከልባቸው ይጸጸታሉ፡፡
እንደው ደርሶ የራስን ባሕልና እውቀት እያጣጣሉ፤ ኋላ ቀር ነው እያሉ ፤የነበረውን እያጠፉ፤ ታሪክና ባህል እንደሌለው ነጭ አምላኪ መሆን ያሳፍራል እናንተ ልጆች ይላሉ ድምፃቸውን ዘለግ አድርገው፡፡ እማማ ዲንጎ በትንሹ እስቲ ይሄን እውቀት አስተምሩኝ ግለጡልኝ የሚል ልጅ እንኳን የለም፡፡ ይዤው አልሄድ፡፡
ይልቅስ ለእናንተ ይበጃችሁ ይላሉ ዙሪያቸውን ወደከበቧቸው ልጆች ዞር ዞር እያሉ፡፡ እንግዲህ ክረምቱ ተግ አድርጎ ያበቀለውን ለሀገር ባሕል መድሀኒት የሚሆኑ የተለያዩ እፅዋት በከተማ ዳርቻና በገጠር በየገዳሙ በየበረሀው ጭምር እየዞሩ ለእነ እማማ ዲንጎ ፈልፍለው የሚያመጡ አዋቂዎች በብዛት ነበሩ፡፡ ዛሬ የሉም፡፡
‹‹የሀገራችን ሰው መቼም ሲያጣጥል አያድርስ ነውና ቅጠል በጣሽ፤ስር ማሽ ይላቸዋል። የመድሀኒቱን ቅጠል ለይቶ ለመቁረጥ ስሩንም ምሶ ለማውጣት እኮ ባሕላዊ እውቀት ይጠይቃል። አለበለዚያ መድሀኒቱ ከየት ይገኛል›› ብለው ይገረማሉ እማማ ዲንጎ፡፡ እነዛ ሰዎች አብዛኞቹ ወደ ሰማይ ቤት ተጉዘዋል፡፡ ‹‹ሆሆይ— እንዴ በእግራቸው የሚተካ ልጅ እንኳን ይጥፋ›› ብለው ከመገረም አልፈው ይተክዛሉ፡፡
‹‹ለአወቀውማ ይሄ እውቀት የሀገር ሀብት ነበር፡፡ የሀገር መድሀኒት፡፡ ፈረንጁም እኮ ዘመናዊ መድሀኒት የሚሠራው በሀገሩ ከኖረው የቆየ የባሕል ሕክምና እውቀት ተነስቶ ነው፡፡ ‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል››› አሉ አባ ይልቃል፡ ፡ ደገሙና እውነት ብለዋል አሉ ዲንጎ፡፡ እሳቸው ነበሩ በየገዳሙ በየታቦቱ፤በየገበሬው መንደር በረሀ ጭምር ሳይቀር እየዞሩ የማይገኙ የቅጠላ ቅጠል መድሀኒቶችን ስለሚያውቋቸው ሰብስበው የሚያመጡልኝ፡፡ ዛሬማ ምን አለ ብላችሁ ነው፡፡
የአባቶቻችሁ እውቀት ከጣሪያ በላይ የዘለለ ነበር፡፡ የትኛው ልጅ በእግራቸው ተተክቶ ያግኘው የማይሆነውን መመኘት ብለው ተከዙ፡፡ በጥንት ጊዜ ከተማ የሚባሉትም ሆነ የገጠር መንደሮች ሁሉም በሳር ክዳን የተሠሩ ጎጆ ቤቶች ነበሩ፡፡ በዚያ ዘመን ክሊኒክ፣ ሀኪም ቤት የሚባል አልነበረም፡፡ ሁሉን ሸፍነው ሕዝቡን ያክሙ ያድኑ የነበሩት የእራሳችን የባህል ሕክምና አዋቂዎች ነበሩ፡፡
እነ እማማ ዲንጎ። ስንቱ ጀግና፤ ስንቱ አድጎ ለትልቅ ደራጃ የበቃ ጎበዝና ቆነጃጅት የተወለደው ሀኪም ቤት አልነበረም፡፡ በባሕላዊ ሐኪሞቻችን እንጂ። ወድቆ የተሰበረው ስሩ የዞረው ሮጦ መሄጃው እነሱው ጋ ነበር፤አሽተው ልክ ያስገቡለታል። እውቅ ወጌሻም አዋላጅም ነበሩ፡፡ በእጃቸው ለደባበሱበትም ሆነ ላከሙበት የሚያስከፍሉት እንደዛሬው ሙላ የሚያላቅቅ ዓይን ያወጣ ገፈፋና ዘረፋ የሞላበት አልነበረም፡፡ በልኩ ነበር፡፡ የዛሬው ዘመን ሲታይ የጥንቶቹን ያስታውሳል። ኸረ እናንተ ብሩካን ሆይ ወደስተየት አላችሁ ብሎ ትውልዱ ቢናፍቃቸው ነውርም የለው፡፡
የካርድ ማውጫ፤ ሀኪምጋ መቅረቢያ፤ ለምንትሴ ለቅብጥርሴ፤ ለምርመራ ወዘተ በሚባል ስመ ብዙ ገቢ ማሰባሰቢያ የሕዝቡን ወገብና አንጀት የሚበጥስ የሂሳብ ክፍያ አልነበረም፡፡ ድሀ ሆይ አትታመም፡፡ አምላክህ ይጠብቅህ፤ አምላክህ ይቁምልህ፤ ከማለት በዘለለ በዚህ ዘመን ሰው ታሞ በሕክምና ይድናል ለማለት ድፍረት አነሰን፡፡ አነሰን እንጂ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2011
ወንድወሰን መኮንን