በቅርሶች ጥገና – የመንግሥት ቁርጠኝነት

ባለፈው ሳምንት በእለተ ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰጧቸው ማብራሪያዎች መካከልም የቱሪዝም ዘርፍና የቅርስ ጥገና ሂደት ይገኙበታል።

በማብራሪያው እንደተመለከተው፤ መንግሥት በቱሪዝም፣ በቅርስ ጥገና እና ልማት ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱን ተከትሎ የተለያዩ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል። በቱሪዝም ዘርፍ በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ በተሠራ ልማት አዳዲስ የገቢ ምንጭ መፍጠርና የሥራ እድል መፍጠርም ተችሏል። በተለይ በአዲስ አበባ በቤተ-መንግሥት እድሳት፣ በአንድነት ፓርክና በሌሎች የመዳረሻ ልማቶች አመርቂ ውጤቶች ታይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራ ክልል ታሪክ፣ ባህል፣ የሚያምር መልክዓ ምድር እንዳለው አመልክተው፣ ለቱሪስቶች ምቹ መሆኑን ተናግረዋል። ያን ታሳቢ ተደርጎ በጎርጎራ እየተሰራ ያለውን ልማት ጠቅሰው፤ የመዳረሻ ልማት ሥራው እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ከተካሄዱ ሥራዎች ቀዳሚው መሆኑን ነው ያስታወቁት። የጎርጎራ ፕሮጀክትን የሚያህል የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ምናልባትም በአፍሪካም በዚያ ደረጃ በግዝፈት፣ በውበት፣ በጥራት የሚደርስበት ሪዞርት መኖሩን እንደሚጠራጠሩ ጭምር አስታውቀዋል። ኅብረተሰቡም ይህን መሰል የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ሥራ ስኬታማ እንዲሆን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ቱሪዝምን በሚመለከት ትኩረት ሰጥተው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ሌላው የቅርስ ጥገናን የተመለከተው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት በቱሪዝም ዘርፉ በጥገና እና እንክብካቤ ረገድ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ቅርሶችን በመለየት ቅድሚያ እየሰጠ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

‹‹የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር በመተባበር የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ማክሮንንም በስፍራው በአካል ይዘናቸው ሄደን የጥገና ሥራው ተጀምሯል›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። በሰላም እጦት ምክንያት ስራው ወጣ ገባ እያለ የሚከናወን ቢሆንም፣ በጥንቃቄና ትውልድን በሚያስመሰግን መልኩ ጥገናው እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል። ጥገናው ለሌሎች ተመሳሳይ ቅርሶች ጥገና ምርጥ ተሞክሮ የሚወሰድበትና በዚህ መንገድ ቢሰሩ ተጨማሪ የቱሪዝም ገቢና የሥራ እድል ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

የአጼ ፋሲል ቤተመንግሥት በጣም አስደናቂ ሥራ ነው ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይሁን እንጂ የቅርሱ አካል የሆነው ግማሽ አካሉ መፍረሱን ጠቁመዋል። የፈረሰውን ፋሲል ስናስጎበኝ የቆየነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ አግባብ አለመሆኑንና መታደስ እንዳለበት አስገንዝበዋል። በመደመር መጽሐፍ ፋሲልን መልሰን እናድስ ብለው እንደነበር ጠቅሰው፤ መጽሐፉ እስኪሸጥ ደግሞ እድሳቱ በሌላ ምንጭ ይጀመር ብለው በአካል ቦታው ድረስ ሄደው ሥራውን ለማስጀመር ሙከራ አድርገው እንደነበርም ያመለክታሉ። በተለያዩ አሉባልታዎችና ሴራዎች ሥራው እንዳይከናወን እንቅፋት መፈጠሩን ነው ለምክር ቤቱ ያብራሩት።

‹‹የዩኒቲ ፓርክ ከመታደሱ በፊት በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት በጣም ቆሻሻ ቦታ ነበር›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ታድሶ በርካታ መቶ ሚሊዮን ብሮችን አስገብቶ የታችኛውን ቤተመንግሥት እያደሰ እንደሚገኝ ይገልጻሉ። በአጼ ኃይለስላሴ የተሠራው ታችኛው ቤተ መንግሥትም በጣም ጥሩ ሥራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ክትትልና ጥገና ባለመኖሩ በከፍተኛ ሁኔታ የመፍረስ፤ የመዳከም አደጋ ውስጥ እንደነበርም ይገልጻሉ።

በአሁኑ ወቅት በታችኛው ቤተመንግሥት እድሳት ሦስት ሺ400 ሠራተኞች እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረው ፣ 13 ፕሮጀክት እንዳሉትም አስታውቀዋል። የእድሳቱ ሥራ በሚቀጥሉት ሁለት ሦስት ወራት እንደሚጠናቀቅ አስታውቀው፣ ቤተመንግስቱ ካለምንም ጥርጥር አዲስ አበባ ውስጥ እጅግ ውብ ከሆኑና ሊታዩ ከሚገባቸው ሥፍራዎች አንዱ እንደሚሆንም ይናገራሉ።

በአጼ ፋሲል ቤተመንግስት ላይ መንግሥታቸው ሊሠራው የነበረው ፕሮጀክትም ተመሳሳይ እንደነበር ለምክር ቤቱ አባላት አስታውቀዋል። የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ቤተመንግሥት እንዳደስነው፤ የአፄ ኃይለሥላሴን ቤተመንግስት በተመሳሳይ መልኩ እንዳደስነው፤ የአጼ ፋሲል ቤተመንግስትም ቢታደስ ተጨማሪ ገቢ እንደሚያስገኝ ውበቱን፣ ክብሩን፣ ታሪኩን ማስጠበቅ እንደሚቻል እምነታቸው መሆኑን ይገልጻሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ቱሪዝምን በሚመለከት ብዙ ሙከራዎች እየተደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በተለይ መዳረሻዎችን ማልማት ላይ ብዙ ስኬቶች ተገኝተዋል፤ ሰላሙ ላይ ካልተሰራ ግን የተሟላ ውጤት ሊመጣ እንደማይችል ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርስ እድሳት ላይ የሰጡትን ማብራሪያ አስመልክቶ ያነጋገርናቸው በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃና ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሀፍታሙ አብርሃ በበኩላቸው፤ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ወደር የሌላቸው ቅርሶች መገኛ ነች። ይሁንና አብዛኞቹ ቅርሶች በጉዳት ላይ ይገኛሉ። ብዙዎቹ ቅርሶች በማይተካ ደረጃ ሰፋፊ ጉዳቶች እየደረሰባቸው ስለመሆኑ በጥናት ተለይተዋል።

ብዙዎቹ ቅርሶች ጉዳት እየደረሰባቸው የሚገኙት ከጥገና እጦትና ከግንዛቤ እጥረት በመነጨ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይሁንና ባለስልጣኑ ባለው ውስን አቅም ቅርሶች እሴታቸውን ሳይለቁ እንዲጠበቁ ተንከባክቦ ለትውልድ የማስተላለፍ እንዲሁም ለሀገር ገፅታ ግንባታና ለቱሪዝም ተጨማሪ አቅም እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እንደሚከወን ያስረዳሉ።

ዶክተር ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ሲሰጡ እንዳነሱትም፤ ያላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት እድሳት ፕሮጀክት በእርሳቸው ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በተገኘ ድጋፍ እየተሠራ ነው የሚሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ የእድሳቱን ሥራም ባለስልጣኑ በኃላፊነት ይዞት እየተከታተለው እንደሚገኝ ያስረዳሉ። በዘለቄታዊነት በቅርሶቹ ላይ ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላትና ቅርሱን ተንከባክቦ ለማቆየትም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ያስረዳሉ።

የላሊበላ ቅርስ እየተጠገነ የሚገኘው በሁለት ደረጃ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ሀፍታሙ፤ የመጀመሪያው አስቸኳይ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን 24 ቦታዎችን በመለየት በጉዳታቸው ልክ ቅድሚያ በመስጠት ‹‹ላሊበላን በዘላቂነት›› በሚል በፈረንሳይ መንግሥት በተገኘ ድጋፍ አማካኝነት እየተሰራ ይገኛል›› ብለዋል።

በፕሮጀክቱ አመርቂ ውጤት ለማምጣት ቅርሱን ከጉዳት ለመታደግና ዘለቄታዊነቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲሻገር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የሚጠቅሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ በተለይ ቅርሱን ለጎብኚዎች ምቹ ማድረግ፣ ገቢን ማሳደግ ላይ ትኩረት በማድረግ ውጤታማ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ይናገራሉ።

በጎንደር የሚገኙ እንደ ጉዛራ፣ ፋሲለደስ፣ ሱሲኒዮስና ሌሎች ዓለም አቀፍ ቅርሶች የሚገኙባቸውን ደረጃ፣ የደረሰባቸውን ጉዳት፣ የችግሮቹን መንስኤና የሚያስፈልጋቸውን የጥገና አይነት ለመለየት በባለስልጣኑ ጥናት መደረጉን አቶ ሀፍታሙ ያመለክታሉ። ቅርሶቹ የሚገባቸውን ያህል ጥበቃና እንክብካቤ በጊዜው ያልተደረገላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሁሉም ቅርሶች በጉዳት ደረጃ ላይ እንደሚገኙና ስጋት ላይ እንደሆኑ ያስረዳሉ። በጥናቱ የጉዳት መጠናቸው ባይለይም በመሠረታዊነት ግን ችግሮች እንዳጋጠማቸው ያስረዳሉ።

እነዚህን ቅርሶች ለመጠበቅ፣ ለማከምና የነበራቸውን ይዘት፣ እሴትና ታሪካዊ ትርጉም ሳይለቁ ለማደስ የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጅቶና የሚያስፈልገው የበጀት መጠን ተለይቶ ነበር። በተጨማሪ ከምሁራን፣ ከመሪዎችና ከማህበረሰቡ ተወካዮች ጋር ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ወደ ተግባር ለመግባት እንደተሞከረ ይናገራሉ። የጉዛራ ቤተመንግስት እድሳትም የዚሁ አካል መሆኑን ያስረዳሉ።

ከጎንደር ታሪካዊ ቅርሶች ውስጥ ዋንኛ የሆነው የፋሲለደስ ቤተመንግስትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ፕሮጀክቶች ስር በመያዙ ምክንያት እሴቱንና ታሪካዊ ትርጉሙን ጠብቆ እንዲታደስ በማሰብ የተጠናውን ሙሉ ጥናት ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ማስረከቡን ያስረዳሉ።

መሪ ሥራ አስፈፃሚው እንደሚናገሩት፤ ቅርሶች ይዘታቸውን ሳይለቁ በማደስ ረገድ መልካም ውጤት እየተመዘገበ ነው። ይህ ሂደት በአዲስ አበባ በብሄራዊ ቤተመንግስት እንደታየ ገልጸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መሪነት የታደሱና እየታደሱ ያሉ ቅርሶች ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። አንድነት ፓርክና የታችኛው ቤተመንግስት እድሳቶችም በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ ያለፉ ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በፕሮጀክት ደረጃ ተይዘው እየታደሱ የሚገኙት ቅርሶች ነባር ይዘታቸውን፣ መገለጫቸውን እንዲሁም ዋና እሴታቸውን እንዳይለቁ ተደርገው የሚታደሱ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ሀፍታሙ፤ ሌላ ቅርጽ እንዲይዙ እንዲሁም ታሪካዊ ሀብትነታቸው እንዳይጓደል ተደርጎ እየታደሱ መሆናቸውን ይገልፃሉ። በሂደቱም መልካም ውጤት እየታየ መሆኑን ያስረዳሉ።

‹‹በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከሚመሩ የቅርስ እድሳት ፕሮጀክቶች ውጪ ባለስልጣኑ በመደበኛነት የቅርስ ጥገና እያከናወነ ነው›› የሚሉት አቶ ሐፍታሙ፤ በያዝነው በጀት ዓመት መሥሪያ ቤቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ወደ 20 የሚደርሱ ቅርሶችን ለመጠበቅ፣ ለመጠገንና ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ።

ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው የጉዛራ ቤተመንግስት መሆኑን ጠቅሰው፤ የዚህን ዓለም አቀፍ ቅርስ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል፤ በጀት ተይዞም ጥራቱን በጠበቀ መልኩ የፕሮጀክቱ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

‹‹በጎንደር አካባቢ ከሚገኙ ቅርሶች ከመደመር ትውልድ መጽሐፍ በሚገኝ ሽያጭ የፋሲል ቤተመንግስትን እድሳት ለማካሄድ የሚያስችሉ ጅምር ሥራዎች አሉ›› የሚሉት አቶ ሐፍታሙ፤ ባለስልጣኑ ግን ከእነዚህ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በራሱ እቅድ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ቅርሶች ለመጠገን እየሠራ እንደሆነ ይናገራሉ።

በዚህ ሂደት የሐረሪ ክልል ጥንታዊ መንደር የሆነው አበርከሌ ወደ ነበረበት ቁመና እንዲመለስ፤ ታሪኩ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሻገር እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ያመለክታሉ። በኦሮሚያ ክልል በአዲስ ዓለም አካባቢ ፖርቹጋል ድልድይና በሌሎች አካባቢዎችም የጥበቃና የጥገና ሥራዎች ባለስልጣኑ እየተደረጉ መሆናቸውን ነው ያብራሩት።

‹‹በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ቅርሶች ለመለየትና መልሶ ለመጠገን የዳሰሳ ጥናት አድርገናል›› ያሉት አቶ ሐፍታሙ፤ በትግራይም እንዲሁ የቅርስ አድን ሥራዎች ለመሥራት ውስን በጀት ተመድቦ መልካም ውጤቶች እየተመዘገበ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ርምጃው ሙሉ ለሙሉ ችግሩን ባይፈታም ቢያንስ ስጋት ላይ በማይጥላቸው ደረጃ ላይ እንዲገኙ የተወሰደ ቅድመ ጥንቃቄ ሥራ መሆኑንም ያነሳሉ። በጥቅሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመጠገን የሚያደርገው ሥራ ውስንነት ያለበት ቢሆንም በእቅድ በተያዙት የቅርስ ጥገና ሂደት መረዳት እንደተቻለ ጥሩ አፈፃፀም እየተመዘገበ ነው ብለዋል።

ቅርሶችን በመንግሥት በጀትና አቅም ብቻ መጠገን እንደማይቻል አስታውቀው፤ድጋፎችን በማፈላለግ፣ ማህበረሰቡን በማስተባበርና ልዩ ልዩ ዘዴዎችን በማመቻቸት የጥገናና እድሳት አድማሱን ለማስፋትና የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ባለስልጣኑ እየሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን  የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You