የዓድዋ ድል ለነፃነቱ ቀናኢ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በብዙ አቅም፣ እብሪት፣ ማን አለብኝነት እና ንቀት የመጣውን የጣሊያን ቅኝ ገዥ ኃይል በአደባባይ ድል በመንሳት፣ ለፍትሕ፣ ለነጻነት እና ለአልገዛም ባይነት ያለውን ቁርጠኝነት በመስዋዕትነት ገድል በአደባባይ ያጸናበት፣ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የነፃነት ፋና ወጊነቱን ያረጋገጠበት ነው።
ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ፤ ልዩነቶቻቸው ምንም ያህል ክፍተት ቢኖረው፤ በሀገር ጉዳይ የማይናወጥ አንድነት እንዳላቸው፤ ለሀገር በክብር መሞት፤ በባርነት ከሚኖር ሕይወት አንድ ሺ አንድ ጊዜ እንደሚሻል፤ በአደባባይ ውድ ሕይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ በደማቸው የጻፉት የጋራ ታሪካቸው ነው ።
ድሉ የመላው ሕዝባችን የትናንት የጋራ መስዋዕት ታሪክ ብቻ ሳይሆን፤ ከዚያም ባለፈ ለዛሬ የጋራ ትርክታቸው ዋነኛ መሠረት ነው። የይቻላል መንፈስን በማነቃቃት ትውልዶች በየዘመኑ ለማየት በብዙ ሲጓጉላት ለኖሩት የበለጸገች ኢትዮጵያ መፈጠር ትልቅ የሥነ ልቦና አቅም እንደሚሆንም ይታመናል።
የድሉ ብስራት፤ በጭቆናና በግፍ አገዛዝ ወስጥ የነበሩ የዓለም ሕዝቦችን አይን የከፈተ፤ ለነፃነትና ለፍትህ በመጮህ ለዛሉ ልቦች አዲስ ተስፋ የጫረ፤ ለተዳፈኑ የማንነትና ራስን የመሆን ጥያቄዎች ትንሳዔ መፍጠር የቻለ፣ ለአዳዲስ የነፃነት ትግሎች መነቃቃት የፈጠረ ትልቅ ዓለም አቀፋዊ ክስተት ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተነሱት የነፃነት፣ የፍትሕ እና ራስን የመሆን፣ የኢትዮጵያኒዝም እና የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄዎች የአስተሳሰብ መሠረት ነው፣ አፍሪካውያን አንድነታቸውን አጠናክረው ዛሬ ላይ ለተቀዳጇቸው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ነፃነቶች ዋነኛ አቅም ነው ።
ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሆነ በሀገር ውስጥ በብዙ ትውልዶች ልብ፣ ትልቅ ስፍራ የነበረውን እና ወደፊትም የሚኖረውን የዓድዋን ድል ለመዘከር፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መገንባቱ፤ ድሉን በተሻለ መልኩ ለመዘከር ትልቅ አቅም መፍጠር የሚያስችል ነው ።
ሙዚየሙ የአሁኑንም ሆነ መጪው ትውልድ ስለ ድሉ ብቻ ሳይሆን፣ ከድሉ በስተጀርባ ያለውን እና ድሉ የፈጠረውን የጋራ ሀገራዊ ትርክት በአግባቡ ተረድተው፣ የዚህ ታላቅ ታሪክ ባለቤት መሆን ሊፈጥር የሚችለውን የታሪክ ሠሪነት መንፈስ እንዲጋሩ የተሻለ ዕድል የሚፈጥር ነው።
የመታሰቢያ ሙዚየሙ፤ በዓድዋ የድል ትርክት ለጭቆናና ለግፍ አገዛዝ እምቢ ያሉ፤ ስለ ነፃነታቸውና ፍትሕ ተስፋቸው ዳግም ያበበ፤ ለተዳፈነ የማንነትና ራስን የመሆን ጥያቄያቸው ትንሣዔ ላገኙ የዓለም ሕዝቦች ጭምር መታሰቢያነት ያለው ፤ የታሪካቸው አንድ አካል ነው። ከዚህም ባለፈ ለዘላቂ ሁለንተናዊ ነፃነታቸው ለጀመሩት ትግል ስኬት፣ የይቻላል መንፈስ ምንጭ በመሆን፣ የማይናወጥ፣ ትውልድ ተሻጋሪ የዓላማ ጽናት መፍጠር ያስችላል ።
ሙዚየሙ ታሪኩን በሚመጥን መልኩ መገንባቱም፤ መንግሥት ለሕዝቦች የአንድነት ታሪክ ያለውን ከፍ ያለ ከበሬታ በተጨባጭ ማሳየት ያስቻለ፤ ትውልዱ ለታሪኩ ቅርብ እንዲሆን በማድረግ የተሻሉ ነገዎችን በቁጭት መሥራት እንዲችል መነቃቃትን መፍጠር የሚያስችል ነው።
እንደ ሀገር አሁን ላለንበት የታሪክ እጥፋት፤ በተለይም ከከፋፋይ ትርክቶች ወጥተን፣ የጋራ ትርክቶቻችንን በማስፋት የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር እንደ ትውልድ ለጀመርነው የለውጥ ንቅናቄ ስኬት ትልቅ አቅም ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ጭምር ነው።
መንግሥት የታሪክ መዛነፎች ሀገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ባለበት በዚህ ወቅት ታሪክን እውነታውን በሚመጥን መንገድ ለመዘከር የጀመረው ጥረት የሚበረታታና ከፍ ያለ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው።
የታሪኩ ዋነኛ ባለቤት የሆነው መላው ሕዝባችን ከቀደሙት አባቶቹ የአንድነትና ዓላማ ጽናት ታሪኮች ተምሮ አስቸጋሪ ወቅቶችን አላስፈላጊ ዋጋዎችን ሳይከፍል መሻገርን የዕለት ተዕለት ሕይወትና እንቅስቃሴው አካል ሊያደርግ ይገባል!
አዲስ ዘመን የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም