ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ 188 ባለኮከብ ሆቴሎች አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቀዋል

አዲስ አበባ፡- ለ37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ሆቴሎች አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ሆቴል ማርኬት ማኅበር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ሆቴል ማርኬት ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን አለሙ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ37ኛው ኅብረት የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ሆቴሎች አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቀዋል።

በጉባኤው ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል 188 ባለ ኮከብ ሆቴሎች አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገዋል ያሉት አቶ ጌታሁን ሆቴሎቹ እንግዶችን ያለ ምንም አገልግሎት ችግሮች ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቀዋል ብለዋል።

ሆቴሎች የአገልግሎት ምቹ አካባቢን በመፍጠር እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እንግዶችን ያለምንም የጸጥታ፣ የውሃ፣ የስልክ፣ የመብራትና ሌሎች አገልግሎቶች ችግር ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ለጉባኤው ከታክሲና አስጎብኚ ማኅበራት ጋር በቅንጅታዊ አሠራር መሠራት እንዳለበት ጠቁመው፣ ለጉባኤው ስኬታማነት ከቱሪዝም ሚኒስቴር፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ከሆቴሎችና የንግድ ማኅበረሰብ ጋር ተቀናጅቶ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።

በሆቴሎች እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚደረጉ ጠቅሰው፣ ባለ ኮከብ ሆቴሎች ለእንግዶች ምቹ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን አመላክተዋል።

የታክሲና አስጎብኚ ድርጅት አገልግሎቶችን ቅንጅታዊ አሠራርን በመዘርጋት ቀልጣፋ ለማድረግ በጋራ መሠራት እንዳለበት በመግለጽ የትራንስፖርት አገልግሎት ደህንነትን በማረጋገጥና ትክክለኛ መረጃን በመስጠት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ለጉባኤው ተሳታፊዎች ትክክለኛ የትራንስፖርት፣ የመረጃና፣ የሆቴል አገልግሎቶችን መስጠት ተገቢ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ በተለይም ለተሳታፊዎች የመጓጓዣ አማራጮችን ማቅረብ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ማኅበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ወደ መዲናዋ ለሚመጡ እንግዶች የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻዎች ለማስተዋወቅ እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ እንግዶች በቆይታቸው የአንድነት፣ ወዳጅነትና፣ እንጦጦ ፓርኮችን ጨምሮ የተለያዩ መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ ለማድረግ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ የሀገሪቱን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ጌታሁን ማኅበሩ የቱሪዝምና ሆቴሉን ዘርፍ ከፍ በማድረግ የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ነው ብለዋል።

37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 9 እና 10 የሚካሄድ ሲሆን 44ኛው የአባል ሀገራት የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ የካቲት 6 እና 7 በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ የሚካሄድ ይሆናል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን  የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You