የጣሊያኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የስደተኞች መርከብ እንዲቆም ባለመፍቀዳቸው በእስር እንዲቀጡ ተጠየቀ

የጣሊያን ዐቃቤ ሕግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቴዮ ሳልቪኒ ስደተኞችን ያሳፈረች መርከብ በሀገራቸው የባሕር ጠረፍ ላይ እንዳትቆም በመከልከላቸው በስድስት ዓመት እስር እንዲቀጡ ጠየቀ። ሳልቪኒ በአውሮፓውያኑ 2019 ነው ስተደኞችን የያዘች መርከብ ወደ ጣሊያን ወደብ ተጠግታ እንድታራግፍ አልፈቀድም ያሉት።

ኦፕን አርምስ በተባለ የተራድዖ ድርጅት የምትንቀሳቀሰው መርከብ ስደተኞችን ጭና ለሦስት ሳምንታት ያህል ውቅያኖስ ላይ ከቆየች በኋላ በመጨረሻ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ላምፔዱሳ ደሴት እንድታርፍ ተደርጓል። ይህ ሲሆን የጣሊያን የአገር ውስጥ ሚኒስትር የነበሩት ሳልቪኒ የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል። ክሱን አስመክልቶ ሲናገሩ፤ እኔ ጣሊያን “የስደተኞች ካምፕ” እንድትሆን አልፈልግም ብለው “ጣሊያን እና ጣሊያናውያንን መጠበቅ ወንጀል ከሆነ ጥፋተኛ ነኝ” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከሊቢያ የባሕር ዳርቻ የተነሱ 147 ስደተኞችን አሳፍራ የነበረችው የኦፕን አርምስ መርከብ ላምፔዱሳ ወደብ እንዳታርፍ ተከልክላ ነበር። የሜድቴራኒያን ባሕር ላይ የሚገኘው የላምፔዱሳ ደሴት ወደ ጣሊያን የሚመጡ ስደተኞች የሚሸጋገሩበት ሲሆን፤ በተለይ በቅርብ ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ መዳረሻቸውን አውሮፓ ያደረጉ ስደተኞች ወደዚህች ደሴት ያመራሉ።

የወቅቱ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሳልቪኒ “የተዘጋ ድንበር” የተባለ ፖሊሲ አራማጅ ነበሩ። ይህ ፖሊስ ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎችን ለመግታት የተዘረጋ ነው ሲሉ ይከራከራሉ። የመርከቧ አባላት ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን በሰጡበት ወቅት መርከቧ ወደ ጠረፍ እንድትመጣ ስላልተፈቀደላት የስደተኞች የጤና እና ንፅህና ሁኔታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሶ እንደነበር ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕግ ጌሪ ፌሬራ ለሲሲሊ ፍርድ ቤት ሲናገሩ፤ “በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ከሰብዓዊ መብት እና ከአንድ ሀገር ሉዓላዊነት ቀድሞ ሊመጣ የሚገባው ጉዳይ ሰብዓዊ መብት ነው” ብለዋል። ባለፈው ጥር ችሎት ፊት የቀረቡት ሳልቪኒ “የመርከቧ ሁኔታ አስጊ እንዳልነበረ” መረዳታቸውን ገልፀዋል። በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2021 የጀመረው ችሎት በሚቀጥለው ወር ብይን ሊሰጥበት እንደሚችል ይጠበቃል። ሳልቪኒ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የመንግሥት ሥልጣናቸውን ሊነጠቁ ይችላሉ።

የስድስት ዓመት እስር እንዲቀጡ የተጠየቀባቸው ሳልቪኒ በኤክስ ገፃቸው በሰጡት ምላሽ፤ “ጣሊያንን መጠበቅ ወንጀል አይደለም። በፍፁም እጄን አልሰጥም። መቼም ቢሆን፤ በፍፁም” ብለዋል። “ምስጋና መንግሥታችን እየወሰደ ላለው እርምጃ ይግባና በሜድቴራኒያን ባሕር ላይ የምንሰማው ሞት እና የሰዎች መጥፋት ቀንሷል። ”የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያመልክተው በ2019 ወደ ጣሊያን በጀልባ የመጡ ሰዎች ቁጥር 11 ሺህ 471 ነበር። ይህ ቁጥር ከሌሎች ዓመታት ሲነፃፀር በጣም ዝቅ ያለ ነው።

የኖርዘርን ሊግ ፓርቲ መሪ የሆኑት ሳልቪኒ ሕገ-ወጥ ስደትን በግልፅ የሚቃወሙ ሲሆን፤ ፋይቭ ስታር ሙቭመንት ከተባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ፓርቲ ጋር በመጣመር ነው ሥልጣን የያዙት። ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ ለምክትላቸው ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል።

አዲስ ዘመን መስከረም 8/2017 ዓ.ም

Recommended For You