
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያና ሶማሊ ላንድ ስምምነት የጋራ ተጠቃሚነትን መርሕን የተከተለ እንጂ የሶማሊያን ድንበርም ሆነ ሉዓላዊነት ያልጣሰ መሆኑን በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ ገለጹ፡፡
አምባሳደር ባጫ ደበሌ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ሃሳብ፤ የባሕር በር ስምምነቱን በአሉታዊ መንገድ ለተረዱ አካላት በሰከነ የዲፕሎማሲ ሥራ ጠቀሜታውን ማስረዳት ይገባል ብለዋል፡፡
ስምምነቱ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እንደመጣስ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም ያሉት አምባሳደር ባጫ፤ ስምምነቱ የማንንም ጥቅም የማይነካ፣ የጋራ ተጠቃሚነትንና አብሮ ማደግን መርህ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ስምምነቱን በተገቢው መንገድ ላልተረዱ የሶማሊያ ተወላጆችና ባለሥልጣናት እንዲሁም ለተቀረው የዓለም ሕዝብ ጉዳዩን በበቂ ሁኔታ ማስረዳት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል የሚኖር ቅሬታን በሁለትዮሽ ግንኙነት መፍታት ሲገባ የማይመለከታቸው ሀገራት ጉዳዩን ማራገባቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እንዲሻክርና ወደአልተፈለገ ግጭት እንዲገቡ በማሰብ በመሆኑ በሰከነ ዲፕሎማሲ ጫናውን መሻገር ያስፈልጋል ሲሉ ሃሳብ ሰጥተዋል።
ላለፉት 20 ዓመታት ሶማሊያ የተረጋጋች ሀገር እንድትሆንና የሶማሊያ መንግሥት እራሱን ከአሸባሪዎች የሚከላከልበትን አቅም እንዲያዳብር በርካታ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች የሕይወት መስዋዕትነት መክፈላቸውንና አሁንም እየከፈሉ መሆኑን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት የመጣስና ሀገሪቷን የመበታተን ፍላጎት ቢኖራት ኖሮ የውድ ልጆቿን ሕይወት ባልገበረች ነበር ሲሉ አምባሳደር ባጫ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የሶማሊያን ድንበርና ሉዓላዊነት ለመድፈር አልሄደም ያሉት አምባsሳደር ባጫ፤ ከጎረቤቶች ጋር በንግድና መሠረተ ልማት በመተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ፍላጎት ማሳየቱን ማስረዳት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ሶማሌላንድ የባሕር በርንና ሌሎች ሥራዎችን በተመለከተ ከበርካታ ሀገራት ጋር ስምምነት መፈረሟን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ያደረገ ስምምነት ስትፈርም ከአንዳንድ አካላት የሚነሳው ተቃውሞ አግባብ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
የወደብ ስምምነቱ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ለማደግ፣ በመሠረተ ልማትና በንግድ የበለጠ መተሳሰርን ያለመ እንጂ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ለመዳፈር የተደረገ አለመሆኑን ሁሉም አካል ሊያውቀው እንደሚገባ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ እንዳታድግ የሚፈልጉ አካላት ስምምነቱን መቃወማቸውን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ወደብ የማግኘትና የመጠቀም እንዲሁም ከቀይ ባሕር ጋር የመገናኘት ፍላጎቷንና መብቷን የሚቃወሙትን በሰከነ የዲፕሎማሲ ሥራ ማስረዳት ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም