የኮንስትራክሽን ዘርፉን በሥልጠና የመታደግ ጥረት

ኢትዮጵያ የሥነ ሕንፃ ፊት አውራሪነቷን ቆመው የሚመሰክሩ፣ ዓለምን ያስደመሙ፣ የኢትዮጵያውያን ድንቅ የዕደ-ጥበብ ዐሻራ ያረፈባቸውና በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶችን የያዘች ሀገር ነች:: የአክሱም ሐውልት፣ የጎንደር ቤተ-መንግሥት፣ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጀጎል ግንብና ሌሎቹም የሥነ-ሕንፃ ቅርሶች ኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የነበረችበትን ከፍታ በሚገባ ያመለክታሉ::

ሀገሪቱ በጀመረችው የግንባታ አቅም ልክ እየተጓዘች አለመሆኗና የሥልጣኔዋ ግንባር ቀደም መገለጫ የሆነው ጥንታዊ የሥነ-ሕንፃ ጥበቧ በነበረበት መቆሙ ዜጎቿን ቁጭት ውስጥ ሲከት ቢኖርም፣ ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ መሠራቷን ተከትሎ ግዙፍ መሠረተ ልማቶችን የገነባችባቸውና እየገነባች ያለችባቸው ሁኔታዎችም እንዳሉ ይታወቃል::

ለእዚህም በሕዝብና መንግሥት ወጪ ግንባታው እየተጠናቀቀ ያለው የዓባይ ግድብና ሌሎች የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመንገድ፣ የባቡርና የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ:: ከሀገሪቱ አመታዊ የካፒታል በጀት ወደ 60 በመቶው ያህል በኮንስትራክሽን ዘርፉ በኩል የሚንቀሳቀስ ነው:: ዘርፉ በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥም ጉልህ ስፍራ ያለው ሲሆን፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርም ይታወቃል::

ይሁንና በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ጉልህ ስፍራ ያህል ውጤት እያስመዘገበ አለመሆኑ ይታወቃል:: ዘርፉ በግንባታ መጓተት፣ በተቋራጮች አቅም ውስንነት፣ በሙስና፣ በቴክኖሎጂ አቅም ውስንነትና በመሳሰሉት ችግሮች ፈተና ውስጥ ይገኛል:: እንደ ኮቪድ 19 ያሉት ዓለም አቀፍ ፈተናዎች በእጅጉ ፈትነውታል::

ይህን የዘርፉን ችግር በሚገባ የተረዳው መንግሥትም ችግሩን ለመፍታት እንዲያስችል የተለያዩ ተቋማትን አደራጅቶ ኢንዱስትሪውን ከገባበት መቀዛቀዝ ለማውጣት እየሠራ ነው:: የዘርፉን የሰው ኃይል አቅም ለማሳደግ፣ የግብዓትና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦት እንዲያገኝ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው::

ዘርፉ የሚመራበትን የኮንስትሪክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል:: የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ማነቆዎች በመፍታት የዘርፉን የተወዳዳሪነት አቅም ለማሳደግ የያዘውን አቅጣጫ ተከትሎ ከተቋቋሙ ተቋማት አንዱ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ተጠቃሽ ነው::

ኢንስቲትዩቱ የዘርፉን ተዋናዮች አቅም በተግባር ተኮር ሥልጠና መገንባት፣ በዘርፉ ችግር ፈቺና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ በኢንዱስትሪው ጥቅም ላይ እንዲውል ይደግፋል:: ዘመኑ የደረሰባቸውን ተስማሚና ወጪ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችና አዳዲስ የሥራ ፈጠራዎችን በኢንዱስትሪው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያስተዋውቃል::

የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት አሠራር ሥርዓቶችን የመዘርጋትና የማማከር ተግባራት ያከናውናል:: የኮንስትራክሽን ምህንድስና እና ማኔጅመንት ልሕቀት ማዕከል የዘርፉን ችግሮች በሚያቃልል መልኩ መገንባትና ጥቅም እንዲሰጥ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር በማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ማድረግም ከተሰጡት ተልዕኮዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው::

የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አሰበ ከበደ እንደሚገልጹት፤ ተጠሪነቱን ለከተሞችና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አድርጎ በደንብ ቁጥር 289/2005 የተቋቋመው የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ተልዕኮውን ፍሬያማ እያደረገ ነው::

ኢንስቲትዩቱ እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባራት መካከል ለዘርፉ ተዋንያን የሚሰጣቸው ሥልጠናዎች ይጠቀሳሉ:: እስከ አሁንም ለተለያዩ የዘርፉ ተዋንያን ሥልጠናዎችን ሰጥቷል:: እኛም በዛሬው የመሠረተ ልማት አምዳችን ሥልጠናዎቹ በሠልጣኞች ላይ ምን ውጤት አስገኙ? በሚያከናውኑት ተግባር ላይስ ምን እሴት ጨመረላቸው? የሚሉትን ለመቃኘት ሞክረናል:: ለእዚህም በሥልጠናው የተሳተፉ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣንና የመሰል ተቋማት ሙያተኞችን ተዘዋውረን አነጋግረናል::

ወይዘሮ ሲሳይ ጉታ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ኃላፊ እንደሚያስረዱት፤ ድርጅቱ ሜጋ ፕሮጀክቶችን የሚሠራ እንደመሆኑ አስቀድሞ የባለሙያዎችን አቅም መገንባት ላይ ትኩረት ያደርጋል:: የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በራሱ ወጪ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ድጋፍ አድርጎላቸዋል:: እስከ አሁንም በሦስት መስኮች ለኮርፖሬሽኑ የግንባታ ባለሙያዎች ሥልጠና የሰጣቸው ሲሆን፤ ሥልጠናዎቹም በግንባታ አስተዳደር፣ በኮንትራክት አስተዳደርና በሙያዊ የፕሮጀክት አስተዳዳር ላይ ያተኮሩ ናቸው:: አጠቃላይ በሦስቱ ዘርፎች ስልሳ የሚሆኑ ሙያተኞች መሰልጠናቸውንም ተናግረዋል::

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ራዕዩ የባቡር መሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን በራሱ አቅም ማከናወን እንደሆነ የተናገሩት ወይዘሮ ሲሳይ እዚያ ደረጃ ላይ መድረስ የሚቻለው ሙያዊ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ሲገነባ እንደሆነ ይገልጻሉ:: የባቡር መሠረተ ልማት ዝርጋታ ውስብስብ ባህሪ ያለው ነው የሚሉት የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ኃላፊዋ፣ ባቡር ወጥ የሆነ ወይም ዳገትና ቁልቁለት የሌለው፣ የተደላደለና ጠመዝማዛነት ያልበዛበትን መንገድ ስለሚመርጥ መልክዓ-ምድርን ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ:: በዚህ ረገድ ሥልጠናው በግንባታው ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን የሚሞላና ኮርፖሬሽኑ ከተያዘው እቅድ አንጻር ለሙያተኞች ትርጉም ያለው እንደሆነ ይገልጻሉ::

እስከ አሁን የባቡር መሠረተ ልማት ግንባታ በውጭ ተቋራጮች የሚከናወን እንደሆነ የገለጹት ወይዘሮ ሲሳይ፤ ‹‹ግንባታውን በሀገር ውስጥ ሙያተኞች ማከናወን ሲችል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪና የውጭ ሙያተኞችን ጥገኝነት የሚያስቀር በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና አቅም የሚፈጥር ነው›› ይላሉ::

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር መስመር ግንባታና ኦፕሬሽን 250 ቴክኒሻኖች፣ 70 የባቡር ካፒቴኖች ከውጭ ሙያተኞች ልምድ እንዲቀስሙ በማድረግ የእውቀት ሽግግር ከተደረገ በኋላ የውጭ ሙያኞችን በመቀነስ አሁን ላይ ሥራው ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ሙያተኞች እንዲሸፈን ተደርጓል:: ኢንስቲትዩቱ የሰጠው ሥልጠናም ኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች በራሳቸው አቅም የባቡር መሠረተ ልማት እንዲዘረጉ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው:: ሥልጠናው መሐንዲሶች በትምህርት ቆይታቸው ያካበቱትን እውቀት እንዲያስታውሱና ዓለም የደረሰባቸውን አዳዲስ አሠራሮችንም እንዲያውቁ ያደረገና ያነቃቃ ነው::

በተለይም ኮንትራትን እንዴት ማስተዳደር እንደሚገባ የተሰጠው ሥልጠና ቀደም ሲል ከነበረው ልማዳዊ አሠራር ያላቀቀና ሁሉም ባለድርሻ አካል በውሉ መሠረት የድርሻውን እንዲወጣ የሚያደርግ መሆኑንም ያመለክታሉ:: ኮንትራት ላይ የሚፈጸም ስህተት በኮንስትራክሽኑ አፈጻጸም ላይ ለሚፈጠር ችግር መነሻ እንደሚሆን ገልጸው፣ ሥልጠናው እንዲህ ዓይነቱን ችግር የሚፈታ እንደሆነ ያነሳሉ::

በሥልጠናው ላይ ከተለያዩ የግልና የመንግሥት ኮንስትራክሽን ዘርፍ የተውጣጡ የሲቪል፣ የኤሌክትሪካል፣ የሜካኒካል፣ የአፈር ጥናት መሐንዲሶችና ሌሎችም የተሳተፉበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ከፍተኛ የልምድ ልውውጥና መማማር የተደረገበት እንደነበርም ያስታውሳሉ::

ኮርፖሬሽኑ የራሱንም የሌሎችንም የግንባታ ሥራዎች ለመሥራት አዲስ ቡድን አደራጅቶ ወደ ተግባር እየገባ እንደሚገኝ የተናገሩት ወይዘሮ ሲሳይ፣ ሙያተኞችን ለማብቃት ተከታታይነት ያላቸው ሥልጠናዎች ያስፈልጋሉ ይላሉ:: ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ለኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ችግሮች መፍትሔ አፈላላጊ ሆኖ በባለቤትነት የተቀመጠ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ሥልጠናዎችን አጠናክሮ መቀጠልና አፈጻጸማቸውንም መከታተል እንዳለበት ያስገነዝባሉ::

በኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የግንባታ ዳይሬክቶሬት ሙያተኛ አቶ አደም የሱፍም ሌላው ሠልጣኝ ናቸው::ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ለኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ሙያተኞች የተለያየ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠቱንና እርሳቸውም የዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑ ሙያተኞች አንዱ መሆናቸውን ይገልጻሉ::

ሥልጠናው ፕሮጀክቶች ከእቅድ ጀምሮ እስከ ፍጻሜያቸው ድረስ ምን ምን ሂደቶችን መከተል እንዳለባቸው ትምህርት የተገኘበት ነው ይላሉ:: አቶ አደም ኢንስቲትዩቱ ‹‹ሙያዊ የፕሮጀክት አስተዳደር›› በተባለው ዘርፍ ዓለም አቀፍ ሰርተፊኬት የሚያስገኝ ሥልጠና እንደሚሰጥ ይገልፃሉ:: ይህ ሥልጠና የሀገሪቱን የኮንስትራክሽን ችግር ከመፍታት በዘለለ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ሀገር ሄደው ከየትኛውም ሙያተኛ ጋር ተወዳድረው የመሥራት ዕድል እንዲያገኙም የሚያደርግ እንደሆነም ይጠቅሳሉ::

የኮንስትራክሽን ዘርፍ ትልቅ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበትና ሰፊ የሰው ኃይል የሚሰማራበት በመሆኑ የተሻለ ክህሎትና እውቀት ያለው ሙያተኛ በማፍራት ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪ ማድረግ ይቻላል ይላሉ:: ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውድቀት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ፕሮጀክቶች ከጊዜ ከገንዘብና ከሰው ኃይል አንጻር በሚገባ አለመታቀዳቸው እንደሆነ ይጠቅሳሉ::

የፕሮጀክት እቅድ አሠራር ሶፍት ዌርን መሠረት ተደርጎ የተሰጠው ሥልጠና የተጠቀሱትን ችግሮች ከመፍታት አንጻር አስተዋጽኦው ከፍ ያለ እንደሆነ አቶ አደም ይናገራሉ:: ባለሥልጣኑ የሚሠራቸው አዳዲስ ፕሮጀክቶችም ከሥልጠናው የተገኙ ክህሎቶችን መሠረት አድርገው እየተሠሩ መሆናቸውንም ነው የገለጹት:: በዚሁ መሠረት በ2015 ዓ.ም በክልሉ 100 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችንና ሰባት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ከኢንስቲትዩቱ በተገኙ ሥልጠናዎች በመታገዝ በተባለው ጊዜና በጀት ሠርቶ ማጠናቀቅ እንደተቻለ ያመለክታሉ::

በአጠቃላይ ኢንስቲትዩቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ችግሮች ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩ በኢንስቲትዩቱ ብቻ እንደማይፈታ ይገልጻሉ:: ችግሩ በትብብር ጭምር የሚፈታ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዘርፉ ተዋንያን በሙሉ ጠንካራ ግንኙነት ቢኖራቸው የታሰበው ለውጥ ላይ መድረስ ይቻላል ይላሉ::

ሌላዋ ሠልጣኝ ወይዘሮ ንግሥት ኃይሉ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮንስትራክሽን፣ የዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ፕሮጀክት ቢሮ፤ ፕሮጀክት ማናጀር ናቸው:: የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ካዘጋጃቸው ሥልጠናዎች በሦስቱ ተሳትፈዋል:: ሦስቱም ሥልጠናዎች ከሥራቸው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው፤ በሥልጠናው ያገኙትን እውቀት በጣም እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ያስረዳሉ::

የሥራ ክፍላቸው የዲዛይንና የኮንስትራክሽን ሱፐርቪዥን ፕሮጀክቶች ላይ የሚያተኩር መሆኑን ገልጸው፣ በተለይም ከሥራቸው አንጻር በአግባቡ እየተረጎሙት እንዳሉ ይናገራሉ:: ሥልጠናው በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እንደፈቱና ከስታንዳርዱ ጋር እያጣጣሙ ለመጓዝ እንዲችሉ እንደረዳቸው እንዲሁም ከዚህ በፊት የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላት በእጅጉ እንዳገዛቸው ይናገራሉ::

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አዳዲስ የግንባታ ጨረታዎችን ተወዳድሮ የሚሠራ አዲስ ቡድን ማቋቋሙን የተናገሩት ወይዘሮ ንግሥት፣ ከዚህ አንጻር የተሰጠው የኮንስትራክሽን አስተዳደር ሥልጠናም ተቋሙ በጨረታ ያሸነፋቸውን ፕሮጀክቶች በወጉ አስተዳድሮ ውጤታማ እንዲሆን ትልቅ ዋስትና እንደሚሰጥ ይገልጻሉ::

‹‹እንደ ኮርፖሬሽን ብቻ ሳይሆን እንደሀገርም ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ እና በጀት የመጠናቀቅ ችግር ይስተዋልባቸዋል›› ያሉት ወይዘሮ ንግሥት፣ ለዚህም ምክንያቱ በእቅድ አለመመራት እንደሆነ ይጠቅሳሉ:: ከዚህ አንጻር በተለይም ሥልጠና ፕሮጀክቶች ተጸንሰው እስከሚወለዱ ድረስ ምን ዓይነት ሳይንሳዊ አካሄድን መከተል እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ ያስጨበጠ መሆኑን ያስረዳሉ:: ፕሮጀክቶች ሲታቀዱ ጊዜን፣ የግንባታውን መጠነ ስፋት፣ ካፒታልን፣ ግብዓትን እና የሰው ኃይልን ተገማች ማድረጋቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ መረዳታቸውን ይገልፃሉ::

በሥልጠናው ያገኙትን መሠረታዊ እውቀትና ልምድ ታሳቢ በማድረግ እቅዶችን እያዘጋጁ እንደሚገኙም ይጠቁማሉ:: በኮንስትራክሽን ዘርፍ ሥራዎች በቡድን እንደሚሠሩ ገልጸው፤ በሥልጠናው የተገኙ አዳዲስ አሠራሮችን ለሌሎች ባለሙያዎችም የማሳወቅ ሥራ መሠራቱን ነው የተናገሩት::

ሥልጠናው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና የሥልጠናውን ተተግባሪነት ከንድፈ ሃሳብ (ከቲየሪ) በዘለለ ፕሮጀክቶች በሚገኙበት አካባቢ እየሄዱ የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን መስጠት እንደሚያስፈልግ እና በዘረፉ የተሻለ አፈጻጸም ካላቸው የግልና የመንግሥት ተቋማት ጋርም የልምድ ልውውጥ የማድረግ ልምድ እንዲኖርም ጠይቀዋል:: ኢንስቲትዩቱ የኢንዱስትሪውን ችግሮች ፈትቶ የተወዳዳሪነት አቅሙን ማሳደግ እንዲችልም የሚሰጠውን ሥልጠና በተግባር የሚመዝንበት አሠራር እንዲኖረው አስተያየት ሰጥተዋል::

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን  የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You