
አዲስ አበባ፡- ከገበሬው ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኢንተርፕራይዝ በውጭ ሀገራት የሚለሙ መተግበሪያዎችን በሀገር ውስጥ መተካት እንደሚያስችል ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ አስታወቀ።
ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ከገበሬው ቴክኖሎጂ ሶሉሽን የተሰኘ የተለያዩ መተግበሪያዎችን ማበልጸግ የሚያስችል ኢንትርፕራይዝን በይፋ አስተዋውቋል።
በወቅቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሀገራዊ የኢኖቬሽን ልማት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰላምይሁን አደፍርስ እንደገለጹት፤ በሀገር ውስጥ በራስ አቅም የሚመረቱ መተግበሪያዎች ለዲጂታል ኢትዮጵያ ዕቅድ መሳካት የላቀ ሚና አላቸው፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሥራዎች ላይ የግሉ ዘርፍ በመሪነት እንዲሳተፍ የተለያዩ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል ያሉት አቶ ሰላምይሁን፤ በዚህም የተለያዩ ፖሊሲዎችና አዋጆች የግሉን ዘርፍ የሚያሳትፉ ሆነው እንዲቃኙ ማድረጉን አስታውሰዋል።
አቶ ሰላምይሁን እንደሀገር የሚገኙ አዲስ ሃሳቦች ገበያ እንዲፈጥሩ ለማስቻል የሥራ ፈጠራ ጀማሪዎችን የሚያበረታታ አዋጅ እንዲኖር መደረጉን ጠቁመው፤ ፐርፐዝ ብላክ የሚያበለጽጋቸው መተግበሪያዎችም ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስሀ እሸቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የግብርና ምርቶችን በማቅረብ የሚታወቀው ፐርፐዝ ብላክ አሁን ደግሞ የተለያዩ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ መስጠት የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን ማበልጸግ የሚያስችለውን ኢንተርፕራይዝ ማቋቋሙን ገልጸዋል፡፡
ኢንተርፕራዙ የተለያዩ መተግበሪያዎችን ለማበልጸግ የሚያስችል ሲሆን፤ ይህም በውጪ ምንዛሬ በበይነ መረብ የሚገኙ መተግበሪያዎችን በመተካት ረገድም ሀገራዊ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው ብለዋል፡፡
ኢንተርፕራዙ በአሁኑ ጊዜ 24 መተግበሪያዎችን በማበልጸግ ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ከእነዚህም ውስጥ ስድስት መተግበሪያዎችን ይፋ አድርጓል፡፡
መተግበሪያዎቹ ከገበሬው የግብርና ምርቶች አቅርቦት መተግበሪያ (KAPS)፣ከገበሬው ኮንሲዩመር ብድር ማነኔጅመንት(KCCM)፣ከገበሬው የኦንላይን መማሪያ አስተዳደር ሥርዓት(KLMS)፣ከገበሬው የቴሌቪዥን መረጃ ማሰራጫ ፣ከገበሬው ኦርደርና ዲሊቨሪ መቆጣጠሪያ (KOT) እንዲሁም ከቻይና ወደ አፍሪካ የተሰኙ ሲሆኑ፤ እነዚህ መተግበሪያዎች ከፐርፐዝ ብላክ በተጨማሪ ለማንኛውም ድርጅት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መተግበሪያዎቹ ከምርት ስርጭት እስከ ወጪ ገቢ ንግድ የሚደርሱ ሥራዎችን የሚያቀላጥፉ፣ ቴክኖሎጂን የሚያስፋፉና ገበሬውን ቀጥታ ከነጋዴው ጋር ለማስተሳሰር የሚያግዙ ናቸው ብለዋል፡፡
መተግበሪያዎቹ ሙሉ በሙሉ የሀገር ልጅ ዕውቀትን፣ ልምድና ክህሎትን በመጠቀም የበለጸጉ መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም