ድሬና ወጣቶቿ

በትምህርት፣ በንግድና በተለያየ የሥራ መስክ ተሰማርተው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ከድካማቸው አረፍ ማለታቸው ተፈጥሯዊ ነው:: በእረፍት ጊዜ ደግሞ አዕምሮንም አካልንም ዘና የሚያደርጉ ነገሮች ያስፈልጋሉ:: በእርግጥ ዘና ስለማለት ሲነሳ ምርጫው ይለያያል::

አንዱን የሚያዝናናው ነገር፤ ሌላው በበጎ የሚያየው ላይሆን ይችላል:: ብቻ ሁሉም የመዝናኛ ምርጫ አለው:: በተለይ ወጣቶች ከትምህርትም ሆነ ከሥራ በኋላ ጊዜያቸውን ባልባሌ ነገር እንዳያጠፉ የተለያዩ የመዝናኛ ማዕከላት ሊስፋፉ እንደሚገባ ብዙዎች ይመክራሉ::

የመዝናኛ ማዕከላት ካልተስፋፉ ወጣቶች በአልባሌ ቦታ ለመዋል ይገደዳሉ፣ ለተለያዩ ሱሶችም ተጋላጭ ይሆናሉ:: ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ መዋያዎች(መዝናኛዎች) ምቹ በማድረግም ከአካባቢ አካባቢም የሚለያይ በመሆኑ የሚሰጡት አስተያየቶችም ከአካባቢ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተያያዙ ናቸው::

ከሰሞኑ በድሬዳዋ በነበረኝ የሥራ ቆይታ በከተማዋ ያሉትን የመዝናኛ በተለይም ወጣቶች ሊውሉባቸው የሚችሉትን ለመቃኘትና አስተያየትም ለመሰብሰብ ሞክሬ ነበር:: በበቂ ሁኔታ የለም የሚለው አስተያየት ይበዛል:: አንዳንድ ወጣቶችንም አነጋግሬ ተመሳሳይ ነበር ምላሻቸው:: አሁን ላይ ግን ተስፋ የሚሰጡ ጅምር ሥራዎች በከተማዋ እየታዩ መሆኑንም ነግረውኛል::

ከእነዚህ ወጣቶች መካከል ወጣት አበበ ወልዴ አንዱ ነው:: አበበ በድሬዳዋ ገንደ ቦዬ ተብላ በምትጠራ አካባቢ ነው የሚኖረው:: ወጣት አበበ፤ ስለአካባቢው ስያሜም እንደነገረኝ፤ የመኖሪያ አካባቢው ተለውጦ ከተማ ከመሆኑ በፊት ነዋሪዎች አርሶአደሮች ነበሩ:: ገጠር በነበረበት ወቅት በአካባቢው የአሳማ ርቢ ይከናወን ነበር:: በዚህ የተነሳ አካባቢው ገንደ ቦዬ ተባለ:: ቃሉ ኦሮምኛ ነው:: ገንደ፣ መንደር ሲሆን፣ ቦዬ፣ ደግሞ አሳማ ማለት ነው::

ወጣት አበበ፤ ድሬዳዋን ሲገልጻት እንኳን ተወልዶ ላደገባት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል ኑሮቸውን በድሬዳዋ ላደረጉም ምቹ እንደሆነች ነው:: ወጣቱ ሊውልባቸው ወይንም ጊዜ ሊያሳልፍባቸው የሚችሉ ምቹ ሁኔታዎች ማሟላት ላይ ግን ከከተማ አስተዳደሩ ብዙ ሥራ ይጠበቃል ይላል:: በዚህ በኩል ለወጣቶች ትኩረት ተነፍጓል ብሎም ያምናል::

ወጣቱ የሙዚቃ፣ የትያትር፣ የሥነጽሑፍ፣ በአጠቃላይ ክህሎቱን ሊያወጣ የሚችልባቸው የተለያዩ ክበባት እንዲሁም ሲኒማ ቤቶች፣ ፓርኮችና ሌሎችም ጊዜ ማሳለፊያዎች ይኖሩ እንደሆንም ለወጣት አበበ ላቀረብኩለት ጥያቄ ‹‹የከተማው ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አደራጅቷቸው የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ወጣቶች እንደነበሩ አስታውሳለሁ:: እንቅስቃሴያቸው ግን ጎልተው ሊወጡ በሚችሉበት ደረጃ ነው ለማለት አያስደፍርም›› የሚል ነበር ምላሹ::

በሙዚቃው ዘርፍ በተለይም በውዝዋዜ የተሻለ ነገር መኖሩን ግን አልሸሸገም:: ውዝዋዜና ዳንስ በግላቸው ከሚያሠለጥኑ መካከልም አንዱ እንደሆነም ገልጾልናል:: ማዕከሉም አሐዱ በሚል ስያሜ ይታወቃል::

ወጣቱ ችሎታውን የሚያወጣበትና አዕምሮውንም ዘና የሚያደርግበት መዋያ በበቂ ሁኔታ አለመኖሩ ለሥነምግባር መጓደል ዳርጎት ይሆን እንደሆነም ጠይቄው በሰጠው ምላሽ፤ ጎልቶ የሚነገር የሥነምግባር ጉድለት በአካባቢው ወጣት ላይ አለማየቱን ነው የገለጸው:: ለዚህም ማሳያ ብሎ የጠቀሰው፤ እርሱ ባቋቋመው የውዝዋዜና ዳንስ አሐዱ ማዕከል ውስጥ የሚሳተፉ የተለያዩ ወጣቶችና ታዳጊዎችን ሁኔታ ለማየት እድሉ ስላለው አብዛኞቹ መልካም የሚባሉ ሆነው ነው ያገኛቸው::

በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ችግር ያለባቸውን በተሻለ ለመቅረጽ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ከመጥፎ ምግባራቸው እንደሚመልሳቸው ነው የተናገረው:: በእርሱ ማዕከል ከሰለጠኑትም ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሱ መኖራቸውን ያስታውሳል::

ጫት ከመቃም ጋር በተያያዘ ወጣት አበበ በሰጠው አስተያየት፤ ‹‹ወጣቱ የማኅበረሰቡ ውጤት ነው:: ጓደኞቹ የሚውሉበትን ነው የሚያየው:: ያየውን ነው የሚከተለው:: ሌላ የሚውልበት ነገር ተመቻችቶለት ቢሆን ለምን እዚህ ቦታ ትገኛለህ ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል:: ስለዚህ ወጣቱን ልንወቅሰው አንችልም:: በእኔ እምነት ወጣቱ በመጥፎ ሊተረጎም የሚችል ነገርም እያሳየ አይደለም›› በማለት ከጫት ጋር የማያያዙ ነገር የተሳሳተ እንደሆነ ያስረዳል::

ከከተማ አስተዳደሩ የሚጠብቀውንም በተመለከተ ቢያንስ በየቀበሌው ሁለት የወጣት ማዕከሎች ቢቋቋሙና በማዕከላቱም የወጣቱን ሥነምግባር ለማነጽም ሆነ በተለያየ ነገር ተጠቃሚ የሚሆንበት ነገር ቢፈጠር የተሻለ እንደሆነ ያምናል:: እርሱ እየሠራበት ያለውን የውዝዋዜና ዳንስ ጨምሮ በተለያየ መንገድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ክበባት ቢጠናከሩና አዳዲሶችም ቢከፈቱ ወጣቱ መልካም የሆኑ ነገሮችን ለመሥራት ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን ይገልጻል::

ከአካባቢውም ሆነ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሠላም ሁኔታን በተመለከተም ወጣት አበበ፤ ጥሩ ነገር ለመሥራትም ሆነ ለጥፋት ለመነሳሳት የወጣቱ ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ያምናል:: ለመጥፎ ድርጊትም ወጣቱን ለመጠቀም ጥረት የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩንም ይገነዘባል::

በድሬዳዋ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ወጣቱን ጨምሮ ማኅበረሰቡ የአካባቢውን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ከአካባቢ ፖሊስ( ኮሚኒቲ ፖሊሲንግ) ጋር በመሆን አንድ ለአምስት ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ነው ያስረዳው:: ድሬዳዋ ፍጹም ሠላምና የፀጥታ ስጋት የማይታይባት እንደሆነችም ተናግሯል:: ሁሉም ለአካባቢው ዘብ ከቆመ ሀገራዊ ሠላም ይጠበቃል ::

ሌላው በከተማዋ ያገኘሁት ወጣት፤ በቅጽል ስሙ ዲጄ ዱስ ይባላል:: በዋና ስሙ ደግሞ ዱርሳ ሀሚን ተብሎ ነው የሚጠራው:: ወጣት ዱርሳ 25 ዓመቱ ነው:: ትምህርት ከ10ኛ ክፍል በላይ መዝለቅ ባለመቻሉ እራሱንና ቤተሰቡን ለመርዳት በሚያስችለው ሥራ ላይ እንደተሠማራ ይናገራል::

ወጣቱ ግለሰቦች፣ ተቋማት የተለያዩ ዝግጅቶች ሲኖሯቸው እንዲሁም ሠርግና ልደት በሙዚቃ በማጀብ ዲጄ ሆኖ ነው የሚሠራው:: በዚህ ሥራ ላይ የተሠማሩ የተለያዩ ሰዎችን በማየትና በጊዜ ሂደትም ፍላጎት አድሮበት ወደ ሥራው እንደገባ አጋጣሚውን አጫውቶኛል::

ለድሬዳዋ ወጣቶች የሚሆን የመዋያ ሥፍራዎችን በተመለከተም ወጣት ዱርሳ እንደነገረኝ፤ ለወጣቱ የሚሆኑ መዝናኛዎች ያንሳሉ:: አሁን ላይ ግን ለውጦች መታየት ጀምረዋል:: ለገሀሬ፣ አሸዋና በሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች ወጣቶች ተደራጅተው በተለይም በስፖርት በእግር ኳስ ሰፊ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው የከተማ አስተዳደሩ ጥረት እያደረገ ይገኛል::

በስፖርቱ ውስጥ የሚሳተፈው ብቻ ሳይሆን፤ ተመልካቹም መዋያ ማግኘት መጀመሩን ይገልጻል:: ወጣቱ በዚህ እንዲቀጥል ከተደረገ ለሱስ ተጋላጭነቱ እንደሚቀንስ፣ ሥራ ፈጣሪ ለመሆንም እንደሚነሳሳ፣ አካባቢውንና ሀገሩን የሚጠቅም ዜጋ ሊወጣ እንደሚችልም ወጣቱ አስረድቷል::

ከመዝናኛዎችም በእውቁ የኦሮሚኛ ዘፋኝ በክብር ዶክተር አሊቢራ የተሰየመው ፓርክ፣ እንዲሁም በከተማዋ እየተሠራ ያለው የስፖርት አካዳሚ ደግሞ ሲጠናቀቅ፣ ወጣቶቹ የተሻለ የጊዜ ማሳለፊያ እንደሚኖራቸው ተስፋ ያደርጋል::

ወጣት ዱርሳ፤ ከሠላምና ከፀጥታ ጋር ስላለው ሁኔታም አካባቢው ፍጹም ሠላም እንደሆነ፣ ነዋሪው 24 ሰዓት ያለ ሥጋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑና እርሱም በሥራ አጋጣሚ እኩለ ሌሊት አልፎ ወደቤቱ የሚሄድባቸው አጋጣሚዎች የበዙ እንደሆነ ነው ያስረዳው::

በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሠላም ተፈጥሮ ሀገር ከፀጥታ ሥጋት እንድትላቀቅ ተመኝቷል:: ወጣቱ በጀመረው ሥራ ውጤታማ ሆኖ ከራሱ አልፎ ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ እድል ፈጥሮ ስኬታማ ለመሆን ነው ፍላጎቱ:: ይህንን ፍላጎቱን ለማሳካት ደግሞ በሥራው ሌትቀን እየተጋ እንደሆነም ተናግሯል::

የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲም በማኅበረሰብ አገልግሎት በአካባቢው ላይ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራ ይገኝበታል:: በዚህ ረገድም ዩኒቨርስቲው እያከናወናቸው ስላለው ተግባር በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የሶሻል ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ወንድይፍራው ደጀኔ (ዶ/ር) እንዳስረዱት፤ ወጣቶች መልካም ባሕሪ እንዲኖራቸው በተለያየ ክህሎትም ብቁ እንዲሆኑ ጥረት እያደረገ ይገኛል::

በሥነምግባር የታነጸና የተለያየ ችሎታ ያለው ትውልድ ለመፍጠር ከታች ጀምሮ መሥራት ይገባል የሚሉት ወንድይፍራው (ዶ/ር)፤ በተለይም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ነው የገለጹት:: ሀገር መውደድ ምን ማለት እንደሆነ፣ ወንድማማችነት፣ ተባብሮና ተዋድዶ በአንድ ላይ ስለመኖርና ተያያዥ በሆኑ ነገሮች ላይ ሥልጠና መሥጠት ከሥራዎቹ መካከል እንደሚጠቀሱ አስረድተዋል::

ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው ቤተሙከራ ውስጥ(ላቦራቶሪ) እንዲጠቀሙ በማድረግና የሚጎላቸ ውንም ቁሳቁስ በማሟላት በትምህርታቸውም ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ሌላው ተግባር እንደሆነም አመልክተዋል::

እንደ ወንድይፍራው (ዶ/ር)፤ በቴክኖሎጂና በፈጠራ ላይ ያተኮረ ሥልጠናም በመስጠት ክህሎታቸው ከፍ እንዲል እንዲሁም በውድድር እንዲበረታቱ ይደረጋል:: እንዲህ ያለው መርሐግብርም በዩኒቨርስቲው የሚከናወነው ሳይንስ ወዳድ ትውልድ ለመፍጠር ታስቦ ነው:: በተለይም ሂሳብና ፊዚክስ ከባድ እንደሆነ አድርጎ የማየቱ ሁኔታንም ለመቀየር መርሐ ግብሩ ያግዛል ብለዋል::

ዩኒቨርሲቲው ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘም፤ ለአብነትም ከሥራና ክህሎት መሥሪያ ቤት ጋር በመሆን በሠሯቸው ሥራዎች የብሎኬት ማመረቻ ማሽነሪዎችን በመስጠትና በሥልጠናም እንደሚታገዙ የማድረግ ተግባራት እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል:: የሥራ ማስጀመሪያ ግብዓቶችን ማሟላት፣ በሥልጠና ማገዝ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን መስጠት ጥሩ የሚባሉ ጅማሬዎች ቢኖሩም አጠናክሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል::

ክብረዓብ በላቸው

አዲስ ዘመን  የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You