ሹመቱ ሀገር ከፖለቲካና ከፓርቲ በላይ መሆኗን ያሳየ ነው!

 ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የሚታዩ መሠረታዊ ለውጦች የሀገሪቱን የቆዩ የፖለቲካ ስብራቶችን ከማከም እና ከመጠገን ባለፈ፣ እንደ ሀገር አዲስ የፖለቲካ ባህል በመፍጠር የሀገሪቱን ነገዎች እና የመጪ ትውልዶችን ዕጣ ፈንታ ብሩህ ማድረግ የሚያስችሉ ጅማሬዎች እንደሆኑ ይታመናል።

ለውጦቹ እንደ ሀገር ለዘመናት አብሮን የተጓዘውን በኃይል እና በሴራ፤ በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ላይ የተመሠረተው የፖለቲካ ባህላችን ትውልዶችን ያስከፈለው ያልተገባ ዋጋ ዛሬ ላይ መካስ የሚያስችሉ፤ ከእኛም አልፎ በተመሳሳይ የፖለቲካ ጥፋት አዙሪት ውስጥ ለሚገኙ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ነው።

ድህነትና ኋላ ቀርነት መገለጫቸው በሆኑ ሀገራት የሚገኙ ባለትልቅ አዕምሮዎች፤ በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት በሚፈጥር ፍረጃ፤ በሀገራቸው ጉዳይ የበይ ተመልካች የሚሆኑበት፤ ከዚያም አልፈው የያዙትን ከፍ ያለ ዕውቀትና ክህሎት ይዘው ለስደት የሚበቁበት ሁኔታ የተለመደ እና ዓመታትን እያስቆጠረ ያለ ነው።

እነዚህ ባለ አዕምሮዎች ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማገልገል ያላቸው የተነቃቃ ማንነት በጊዜ ሂደት ውስጥ እየተቀዛቀዘ፤ እስከ መሻታቸው ሲያልፉ ማየት እንግዳ ጉዳይ አይደለም። ይህም በሀገራቸው የአዕምሮ ግንባታ ውስጥ ከሚፈጥረው ክፍተት ባላነሰ፤ አዕምሮው ሊፈጥረው የሚችለውን ሀገራዊ አቅም የዜሮ ድምር ያደርገዋል።

ሀገራችንም በዚህ በኩል ከፍተኛ ዋጋ ለመክፈል ከተገደዱ ሀገራት በዋነኛነት ተጠቃሽ ናት። ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በለውጥ ስም በተለያዩ ወቅቶች በተካሄዱ ኃይልን መሠረት ያደረጉ የፖለቲካ ንቅናቄዎች፤ በአመለካከታቸው ምክንያት ብዛት ያላቸው ባለ ምጡቅ አዕምሮዎች ለስደት፤ የተቀሩትም ሀገር ቤት ተቀምጠው፤ በሀገራቸው ጉዳይ የበይ ተመል ካች ለመሆን የተገደዱበት ሁኔታ ሰፊ ነበር።

አብዛኞቹ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን የማገልገል ጥልቅ ፍላጎት ቢኖራቸውም፤ ሀገሪቱ ውስጥ ከነበረው የፖለቲካ እሳቤ የተነሳ ማድረግ የፈለጉትን ማድረግ ሳይችሉ እንደወጡ የቀሩ ቁጥራቸው ብዙ ነው። በሀገር ውስጥ ሆነውም በብዙ ቁዘማ ዘመናቸውን የጨረሱም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።

ይህ ከአሮጌው የፖለቲካ አስተሳሰባችን የተቀዳውንና ሀገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ ያስከፈለውን የፖለቲካ ባህል ለመለወጥ የለውጥ ኃይሉ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የሄደበት እና እየሄደበት ያለው አዲስ የፖለቲካ እሳቤና እሳቤው የፈጠረው ተጨባጭ እውነታ በዘርፉ የነበረውን ሀገራዊ ስብራት በመጠገን ሂደት ውስጥ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።

ይህ የመንግሥት/የብልጽግና አዲስ የፖለቲካ መንገድ አቅም ያላቸውን ዜጎች በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ምክንያት ከመሰደድና በሀገራቸው ጉዳይ የበይ ተመልካች ከመሆን ወጥተው ባላቸው አቅም ለከፍተኛ ለመንግሥት ኃላፊነት የሚበቁበትን፤ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ባላቸው እውቀትና ክህሎት የሚያገለግሉበትን ዕድል መፍጠር ያስቻለ ነው ።

ለዚህም በቀደመው ጊዜ የተፎካካሪ ፓርቲ አባል የሆኑትን፤ ከኢዜማ፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን የትምህርት ሚኒስትር ፤ ከአብን ፣ ዶ/ር በለጠ ሞላን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር፤ ከኦነግ አቶ ቀጀላ መርዳሳን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አድርጎ መሾሙ፤ በዚህም አዲስ የፖለቲካ ባህል መጀመሩ ይታወሳል።

ከዚህም ባለፈ ከትናንት በስቲያ የብልጽግና ፓርቲ አባል ያልሆኑትን አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ዶ/ር መቅደስ ዳባን የጤና ሚኒስትር አድርጎ በመሾም ፤ ባላቸው ከፍ ያለ እውቀትና የዳበረ ልምድ ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ የሚያስችል ተጨማሪ አዲስ የፖለቲካ ባህል ተግባራዊ አድርጓል።

ውሳኔው ከፓርቲ ታማኝነት ባለፈ ዜጎች ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ታማኝ በመሆን፤ ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን ማገልገል የሚያስችላቸውን ዕድል መፍጠር ያስቻለ የብልጽግና /የገዥው ፓርቲ አዲስ አካሄድ፤ ብዙ አቅም ኖሯቸው ሀገራቸውን ማገልገል ለሚሹ ዜጎች ትልቅ ብስራት ይዞ የመጣ ነው።

ይህ እያደገ የመጣ የፖለቲካ ባህል የሀገሪቱን የቀደመ የመገፋፋትና በጠላትነት የመተያየት የፖለቲካ ባህል በመለወጥ፤ የሀገር ዕድገት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን በተጨባጭ ማሳየት ያስቻለ፤ ዜጎችም ሀገራቸውን ባላቸው አቅም በማገልገል፤ ከዚህ የሚገኘውን ደስታ እንዲያጣጥሙ የሚያስችል ነው !

አዲስ ዘመን  የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You