እንደምን ሰነበታችሁ … የ2011 ዓ.ም ግንቦት ወር ቆይታውን እያጠናቀቀ ነው። ታዲያ ለዛሬ ግንቦት ወር ከማለቁ በፊት በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ታሪክ ጉልህ ስፍራ የያዘው አንጋፋው አዲስ ዘመን ጋዜጣና ግንቦት ስላላቸው ታሪካዊ ቁርኝት በጥቂቱ ላካፍላችሁ።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ 78 ዓመታት ያስቆጠረ አንጋፋ የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ነው። ይህ አንጋፋ ጋዜጣ የተመሰረተው በግንቦት የመጨረሻ ቀን (ግንቦት 30 ቀን) 1933 ዓ.ም ነው። በራሷ አገር በቀል ቋንቋ የሚታተም የ78 ዓመት እድሜ ያለው ጋዜጣ ያላት አፍሪካዊት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ትቀራለች? ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በስደት ከቆዩበት እንግሊዝ አገር ከተመለሱ ከአንድ ወር በኋላ አዲስ ዘመን ጋዜጣ መታተም ጀመረ።
በጋዜጣው የመጀመሪያ ዕትም የመጀመሪያ ገጽ ላይ ንጉሰ ነገሥቱ በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ምክንያት ከአምስት ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ አዲስ አበባ ሲገቡ የሚያሳየውን ፎቶግራፍ እና ስለጋዜጣው ዓላማ የሚገልፅ ጽሑፍ ወጥቶ ነበር። በጽሑፉ ውስጥ ከተካተቱ ሃሳቦች መካከልም የሚከተሉት ይገኙበታል።
‹‹ይህ አዲስ ዘመን ተብሎ የተሰየመው ጋዜጣ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ለመላው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የረዳትነቱን ስራ ይሰራ ዘንድ ተመሰረተ። ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ለኢትዮጵያ አዲስ በሆነው ዘመን ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም የሚያስፈልገውን ስራ ሁሉ እያመለከተ፤ ይልቁንም ሕዝብ ለአገሩ፤ ለመሪውና ለንጉሰ ነገሥቱና ለንጉሰ ነገሥቱም መንግሥት ማድረግ የሚገባውን እየገለፀ የበጎን ስራ መንገድ የሚመራ እንዲሆን ይህ ጋዜጣ በግርማዊ ንጉሰ ነገሥት ተመሰረተ። ስራውም በሦስት ቃሎች ይጠቃለላል።
እውነት፤ ረዳትነትና አገልግሎት። እውነት ስንል በዚህ ጋዜጣ የሚነገረው ነገር ሁሉ መሰረቱ በፍጹም እውነትን እየተከተለ ለአንድ ጥቅም ብቻ ያልሆነና ለመላው ጥቅም የሚሰራ እንዲሆን ነው። አገልግሎት ስንል የኢትዮጵያን ነፃነት ለመመለስ ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው የራሳቸውን ጥቅም ሁሉ አስወግደው ለሕዝባቸውና ለአገራቸው ሲሉ የሰው አቅም ሊሸከመው የማይችለውን ድካም ተቀብለው ማንኛውም ሰው ሊያደርገው ያልተቻለውን በኢትዮጵያ ሕይወት ውስጥ እስከዛሬ ድረስ ያልታየውን ስራ ከፍፃሜ ላደረሱ ለተወደዱ ንጉሰ ነገሥታችንና ላቆሙት መንግሥት የሚያገለግል እንዲሆን ነው።
ግርማዊ ንጉሰ ነገሥታችን ሚያዝያ 27 ቀን አዲስ አበባ ገብተው ለሕዝባቸው ሲናገሩ “ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁም ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው። በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈፀም ያለብን አዲስ ስራ ይጀመራል” ብለው ነበር።
በጋዜጣው የመጀመሪያው ዕትም ላይ እንደሰፈረው፤ ጋዜጣው “አዲስ ዘመን” የሚለውን ስያሜ ያገኘው ንጉሰ ነገሥቱ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ ሲገቡ ከተናገሩት ንግግር ጋር በተያያዘ ነው። ይህ አንጋፋ ጋዜጣ ከ1933 ዓ.ም ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በአማርኛ እየታተመ ለአንባቢያን በመድረስ ላይ ይገኛል።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስም ሲነሳ አንጋፋውና ዝነኛው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ መነሳቱ አይቀርም። ጳውሎስ ኞኞ ይችን ዓለም የተሰናበተውም በዚሁ በግንቦት ወር ነው። በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ታሪክ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ፀሃፌ ተውኔት፣ ሰዓሊ፣ የታሪክ ፀሐፊ … ጳውሎስ ኞኞ ያረፈው ግንቦት 29 ቀን 1984 ዓ.ም ነው።
ከግሪካዊው መርከበኛ ኞኞ እና ከወይዘሮ ትበልጫለሽ አንዳርጌ ኅዳር 11 ቀን 1926 ዓ.ም በቁልቢ ገብርኤል አካባቢ የተወለደውና የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የነበረው ጳውሎስ ኞኞ፤ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ታሪክ ያለው ቦታ ግንባር ቀደም ነው። እናቱ ያወጡለት ስም “አማረ” የሚል ነበር።
የጳውሎስ ኞኞ ስም ሲነሳ ወደአብዛኛው ሰው አዕምሮ የሚመጣው በቀለም ትምህርት ብዙም ሳይገፋ በድፍን ኢትዮጵያ ዝነኛና ተወዳጅ ለመሆን ያበቃው የጋዜጠኝነት ስራው ነው። በዘመናዊ ትምህርት ከአራተኛ ክፍል ያልተሻገረው ጳውሎስ፤ በተፈጥሮ የታደለው የማንበብ፤ የመጠየቅና የመመራመር ተሰጥኦ በጋዜጠኝነት ሙያው አንቱታን አትርፎለታል።
በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሁም በኢትዮጵያ ሬዲዮ ሰርቷል። በተለይ ደግሞ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይሰራበት የነበረው “አንድ ጥያቄ አለኝ” የተባለው አምድ ተወዳጅነትንና ታዋቂነትን አትርፎለታል።
“ጋዜጠኝነትስ እንደጳውሎስ!” የተባለለት ይህ ሰው፤ በርካታ መጻሕፍትንና ትያትሮችንም ለአንባቢያን አበርክቷል። ከመጽሐፍቱ መካከል “የሴቶች አምባ”፣ “አጤ ምኒልክ”፣ “አጤ ቴዎድሮስ”፣ “አስደናቂ ታሪኮች”፣ “የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት”፣ “አጤ ምኒልክ ከውጭ ሀገራት የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች”፣ “አጤ ምኒልክ ከሀገር ውስጥ የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች”፣ “አራዳው ታደሰ እና የጌታቸው ሚስቶች”፣ “የኔዎቹ ገረዶች”፣ “ቅይጥ”፣ “ምስቅልቅል”፣ “እንቆቅልሽ” ፣“ድብልቅልቅ”፣ “እውቀት”፣ … ዋናዎቹ ናቸው።
ለሕትመት ከበቁት ስራዎቹ በተጨማሪ፣ ያልታተሙት ስራዎቹም በርካታ ናቸው። ከነዚህም መካከል ‹‹የአጤ ዮሐንስ ታሪክ››፣ ‹‹የአዲስ አበባ ታሪክ››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ››፣ ‹‹ሰዎቹ››፣ ‹‹የልጅ ኢያሱ ታሪክ›› እና ‹‹አዜብ›› ይጠቀሳሉ።
በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰውና ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ የሆነው የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክቶች በውስጡ ሰርፀው እንደቀሩ በተደጋጋሚ ተናግሯል። በተለይም ‹‹ሁሉን እወቅ፤ የሚሆንህን ያዝ›› ለሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት የተለየ ትኩረትና ፍቅር እንደነበረው ገልጿል። ጳውሎስ ኞኞ ከትዳር አጋሩ ወይዘሮ አዳነች ታደሰ ያፈራውን ልጁን ስሙን ‹‹ሐዋርያው›› ብሎ በመሰየም ለሐዋርያው ጳውሎስ ያለውን ፍቅርና አድናቆት ገልጿል።
መንገድ ላይ ወድቃ የሚያገኛትን ቁራጭ ወረቀት ሁሉ በማንሳት ማንበብ ልማዱ የነበረው ይህ አንጋፋ ባለሙያ ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችንም ይናገር ነበር። ከዚህም በተጨማሪ አብዝቶ ጠያቂና ተመራማሪ እንደነበር ይነገርለታል። በሁሉም ጉዳዮች ላይ ለሚጠየቃቸው ጥያቄዎች ምላሾችን ከበቂ ማብራሪያዎች ጋር የመስጠት ብቃቱ ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ በእጅጉ የተለየ ያደርገዋል።
ጳውሎስ የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር በተባ ብዕሩ ሞግቷል። ይህ ተጋድሎውም ለማስፈራሪያ፣ ለዛቻና ለእንግልት ዳርጎታል። ጳውሎስ ጋዜጠኛ ብቻ አይደለም፤ ብዙ የሙያ ዓይነቶችን ከባለሙያዎቹ ባላነሰ መልኩ ይከውን ነበር ይባላል። ግልፅነት፣ ድፍረት፣ ለወገንደራሽነትና ጨዋነትም የጳውሎስ መገለጫዎች እንደነበሩ ብዙዎች ምስክር ናቸው። በድርቅና በረሀብ ለተጎዱ እንዲሁም ጠያቂና ዘመድ ለሌላቸው ሰዎች ደራሽ ነበር።
ጳውሎስ የትዳር አጋሩንና ትዳሩን አክባሪ፣ ለታሪክና ለባህል ተቆርቋሪ፣ ለማኅበራዊ ሕይወት መጠንከር ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ሰው ነበር። የዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ አድናቂ እንደነበርም በተደጋጋሚ ተናግሯል። እንደሚያደንቅ ይገልፅ ነበር።
አንድ ታላቅ የአገራችን ጋዜጠኛ ‹‹ጋዜጠኛ ከሆኑ አይቀር እንደ ጳውሎስ ነው፤ በዚህ በቴክኖሎጂ ዘመን እንኳ ጳውሎስን የሚተካ ጋዜጠኛ/ሰው እስካሁን አልተገኘም›› ብለው ነበር። ለእውነት ሟች የነበረው ጳውሎስ፣ በመጨረሻዎቹ የእስትንፋሱ ቀናት እንኳ ‹‹እኔ እንደማልድን አውቀዋለሁ፤ ግን ብሞትም እውነት እየተናገርኩ ነውና ከሞትኩ ነፍሴ አትጨነቅም›› ብሎ ነበር።
ወርሃ ግንቦትና አንጋፋው ጋዜጣ አዲስ ዘመን ይህ ዓይነት ታሪካዊ ቁርኝት አላቸው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2011
አንተነህ ቸሬ