ዕዳን ወደ ትውልድ ላለማስተላለፍ የተያዘው አቋም የሚበረታታ ነው!

 በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ከመጣበት ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ7 በመቶ በላይ እያደገ መሄዱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ሀገሪቱ በበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት ይህን መሰል ዕድገት ማስመዝገብ መቻሏ እንደ ሀገር ጠንካራ ሥራ መሠራቱን የሚያመላክት ነው፡፡ ቀላል የማይባለው የሀገሪቱ ክፍል በጦርነትና በጸጥታ ችግር ውስጥ ሆኖ በቆየበት ወቅት ከስድስት በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉ ከለውጡ ወዲህ የተቀየሱ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤታማ መሆናቸውን የሚያመላክት ነው፡፡

ከለውጡ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታ የማታውቀውን ከወጭ ንግድ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ አግኝታለች፡፡ ሀገሪቱ ፍጹም ሰላም በነበረችባቸው ዓመታት እንኳን ከወጭ ንግድ ሲገኝ የነበረው ዓመታዊ ገቢ ከሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ዘሎ አያውቅም፡፡

ከ2010 ዓ.ም በኋላ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብቶች እንድታጤንና ለውጭ ገበያም በስፋት እንድታቀርብ ዕድል ከመክፈቱም ውጪ በከፍተኛ ወለድ ስትበደር የነበረበትን አካሄድ በማቆም በአንፃሩ የልማት አጋሮቹ ከሆኑት ዓለም አቀፍ ተቋማትና ከመንግሥታት ትብብር በአነስተኛ ወለድ ለረዥም ጊዜ በሚሰጡት ብድሮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡

የዓለም ባንክ በፈረንጆቹ 2020 ባወጣው መረጃ ኢትዮጵያ ከሀገር ውስጥና ከውጭ የወሰደችው ብድር 56.6 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ይህም በአብዛኛው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ብድር የሚከፈልበት የብድር ዓይነት መሆኑ ችግሩ ለትውልድ የሚሻገር ጭምር ነው፡፡ ባለፈው መንግሥት የተወሰደውን ብድር ተጠቅሞ ተጨማሪ ገቢ ማስገባት አለመቻሉ፤ በቂ ሥራ አለመፈጠሩና ገንዘቡ የውጭ ምንዛሬ አለማምጣቱ ለትውልድ ተሻግሮ ችግር ፈጥሯል፡፡

ይህንኑ በመረዳት በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ከተደረገበት ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ከየትኛውም ሀገር ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ ወለድ የሚያስከፍሉ ብድሮችን ሙሉ በሙሉ አቁሟል፡ ፡ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳረጋገጡት መንግሥት አንድም ዶላር በዚህ መልኩ አልተበደረም፡፡

ይልቁንም ከ2011 እስከ 2015 ባሉት ዓመታት በቀድሞ መንግሥት የተወሰደውን የተከማቸ ብድር ኢትዮጵያ ስትከፍል የቆየች ሲሆን፤ በእነዚህ ዓመታትም 9ነጥብ 9ቢሊዮን ዶላር ለአበዳሪዎች ከፍላለች፡ ፡ በዚህም ከሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት ውስጥ 32 በመቶ ይሸፈን የነበረውን የዕዳ መጠን ወደ 17 በመቶ ማውረድ ተችሏል፡፡ በቀጣይም መንግሥት የዕዳ መጠኑን ወደ 10 በመቶ ለማውረድ እየሠራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ከሚጎትቱ ፈተናዎች መካከል አንደኛው ባለፉት መንግሥታት የተወሰዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከፈሉና ከፍተኛ የወለድ ምጣኔ የሚታሰብባቸው የብድር ዓይነቶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በእነዚህ የብድር ዓይነቶች ተዘፍቃ የቆየች በመሆኑ ለልማት ሊውል የሚችለውን የበጀቱን 1/3ኛ ገንዘብ በየዓመቱ ይህንን ብድር ለመመለስ ተገዷል፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።

መንግሥት ካለው ውስን ገቢ ላይ በየዓመቱ ከበጀቱ 1/3ኛ የሚሆነውን ዕዳ ባይከፍል ኖሮ ኢትዮጵያ ተጨማሪ አዲስ የውጭ ብድር መውሰድ የማትችልበት የመጨረሻው ጫፍ ላይ ከመድረሷም ባሻገር ብድር መክፈል የማይችሉ ሀገሮች ተርታ ውስጥ የመውደቅ አደጋ ይገጥማት ነበር።

ይህ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረግ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚጎዳ ከመሆኑም ባሻገር፣ ከዚህ ምድብ የመውጣት ሂደትንም አስቸጋሪ ያደርገዋል። በውጤቱም ኢትዮጵያ የምትፈልገውን የኢንቨስትመንት ካፒታል ከውጭ የምታገኝበት ዕድል ይዘጋል፣ የማትወጣው የኢኮኖሚ ፈተና ውስጥ ይከታታል፤ እንደ ሀገርም ውድቀት ይከተላል፤ ዕዳውም ለመጪው ትውልድ ይተርፋል።

በአጠቃላይ መንግሥት ከፍተኛ ወለድ የሚያስከፍሉ ኮሜርሻል ብድሮችን ሙሉ በሙሉ ማቆሙና የተከማቸው ዕዳ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዳይተላለፍ ካለው ውስን ሀብት ላይ እዳ ለመክፈል የወሰነው ውሳኔና እያደረገ ያለው ጥረት ሀገርንም፤ ትውልድንም የሚታደግ ተግባር በመሆኑ በእጅጉ ሊመሰገን ይገባዋል!

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You