“ዘንድሮ በጅማ ዞን ከአንድ ሔክታር 131 ኩንታል ሩዝ ተገኝቷል”

መሐመድጣሃ አባፊጣ የጅማ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ለማግኘት እና የሥራ እድልን ለመፍጠር ወሳኝ የሆነ ዘርፍ ነው፡፡ በተለይ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋና መሠረት በመሆኑ መንግሥት ዘርፉን ለማዘመን ብዙ ርቀት ተጉዟል፡፡ በተለይም በተለያዩ ክልሎች በበጋ ስንዴ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተገኝተዋል።፡

ከሰሞኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በተንቀሳቀሰበት ወቅት መዳረሻው ከሆነው አንዱ በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የጅማ ዞን ሲሆን፣ ዞኑ ከግብርናው ዘርፍ ጋር ተያይዞ እያካሔደ ያለውን ተግባር ለመቃኘት ሞክሯል፡፡ በዞኑ የአዝርዕት ልማትን በተመለከተ እና በተለይም በሩዝ እና በቡና ምርት እየተከናወነ ስላለው እንቅስቃሴ አዲስ ዘመን ከዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድጣሃ አባፊጣ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በግብርናው መስክ በዞኑ እየተከናወኑ ያሉ አንኳር ሥራዎች ምን ምንድን ናቸው?

መሐመድጣሃ፡- ግብርና ትልቅ ሴክተር ነው። ሰፊም ሕዝብም የያዘ ነው፡፡ እንደ ክልላችን አራት አንኳር ጉዳዮችን ለማሳካት ማዕከል አድርገን እየሠራን ነው፡፡ የመጀመሪያው ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ነው፤ እንዲህም ሲባል የሚጀምረው ከአርሶ አደሩ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ወረዳ፣ ዞንና ወደክልል እያለ ቀጥሎም ወደ ሀገር ይሄዳል፡፡ ትልቁ ነገር ግን በአባወራ ደረጃ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ላይ መሠረት አድርገን እየሠራን ነው። ሁለተኛው እንደሚታወቀው ሀገራችን የምትታወቀው ምርትን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ሳይሆን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ የግብርና ውጤቶችም ሆኑ ግብዓቶች ወደሀገራችን የሚገቡት በብዛት ነው። ትርፍ ምርቶችን በማምረት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት፤ እንዲሁም ወደ ውጭ የመላክ እና የሁሉም የግብርና ዘርፎች ከፍተኛ የሆነ የሥራ እድል የመፍጠር እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት አድርገን እየሠራ ነው፡፡

የጅማ ዞን የቡና መገኛ ነው፡፡ “ኮፊ አረቢካ” የተገኘው ጮጬ ከታ ሙድጋ በሚባልበት ቦታ ነው። ከዚህም የተነሳ የምንታወቀው በቡና ነው፡፡ ነገር ግን ዞናችን ያለው የመሬት ስፋት ወደ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ነው፡፡ በዞናችን ማንኛውም ምርት ከተመረተ ውጤት ማምጣት እንደምንችል በትንንሽ የአርሶ አደር ማሳ ሠርተን ማረጋገጥ ችለናል፤ በተለይ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት እንደክልላችን የተቀመጡ “ኢኒሼቲቮች” ሁሉም በሚያስብል ሁኔታ በዞናችን ይሠራሉ፡፡

ትልቁ ነገር እንደክልላችን የግብርና ችግሮች ምንድን ናቸው? በሚል ጥናት ተካሂዷል፡፡ ግብርናን ለማዘመንና ግቦቹን ለማሳካት ማነቆ የሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው? የሚሉት ተጠንተዋል፡፡ በዛ መሠረት ወደ ዘጠኝ ወሳኝ የሆኑ አካባቢዎች ተለይተው እነዛ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶባቸዋል፡፡ መሠራት አለባቸው ተብለው የተቀመጡ የግብርና ኢንሼቲቮች አሉ፡፡ እነዚያ ሁሉ በዞናችን ይሠራሉ።

ከዚያ ውስጥ ቁጥር አንድ የአዝርዕት ልማት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ አስር “ኢኒሼቲቮች” አሉ፡፡ እነዚያ አስሩም በዞናችን ይሠራሉ፡፡ ለምሳሌ በ2014/2015 የምርት ዘመን ጅማ ዞን ያረሰው 578 ሺ ሔክታር መሬት ነበር፡፡ ዘንድሮ ብቻ ያቀድናቸውን ግቦች ለማሳካት ከ200 ሺ ሔክታር በላይ በመጨመር ያረስነው 841 ሺ ሔክታር መሬት ነው። ከዚያ ውስጥ 135ቱ ሺ ሔክታር መሬት ላይ ያመረትነው ሩዝ ነው፡፡ ስንዴ፣ ገብስ እንዲሁም በቆሎም በዞናችን የሚመረት የሰብል አይነቶች ናቸው። ጅማ ዞን በጣም የሚታወቀው በበቆሎ ምርት ሲሆን፣ “ሜይዝ ቤልት” በሚልም ይታወቃል፡፡ የቅባት እህልን በተመለከተ እንደ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ ማሾ እና የመሳሰሉትን በብዛት ይመረታሉ፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው። በ2014/2015 የምርት ዘመን በሔክታር ይመረት የነበረው ወደ 31 ኩንታል ነው፡፡ በ2015/2016 የምርት ዘመን በሔክታር ይገኝ የነበረውን ወደ 31 ኩንታል፤ ቢያንስ ወደ 35 ኩንታል ማድረስ አለብን ብለን አቅደን ወደ 33 ነጥብ ስምንት ኩንታል ማግኘት ችለናል።

በዚህ መሠረት ዘንድሮ በመኸሩ በጅማ ዞን ብቻ በ2015/2016 የምርት ዘመን ከ31 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት ችለናል፡፡ ከአምናው ተመሳሳይ የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ልዩነት አለው፡፡ ዞናችን እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም እየታወቀ የመጣው በሩዝ ምርት ነው፡፡ ሩዝ የጀመርነው በ2013/2014 የምርት ዘመን በአራት ወረዳ ሲሆን፣ እሱም ይመረት የነበረው በሁለት ሺ በማይበልጥ ሔክታር መሬት ላይ ነው፡፡ አጋጣሚ ሆኖ በወቅቱ የተገኘው ውጤት ጥሩ ነው የሚባል ነበር፡፡ በ2014/2015 የምርት ዘመን ከሁለት ሺ ሔክታር ወደ 30 ሺ ሔክታር ስናሳድገው፤ በአራት ወረዳ ላይ ብቻ የተወሰነውን ወደ 12 ወረዳ ከፍ ማድረግ ችለናል። በ2015/2016 የምርት ዘመን ከ30 ሺ ሔክታር መሬት ወደ 235 ሺ ሔክታር መሬት በሩዝ መሸፈን የቻልንበት ነው፡፡

የዚህን እድገት ስናይ ጭማሪ ሳይሆን እያሳየ የመጣው ፈጣን የሆነ የምርት እድገት ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልልም አዲስ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራ ሥራ ተብሎ በዘንድሮ የመኸር ወቅት የዘር ምንጭ የነበረው የጅማ ዞን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የሩዝ ምርት በእጃችን አለ፡፡ ከዚህ የተነሳ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ የሩዝ አምራች ዞን ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡

ሌላው ከበጋ ስንዴ ጋር ተያይዞ ያለው ሥራ ሲሆን፣ የበጋ ስንዴ በዞናችን በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ይመረታል። እሱንም የጀመርነው ከአራት ዓመት በፊት ነው፡፡ በ2012 የምርት ዘመን 50 ሔክታር መሬት ላይ የጀመርን ሲሆን፣ በአሁን ወቅት ወደ 441 ሺ ሔክታር መድረስ ችለናል። በምርቱም ሆነ በምርታማነቱ እንዲሁም በሽፋን ረገድ በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራንበት ነው፡፡ አራቱ የግብርና ምሰሶዎች የምንላቸው ማለትም ምርትን መጨመር፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ኤክስፖርት ማድረግ እና ኢምፖርትን መቀነስ ሲሆን፣ ከዚህ ባለፈ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ መሥራት አለብን የሚለውን በአዝርዕት ልማቱ ማሳካት ችለናል ማለት ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ቡና ብቻ ሳይሆን ስንዴን ወደ ውጭ ኤክስፖርት ማድረግ የቻልንበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ሌሎችንም የግብርና ውጤቶች ወደውጭ የመላክና ለሀገር ውስጥም በከፍተኛ ሁኔታ እያቀረበ ያለ ዞን ነው፡፡ እነዚህ በተለይ ስንዴና ሩዝ እንደኢኒሼቲቭ የተመረጡ ናቸው፡፡ ዘንድሮ በዞናችን ከአንድ ሔክታር መሬት የተገኘው ከፍተኛው የሩዝ ምርት 131 ኩንታል ነው፤ ዝቅተኛ ምርታማነቱ ደግሞ 42 ኩንታል ነው፡፡

የጤፍ ምርትን በተመለከተ ደግሞ የፈለግነውን ያህል ቴክኖሎጂ ብንጠቀም በሔክታር የሚገኘው ምርት ከ10 እስከ 15 ኩንታል ነው፡፡ እንደሚታወቀው የሕዝብ ብዛት ደግሞ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ በሒደት የከተማው ነዋሪ የገጠሩን ይበልጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ትናንት በለመድነው የግብርና ሥራ የምንቀጥል ከሆነ ግብርናችን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አይችልም፡፡ ግብርናችን እያደገ ያለውን የሕዝብ ቁጥር መሸከም ስለማይችል ከለመድነው የምርታማነት አሠራር መውጣት ይኖርብናል፡፡

ለምሳሌ በምስራቁ ያለው የዓለማችን ክፍል የሚመረተው በብዛት ሩዝ ነው፡፡ ቻይና በአሁኑ ወቅት የሕዝብ ቁጥሯ አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ነው። ከአንድ ሔክታር ከ130 በላይ የማታመርት ከሆነ ሕዝቧን መቀለብ አትችልም፡፡ የእኛም የሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ለዚህ መፍትሔ ሊሆን የሚችለውን መላ መፍጠር የግድ ነውና እኛም ምርታማነቱን በስፋት ሊሰጥ ወደሚችለው የሩዝ ምርት ትኩረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡

ትናንት የነበረን የአመጋገብ ስልት ሰው እንጀራ ይበላ የነበረው ጤፍን ከማሽላ ጋር ቀላቅሎ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከጤፍ ጋር የሚቀላቀለው ሩዝ ሲሆን፣ እሱም የጤፍን ግማሽ በመያዝ 50 እጅ መሆን ችሏል። ከዚህ የተነሳ ሩዝ ማምረት ብቻ ሳይሆን ወደየሰው የምግብ ጠረጴዛም እንዲመጣ ማድረግ በማስፈለጉ ያንን እያደረግን ነው፡፡

በስንዴውም እንደዛ ነው፡፡ በሔክታር 83 ኩንታል በዞናችን ያገኘን ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ከፍተኛው ነው። ማንኛውም አርሶ አደር ጠንክሮ ከሠራ ከ83 እስከ 85 ኩንታል በሔክታር ያገኛል፡፡ በአማካይ ግን እንደዞናችን ያለነው በሔክታር 39 ኩንታል ላይ ነው፡፡ ስንዴ ከበቆሎ ቀጥሎ በአገራችን የምንመገበው ምርት ነው። ስንዴ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ዳቦ ከመሆኑም በተጨማሪ ምርታማነቱ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ምዕራባውያን ደግሞ በብዛት የሚያመርቱትም ሆነ የሚመገቡት ስንዴን ነው። ስለዚህ እኛ ምሥራቁ የዓለም ክፍል የሚጠቀመውን ሩዝንም ሆነ ምዕራቡ ዓለም የሚጠቀመውን ስንዴ በስፋት ማምረት እየጀመርን ነው፡፡ ያለው ሁኔታ ደግሞ ጭማሪ እያሳየ ነው፡፡ አርሶ አደሩም እየለመደው ነው፡፡ ስለሆነም አሁን የጀመርነውን አቅጣጫ የምንከተል ከሆነ አራቱን በምሰሶነት የያዝነውን እቅድ እናሳካለን የሚል እምነት አለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በጅማ ዞን የተፋሰስ ሥራን በተመለከተ በይፋ ወደሥራ መገባቱ ተገልጿልና ከተፋሰስ ሥራ ጋር በተያያዘ የተከናወነው ምንድን ነው?

መሐመድጣሃ፡- በተፈጥሮ ጨዋማነት የተጠቁ የአፈር አይነቶችን ምርታማነት ከመጨመር አንጻር በዞናቸው በጣም በከፍተኛ ሁኔታ በመሠራት ላይ ነው። ከለውጡ ወዲህ የአፈር ምርታማነትን ለመጨመር በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራን ነው፡፡ የ2016ን የተፋሰስ ልማት ጅማ ዞን፣ ኦሙናዳ በሚባል ወረዳ ውስጥ ጀምረናል፡፡ ዘንድሮ 510 ተፋሰሶችን ለይተን በ510 ቀበሌዎች ውስጥ በጂ.ፒ.ኤስ የሚሄዱትን ቢያንስ 255 ሺ ሔክታር እንሸፍናለን፡፡ በኪሎ ሜትር ደግሞ 116 ኪሎ ሜትርን የተለያዩ ውሃ የሚቆጥቡ፣ የሚያቁሩ ሥራዎችን እንሠራለን ብለን አቅደናል፡፡ በተፋሰስ ልማቱ ወጣት፣ ሴት፣ የመንግሥት ሠራተኛ፣ ነጋዴዎችና የከተማ ነዋሪዎች ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ በተፈጠረውም ንቅናቄ ወደሥራ ገብተናል፡፡ አርሶ አደሩ ከዚህ ሥራ ጋር በተያያዘ ያለው አስተውሎት ጥሩ የሚባል ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፉት ዓመታት በተሠራው ሥራ እንደ ሩዝ አይነት ምርቶች በዞናችን እንዲመረቱ ያደረጉት በአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራችን ነው፡፡ ምርቶች እንዲጨምሩ የሆኑበት ምክንያት በአፈር እና ውሃ ጥበቃ ላይ በተሠራው ሥራ ነው፡፡ ይህ የዘንድሮውም የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራ የሚቆየው ለሁለት ወር ነው። በበጎ አድራጎት ሥራ ማዕቀፍ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ እንደየቀበሌው ነባራዊ ሁኔታ እየታየ በሳምንት ሁለት እና ሦስት ቀን በተፋሰስ ሥራ ላይ የሚሰማሩ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በዞኑ የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል እየተሠራ ያለ ሥራ ካለ ቢገልጹልን?

መሐመድጣሃ፡- ከአፈር አሲዳማነት ጋር ተያይዞ በዞናችን አንድ የሚታወቅ ነገር አለ፤ እሱም የፐርሚ (ትል) ኮምፖስት ሥራ ሲሆን፣ በጣም እየተሠራበት ነው፡፡ ከዚህም የተፈጥሮ ማዳበሪያ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራን እንገኛለን፡፡ መደበኛው የኮምፖስት ሥራ ደግሞ አለ፡፡ በዚያ ላይም እየሠራን ነው፡፡ ዞናችን ከፍተኛ የሆነ ዝናብ የሚያገኝ ነው፡፡ ስለዚህ ዝናብ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያገኙት የምዕራብ ኢትዮጵያ ጅማን ጨምሮ ኢሉ አባቦር፣ አራቱ ወለጋ ዞኖች እና ደቡብ አካባቢን በአሲዳማነት የተጠቃ መሬት ነው፡፡ ምክንያቱም ዝናብ እየዘነበ ሲሄድ ለአሲዳማነት ይጋለጣል፡፡ አፈሩ በየጊዜው እየተጠቃ ስለሚሄድ ከአራት ሺ አንድ መቶ የአርሶ አደር ማሳ ከሁለተኛው ሩብ ዓመት እስከ ሦስተኛው ሩብ  ዓመት፤ በሁለተኛው ሩብ ዓመት እስከ ሁለተኛው ሩብ ዓመት የአፈር ናሙና ወስደው አጥንተናል፡፡ በ90 ከመቶ በላይ የዞናችን መሬት በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የተፈጥሮ ማዳበሪያና የፐርሚ ኮምፖስትን በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቀምን ነው። እስካሁን ቢያንስ ከ350 ሺ ኩንታል በላይ ፐርሚ ኮምፖስት አምርተናል፡፡ ከ15 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ መደበኛ ኮምፖስት አምርተናል፡፡ ይህንንም አንድ ላይ አያይዘን እየተጠቀምንበት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከእንስሳት እርባታ ጋር ተያይዞ ያለው እንቅስቃሴም ሆነ ለአርሶ አደሩ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ምን ይመስላል?

መሐመድጣሃ፡- በዞናችን በከፍተኛ ሁኔታ በእንስሳት እርባታው ዘርፍ እየተሠራ ይገኛል። የጀመርነው ከማር ልማት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ጅማ ከፍተኛ የሆነ የደን ሽፋን ያለበት ዞን ነው፡፡ የትኛውንም አርሶ አደር ኑሮ መለወጥ እንደሚቻል ተጠንቶ “የጅማ ዲክላሬሽ” በሚል “ኦሮሚያን የማር ባሕር እናደርጋለን!” ተብሎ በ2013 ዓ.ም ጅማ ላይ ይፋ የተደረገ መርሐግብር አለ፡፡ በዚህም ከባሕላዊ የንብ ቀፎ ወደዘመናዊ ቀፎ አርሶ አደሩ እንዲሻገር እና መንግሥት ደግሞ ዘመናዊ የንብ ቀፎ የሚሠራበትን ግብዓት ለአርሶ አደሩ እንዲያቀርብ ተደረገ፤ አርሶ አደሩ ደግሞ ለዘመናዊው የንብ ቀፎ የእጅ ዋጋ ብቻ እየከፈለ እየተጠቀመ ወደሥራ እንዲገባ የማድረግ ሥራ ተጀመረ፤ በአሁኑ ወቅት በዚህ አግባብ እየተሠራ ነው፡፡

በ2013 ዓ.ም ወደዚህ ሥራ ስንገባ በዞናችን ወደ 62 ሺ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ነበረን፡፡ በዚህ ዓመት ወደ 13 ሺ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ችለናል። በ2014 ዓ.ም ወደ 62 ሺ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ለአርሶ አደሩ አቅርበናል፡፡ በ2015 ዓ.ም አምና ያሰራጨነው 84 ሺ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በስድስት ወር ውስጥ ቢያንስ 167 ሺ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ወደ አርሶ አደሩ ዘንድ ማድረስ ችለናል። ዘመናዊ የንብ ቀፎ ለምርቱ ነው። እኛ ባካሔደነው ቅኝት መሠረት ከአንድ ባሕላዊ የንብ ቀፎ የሚገኘው ማር ሰባት ኪሎ ግራም ነው፡፡ በዞናችን በማር ምርት በተለያየ ወረዳ አቅም ያላቸው አርሶ አደሮች አሉን፡፡ 93 ኪሎ ግራም ከአንድ ዘመናዊ ቀፎ ተገኝቷል። ስለዚህ ነው ከባሕላዊ ወደ ዘመናዊ የተላለፍነው፡፡ 93 ኪሎ ግራም ያለን አቅም ሲሆን፣ በአማካይ ግን 33 ኪሎ ግራም ይገኛል፡፡

ዘንድሮ ወደ 54 ሺ ቶን ማር ይገኛል ብለን እየሠራን ነው፡፡ ከዚያ ውስጥ አስር ሺ ቶኑ ለውጭ ኤክስፖርት የሚቀርብ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ምርቱ የሚቆረጥበት ሰዓት እየደረሰ ነው፡፡ ኤክስፖርት ለማድረግ ከአንድ ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራርመናል፡፡

በእንስሳት ዘርፉ ሁለተኛው እየሠራን ያለነው ከዝርያ ማሻሻል ጋር ተያይዞ ያለውን ሥራ ነው፡፡ ዘንድሮ ለኅብረተሰቡ ከ217 ሺ ላሞች በላይ መስጠት ችለናል። እንደሚታወቀው የወተት እጥረት በዞናችን አለ፤ ምክንያቱም እኛ የምንጠቀመው በአካባቢ የሚገኘውን የላሞች ዝርያን ነው፡፡ በአካባቢ የሚገኙ ዝርያዎች ደግሞ ምርታማነቻው በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ቢያንስ አንድ አርሶ አደር በቀን ከአንዲት ላም ሊያገኝ የሚችለው አንድ ሊትር ወተት ወይም ከዚያም በታች ሊሆን ይችላል። ቢበዛ እስከ አንድ ነጥብ አምስት ሊትር ወተት ድረስ ቢሄድ ነው። እሱንም ላሞቹ ቁጡ ስለሆኑ እና ታስረው የሚታለቡ በመሆናቸው ሲንቆራጠጡ ወተቱን ሊደፉት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እሱን ዝርያ ማሻሻል አለብን፡፡

ስለዚህ የአካባቢን ዝርያ ከሆሊስቲን ፊሪጂያን እና ጀርሲ ከሚባሉ ከውጭ ከመጡ ከብቶች ጋር እያዳቀልን እንገኛለን፡፡ የመጀመሪያው ትውልድ የሆነው 50 በመቶ የውጪውንና 50 በመቶ የአካባቢው የያዘ ነው። ሁለተኛው ትውልድ ደግሞ ወደ 75 በመቶ ከፍ ማለት ቻለ። እነዚህ በቀን በትንሹ እስከ 11 ሊትር ወተት መስጠት ቻሉ። ሦስተኛው ትውልድ የሚባለው ደግሞ ወደ 82 ነጥብ አምስት ሊትር ወተት ማግኘት ያስቻለ ነው፡፡ ስለዚህም ለምርቱም ለዝርያውም የማሻሻል ሥራ እየሠራን እንገኛለን። በሁሉም ወረዳዎች የዝርያ መሻሻል ክላስተሮች አሉን፡፡ በዛም ከፍተኛ የሆነ ተሞክሮ አለን።

በወተት ምርት ዘንድሮ በዓመቱ መጨረሻ ወደ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ሊትር ወተት እናገኛለን ብለን አቅደናል፡፡ ይህ በስድስት ወር ወደ 560 ሚሊዮን ሊትር ወተት ላይ እንገኛለን፡፡ በዞኖችን የማደለቡ ሥራ በጣም የተለመዱ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቡና ምርታማነት ላይ የተደረገ ማሻሻያ ካለ ቢያብራሩልን?

መሐመድጣሃ፡- ዞናችን በብዛት የሚታወቀው በቡና መገኛነቱ እንደመሆኑ የቡና ጂም ባንክ ያለበት ነው። አያድርገውና በዓለማችን ቡና ቢጠፋ በዞናችን ያለው ቡና ጂም ባንክ መፍትሔ መሆን ይችላል። ይህ ጂም ባንክ ከስድስት ሺ 500 በላይ ዝርያዎች የተከማቹበት ነው፡፡ ይህም ጂም ባንክ የሚገኘው ጮጬ ከታ ሙዱጋ የሚባል ላይ ነው፡፡

የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በርካታ ሥራዎችን መሥራት ችለናል። የሠራነውን ሥራ ለመጥቀስ ያህል በመጀመሪያ አርሶ አደሩ ዘንድ ያለውን የቡና አመራረት ምልከታን መቀየር ነበር፡፡ አርሶ አደሩ ዓለም አቀፍ የቡና ጥራት ውድድርን እንዲሳተፍ ለማድረግ መጀመሪያ የቡና ብዛት ላይ ሳይሆን ጥራት ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ሠርተናል፡፡ አርሶ አደሩ ብዛት እንጂ ጥራት ላይ ትኩረት ያለማድረጉን አተያይ ለመቀልበስ በተደረገው ጥረት የዓለም አቀፍ የቡና ውድድር ውስጥ እንዲገባ አድርገናል፡፡ ቢያንስ 150 አርሶ አደሮችን አምና ማሳተፍ ችለናል፡፡

እነዚያ አርሶ አደሮች 30ዎቹ ምርጥ 50 ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሦስቱ ደግሞ እንዲሁ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ አስር ውስጥ መግባት ችለዋል፡፡ አስር ውስጥ ከገቡ ሦስቱ አርሶ አደሮች ውስጥ አንደኛው የወጣው ሦስተኛ ነው፡፡ ይህም አርሶ አደር ጌራ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን፣ አንድ ኪሎ ግራም ቡና የሸጠው ሰባት ሺ ብር ነው፡፡ ስለዚህ ቡና ጥራቱን መጠበቅ ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለራስም የሎተሪ መድረስ ያህል ነው፡፡ ይህ አርሶ አደር፣ እንዲያቀርብ የተፈቀደለት አንድ ሺ 40 ኪሎ ግራም ቡና ነው፡፡ ሁለቱ አርሶ አደሮቻችን የወጡት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ነው። ስለዚህ 50 ምርጥ ውስጥ የገቡ 30ዎቹ አርሶ አደሮች በየደረጃቸው ግማሹ 500 ኪሎ ግራም ቡና እንዲያቀርብ እየተደረገ ነው፡፡ ሌሎቹ አርሶ አደሮቻችን የእነርሱን ትጋት አይተው ተነሳሽነታቸው ጨምሯል፡፡ ሁሉም ቡናን በጥራት ወደማምረቱ እየገቡ ነው፡፡ እኛም አንዱ የሠራነው ሥራ ይህ ነው፡፡

ሌላው የሠራነው ሥራ ብራንዲግ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የጅማ ቡና ብራንድ አልነበረውም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጅማ ቡና የሚባል አይታወቅም ነበር፡፡ ነገር ግን በጣም ከፍተኛ የሆነ ሥራ በመሥራት ሦስት አካባቢዎች ጅማን እንዲያስጠሩ ሥራ መሥራት ተቻለ፡፡ ለምሳሌ በጅማ ከተማ አካባቢ፣ ሊሙ አካባቢ እና አጋሮ ጎማ አካባቢ ያለ ቡናን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ብራንዲንግ ሰጥቷቸዋል፡፡ ስለዚህ የጅማ ቡና፣ የከታ ሙድጋ ቡና እና የሊሙ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሸጠው በስሙ ነው፡፡

ሌላው የሠራነው ትልቁ ሥራ፤ እንደሚታወቀው ከፍተኛ ቡና የሚመረተው እዚህ ዞናችን ውስጥ ነው። ቡና ለመሸኘት ግን ቡናው የግድ አዲስ አበባ መድረስ አለበት፡፡ አዲስ አበባ ሳይደርስ የትኛውም ቡና ወደ ውጭ አይሸኝም፡፡ የዞናችን አርሶ አደሮች “ስለምን አዲስ አበባ ድረስ እንሄዳለን?” በሚል ይህን ጥያቄ ደጋግመው ያነሳሉ። ዩኒየኖችም ሆኑ ባለሀብቶች ይህንኑ ይጠይቃሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል “ከታ ሙድጋ” የሚባል ዩኒየን ቡናን በማቅረብ ረገድ እንደ ሀገር ታዋቂ ነው። ለመጋዘን ኪራይ ብቻ በዓመት አዲስ አበባ ላይ 150 ሚሊዮን ብር ይከፍላል፡፡ ምክንያቱም ቡና እዛ ካልደረሰ እና ካልተቀመሰ ወደ ውጭ ሀገር አይሄድም፡፡ ቡና ያለው ጅማ ነው፤ ቅምሻው ያለው አዲስ አበባ ነው፡፡

ይህ በመሆኑ አዲስ አበባ ድረስ የመሄድን ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት ከኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ጋር በመሆን ተወያየን፤ እንዲያ በመሆኑ ጅማ ላይ የቡና ቅምሻ ማዕከልና ሰርተፊኬሽን እንዲኖር በማድረግ ቀጥታ ከጅማ ወደ ወደብ እንዲሔድና እንዲሸጥ ማድረግ ችለናል። የተከፈተው የጅማ ማዕከል ብቻ ሳይሆን ሐዋሳ፣ ጊምቢ ላይም አለ፡፡ ከቦንጋ፣ ከኢሉ አባቡር እና ከበደሌ አካባቢ የሚመጣው ቡና ማዕከሉ ጅማ ላይ ሆኗል፡፡ ማዕከሉ የተከፈተው በ2015 ዓ.ም ስምንተኛው ወር ላይ ነው፡፡

ሌላው የሠራነው ነገር ከጅማ ዞን ቡናን ኤክስፖርት የሚያደርጉት 486 አርሶ አደሮች ሲሆኑ፣ እነዚህ አርሶ አደሮች ቡናቸውን ወደውጭ ሀገር የሚልኩት ቀጥታ ነው፡፡ ከሁለት ሔክታር በላይ ቡና ያላቸው አርሶ አደሮች ቡናቸውን ቀጥታ ወደ ውጭ ይልካሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል ቡናቸውን ለማስቀመስና ወደ ውጭ ሀገር ለመላክ ይሔዱ የነበረው አዲስ አበባ ነበር፡፡ ለምሳሌ አምና በዞናችን አንድ አርሶ አደር ቡናውን ወደ ውጭ አገር ልኮ ለሀገር አንድ ሚሊዮን ዶላር ያመጣ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ፣ አዲስ አበባ መሔድ አይጠበቅበትም፤ ጠዋት ላይ ጅማ ባለው ማዕከል ያቀርባል፤ ከሰዓት በኋላ ወደ ማሳው መመለስ ይችላል፡፡ እንደ ቀድሞው ከሥራው ተስተጓጉሎ ሦስትና አራት ቀን ሰዓቱ በመንገድ የሚያልቅበት ጊዜ አብቅቷል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቡናን በኩታ ገጠም የማልማቱ ሥራስ ምን ይመስላል?

መሐመድጣሃ፡- በሰብል ምርት ብቻ ሳይሆን ቡናንም በኩታ ገጠም ደረጃ በሰፊው እየሠራንበት ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የቡና የኤክስፖርት መጠናችንን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደግን እንገኛለን፡፡ ዘንድሮ ከቡና ገበያ ጋር ተያይዞ በብዛት ወደውጭ ኤክስፖርት አልተደረገም። እስካሁን ዘንድሮ ኤክስፖርት የተደረገው ወደ 75 ሺ ቶን ቡና ነው፡፡ እቅዳችን የነበረው ግን 205 ሺ ቶን ነው፡፡ ከገበያ እና ከዋጋ ጋር በተያያዘ ቡናው በብዛት ወደ ውጭ እየወጣ አይደለም። አምና ግን ወደ ውጭ ኤክስፖርት የተደረገው ከጅማ ዞን ብቻ 169 ሺ ቶን ቡና ነበር፡፡

ቡናን በኩታ ገጠም እየሠራንበት ያለው ወደ 39 ሺ ሔክታር መሬት ላይ ነው፡፡ አጠቃላይ እንደዞናችን 530 ሺ ሔክታር መሬት ላይ ቡና ተሸፍኗል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሆኑት አዲስ ቡናዎች ናቸው፡፡ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ከግማሽ በላይ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተከልናቸው ቡናዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ 39 ሺ ሔክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠሙ የተተከለ ነው፡፡ ይህንንም እያስፋፋን እየሄድን ነው፡

አዲስ ዘመን፡- በዞኑ የሻይ ምርትን በተመለከተ ምን እየተሠራ ነው?

መሐመድጣሃ፡- ሻይ ቅጠል ማምረት የጀመርነው በ2014 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ነው፡፡ አምና በ2015 ዓ.ም እንዲሁ የተከልን ሲሆን፣ በሁለት ዓመት ውስጥ የተከልነው ችግኝ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ነው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ 136 ሚሊዮን ችግኝ በአስር ሺ ሔክታር ላይ በክረምቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለመትከል አቅደናል። በ2014 ዓ.ም ላይ የተከልነው በአሁኑ ሰዓት የምሥራች መስጠት ጀምሯል፡፡ በሻይ ቅጠሉ በኩል በሀገራችን ደረጃ የሚታወቀው ጉመሮ እና ውሽውሽ ነው። ስለዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ችግኞችን ያመጣነው ከዚያው ነው፡፡

ዘንድሮ ግን ችግኙን እያፈላን ያለነው ራሳችን ነን። 136 ሚሊዮኑን ችግኝ የምናፈላው ራሳችን ነን። በ16 ወረዳዎች ወስጥ ችግኙን ለማፍላት አቅደናል። እንደሚታወቀው የሻይ ቅጠል የኢንዱስትሪ ምርት ነው፡፡ ስለዚህም ትንንሽ የሆኑ የሻይ ማምረቻ ማሽኖች እንዲመጡ እያደረግን ነው።

እንደ ዓለማችን በሻይ ምርት የምትታወቀው ቻይና ስትሆን፣ ከእነሱም ሆነ ከኬንያ ኮቴጅ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች እንዲመጡ እየተደረገ ነው፡፡ አንዳንዴ ምርቱና የገበያ ትስስሩ የሚሄደው እየተጋጨ ነው። ስለሆነም እኛ የምናደርገው ምርቱንም ሆነ የገበያ ትስስሩን አንድ ላይ አያይዘን እንሔዳለን፡፡ ወጣቶችን አደራጅተን ከዚህ በፊት የማይለሙ መሬት ላይ እየሠራን ነው። ከዚህ የተነሳ ያለው ሁለት ጥቅም ነው። አንደኛ ቡና ኤክስፖርት ይደረጋል፤ ለሀገር ውስጥ ፍጆታም ይሆናል። የአፈር አሲዳማነትንም በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ጅማ ዞን በአሲዳማ አፈር በጣም የተጠቃ ነው፡፡ እንደ እነሻይቅጠልና የመሳሰሉ ምርቶች አሲዳማነቱን እየቀነሱ ስለሚሔዱ ወሳኝ ናቸው። ከዚህ የተነሳ ሌላው ቀርቶ ዘንድሮ የምንተክለው ባሕር ዛፍ እያነሳን ነው፡፡ ሻይቅጠሉ የሚተከለው በአስር ሺ ሔክታር መሬት ላይ ነው፡፡ በአንድ ሔክታር የሚተከለው ችግኝ በአማካይ 13 ሺ 600 ችግኝ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

መሐመድጣሃ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You