በበርካታ ችግሮች ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ የማምረቻ ዘርፍ ችግሮቹ እንዲቃለሉና መዋቅራዊ የምጣኔ ሃብት ሽግግር እቅድ እንዲሳካ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ጥረቶች ሀገሪቱ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ካላት እምቅ አቅምና ከዘርፉ ችግሮች ስፋት አንፃር ሲመዘኑ በቂ ባይሆኑም አበረታች ውጤቶችን አስገኝተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በዕቅድ በተያዙ ዋና ዋና ግቦች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ይገልጻሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ በስድስት ወራት ውስጥ ከ18 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 129 የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብ ከእቅዱ በእጅጉ የበለጠ (እጥፍ ገደማ የሆነ) አፈፃፀም ተመዝግቧል፡፡ 30 ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚያስመዘግቡ 301 የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን በአምራች ዘርፉ ለማሠማራት ታቅዶ፣ ከ29 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 292 ባለሃብቶች አምራች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ተችሏል፡፡ 43 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ተሸጋግረዋል። አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ለመግባት የሚወስድባቸውን ጊዜ ለመቀነስ የወጡት እቅዶችም ከእቅድ በላይ አፈፃፀም አስመዝግበዋል፡፡
ሚኒስትሩ በስድስት ወራቱ 85ሺ 620 ቶን ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 228 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር ጠቅሰው፣ የቀረበው የምርት መጠን 74ሺ956 ቶን (88%)፣ የተገኘው ገቢ ደግሞ 140 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር (62%) መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ይህ አፈፃፀም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ340 ቶን ምርት እና የ53 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ቅናሽ አሳይቷል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በምግብና መጠጥ ዘርፍ ከእቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ዝቅተኛ አፈፃፀም (36%) ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡ የጨርቃ ጨርቅ እና የምግብና መጠጥ ምርቶች ከ118 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛበ አስገኝተዋል ብለዋል፡፡
የጅቡቲ ጉምሩክ አሠራር በየጊዜው መቀያየር፣ ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች (የሩስያ-ዩክሬን ጦርነት፣ በቀይ ባሕር ላይ ያለው የሎጀስቲክስ ስጋት…)፣ የዋጋ ግሽበት፣ የሎጂስቲክስ ወጪ መናር፣ ከአጎዋ (AGOA) ጋር የተያያዙ ተፅዕኖዎች እና የፀጥታ ችግሮች በአፈፃፀሙ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደሩ ችግሮች እንደሆኑም አቶ መላኩ ያብራራሉ፡፡
በስድስት ወራት የቀረበው የምግብና መጠጥ፣ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን እና የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች የተኪ ምርት መጠን ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ ሲሆን፣ ከ13 ሚሊዮን በላይ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ምርቶች ቀርበዋል፡፡ በዚህም ከ994 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል፡፡ የምግብና መጠጥ ምርቶች ከ724 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማዳን ቀዳሚ ሲሆኑ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ የቆዳ እና የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ ምርቶች ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡
በስድስት ወራት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ቶን ግብዓት ለማቅረብ ታቅዶ፣ ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ቶን ግብዓት ቀርቧል። በጨው አቅርቦት ረገድ፣ 157 ሺ ኩንታል ጨው ለማቅረብ ቢታቀድም ማቅረብ የተቻለው የጨው መጠን 99ሺ ኩንታል (63.4%) ነው፡፡
በኢንዱስትሪዎች መካከል 21ሺ516 ቶን የግብዓት አቅርቦት ትስስር ለመፍጠር ታቅዶ፣ 37ሺ542 ቶን በማቅረብ ከእቅዱ በላይ ማሳካት ተችሏል፡፡ ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር በመፍጠር በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ከመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር ውጤታማ የግብዓት ትስስር እንዲፈጥሩ መደረጉና ተገቢ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች መከናወናቸው በግብዓት ትስስር ረገድ ከእቅድ በላይ የሆነ አፈፃፈፀም እንዲመዘገብ ዋና ምክንያት ሆኗል፡፡
የኃይል አቅርቦትን በተመለከተ፣ በግማሽ ዓመት ውስጥ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች 291ሺ ኪሎዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የቀረበ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት (257ሺ ኪሎዋት) ጋር ሲነፃፀር የ34ሺ ኪሎዋት (1.26%) ብልጫ አለው፡፡ ለ52 አምራች ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት ለማሻሻል ታቅዶ፣ 57 ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት የማሻሻል ሥራ ተከናውኖላቸዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ የምግብና መጠጥ አምራቾች ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዙ፣ በቆዳ እና በማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች በአንፃራዊነት ዝቅ ያለ አፈፃፀም አሳይተዋል፡፡
ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ለሥራ ማስኬጃና ለሊዝ ፋይናንስ ለማቅረብ የታቀደው ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ነበር፤ ሦስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በማቅረብ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የ882 ሚሊዮን ብር (35%) ብልጫ ያለው አፈፃፀም ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ በቅንጅት መሠራቱ እና በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል የተሻለ የሊዝ ፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር መደረጉ ለአፈፃፀሙ ከፍ ማለት አስተዋፅዖ አበርክተዋል።
በስድስት ወራት ውስጥ ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች 30 ቢሊዮን ብር ብድር ለማቅረብ ታቅዶ፣ 23 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ብድር ማቅረብ መቻሉንም ተገልጿል፡፡ አፈፃፀሙ 79 በመቶ ብቻ የሆነው ባንኮች ለአምራች ዘርፉ ቅድሚያ ሰጥተው በማበደር የዘርፉ ድርሻ 24 በመቶ እንዲያድግ በመንግሥት የተሰጠውን አቅጣጫ በአግባቡ ባለመፈፀማቸው መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ለአምራች ኢንዱስትሪዎች 339 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማቅረብ ታቅዶ 274 ሚሊዮን ዶላር ቀርቧል፡፡ በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ረገድ በዘንድሮው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የቀረበው የውጭ ምንዛሪ፣ ባለፈው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከቀረበው (129 ሚሊዮን ዶላር) ጋር ሲነፃፀር ከ145 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጭማሪ የተመዘገበ ቢሆንም፣ ሀገሪቱ ያጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት የግማሽ ዓመቱ አፈፃፀም ከ81 በመቶ እንዳያልፍ አስገድዷል፡፡
በሰው ኃይል አቅርቦት ረገድ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በሚፈለገው ልክ በቅንጅት ባለመሠራቱ፣ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ ከታቀደው 54ሺ506 ሠራተኛ መካከል ማሳካት የተቻለው 40ሺ687 (75%) ነው፡፡ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች ከእቅድ በላይ፣ የምግብና መጠጥ አምራቾች 95 በመቶ እንዲሁም የቆዳ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ኢንዱስትሪዎች 60 በመቶ ገደማ አፈፃፀም ሲያስመዘግቡ፤ የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ግን ዝቅተኛ አፈፃፀም አስመዝግበዋል፡፡
በግማሽ ዓመት በአምራች ኢንዱስትሪው ለ142ሺ 519 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ 120ሺ 793 የሥራ እድል ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ ውስጥ 105ሺ 910 የሚሆነው የሥራ እድል የተፈጠረው በሀገር ውስጥ ባለሃብቶች አማካኝነት ነው፡፡
የአምራች ዘርፉን አማካይ የማምረት አቅም 60 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ፣ ባለፈው የበጀት ዓመት ከደረሰበት 55 ነጥብ 79 በመቶ በዘንድሮው በጀት ዓመት አጋማሽ ወደ 56 ነጥብ 04 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡
ስምንት አዳዲስ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ፣ ስድስት አዳዲስ የምግብና መጠጥ ምርቶች የውጭ ገበያውን እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፡፡ ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ የታቀዱ የሌሎች ዘርፎች ምርቶች በምርምር ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት በተደረገ ጥረት፣ የብረታ ብረት ምርቶች በናሚቢያ እንዲሁም የምግብና መጠጥ ምርቶች ደግሞ በማልዲቭስ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪውን የሀገር ውስጥ ገበያ ድርሻ ለማሳደግ በተከናወኑ ሥራዎች፣ የዘርፉን የገበያ ድርሻ ባለፈው የበጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ከነበረበት 38 በመቶ፣ በስድስት ወራት ውስጥ ወደ 39 ነጥብ ሰባት በመቶ በማሳደግ፣ ሁሉም ንዑስ ዘርፎች ከፍተኛ አፈፃፀም እንዲያስመዘግቡ ማድረግ ተችሏል፡፡
የፀጥታ ችግሮች፣ የመሥሪያ ቦታዎች በበቂ ሁኔታ አለመዘጋጀት እና በአዲስ አወቃቀር ምክንያት የአንዳንድ ክልሎች ፈጥነው ወደ ሥራ አለመግባት አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም መሠናክል ሆነዋል፡፡ ይህም 2313 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም ቢታቀድም፣ 1493 ብቻ ለማሳካት አስገድዷል፡፡
422 አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ መካከለኛ እንዲሁም 10 መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ተሸጋግረዋል፡፡ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ የተከናወነው የሽግግር አፈፃፀም ከእቅዱ በእጅጉ የበለጠ ነው፡፡ በአዲሱ የአምራች ኢንዱስትሪዎች አደረጃጀት ደንብ መሠረት መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ከፍተኛ ለማሸጋገር የሚጠይቀው የካፒታል መጠን 90 ሚሊዮን ብር በመሆኑ፣ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚደረገው ሽግግር አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ሆኗል፡፡
የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም አጠቃቀም ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ የሚባል አፈፃፀም ቢመዘገብም፣ የፀጥታ መደፍረስ እንዲሁም የኬሚካልና የጨው እጥረት በሥራው ላይ ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡ የለሙ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ምርቶችን በማሳደግና በማሻገር ረገድ ከእቅድ በላይ የሆነ አፈፃፀም ተመዝግቧል፡፡
የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት፣ ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ብድር በሚፈለገው መጠን አለመቅረብ፤ በሀገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች እየተከሰቱ ያሉ የፀጥታ ችግሮች፣ በዘርፉ የሠለጠነ የተሟላ የሰው ሃብት አለመኖሩ፤ የአጎዋ (AGOA) መቋረጥ፣ የሎጂስቲክ ችግር … በስድስት ወራት ያጋጠሙ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው፡፡
የማምረት አቅም አጠቃቀምን ማሳደግ፤ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲና የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ውጤታማ እንዲሆኑ መደገፍና መከታተል፤ የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄን አጠናክሮ ማስቀጠል፤ የወጪ ንግድን ተኪ ምርቶችንና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ማሳደግ እንዲሁም የሠለጠነ የሰው ኃይል የማቅረብ ተግባራት ልዩ ትኩረት የሚሹ የዘርፉ ጉዳዮች እንደሆኑ አቶ መላኩ አስታውቀዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው፣ የግማሽ ዓመቱ እቅድ አፈፃፀም ኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ መነኻሪያ እንድትሆን የሚደረገው ጥረት አበረታች በሆነ ጉዞ ላይ እንደሚገኝ አመላካች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፖሊሲው ዝግጅት ተጠናቆ ትግበራው መጀመሩ እቅዱን ለማሳካት ትልቅ አቅም ይፈጥራል ሲሉም ተናግረው፣ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለሚወስኑ ግብዓቶች የተሰጡ ትኩረቶች በአምራች ዘርፉ አፈፃፀም ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚመዘገብ ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡
‹‹የአምራች ዘርፉ የወጭና ተኪ ምርቶችን በመጨመር የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግና በማዳን፣ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም እንዲሁም የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ አቅም ያለውና ኃላፊነትም የተጣለበት ክፍለ-ኢኮኖሚ ነው፡፡ የማምረት አቅም አጠቃቀምን በማሻሻል የዘርፉን ምርታማነት ማሳደግ ይገባል፡፡ የማምረት አቅም አጠቃቀም ሲሻሻል የሥራ ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲሁም የተኪ ምርት መጠን ይሻሻላል፡፡ የመንግሥት ግዢዎች በሀገር ውስጥ ምርቶች እንዲሸፈኑ የተቀመጠውን አቅጣጫ በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋል›› ይላሉ፡፡
የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ዓላማ የአምራች ዘርፉን ችግሮች በቅንጅት መፍታት እንደሆነ አመልክተው፣ ለአብነት ያህል የኃይል አቅርቦት ከፍተኛ መሻሻል ሊያሳይ የቻለው ቅንጅታዊ አሠራርን በማስፈን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ድርሻቸው እየደገ የመጣውም በትብብር በመሠራቱ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ፍላጎትን፣ የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ አቅምን መሠረት በማድረግ 96 የኢንዱስትሪ ምርቶች ሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ስለመለየታቸውም አቶ ታረቀኝ ያስረዳሉ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች ባካሎ (ዶ/ር)፣ የአምራች ዘርፉን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ከቀበሌና ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግሥት ያሉ መዋቅሮች የዘርፉን እድገት ዘላቂ በሚያደርግ መልኩ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በየአካባቢው ያለውን ሀብት በጋራ አስተባብሮ መጠቀም ይገባል›› ይላሉ፡፡ ኅብረተሰቡ ስለአምራች ዘርፉ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ የሀገር ውስጥ ምርቶች ገበያ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል፡፡
የአምራች ዘርፉን ችግሮች ለመፍታት አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል ተብሎ ታምኖባቸው በመንግሥት ትኩረት ከተሰጣቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች መካከል አንዱ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የተሰኘው ንቅናቄ ነው፡፡ በንቅናቄው በኢንዱስትሪ ደረጃ ከተለዩ 2167 ችግሮች (የግብዓት፣ የመሠረተ ልማት፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት፣ የመሥሪያና የማስፋፊያ ቦታ ዝግጅት፣ የጉምሩክና የሎጂስቲክስ አገልግሎት … ችግሮች) መካከል፣ 1034 የሚሆኑት መፍትሔ እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን በቀሪዎቹ 1133 ላይ ደግሞ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ መላኩ ገልፀዋል፡፡
‹‹የሀገር ውስጥ ምርቶች ጥራት እየተሻሻለ መምጣቱ በዘርፉ ከሚታዩ ተስፋ ሰጪ አፈፃፀሞች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ የአንዳንዶቹ ምርቶች የጥራት ፍጥነት አስደናቂ ነው፡፡ በሸማቾች በኩል ያሉ የአመለካከት ክፍተቶችን በማስተካከል የሀገር ውስጥ ምርቶች የተሻለ ገበያ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል›› ይላሉ፡፡
‹‹የኢኮኖሚ እድገት የሚመዘገበው ነፃ የሆነ የሰው፣ የምርትና የፋይናንስ እንቅስቃሴ ሲኖር ነው፤ በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ የሚያሳድር ችግር ከተፈጠረ እድገት አይታሰብም›› የሚሉት አቶ መላኩ፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች በአምራች ዘርፉ እድገት ላይ ተፅዕኖ እያሳደሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ስለሆነም የሕግ ማስከበር ሥራዎችን በማከናወን ለችግሩ እልባት መስጠት እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አቶ መላኩ የአምራች ዘርፉ ጥልቀት ያለው የአመለካከት ችግር እንዲሁም የክህሎት ክፍተት እንዳለበት ገልጸው፣ ጠንካራ የማስፈፀም አቅም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን በዘርፉ የሚስተዋሉ የአመለካከትና የክህሎት ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም