
ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት፣ የውጭ ቀጥታ የኢንቨስትመንት ፍሰትንም ለመጨመር የተለያዩ የሕግና የፖሊሲ ርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች። የኢንቨስትመንት ሕጉን ጨምሮ ለዘርፉ ማነቆ በነበሩ የተለያዩ ድንጋጌዎችም ላይ ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል።
ይህን ሁሉ እርምጃ ተከትሎም የቴሌኮምና የፋይናንስ ዘርፉን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፎች ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ክፍት ተደርገዋል። የሪፎርም ሥራዎቹ ሁሉ ዋንኛ ማጠንጠኛም ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳር መፍጠር ነው።
በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ ያለመ “በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2025” ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ እንዳሉት፤ የቴሌኮምና ፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ የሚያስችሉትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ የተለያዩ የሕግና ፖሊሲ ርምጃዎችን ወስዳለች። ይህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
የኢኮኖሚ ማሻሻያ ርምጃዎቹ ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማሳካት እንደሚያግዙ ጠቅሰው፣ በተለይ ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆነው የቆዩ ዘርፎችን ለመክፈት እንዲያስችል የተደረገው ሀገራዊ ሪፎርም እንዲሁም የህግና የፖሊሲ ማሻሻያዎች በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ይህም ኢትዮጵያ በትክክለኛው የዕድገት ጎዳና ላይ እንድትገኝ አድርጓታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያላት የሕዝብ ቁጥር ብዛት፣ ያልተነኩ የኢንቨስትመንት ዕድሎችና የተዘረጉ ምቹ የአሠራር ሥርዓቶች ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን አመልክተው፣ ለዘርፉ ተዋናዮች የተዘረጉ የማበረታቻ ሥርዓቶችም ባለሀብቶች ኢንቨስትመንታቸውን እንዲያስፋፉና ዘላቂነትን እንዲያረጋግጡ የሚያግዙ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ፖሊሲዎችን ለሥራ ምቹ ማድረግ፣ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት እና ቀልጣፋ ግንኙነት እንዲኖር ማስቻልን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደርጉ ፎረምም ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አቅም ለማሳየት ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰው፣ ተሳታፊዎችም በዘርፉ በሚስተዋሉ ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ መወያየት መቻላቸው የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የዘርፉን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ያለመታከት እየሠራ መሆኑን አመልክተው፣ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተፈጠሩ መልካም እድሎችን ተገንዝበው በመረጡት ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን ሥራ ላይ እንዲያውሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ሰፊ መሬት፣ ከፍተኛ የውሃ ሀብት፣ ወጣትና የተማረ የሰው ኃይል ብሎም የተሟላ መሰረተ ልማት ያላት መሆኗ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንዳደረጓት ተናግረዋል።
ባለሀብቶችን በአፋጣኝ ለማገልገልና ምቹ የአሠራር ሥርዓት ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ ቀላል እና ምቹ አሠራር የሚፈጥር በዲጂታል አሠራር የታገዘ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመሩንም ጠቁመዋል።
መንግሥት የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እና በግሉ ዘርፍ የሚመራ ቀጣይነት ያለው ምጣኔ ሀብት ለመገንባት የሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያን ተግባራዊ አድርጓል ሲሉም ጠቅሰው፣ በማሻሻያው የግሉ ዘርፍ ተሳትፎና ኢኮኖሚያዊ ተዋናይነት ቅድሚያ እንደተሰጠው አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ወደ ሥራ መግባቱም ተወዳዳሪ እና በግሉ ዘርፍ የሚመራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለውም አመላክተዋል።
ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ለግሉ ዘርፍ የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት በአግባቡ በመጠቀም በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱም ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የተገበረችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ተቋማዊ እና መዋቅራዊ ችግሮችን የሚፈቱ ሪፎርሞች ዘላቂ ሀገራዊ ዕድገትን ማምጣት የሚያስችሉ ናቸው። የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎቹ እንዲሁም የንግድና ኢንቨስትመንት ምኅዳሩን የመክፈት ርምጃዎችም ትልቅ ውጤት እያመጡ ናቸው።
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2025 የቢዝነስ ፎረም የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት አቅምና ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎችን ማስገንዘብ የተቻለበት መሆኑን የገለጹት አቶ አህመድ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የግሉን ዘርፍ ለማበረታታት ያከናወነቻቸውን ሥራዎች እና በቅርቡ ወደትግበራ ያስገባችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ኢንቨስትመንትን ማበረታታትን ያለመ ነው። በፎረሙም የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙንና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተከናወኑ ተግባራትን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች ማስገንዘብ ተችሏል።
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማበረታታት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትንም በስፋት ወደ ኢኮኖሚው ማምጣትን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በዚህ መድረክ ላይም አስፈላጊ ሂደቶችን ያጠናቀቁ አምስት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ተፈራርመዋል ሲሉ አስታውቀዋል። ሌሎች የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ሥራ ላይ ለማዋል በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የኢንቨስትመንት ማነቆዎችን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን ሚኒስትሩ አመልክተው፤ ከባለሀብቶች ጋር በቅርበት በመሥራት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርጋት ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2025 ቢዝነስ ፎርም ላይ በሀገሪቱ ያሉ የኢንቨስትመንት አቅሞች፣ መልካም እድሎችና የኢንቨስትመንት አማራጮችን አስመልክተው ለፎረሙ ተሳታፊዎች ባደረጉት ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ስትራቴጂካዊ መገኛና ሰፊ ተደራሽነት ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ሀገር እንደሚያደርጋት ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያ ሰፊና በማደግ ላይ ያለ የሀገር ውስጥ ገበያም አላት፤ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) መሥራች መሆኗም የ560 ሚሊዮን ሕዝብን የገበያ እድል ማግኘት ያስችላታል። የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠናም አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ሰዎችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ግዙፍ ነጻ ንግድ ቀጠና ነው። ይህም ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካ ገበያ ለመግባት ቀዳሚ ተመራጭ ሀገር ያደርጋታል።
ሀገሪቱ በቂ የሰው ኃይልን ጨምሮ በርካታ የኢንቨስትመንት ዕድሎች አሏት ያሉት ሚኒስትሯ፤ 130 ሚሊዮን ከሚጠጋው አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሯ 54 ሚሊየኑ ወጣትና የሰለጠነ የሰው ኃይል መሆኑም ሌላኛው ምቹ ሁኔታ መሆኑን አንስተዋል።
ከሰሀራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አምስት ግዙፍ ኢኮኖሚዎች አንዱ የኢትዮጵያ መሆኑ ለኢንቨስትመንት ሥራዎች ተጨማሪ ዕድል መሆኑን ተናግረው፤ ለአብነትም ባለፈው ዓመት ስምንት ነጥብ አንድ በመቶ ዕድገት ማስመዝገቧን ጠቅሰዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ለዘርፉ በሰጠችው ልዩ ትኩረት የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እያደገ መጥቷል። በፈረንጆቹ 2023/24 ሶስት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች። ይህ ውጤት ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ፣ በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ 3ኛዋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን አድርጓታል።
በጥቅሉ ሲታይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዓለም ላይ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ ኢኮኖሚዎች አንዱ ነው ያሉት ዶክተር ፍፁም፤ ባለፈው ዓመት የግብርናው ዘርፍ በስድስት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ደግሞ ዘጠኝ ነጥብ ሁለት በመቶ፣ የአገልግሎት ዘርፉ ሰባት ነጥብ ሰባት በመቶ ዕድገት ማስመዝገባቸውንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና ሌሎች የፖሊሲ ማሻሻያ ርምጃዎች ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ ፍሰት ተጨማሪ መደላድል እንደሚፈጥሩ አመላክተው፤ በዚህም በሀገር ውስጥ ካለው ሰፊ ገበያ ባለፈ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ገበያ ውስጥ ለመግባት የሚያስችል ቁመና ላይ እንድትገኝ አድርጓታል ብለዋል። ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ዕድሎቹን በመገንዘብ በመረጡት ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን ሥራ ላይ ቢያውሉ ውጤታማ እንደሚሆኑም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እምቅ አቅም ለማስተዋወቅ ሲሠራ ቆይቷል። በፎረሙ ላይ ከ59 ሀገራት የተወጣጡ ተሳታፊዎች እየተካፈሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የዘርፉ የተሻሻሉ ሕጎች፣ አዋጆችና ደንቦች ዘርፉን በማነቃቃት ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ መሆናቸውንም ጠቅሰው፤ ባለሀብቶች መንግሥት ትኩረት በሰጠባቸው የግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ማኑፋክቸሪንግ እና አይሲቲ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሠራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
ኮሚሽነሩ እንዳስታወቁት፤ ይህ መድረክ ኢንቨስትመንቱን ለመደገፍ የተሠሩ የሪፎርም ሥራዎችን ማስተዋወቅ፣ መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየት፣ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ማስተዋወቅና የበሰሉ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ሥራ ማስገባትን ዓላማ አድርጎ የተካሄደ ነው። በዚህም ከተጠበቀውም በላይ ዓላማውን ማሳካት ችሏል።
በፎረሙ ላይ ለመሳተፍ ከ59 በላይ ሀገራት ተሳታፊዎች መምጣታቸውን ጠቁመው፤ ይህም ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተመራጭ ሀገር መሆኗን እንደሚያመላክት ተናግረዋል።
በሀገሪቱ ከ30 በላይ የሚሆኑ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እንዳሉ የጠቆሙት ኮሚሽነር ዘለቀ፤ ስምምነት ከተፈረሙት አምስት ኩባንያዎች መካከል ሦስቱ ወደተለያዩ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እንደሚገቡ አመላክተዋል።
በፎረሙ ላይ ከተሳተፉት የውጭ ኩባንያዎች መካከል በቴሌኮም ዘርፍ ኢንቨስት ያደረገው ሳፋሪኮም አንዱ ነው። የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዊም ቫንሄለፑት፤ ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ኢንቨስተሮች ቀጣይነት ያለው ምቹ የንግድ ከባቢን ለመፍጠር እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት እንደሚበረታቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸው፣ ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስትከፍት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ይዞ በመግባት የሀገሪቱ አንዱ ትልቁ የውጭ ኢንቨስትመንት መሆን ችሏል ብለዋል።
ከዚህ ውስጥም አንድ ቢሊዮን ዶላሩ የሥራ ፈቃድ ለማግኘት አስፈላጊ ሂደቶችን ለማጠናቀቅ የዋለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቀሪው ገንዘብ ደግሞ በሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት መዋሉን አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ኩባንያው ኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ሲወስን የፋይናንሽያል ውሳኔ ብቻ አይደለም ያሳለፈው፤ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ላይ በመተማመን ኢኮኖሚውን ለማሳደግ፣ ለአዲስ ባለሀብቶች አርአያ ለመሆን፣ ለጠንካራ የሀገር ውስጥ ንግድ መስፋፋት እንዲሁም ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ እድሎችን ለመፍጠርም አልሞ ነው።
ለ27 ዓመታት 24 በሚደርሱ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በቴሌኮም ዘርፉ ላይ ተዘዋውረው የመሥራት እድል እንደነበራቸው ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት ሥራዎች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ከመጀመሪያዎቹ ሦስት ሀገራት ተርታ እንደሚመድቧት ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ከሶስት ሺህ በላይ የቴሌኮም ማማዎችን ገንብቷል፤ የ4ኛ ትውልድ የኔትዎርክ ሽፋንን ከ50 በመቶ በላይ ወደሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ አስፋፍቷል።
በዚህም 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ቋሚ የሞባይል ደንበኞችን በማፍራት፣ የኤምፔሳ ተጠቃሚዎችን ብዛትም ወደ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በማሳደግም 16 ቢሊዮን ብር ግብይቶች አከናውኗል።
ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በምትሠራው ሥራ፣ የገበያ ነፃነቷን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ውስጥ ሳፋሪኮም የገበያ ዕድሎችን በመክፈት እና ግንኙነቶችን በማጠናከር ረገድ ቁርጠኛ እንደሆነም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አመላክተዋል።
ያላቸውን ልምድ መነሻ በማድረግም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ውጤታማ እንደሚሆኑም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
3ኛው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2025 ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ባሉ የልማት አጋሮች ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን፤ ግንቦት 4 እና 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም