ሆድ እንጂ ሀገር የሌላቸው

የእነተሰማ መንግሥቴ የዕለቱ አጀንዳ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሳ ጥያቄ የተሰጠ ምላሽ እና የዩቲበሮች በሬ ወለደ ወሬ ላይ ያተኮረ ነበር። ቀድሞ የተጀመረው የዩቲዩበሮች በሬ ወለደ ወሬ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያ ያጠነጠነ ሲሆን፤ አንዳንድ ቀድሞ የሚሠሩ ሥራዎችን ዩቲዩበሮች እንደአዲስ አጀንዳ አድርገው ማውራታቸው ተሰማን በእጅጉ አበሳጭቶታል፡፡

ተሰማ ‹‹የጦርነት ነጋሪት መጎሰም እና ግጭት ማቀጣጠልን እንደደንበኛ ሥራ የቆጠሩት ዩቲዩበሮች የውሸት ወሬ እየነዙ ማነብነባቸው አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ አስደንጋጭ ነው፡፡ በተለይ ያለሁባት ከተማ ብቻ ሳትሆን የዋልኩባት መንደር ሳትቀር በዕለቱ ስትታመስ እንደነበር ሲናገሩ፤ ደንግጬ በተደጋጋሚ በመገረም አፌን በእጄ ላይ ጭኜ የምገባበት ጠፍቶኝ ያውቃል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚቀርብላቸው ጥያቄ መልስ በሚሰጥበት ጊዜ የሚደረገውን ነገር አሁን እንደአዲስ እየተደረገ ነው ለማለት የሄዱበት መንገድ እጅግ የሚያበሳጭ ነው›› ሲል ተናገረ፡፡

ገብረየስ፤ ‹‹አልገባኝም ምን ሲሉ ሰምተህ ነው?›› አለው፡፡ ተሰማ በጣም መበሳጨቱን በሚያሳብቅ መልኩ፤ ‹‹ምን ጊዜም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሮች ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚቀርብላቸው ጥያቄ መልስ በሚሰጡበት ጊዜ ለደህንነት ሲባል በሌላ በኩል የቀጥታ ስርጭት አስተላላፊ መገናኛ ብዙኃኖችም ካሜራቸውን እና ቀረፃውን የሚያከናውኑባቸውን ቁሳቁሶች አስተካክለው እንዲያሳድሩ የምክር ቤቱ ሠራተኞች ከመውጫ ሰዓታቸው ከአንድ ሰዓት በፊት ቀድመው እንዲወጡ ይደረጋል፡፡ ማለትም አስራ አንድ ሰዓት የሚወጡትን አስር ሰዓት ይወጣሉ፡፡ ይህ ምንም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ አንዳንዶች ጠንከር ያለ ሥራ ካላቸው ላይወጡ እና እያመሹ ሊሠሩ ይችላሉ፡፡

ከሃያ ዓመትም ሆነ ከአስር ዓመት በፊት አካሄዱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ጉዳይ ዩቲዩበሮች ልክ ዛሬ እንደታዘዘ አድርገው አጋንነው እንዴት እንደሚያወሩት ብትሰማ ትገረማለህ፡፡ በሌላ በኩል በፕሮቶኮሉ መሠረት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ የሚገባው ከቀናት በፊት ነው፡፡ ይህም ዛሬ የመጣ ሳይሆን ቀድሞም የነበረ አሠራር ነው፡፡ የዩቲዩበሮቹ ወሬ ግን ልክ ዛሬ ብቻ እንደተደረገ አስመስለው ለሕዝቡ አዲስ ዜና ይዘው እንደመጡ ሲናገሩ መስማት ያበሽቃል።›› ብሎ ምሬቱን ገለፀ፡፡

ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹ቢሆንም ተደማጭነት እንዳላቸው እና የተመልካች ድሃ አለመሆናቸውን መካድ አትችልም።›› ሲለው፤ ተሰማ ቆጣ ብሎ፤ ‹‹መቼም የዩቲዩበሮች ወሬ እውነት እና ትክክለኛ ነው ብለህ ከሞገትከኝ የታመምከው ከእነርሱ በላይ አንተ ነህ፡፡ አልሰማህ ይሆናል እንጂ አብዛኞቹ ሚዲያ የሚከፈትላቸውና ዩቱቡን የሚዘውሩት ሰዎች ከውጭ ገንዘብ እየተላከላቸው በሀገርና በሕዝብ ላይ ጦርነት የሚያውጁ ናቸው፡፡ እነሱ ሆዳቸው እና ኪሳቸው ይሙላ እንጂ ስለሀገር እና ሕዝብ ቅንጣት ታክል ግድ የላቸውም›› ሲል ምላሽ ሰጠው፡፡

ገብረየስ ነገሩን ለማርገብ እና ለመገላገል በሚመስል መልኩ መሐላቸው ገባ፤ ‹‹ሁለታችሁም ትክክል ናችሁ፡፡ ብዙ ውሸታም ዩቲዩበሮች አሉ፡፡ አንዳንዴ የተፈፀመውንም እጅግ አጋንነው ያወራሉ፤ አንድ ሰው ሲሞት እልፍ እንዳለቀ አደማምቀው ማውራታቸው አይካድም፡፡ ነገር ግን ደግሞ በተቃራኒው ቢዋሹም አድማጭ ተመልካች እንዳላቸውም የሚካድ አይደለም፤ ይህ እኛ ተመልካቾች እራሳችንን ቆም ብለን እንድናይ የሚደርገን ነው፡፡›› ብሎ የሁለቱም ሃሳብ ትክክል መሆኑን ተናገረ፡፡

‹‹ተመልካች ወይም አድማጭ የማግኘት ጉዳይ እውነትን ከመናገር ጋር በእጅጉ የተቃረነ ነው። መጥፎ ነገር የመስማት ፍላጎት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች የሚነገረው ውሸት እንደሆነ እያወቁም፤ ደጋግመው ሊያዳምጧቸው ይችላሉ፡፡ ይህ በየትኛውም ዓለም እየታየ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ‹እዚህ አገር ጦርነት አለ፤ ይህን ያህል ሰው ሞተ፤ ይህን ያህል ንብረት ወደመ› የሚል ተደጋጋሚ ዘገባዎችን ሲያስተላልፉ በየትኛውም ዓለም ተደማጭ እየሆኑ መቀጠላቸው የተለመደ ነው፡፡ ይህ የሰዎች ተፈጥሮ ነው፡፡ ዩቲዩበሮቹም ተደማጭነትን ያገኙበት ምክንያት ተመሳሳይ ነው፡፡ እውነተኛ መረጃን ለሕዝብ አቅርበው ሳይሆን የሚያቀርቡት ነገር በአብዛኛው ግጭት እና ጦርነት ላይ ያተኮረ በመሆኑ ነው፡፡›› ሲል ተሰማ የሚያስበውን ገለፀ፡፡

ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹በእርግጥ ትክክል ነው። በየትኛውም ዓለም ግጭት ላይ ትኩረት አድርገው የሚተላለፉ ዘገባዎች ምን ያህል ተቀባይነት እንዳላቸው ለማወቅ እነአልጀዚራ፣ ቢቢሲም ሆነ የትኛውም በዓለም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ያሉ ከፍተኛ ተደማጭነትን ያተረፉ መገናኛ ብዙኃኖች የሚያስተላልፉትን ማየት በቂ ነው፡፡ ቀኑን ሙሉ በቱኒዚያ፣ በሶሪያ ወይም በአንድ በሌላ ሀገር ስላለው ግጭት ዘገባ ሲያስተላልፉ ይውሉ የነበሩ መገናኛ ብዙኃን ብዙ ተመልካች አግኝተዋል፡፡ የሩሲያን እና የዩክሬንን ጉዳይ የሚዘግቡ፤ አሁን ደግሞ በእስራኤል እና በጋዛ መካከል ያለውን ጦርነት ቀኑን ሙሉ የሚያስተላልፉ በተሻለ መልኩ ሕዝብ እያያቸው ነው።›› ሲል ተናገረ፡፡

ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹የውጪዎቹ መገናኛ ብዙኃኖች ግጭትን ቢያሳዩም ቢያንስ አይዋሹም፡፡ ብዙ ጊዜ ከራሳቸው ሀገር ብሔራዊ ጥቅም አንፃር ዘገባዎችን ከማስተላለፍ አልፈው አያውቁም፡፡ የእኛዎቹ ዩቲዩበሮች ግን የሚያስተላልፉት ዘገባ በተለይ አንዳንዶቹ ሙሉ ለሙሉ ውሸት ይበዛበታል፡፡ ዓላማ እና ግብ የለውም። ዓላማ ከተባለ ዓላማቸው ተመልካች ማግኘት ብቻ ነው፤ አልፎ ተርፎም ከውጭ ገንዘብ የሚልኩላቸውን ግለሰቦችና ሀገራት ፍላጎት ለማሟላት በማሰብ ነው›› ብሎ ዘውዴን እየተመለከተ‹‹

እነዘውዴ እንደሚሉት ‹ውሸት እና የስንቅ አቁማዳ እያደር ይቀላል› ብለን፤ ውለው አድረው ተመልካች ውሸታቸውን ሲያውቅ ይቀሉና ይተዋቸዋል ብለን ብናስብም አሁንም ተመልካች አላጡም፡፡ እንደውም በሬ ወለደ ማለታቸው ተቀባይነት አግኝቶ ተከታዮቻቸው ተከትለው በሬ ይወልዳል ብለው አምነው እነርሱ የሚያወሩትን ከማስተጋባት አልፈው በእርግጠኝነት ትክክል ናቸው ብለው ወደማመኑ ደርሰዋል፡፡›› አለ፡፡

ገብረየስ፤ ‹‹ነገር ግን አንድ ነገር መታወቅ አለበት። ዩቲዩበሮቹ ለምን እንዲህ ለመዋሸት ተገደዱ? እንዴትስ ተመልካች አገኙ? የሚለው በደንብ ሊጤን ይገባዋል።›› ሲል፤ ዘውዴ ፈገግ አለ፡፡ ‹‹ በእርግጥ ቢያንስ ዩቲዩበሮቹ የሆነ መነሻ አላቸው፡፡ ሁሉም መነሻቸውም ሆነ መድረሻቸው ውሸት አይደለም። ለምሳሌ የፌዴራል መንግሥት እና ሸኔ ታንዛኒያ ወይይት አድርገዋል፡፡ ውይይት ማድረጋቸው ውሸት አይደለም። የተነሳው ፍሬ ነገር ግን ከዩቲዩበሮቹ ወሬ የተለየ ሊሆን ይችላል። እንደሞኝ የሚናገሩት ሁሉ ውሸት ነው ብሎ መደምደምም ሆነ እውነት ነው ብሎ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡›› ሲል እምነቱን ገለፀ፡፡

ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹በእርግጥ የሚናገሩት ጭራሽ ሙሉ ለሙሉ ምንም እውነት የለውም ማለት አይቻልም። አንዳንዴ እውነት አላቸው፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ በሬ ወለደ አይነት ውሸት ይታያል። ሀገራችን ውስጥ በተለያየ ስፍራ በቀላል ሊፈታም በሚችል ምክንያት ጦርነት እና ግጭት እንዲሁም መፈናቀሎች ያጋጥማሉ። ዘገባቸው ግጭቱን ይበልጥ እንዲቀጣጠል በሚገፋፋ መልኩ የሚካሔድ ነው፡፡ ለምሳሌ አንተ የጠቀስከውን የሸኔን ጉዳይ ብንወስድ ሸኔ ብዙ ጥፋት እያስከተለ ነው፡፡ መንግሥትም ሸኔ ላይ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ዩቲዩበሮቹ የ24 ሰዓት ወሬያቸው ሸኔ ይሔን ያህል ሰው ገደለ፤ አገተ፤ መኪና አቃጠለ ሰው አፈናቀለ የሚል ነው። በእርግጥ ድርጊቱ ሳይፈፀም አይደለም፡፡ ነገር ግን ድርጊቱ የተፈፀመበት መጠን የጥፋቱ ስፋት ዩቲዩበሮቹ እንደሚገልፁት አይደለም፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ሸኔ ላይ የወሰደውን እርምጃ በተመለከተ ሳት ብሏቸው እንኳን መግለፅ አይፈልጉም፡፡

ዩቲዩበሮቹ ፍፁም ሚዛናዊነት የጎደላቸው ናቸው፡፡ ይህ ድርጊታቸው ሀገርን እና ሕዝብን ከመጥቀም ይልቅ ሊጎዳ እንደሚችል ፍፁም አይረዱም፡፡ መንግሥት ሸኔን ለማወያየት ሞክሯል። ነገር ግን የተፈለገው ውጤት አልመጣም፡፡ በዚህ ላይ ዩቲዩበሮች ምን ሲሉ እንደነበር ያየ እና ያዳመጠ ይፍረድ፡፡ ቀድሞ ነገር እታገልለታለሁ የሚለውን ሕዝብ ሠላም ስላሳጣ ደግ እንዳደረገ እርሱን በተመለከተ ለ24 ሰዓት ግለሰቦችን አገተ፣ መኪና አቃጠለ ሰዎችን ገደለ እያሉ ማስተጋባት ምንም እርባና የለውም፡፡

ሚዲያውን መልካም ነገር ማስተላለፊያ ከማድረግ ይልቅ በተቃራኒው መሔድ የሚያስገኘው ምንም ዓይነት ውጤት የለም፡፡ ዜና ከሆነም ዜና የሚደመጠው አንዴ ነው፡፡ በሌላ በኩል ምናልባት ሌላው ዩቲዩበር ያንኑ መልሶ አንድ ሰው ሲሞት 10 ሰው እንደሞተ፤ አንድ መኪና ሲቃጠል መቶ መኪና እንደተቃጠለ አጋንኖ ያወራዋል። ይህ በሌላው ዓለም ኢትዮጵያ ውስጥ ሠላም እንደሌለ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ውለው ማደር እንዳቃታቸው በሚያስመስል መልኩ እንድትታሰብ ከማድረግ ውጪ የሚያስገኘው ምንም ጥቅም የለም፡፡›› አለ፡፡

ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹ አንተን ያልገባህ አንድ ነገር አለ። ችግር መኖሩን መካድ ተገቢ አይደለም፡፡ ሚዲያው ተገቢውን ሚና እየተጫወተ አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት ዩቲዩበሮች እንደፈለጉ ሲናገሩ መረጃ የተራበ ሕዝብ ያዳምጣቸዋል፡፡ ያቀረቡት እውነትም ሆነ ውሸት እሳት በሌለበት ጭስ አይታይም እያሉ ከሚናገሩት መካከል ግማሹንም ቢሆን ያዳምጣቸዋል፤ በግማሽም ቢሆን ያምናቸዋል፡፡›› ሲል ተናገረ፡፡

ገብረየስ ደግሞ፤ ‹‹ሁሉም በልኩ መቅረብ እያለበት፤ ማጋነኑ ተገቢ አይደለም፡፡ ከመንግሥት የጎደለውን መሙላት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ነው፡፡ በእርግጥ እንደተባለው ኢትዮጵያ ውስጥ ዩቲዩበሮች እንዳራገቡት ምንም ሠላም የለም ማለት አይቻልም። መስቀል፣ እሬቻ፣ መውሊድም ሆነ ጥምቀት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ወጥቶ አክብሮ በሠላም ወደ ቤቱ ገብቷል፡፡›› ሲል፤ ተሰማ በፍጥነት ፈገግ ብሎ፤ ‹‹ ዩቲዩበሮቹ መች ይሔ ይታያቸዋል፤ ነገር ግን በእነዛ በዓላት ላይ የሆነ ግጭት ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ ወሬያቸው መከራ ያሳየን ነበር። አሁንም አማራ ክልል ስላለው ግጭት ሲገልፁ፣ ሲያብራሩ እና ሲተነትኑ (ሲተረትሩ) ሰው ቤቱ አንድ ቀን የሚያድር አይመስልም፡፡ ስላለፉት አምስት ዓመታትም ሲናገሩ፤ መንግሥት የአማራ ክልልን ሕዝብ አስጨረሰ የሚል ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት አምስት ዓመታት በአማራ ክልል ብቻ 3ሺህ 200 ኪሎሜትር የመንገድ ሥራ ተጀምሯል። ከዚህ ውስጥ 1300 ኪሎ ሜትር ተጠናቆ ሥራ ጀምሯል።

በእነዚህ ዓመታት ባሕርዳር ላይ የተሠራው ድልድይ 2ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገደማ መውሰዱን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰምተናል። 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጥቶ ድልድይ ሲሠራ ይህ የመጀመሪያው ነው። ይሄ ድልድይ በአማካኝ 50 ሜትር ስፋት አለው። በሁለት መንገድ ሦስት ሦስት መኪና የሚያሳልፍ ነው። በሁለት መንገድ መኪና ብቻ ሳይሆን ሳይክልም የሚሄድበት ሦስት ሦስት ሜትር ስፋት አለው። በሁለቱም በኩል አምስት፤ አምስት ሜትር እግረኛ መንገድ አለው። ይህ ሁሉ ለዩቲዩበሮቹ አይታያቸውም፡፡

ዩቲዩበሮቹ የሚታያቸው የተቸገረ በጦርነት ውስጥ ያለ ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ በእርዳታ በኩልም ቢሆን መንግሥት ከውጪ ያገኘውን እርዳታ አሳልፎ ለገበያ እንዳቀረበ ያስተጋባሉ፡፡ ነገር ግን እንደውም ላጋጠመው ድርቅ የውጪ ድርጅቶች የሰጡት እርዳታ 4 ቢሊየን ብር የሚገመት ብቻ ነበር፡፡ መንግስት 15 ቢሊየን ብር ለድርቅ አውጥቷል፡፡ ይሔንን ለመዘገብ ያንቃቸዋል። ምክንያቱም ግባቸው በጎ ነገር ሳይሆን መጥፎ ነገርን በማሳተጋባት የተመልካች ቁጥርን ማብዛት ነው፡፡

በማይረባ ጉዳይ ላይ ተጠምዶ ዋናውን ጉዳይ ረስቶ፤ የኢትዮጵያን ዕድገት ለመገደብ መሞከር በእኔ በኩል በምንም መልኩ ጠቃሚ አይደለም፡፡ ስለዚህ በእኔ እምነት በተለይ አጋናኝ እና ውሸት የሚያወሩ ዩቲዩበሮች በጊዜ መላ ቢባሉ ደስ ይለኛል፡፡›› ብሎ ተሰማ ፍላጎቱን ገለፀ፡፡

ፀጥ ብሎ ሲያዳምጥ የቆየው ዘውዴ በረዥሙ ተነፈሰ፤ ‹‹ለነገሩ ከዚህ በላይ ምንም ማለት አልችልም ‹የት ሔጄ ልፈንዳ አለች ጎማ ብሶቷን ስታሰማ› እንደሚባለው ቃሌ ይሔ ነው፡፡›› ብሎ ሲነሳ ተሰማ እና ዘውዴ ከፋቸው፤ ‹‹ በጊዜ ተነሳህ ምን ነው? ትንሽ ብንቆይ አይሻልም፡፡›› አለው ገብረየስ፤ ‹‹ምኑን ቆየሁት፤ ከዚህ በላይ መቆየቱ ትርፍ ያለው አይመስለኝ፡፡›› ብሎ ዘውዴ ከግሮሰሪው ወጣ፡፡

የፌኔት እናት

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You