
አዲስ አበባ፡- ከሰሞኑ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተካሄዱ ሕዝባዊ ውይይቶች ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያግዙ ግብዓቶች የተገኙበት መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ መንገሻ ፈንታው(ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ 15 ከተሞች አብዛኛውን የክልሉን ሕዝብና ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ያሳተፈ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ሕዝባዊ ውይይቱ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያግዙ ግብዓቶች የተገኙበት ነው፡፡
የውይይት መድረኮችን የብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በጋራ መርተውታል ያሉት ቢሮ ኃላፊው፤ የውይይቱ ዋንኛ ዓላማ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም ክልሉ ላይ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንና የክልሉ ሁለንተናዊ እድገት ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መግባባት ላይ መድረስ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ከሕዝቡ በርካታ ክልሉን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያግዙ ግብዓቶች ተገኝተውበታል ብለዋል፡፡
ክልሉ ላይ የተፈጠረው ችግር የክልሉ ልዩ ኃይል ሪፎርም በአግባቡ አለመመራትና በሩስያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የ2015 ምርት ዘመን ማዳበሪያ መዘግየት ዋንኛ መንስኤዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸው ችግሮች በወቅቱ አለመፈታት ሌላኛው መንስኤ ሆኖ ተነስቷል፡፡ ችግሮችን በውይይትና በምክክር መፍታት ሲቻል የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ የተፈጠረው ኢመደበኛ ታጣቂ ኃይል የክልሉንና የሀገሪቱን ሰላም በማይፈልጉ አካላት ተጠልፎ ክልሉን ቀውስ ውስጥ አስገብቶታል ብለዋል፡፡
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ በክልሉ በተከሰተው አለመረጋጋት በርካታ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ከፍተኛ ንብረትም ወድሟል፤ በጥቅሉ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች አስከትሏል፡፡ የሕዝቡ ጥያቄዎች እንዳይፈቱም እንቅፋት ፈጥሮ ቆይቷል፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍ በተሠሩ የተቀናጁ ሥራዎች አንጻራዊ ሰላም ማስፈን ተችሏል ያሉት ዶክተር መንገሻ፤ ውይይቱን ተከትሎ በቀጣይነት ሰላሙን አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚሠሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሕዝቡ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ትኩረት ሰጥቶ መሠራት እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመው፤ እነዚህ ጥያቄዎች በተዋረድ መልስ እንዲያገኙ አመራሩ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለበትም በውይይቱ ተመላክቷል፡፡
መንግሥት ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ አማራዎች የሚደርስባቸውን የሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ለማስቆም መሥራት እንዳለበት ሕዝቡ ጥያቄ ማቅረቡን ጠቁመው፤ የክልልና የፌዴራል መንግሥት በመተባበር የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ተፈናቃዮችን ወደቦታቸው ለመመለስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በጥቅሉ ሕዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች የክልሉና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ለቅመው ይዘዋል ያሉት ቢሮ ኃላፊው፤ በክልል የሚፈቱትን በክልል፣ በፌዴራል መፈታት የሚገባቸውንም በፌዴራል መንግሥቱ አማካኝነት እየተፈቱ እንደሚሄዱ ጠቁመዋል፡፡
ሕዝባዊ ውይይቱ በተዋረድ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፤ ሕዝቡ አሉኝ የሚላቸውን ጥያቄዎች እንዲያነሳ ይደረጋልም ብለዋል፡፡
ሁሉም ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙት አስተማማኝ ሰላም ሲሰፍን ነው ያሉት ኃላፊው፤ ሕዝቡ መንግሥት በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያለውን ቁርጠኝነት ተገንዝቦ የድርሻውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም