«ግጭት ያለንን ያሳጣናል እንጂ ምንም አይጨምርልንም»

-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል። በወቅቱም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም ሰላምና ፀጥታን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት ከተነሱ እና ምላሽ ከተሰጠባቸው ጥያቄዎች መካከልም፤ ከአሸባሪው ኦነግ ሸኔ ጋር የተደረገው ንግግር ያልተሳካው በምን ምክንያት ነው? በአማራ ክልል የተወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የአማራ ክልል ነባራዊ ሁኔታ ከውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ምን ያህል የፀዳ ነው? መንግሥት የተዛቡ ችግሮችን ለማረምና አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን የተመለከተ ማብራሪያ ቢሰጥ!? በመንግሥትና በፓርቲ ውስጥ ያሉ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች ያላቸው ተዋንያንን ለማስተካከል ምን ያህል ዝግጁ ነው ምንስ እየተሠራ ነው? የዋጋ ንረት መባባስ፣ የንግድ ሥርዓቱ ችግር ያለበት መሆኑ ይታወቃል፤ ከማክሮ ኢኮኖሚ አመላካች ነጥቦች አንጻር ኢኮኖሚው ያለበት ደረጃ ቢገለጽ!? የሚሉት ይገኙበታል።

በሌላም መልኩ፣ ኢትዮጵያ በውጭ ብድር የዩሮ ቦንድ ወለድን መክፈል አልቻለችም የሚል መረጃ ተሰራጭቷልና በዚህ ጉዳይ ማብራሪያ ቢሰጡን!? የማዳበሪያ ስርጭትና ምዝበራን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ይታወቃል፤ ነገር ግን በአንዳንድ ክልሎች አሁንም ጥያቄ እየተነሳ ነውና ምን እየተሠራ ነው? የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አዲስ በመሆኑ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የታሰበ ነገር ካለ ቢብራራ!? ከሶማሌላንድ ጋር የተፈጸመው ስምምነት በዓለም ላይ በተፈጠሩ ውጥረቶች ምክንያት አካባቢው ችግር ውስጥ ባለበት ወቅት፤ አልሸባብ ባልተገታበት፤ ግብፅ አሁንም ኢትዮጵያን ለመጉዳት እያሴረች ባለችበት ወቅት መሆኑ ውሳኔው በጥበብ ይመራል ብዬ አምናለሁ። ይህንን ስምምነት ተከትሎ የተነሳውን ጩኸት ለመመከት በመንግሥት በኩል ምን ዝግጅት ተደርጓል? ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ጋር ያለውን ፖለቲካዊ ቅራኔዎችን ለመፍታት የታሰበ ነገር ካለ ቢብራራ!? የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለእነዚህና ሌሎችም ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ እኛም የምላሽና ማብራሪያቸውን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፡- ቅድሚያ ሰጥቼ መልስ ልሰጥባቸው የምፈልጋቸው ጉዳዮች በፀጥታና በሠላም ጉዳዮች ላይ በማተኮር ይሆናል። ከሁላችሁም እንደተነሳው ሠላም ለምናስበው ልማት ብልጽግናና አብሮነት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ሠላም በውድ ዋጋ የሚገኝ፣ በከበረ ዋጋም የሚጠበቅ እጅግ አስፈላጊ የሆነ መሠረታዊ ነገር ነው። ሠላም በሌለበት ሁኔታ ትላልቅ ነገር ማለም፤ ማቀድ ያስቸግራል። የኢትዮጵያን ሠላም፤ ደህንነትና ፀጥታ የሚያውኩ አንኳር አንኳር ጉዳዮች ምንድን ናቸው ያልን እንደሆነ አንደኛ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፍላጎት የማሳኪያ ስልትና ልምምድ ችግር አለበት።

አንድ ግለሰብ ወይም ግሩፕ የፖለቲካ ፍላጎትን ማስፈጸም ሲፈልግ ተደራጅቶ ሀሳብ ሰንቆ በሃሳብ አሸንፎ ሥልጣን የመያዝ ልምምዱ ባለፉት 50 ና 60 ዓመታት ያልታየ በመሆኑ እንደ ባሕል እየተወሰደ ያለው የፖለቲካ እሳቤ ያላቸው ማንኛውም ኃይሎች ፍላጎታቸውን በሃሳብ ሳይሆን በጠመንጃ ማሳካት መፈለግ አንዱ አደገኛ ስብራት ነው። ሁለተኛው የችግር መፍቻ መንገድ ነው። ማንኛውም ችግር በግለሰቦች በቡድኖች በሕዝቦች መካከል ሲያጋጥም ችግሩን ለመፍታት የመነጋገር፤ የመወያየት በሽምግልና ጉዳዩን የማየት ልምምድ እየቀነሰ መምጣት ነው።

ሦስተኛው የሠላም ጅማሮዎች ሲኖሩ ከግራም ሆነ ከቀኝ በሠላም መንገድ ላይ ወጥመድ ማስቀመጥ ስላለ ነው። ለሠላም የሚደረግ ጉዞ አበጀህ በርታ የሚባልበት ሳይሆን ወጥመድ እንቅፋት እየተቀመጠ ወደኋላ እንዲመለስ የማድረግ ልምምዱም የሰፋ በመሆኑ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች በኢትዮጵያ አንድነትና በጥቅም ጉዳይ ላይ የሚነሱ ችግሮች ቢሆኑ ምንም አይደለም፣ አብዛኛው የኢትዮጵያን አንድነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል አድርጎ የሚነሱ ጉዳዮች ቢሆኑ ምንም አይደለም።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል አድርጎ ቢነሳ ኖሮ ኢትዮጵያውያን ቀይ ባሕርን ለመጠቀም የምናደርገው ሠላማዊ ሙከራ መላው ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን እውነት የተገነዘቡ ወዳጆቿ ሁሉ በቀና ዓይን የሚመለከቱት መሆን በቻለ ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ አንድነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል ሳይደረግ ግለሰቦች ለግል ጥቅማቸው ወይም ለግሩፕ ጥቅማቸው ሲሉ እነዚህን ወሳኝ ሀገራዊ ጥቅሞች ድርድር ውስጥ ስለሚያስገቡ በቀላሉ ወደግጭት እየገባን የምንገዳደልበት፤ የምንጎዳዳበት፤ ልማታችን የሚደናቀፍበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ከሠላም ድርድር ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ድርድሩ ምን አመጣ? ምንስ ተገኘ? የሚል ጥያቄ ሲነሳ እንጂ ጦርነት ምን አስገኘልን ምንስ አተረፍን የሚል ጥያቄ አይታይም። ማንሳት መወያየት የነበረብን ወደጦርነት ገብተን አንደኛው ወንድም ሌላውን ወንድሙን ገድሎ፤ አቁስሎ፤ አጉሎ ምን አተረፍን የትኛው ፍላጎታችን አልያም ጥያቄያችን ምላሽ አገኘ ብለን ብንገመግም ብናገናዝብ፤ ከዚያ ቀጥለን ሠላሙስ ምን አመጣ ብንል የተሟላ ይሆን ነበር። አብዛኛው ጥያቄ ግን የሠላም ድርድሩ ምን አመጣ ነው። ይህ በመሆኑ ምክንያት አበክረን የምንፈልገው ሠላሙን ሳይሆን ግጭቱን አንደሆነ ያመላክታል።

በዚሁ አግባብ በሀገራችን ውስጥ በተለያየ ስፍራ በሚገባም በማይገባም በቀላል ሊፈታም በሚችል ምክንያት ሁሉ ጦርነት ግጭት መፈናቀል ይታያል። ለምሳሌ የሸኔን ጉዳይ ብንወስድ አንዱ የሚነሳው ጥያቄ ከሸኔ ጋር የተደረገው ድርድር ግልጽ አይደለም፤ ምንም ተስማምታችሁ ነው ወደ ሀገር ውስጥ የመጡት? ምን ቃል ተገብቶላቸው ባይመለስላቸው ነው ወደ ግጭት የገቡት? የሚል ጥያቄ በግራም በቀኝም ይነሳል። ያው ሁላችሁም እንደምታስታውሱት የሠላም ጥሪው የኢትዮጵያ ተፋላሚ ኃይሎች ከያሉበት ሀገር ወደሀገራቸው ተመልሰው የሃሳብ ትግል እናድርግ የሚለው ጥሪ በመጀመሪያው ቀን የፓርላማ ንግግር ውስጥ የተካተተ ነው።

ከለውጡ ጅማሮ ከተደረገው ንግግር ውስጥ አንዱ የቀረበው ጥሪ ለሁሉም ኃይሎች ይህ ነበር። ከለውጡ ሦስትና አራት ወራት በኋላ ፓርላማ ላይ በነበረን ንግግር አንዳንዶቹን ስማቸውን በመጥቀስ ከእንግዲህ በኋላ ልንገዳደል አይገባም ወደሀገራችሁ ግቡ፤ ወደሀገራችሁ ለመግባት የሚያስቸግራችሁን ነገር እኛ እናስተካክላለን በሠላማዊ መንገድ ታገሉ ሥልጣን በሃሳብ ትግል ሊገኝ ይችላል የሚል ጥሪ ረበው ከዚህ ቤት ነው።

ከዚያ በኋላ ኦነግም ፤ኦብነግም፤ ግንቦት 7ትም፤ ኢሕአፓም ሌሎችም ፓርቲዎች ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ጥሪ ቀርቦላቸው ወደሀገር ውስጥ ገብተው በተለያየ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ሁኔታ ከኦነግ ጋር የተደረገው ስምምነት ምን ነበረ? ብሎ ማንሳት ምናልባት ነገርየውን በሴራ ዓይን ከማየት ያለፈ ጥቅም ያለው አይመስለኝም። ለኦነግ የቀረበው ጥሪ ለኦብነግ ከቀረበው ጥሪ ልዩነት የለውም አንድ ነው። ለኦነግ የቀረበው ጥሪ ለግንቦት ሰባት ከቀረበ ጥሪ ምንም ልዩነት የለውም።

በነገራችን ላይ ኦነግን ወክለው በኃላፊነት ደረጃ አሥመራ ላይ ንግግር ያደረጉት ሰዎች አብዛኞቹ አዲስ አበባ ናቸው ። ከፊሉም በዚህ መንግሥት ውስጥ ተካተው የመንግሥት ኃላፊነት ወስደው ሥራ እየሠሩ ነው። የተለየ ድርድርና ምክክር ካለ ግማሾቹ እዚህ ገብተው ሥልጣን የሚጋሩበት ሌሎቹ ደግሞ ጫካ ገብተው ሰው የሚያሰቃዩበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ሀሳቡ ለሁሉም አንድ ነው።

ታንዛንያ በነበረው ድርድር የግልጸኝነት ችግር አለ ብለው ለሚያስቡ ኃይሎች ወደ ታንዛንያ ድርድር ስንጀምር ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልጽ ድርድር እንደምንጀምር ተገልጿል፤ ድርድር ከጀመርን በኋላ በነበሩ ውይይቶች ሲጨመቅ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ነገር አሳካን ብለን ለመናገር የሚያስችል ድምዳሜ ላይ ባለመደረሱ ምንም ነገር ማቅረብ አልቻልንም። ወደፊት ልቦና ሰጥቷቸው የኢትዮጵያን ሕግና ሥርዓት አክብረው በውይይት አምነው ድርድሩ ሲፈጸም ደግሞ በግልጽ ለተከበረው ምክር ቤት እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሪፖርት ይቀርባል።

ከሸማቂያን ጋር መነጋገር መደራደር ግን በኢትዮጵያ ያለ አዲስ ልምምድ አይደለም፤ ለምሳሌ እንግሊዝን ብንወስድ ከአይሪሽ ሪፐብሊካን አርሚ ጋር ለረጅም ዓመታት ይደራደሩ ነበር፤ በኮሎምቢያ ከፋርክ አማጽያን ጋር ለረጅም ጊዜ ድርድር ይካሄድ ነበር። ድርድር እያካሄዱ ችግርን መፍታት እዚህ የጀመርነው ጉዳይ ሳይሆን የዓለም ልምምድ ነው። ከሁቲም ጋር ብዙ ኃይሎች ንግግር ምክክር ያደርጋሉ። ንግግር ማለት ውይይት ማለት ለመነጋገር በር መክፈት ማለት በሁሉም ጉዳይ ላይ መግባባት ላይሆን ይችላል።

ሸኔ በአሥመራ የነበረው ድርድር በመንግሥት ሳይሟላ ቀርቶ ቃል የተገባው ነገር ሳይፈጸም ቀርቶ ከሆነ ወደ በረሃ የገባው እታገልልሃለሁ ለሚለው ሕዝብ ተጨንቆ መብት ስላጣ ፣ሠላም ስላጣ ፣ ልማት ስላጣ በርሃ ገብቶ ከሆነ ያንኑ ሕዝብ እያገቱ ልማት እንዳይሠራ እያደረጉ ከሆነ ዘረፋ መፈጸም ለኦሮሞ ሕዝብ ምንም ዓይነት ፋይዳ አያመጣም። አሁን ሸኔ ተሠማርቶ ያለው ግለሰቦች ማገት፣ መኪና ማቃጠል፣ ልማት እንዳይሠራ ማድረግ ነው። ይህ በማንኛውም የትግል መስፈርት ለሆነ ዓላማ መሳኪያ የሚደረግ የትግል ስልት ተብሎ ሊወሰድ አይችልም። አይችልም! ጥፋት ነው።

እንበልና እንካችሁ ውሰዱስ ቢባሉ በምን ሞራል ነው የዘረፍከውን፣ የገደልከውን፣ ያገትከውን ሕዝብ ነገ ልምራህ የምትለው? ይህ አግባብ አይመስለኝም። ልቦና ገዝቶ ወደሠላም መድረክ ራስን ማምጣት ያስፈልጋል። የራስን ሕዝብ እያሰቃዩ እታገልልሀለው ማለት ጥቅም የለውም። ለኦሮሞ ሕዝብ የሚያስፈልገው በሰላም፣ በንግግር፣ በውይይት አማራጭ ሀሳብ በማቅረብ የተሻለ ሀሳብ ያለው ሰው በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የሚይዝበትን ዲሞክራሲያዊ ልምምድ ማሳደግ ብቻ ነው።

ይህ በድርድርና በነሱ ወገን የሚታይ ቢሆንም እዚህ መሐል ተቀምጠው በሸኔም በሌሎችም አማጺያኖች የማይጨበጥ ተስፋ የሚጠብቁ ሰዎች ደግሞ አሉ። ኦሮሚያ ውስጥ አርሲ አካባቢ አንድ የሚታወቅ አባባል አለ። አንድ ሞኝ አዳኝ ለአደን ካልወጣሁ ብሎ፤ ከቤተሰብ ተሰናብቶ አደን ከወጣ በኋላ አንበሳ ሊገል ወጥቶ፤ በአራተኛው ቀን በአንበሳ ይበላል። በአንበሳ መበላቱ ጭምጭምታ ወሬ ተሰምቷል። ግን መበላቱን የማይቀበሉ ሰዎች በየቀኑ አዳዲስ ዜና ያመጣሉ። ዛሬ ሞኞ ወይም ጎጊቻ አራት አንበሳ ገደለ ሰሞኑን በድል ይመለሳል ይላሉ።

በሳምንቱ የለም አራቱን አንበሳ እየገፈፈ ቆዳቸውን እስኪያወጣ ድረስ ትንሽ ጊዜ ወስዶበት ነው ይመጣል ይላሉ። በሳምንቱ የነዛን አራት አንበሶች ቆዳ ሰፍቶ ልብስ አድርጎ ለብሶ ሊመጣ ነው ይላሉ። በሳምንቱ በዛ አካባቢ ያለ ገዢ በጀግንነቱ ተደሞ ሽልማት ሊሸልመው ድግስ እያዘጋጀ ስለሆነ እሱ ይዞት ነው ይመጣል ይላሉ። ያ የተበላው ሞኞ እስካሁን ይመጣል ይመጣል እየተባለ ይጠበቃል።

ይሄን በሞኝነት የመጠበቅ ነገር ትተን ኢትዮጵያ ውስጥ በሠላም፣ በምርጫ፣ በዲሞክራሲ ካልሆነ በስተቀር በጠመንጃ፣ በአፈሙዝ ከእንግዲህ በኋላ ሥልጣን ይዞ ማስተዳደር አይቻልም። በብዙ ምክንያት አይቻልም። ያለው አማራጭ ሀሳብ ማደራጀት፣ መትጋት፣ ሕዝብ ማሳመን፣ በዚያ የሀሳብ ልዕልና ሥልጣን መያዝ ብቻ ነው። እና ተስፈኝነት የማይጨበጥ ነገር እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። ይህ ተስፈኝነት ነው ሠላሙን በአንድ በኩል እንዳይመጣ የሚገዳደረውና የሚያስቸግረው ብዬ ስለማስብ ነው።

ከአማራ ክልል አንጻር በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት በአማራ ክልል በሁሉም ዞኖች ፣ከከሚሴ በስተቀር በሁሉም ዞኖች ከሕዝብ ጋር ውይይት ለማድረግ እድል አግኝቻለሁ። በተደጋጋሚ ከአማራ አካባቢ ከተወለዱ ምሑራን፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ባለሀብቶች፣ ወጣቶች ውይይት ለማድረግ እድል አግኝቻለሁ። በነዚያ የውይይት ጊዜ ውስጥ ከሞላ ጎደል በሁሉም አካባቢ የጋራ በሚባል መልኩ የሚነሱ ሦስት ወሳኝ ጥያቄዎች ነበሩ።

አንድ የልማት ጥያቄ..ተጎድተናል፣ ወደኋላ ቀርተናል፣ ልማት የለም የሚል። ሁለት የሕገመንግሥት ጥያቄ..ሕገመንግሥቱ አግሎን ተነስቷል ማሻሻያ ያስፈልገዋል የሚል። ሦስት የወሰን ይገባኛል ጥያቄ። ከዚህ በተጨማሪ በመልካም አስተዳደር በአንዳንድ ጉዳዮች የሚነሱ እዛም እዛም እንዳየአካባቢው የሚለያዩ ጥያቄዎች ነበሩ። እነዚህን ጥያቄዎች ከተወያየን በኋላ አደራጅተን የአማራን ሕዝብ ጥያቄ መመለስ አለብን ይሄንን ጥያቄ ቸል ብለን በመሄድ ዘላቂ ሠላም ልናረጋግጥ አንችልም የሚል ቁርጠኛ አቋም ነበረን።

ለምሳሌ ልማትን በሚመለከት ባለፉት አምስት ዓመታት በአማራ ክልል 53 የመንገድ ፕሮጀክቶች ቀርጸን ሥራ ጀምረናል። እነዚህ ፕሮጀክቶች 3200 ኪሎ ሜትሮችን ይሸፍናሉ። ጣሊያን ትልቁ ልማት በኢትዮጵያ የሠራው የሚባለው ኃይል በቆይታው በአምስት ዓመታት ውስጥ እንደሀገር 6 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ ተሠርቷል። ባለፉት አምስት ዓመታት በአማራ ክልል ብቻ 3200 ኪሎሜትር የመንገድ ሥራ ተጀምሯል። ከዚህ ውስጥ 1300 ኪሎ ሜትር ተጠናቋል። ተጠናቆ ሥራ ጀምሯል።

የባሕር ዳር ድልድይን ብቻ ብንወስድ ዓባይ የነበረው ድልድይ በማንኛውም ሰዓት ሊፈርስ ይችላል ጎንደርና ጎጃምን ማገናኘት ያስቸግሯል የሚል ጥያቄ ቢኖርም በአንድም ዞን በነበረን ውይይት አሁን እኛ የሠራንውን ዓይነት ድልድይ እንዲሠራ ጥያቄ አልቀረበም፤ ሊቀርብም አይችልም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶ ስለማይታወቅ። ሰው የማያውቀውን ነገር አይጠይቅም።

አሁን ባሕርዳር ላይ የሠራንው ድልድይ እና አፕሮች ሮዱ ሲደመሩ 2ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገደማ ወስደዋል። 2ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር አውጥተን ድልድይ ስንሠራ የመጀመሪያችን ነው። ይሄ ድልድይ አፕሮቹ 51 ሜትር ራሱ ድልድዩ 49 ሜትር በአቭሬጅ 50 ሜትር ስፋት አለው። በሁለት መንገድ ሦስት ሦስት መኪና የሚያሳልፍ ስድስት ሌን አለው። በሁለት መንገድ መኪና ብቻ ሳይሆን ሳይክልም የሚሄድበት ሦስት ሦስት ሜትር አለው። በሁለት መንገድ አምስት፤ አምስት ሜትር እግረኛ መንገድ አለው።

ውበቱን ትተን በዚህ ስፋት ልክ እና ያን ርዝማኔ የያዘ መንገድ ድልድይ ኢትዮጵያ ውስጥ ስንሠራ የመጀመሪያችን ነው። በጥራቱም፤ በዋጋውም። ይሄ የሆነበት ምክንያት ያ የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት፣ ምላሽ ሳንሰጥ እንዲሁ መቀጠል አይቻልም ከሚል ነው። እዚህ ጋ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር ይሄ 3200 ኪሎ ሜትር መንገድ እንደዚህ ቀደሙ አማራን ከትግራይ፣ አማራን ከቤኒሻንጉል፣ አማራን ከኦሮሚያ፣ አማራን ከአፋር የሚያገናኝ መንገድ አይደለም።

መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ አማራን ከአማራ በዞን እና በወረዳ የሚያገናኝ/ ኮኔክት የሚያደርግ መንገድ ነው። ከዚህ ቀደም የፌዴራል መንገድ ተብሎ የሚቆጠረው ከዚህ መቀሌ የሚሄደው፣ ከዚህ ጎንደር የሚሄደው ወይንም ከጎንደር መተማ የሚሄደው ወደ ሱዳን የሚሻገረው ሊሆን ይችላል። እነዚህ መንገዶች ግን አብዛኞቹ ዞኖችን ከዞኖች፣ ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኙ ናቸው።

ይህ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ እንዲደረግ ያደርጋል። የዞን ጥያቄን ለመመለስ የምናደርገውን ጥረት በተጨባጭ ያመላክታል። ሁለተኛ 3200 ኪሎ ሜትር አንድም ኪሎ ሜትር ሽሮ ፈሰስ የለውም፣ አስፓልት ኮንክሪት ነው። ለጊዜው ለመመለስ ሳይሆን ጠንካራ ለትውልድ የሚሸጋገር መንገድ መሥራትን ታሳቢ ያደረገ ነው። ሦስተኛ በጥገና የምንሠራቸውን አይጨምርም። ቀድመው ተሠርተው በጥገና የምንሠራቸውን አይጨምርም።

ይሄ ጉዳይ ከመንገድ አንጻር በቂ ነው ባይባልም በአማራ ክልል የተነሳውን የልማት ጥያቄ ለመመለስ መንግሥታችን ብዙ ርቀት እንደሄደ አመላካች ነው። ከዚያ በላይ አስር ሺህ፣ ሀያ ሺህ፣ ሠላሳ ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ ቢሠራ አይበቃም። አማራ ክልል ትልቅ ክልል ነው ብዙ ሊገናኙ የሚገባቸው ቦታዎች አሉ። በአምስት ዓመት ውስጥ የሞከርናቸው ሙከራዎች ግን ለሕዝቡ ጥያቄ ያለንን ክብር የሚያሳዩ ናቸው።

ከዚያ በተጨማሪ ሁላችሁም እንደምታውቁት የአማራ ክልል ለቱሪስት ምቹ የሆነ ነው ፣ ታሪክ አለው፣ ባሕል አለው፣ የሚያምር መልክዓ ምድር አለው ያን ታሳቢ አድርገን በጎርጎራ ላይ የሠራንው የጎርጎራ ፕሮጀክት በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። አንዱም ፕሮጀክት ጎርጎራን አያክልም።

ምናልባት እስካሁን እኔ ባለኝ እውቀት በአፍሪካም በዚያ ደረጃ ግዝፈት ያለው፣ ውበት ያለው፣ ጥራት ያለው ሪዞርት መኖሩን እጠራጠራለሁ። እኔ አይቼ አላውቅም። በዚያ ጥራት ልክ ለትውልድ እንዲሸጋገር ተደርጎ የተሠራው ሕዝቡ ለልማት ያለውን ጥያቄ በመንግሥት በጀት ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የፋይናንስ ምንጮችም አድርገን ብንመልስ የሰውን ድካም የሚገነዘብ ሕዝብ ስለሆነ ድካማችንን እያየ እያገዘን በቀጣይነት ጥያቄዎቹ ምላሽ እያገኙ ይሄዳሉ ከሚል እሳቤ ነው።

የላሊበላን ውቅር አብያተክርስቲያን እንደምታውቁት ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ፕሬዚዳንት ማክሮንን እዛው ድረስ በአካል ይዘናቸው ሄደን የጥገና ሥራ ተጀምሯል። በሠላሙ ምክንያት ወጣ ገባ ቢልም የሚሠራው ሥራ የላሊበላን ቤተክርስቲያን የሚያክል እጅግ ድንቅ የእጅ ሥራ ሳይበላሽ ለትውልድ እንዲሸጋገር የሚያደርግ በጣም በጣም ጠቃሚ እሳቤና የሥራ ጅማሮ ነው። አካሄዱ መልካም ነው፤ አልፎ አልፎ በሠላም ምክንያት ወጣ ገባ የሚል ነገር አለ። ግን ያ የሆነበት ዋናው ምክንያት በቱሪስት መስሕብነት ድንቃ ድንቅ ቦታዎች በደንብ ቢሠሩ ተጨማሪ ገቢ ተጨማሪ የሥራ ዕድል ሊገኝ ይችላል ከሚል እሳቤ ነው።

ሁላችሁም እንደምታስታውሱት የፋሲል ቤተመንግሥት በጣም አስደናቂ ሥራ ነው የተሠራው። ግን ግማሽ አካሉ ፈርሷል ። የፈረሰውን ፋሲል ነው ስናስጎበኝ የኖርነው። ይህ አግባብ አይደለም ፤መታደስ አለበት የመደመር መጽሐፍ ፅፈን ፋሲልን መልሰን እናድስ መጽሐፍ እስኪሸጥ ከሌላ ምንጭ እንጀምር ብለን በአካል ቦታው ድረስ ሄደን ሥራውን ለማስጀመር ሙከራ አድርገን ነበር። በተለያዩ አሉባልታዎችና ሴራዎች ሥራው እንዳይከናወን አስቁመውታል።

ሁላችሁም እንደምታውቁት የዩኒቲ ፓርክ ሲታደስ ከመታደሱ በፊት በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት በጣም ቆሻሻ ቦታ ነው። አሁን ታድሶ በርከት ያሉ መቶ ሚሊዮኖች አስገብቶ ታችኛውን ቤተመንግሥት እያደሰ ነው። ታችኛው ቤተመንግሥት በንጉሡ የተሠራ ቤተመንግሥት በጣም ጥሩ ሥራ ቢሆንም ክትትልና ጥገና ባለመኖሩ በከፍተኛ የመፍረስ ፤የመዳከም አደጋ ውስጥ ነበር።

ዛሬ ታችኛው ቤተመንግሥት ሦስት ሺህ አራት መቶ ሠራተኞች ያሉት አስራ ሦስት ፕሮጀክት አለው፤ በሚቀጥሉት ሁለት ሦስት ወራት ይጠናቀቃል። ካለምንም ጥርጥር አዲስ አበባ ውስጥ እጅግ ውብ ከሆኑና ሊታዩ ከሚገባቸው ሥፍራዎች አንዱ ነው። ልክ እንደ ዓድዋ ትልቅ እንደ ዓድዋ ጥርት ያለ የኢትዮጵያ ልክና አስፕሬሽን የሚያሳይ ነው። ፋሲል ላይም ያሰብነው ይህንኑ ነበር። ሌላ ጉዳይ ሳይሆን ልክ የምኒሊክን ቤተመንግሥትን እንዳደስነው የኃይለሥላሴን እንዳደስነው የፋሲልም ቢታደስ ተጨማሪ ገቢ ያስገባል ውበቱን፣ ክብሩን፣ ታሪኩን ማስጠበቅ ይቻላል ከሚል እሳቤ ነው።

ከዚያም ባሻገር ጦርነት አገደን እንጂ የጣናን ውሃ እስከ ጎንደር በመውሰድ ለማገናኘትም በርካታ የጥናት ሥራዎች ተሠርተዋል። በልማት ዙርያ በቱሪዝም፣ በመንገድ፣ በግብርና አንዳንድ ግድቦች ሲጀመሩ በወግ ያልተጀመሩ ተጨማሪ ሀብት የሚያስወጡ በጥረት እንዲሠሩ የተወሰነና እየተሠሩ ያሉ ግድቦች አሉ።፤ ያለቁ ግድቦች አሉ በኢንዱስትሪ የጨረስናቸው ኢንዱስትሪያል ፓርኮች አሉ። አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችም ባሕርዳር አካባቢ እንደሚታዩት በተወሰነ ደረጃ ለማስፋፋት ተሞክሯል።

ይህ ሁሉ ጉዳይ የመጣው ሕዝቡ አበክሮ ያነሳው የልማት ጥያቄ ቀዳሚ አጀንዳ ስለነበረ ባለን ውስን አቅም ያን እየመለስን ካልሄድን በስተቀር የተረጋጋና የሚያድግ ሀገር ማየት ስለማንችል ነው። ሁለተኛው ከልማት ቀጥሎ የሚነሳው የሕገመንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ ነው። ቀደም ብሎ ከለውጥ በፊት በነበረው ሁኔታ ሕገመንግሥት ማሻሻል የሚባል ጥያቄ የሚያስተናግድ ሁኔታ አልነበረም።

አንድ ጥያቄ ምላሽ አገኘ የሚባለው ጥያቄውን የሚቀበል አመለካከት ካለ ሀምሳ በመቶ ለመልስ ተዘጋጀ ማለት ነው። እውነት አላቸው፤ የሕገመንግሥት ማሻሻያ ጥያቄ በኦሮሚያም ይነሳል በርካታ ጥያቄዎች አሉ፤ በሶማሌም በአፋርም በተለያዩ ቦታዎች ይነሳሉ። ከዚያ በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ትናንሽ በሚባሉ አጀንዳዎች ላይ ስንጋጭ ፤ስንጨቃጨቅ የምንገኝ ሰዎች ስለሆንን፤ ከነዚህ ጉዳዮች ወጥተን የተስማማንበትን የጋራ የሆነና ዘለግ ላለ ግዜ የሚቆይ ሕገመንግሥት ቢኖረን መልካም ነው ከሚል እሳቤ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል።

ለምን ሆነ ያ? ደርግ መጥቶ የንጉሡን ሕገመንግሥት ቀዶ የራሱን ሕገመንግሥት ፃፈ። ውስጣችን አልተቀበልነውም ፈርተን ዝም አልን፤ ኢሕአዴግ ሲመጣ ቀዶ የራሱን ፃፈ። አልተቀበልነውም ለውጥ ሲመጣ ይቀደድ አልን፤ እኛም ብንፅፍ እኛ ስንሄድ መጭው ከሚቀደው ሕዝቦች ተወያይተው ተመካክረው አንዱ ያለውን ሀሳብ አንደኛው እንዲቀበል በሀሳብ አሳምኖ ምናልባትም የማንግባባበት ጉዳይ ካለም በሕዝበ ውሳኔ አድርገን ከእኛ ባሻገር የሚዘልቅ ሕገመንግሥት ይኑረን ሕገመንግሥት ከመንግሥታት ጋር የሚቀየር መሆን የለበትም በሚል እሳቤ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል፤ ለናንተም ሪፖርት አቅርቧል። እኔ ያለኝ ተስፋ የአማራ ክልል፣ የኦሮሚያ ክልል ሌሎችም ክልሎች ይህንን ኮሚሽን አግዘው ሀሳባቸውን አጀንዳቸውን አስጨብጠው በውይይት ዘላቂ ሕገመንግሥት ብናሻሽል እግረ መንገዱን ሁለተኛው የአማራ ጥያቄ ምላሽ ያገኛል ማለት ነው።

ሦስተኛው ጥያቄ የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ነው። ከወሰን ጋር ተያይዞ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት የይገባኛል ጥያቄው ሁሌም በተለያየ ደረጃ ይነሳ ነበረ። ግን ጠያቂዎች የሚታሠሩበት፤ ጥያቄውን ማንሳት እንደ መብት የማይታይበት ሁኔታ ተቀይሮ አሁን ጥያቄውን ማንሳት ይቻላል። ችግር ካለ ተወያይተን ተመካክረን የሕዝብ ይሁንታ ማዕከል አድርገን መወሰን አለብን በሚል እሳቤ በትግራይም፤ በአማራም በኩል ያሉ የይገባኛል ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ያሰብነው ዘላቂ ሠላምን በሚያረጋግጥ መንገድ ቢሆን ይሻላል። ትግራይን ነጥቄ ይዤ በጉልበት ልያዘው ቢል አማራን ነጥቄ ይዤ በጉልበት ልያዘው ቢል የግዜ ጉዳይ እንጂ ዘላቂ የሆነ ሠላም ማምጣት አይቻልም።

ሁለቱ ሕዝቦች ደግሞ አይነጣጠሉም። አብረው የሚኖሩ ናቸው። አንስተን የምናቀያይረው ነገር አይደለም። ያለው መፍትሔ በሰከነ መንገድ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሑራን ተሳትፈውበት በምክክር በውይይት ሠላምን በሚያረጋግጥ መንገድ እንፍታው። ለምሳሌ ደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄ በጣም ትልቅ አጀንዳ ነበር፤ አጨቃጫቂ አጀንዳ ነበር፣ እዚህ ምክር ቤት ተደጋጋሚ ጥያቄ ይነሳ ነበር፤ ስከኑ ተወያዩ ሕዝብ ይወስን ተብሎ በሕዝበ ውሳኔ የመጣውን ውጤት ታውቃላችሁ። ልክ እንደዚሁ እዚያም አካባቢ ሠላማዊና በውይይት ላይ የተመሠረተ ነገር ካልተከተልን በስተቀር ዘላቂ ሠላም በሕዝቦች መካከል ማረጋገጥ እንቸገራለን።

እስከዛ ድረስ ግን ያ ሕዝበ ውሳኔ እስኪካሄድ አንኳር አንኳር ጉዳዮች ቢመለሱ ያልነው፦ አንደኛ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀዬአቸው ይመለሱ፣ ኢትዮጵያውያን ናቸው ወደ ቀዬአቸው ይመለሱ። ሁለተኛ ሕዝብ እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ ሕገመንግሥታዊ ስለሆነ በውክልና ልንገዛው ስለማንችል ሕዝቡ ከሰፈረ በኋላ በቀበሌ በወረዳ ደረጃ ከራሱ ልጆች የሚያስተዳድሩትን ሰዎች መርጦ እንዲያስተዳድር እናድርግ፤ ለጊዜው። ሦስተኛ በምሑራን በሃይማኖት አባቶች፣ በሽማግሌዎች፣ በወጣቶች ውይይት እያደረግን በሁለቱም ሕዝቦች መካከል ያሉ ጥያቄዎች እንዲስተናገዱ አድርገን በሕዝበ ውሳኔ ሕዝቡ ወደፈለገበት እንዲጠቃለል እናድርግ። ይህንን ካደረግን ዘላቂ ሠላም ልናመጣ እንችላለን።

ከዚህ ውጭ ያለን አማራጭ ግን ጊዜያዊ ድል እንጂ ዘላቂ ሠላም አያረጋግጥም የሚል አቋም ወስደን ለሁለቱ ክልሎች ነግረን ሥራ ልንጀምር ስንዘጋጅ ግጭቶች አጋጠሙን። አሁን የፌዴራል መንግሥት አቋም ከኦሮሚያ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ወደ ሥፍራቸው መመለስ አለባቸው። በኦሮሚያ ሄደው መኖር መብታቸው ነው። ይህ መብታቸው መከበር አለበት ብለን እንደ ፓርቲ ወስነን የሁለቱ ክልል አመራሮች የተፈናቀሉበት አካባቢ ድረስ ሄደው፤ የሕዝቡን ዝግጁ መሆን አይተው፤ ቀዬአቸው መጠበቁን አይተው እንዲመለሱ ሥራ ጀምረዋል። እነዚህ ሰዎች እንዳይመለሱ ባሉበት እንዲቆዩና ለፖለቲካ መሣሪያ እንዲሆኑ ሆስቴጅ ተደርገዋል።

እነዚህ ዜጎች መመለስ አለባቸው፤ ሀገራቸው ነው። ያ ስብራት ትክክለኛ ስብራት አይደለም መጠገን አለበት። ወንድም ከወንድሙ ጋር እንዳይኖር መደረግ የለበትም። እንደዚሁም የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች ከኦሮሚያም ከአማራም ካሉ መመለስ አለባቸው። ይህንን ለማድረግ ሁላችንም ዝግጁ መሆን አለብን። እንደዚያ ካልሆነ በጋራ የጋራ ሀገር ገንብተን መኖር አንችልም።

ለዚህ ደግሞ የሁሉም ልቡ የተከፈተ መሆን ይኖርበታል። እኛ ያሰብነው አማራጭ ይኸው ነው። ባለፈው እንዳነሳሁት ግን ከዚህ የተሻለ አማራጭ የትግራይ ምሑራን፤ የአማራ ምሑራን ማምጣት ከቻሉና ጉዳዩ ከጦርነት በመለስ በሠላማዊ መንገድ ሁለቱን ሕዝቦች ሳያጨቃጭቅ የሚፈታበት መንገድ ካለ፤ የፌዴራል መንግሥት ተባባሪ ይሆናል።

እኔን ደግፈህ አንዱን ካልገፋህ ከተባለ ግን የፌዴራል መንግሥት ለሁሉም ሕዝቦች በእኩል ማየት ስላለበት ይቸገራል። ይሄንን ችግሩን መገንዘብ አስፈላጊ ይመስለኛል። እኛ የምንፈልገው ተወያይተን ተስማምተን የሕዝቦችን ይሁንታ፣ የሕዝቦችን ፍቃድ ታሳቢ ያደረገ ነገር ቢሆን ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ ይችላል ብለን እናምናለን። በዚህ አግባብ ነው ጥያቄዎችን እየመለስን የሕዝብን እርካታ ደረጃ በደረጃ ለማረጋገጥ የሞከርነው።

በቅርቡ እንኳን ታስታውሱ እንደሆነ፤ የክልሉ አዲሱ አመራር ሕዝቡን ሲያወያይ፤ ሁለት አንኳር ጥያቄ ተነስቷል ።አንደኛው የሠላም ጥያቄ፤ ሠላም እንፈልጋለን የሚል፣ ሁለተኛው የፌዴራል መንግሥት ያወያየን የሚል፤ የክልሉ መንግሥት እነዚህን ጥያቄዎች እንደተነሱ ሲያቀርብ፤ የነበረን ምላሽ ለሠላሙ ጥሪ ይደረግ፤ በሠላማዊ መንገድ ገብቶ ሠላማዊ የፖለቲካ ትግል ማድረግ የሚፈልግ ኃይል ካለ በራችን ክፍት ነው፤ ይሄ ይነገር ተባለ፤ ተነገረ። በዛ አግባብም በርካታ ሰዎች ገብተው ሠልጥነው ወደ ሕዝባቸው ተቀላቅለዋል።

ሁለተኛው የፌዴራል መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች አማራ ክልል ሄደው የአማራ ክልል ሕዝብ ብሶት ችግር ያድምጡ። ያልመለስነው፤ ያልገባን ነገር ካለ ብናይ ይሻላል ብለን ወስነን፤ ሁሉም አመራር ተሠማርቶ ውይይት ተደርጓል። የውይይቱን ውጤትና የተነሱ ጉዳዮች በቅርቡ እንደፓርቲ የምንመክርበት ይሆናል። ተመካክረን ያጎደልነው ካለ ሞልተን፤ ለጊዜው ያልቻልነው ካለ ታገሱን ብለን መልሰን ስናበቃ ያልታወቀ ካለ አሳውቀን በውሸት በሚዲያ የሚዛቡ ወሬዎች ካሉም አጥርተን ከሕዝባችን ጋር መቀጠል ነው የምንፈልገው።

የሠላም ጥሪው በተደጋጋሚ ተጠርቷል። አሁንም ሸኔም፣ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎችን በሰላም በውይይት መሣሪያቸውን አስቀምጠው ሠላማዊ የፖለቲካ ትግል ማድረግ ቢችሉ የፌዴራል መንግሥትም የክልል መንግሥታትም ዝግጁ መሆናቸውን በድጋሚ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ። የምንፈልገው ሠላም ነው። የምንፈልገው ውይይት ነው። የምንፈልገው አብረን ሀገራችንን ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ማሸጋገር ነው።

ይሄ ጥያቄ እንዳልተነሳ ሳይሆን በተደጋጋሚ የተሰጠ አማራጭ/ኦፈር መሆኑን ተገንዝበን፤ አሁንም ያለው ፍላጎት ይህ እንደሆነ ከግምት እንዲገባ ነው። ከግጭት፣ ከፀብ፣ከጥላቻ፣ ከስድብ የምናተርፈው ነገር የለም። ግጭት ያለን ያሳጣናል እንጂ ምንም አይጨምርልንም። እስካሁን የነበሩት ግጭቶች በኦሮሚያ ወለጋ አካባቢ የነበረው ግጭት፤ የነበረ አጎደለ እንጂ የጨመረው ነገር የለም። አማራ አካባቢ ያለው ግጭት ትግራይ አካባቢ የነበረው ግጭት አጎደለ እንጂ የጨመረው ነገር የለም። ከግጭት ከመክሰር፤ ከመጉደል ውጭ ትርፍ አይገኝበትም። ላለመጋጨትና በሰላም ነገር ማየት፤ በሠላም ተወያይቶ መፍታት መለማመድ ጥሩ ሀሳብ ይመስለኛል።

ለዚህ ቅድም የተነሳው የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ምሑራን፣ ወጣቶች የሚጠበቅባቸውን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። ሠላም ካለ ሀገር ስለሚቀጥል ሁሉም ሰው ሚናውን ይጫወት። የፌዴራል መንግሥት ግን ለሠላም ዝግጁ ነው። ሕዝቡም የሚደገፍበትን ነገር ቢያውቅ ጥሩ ነው። ጉም ምንም ያህል ተራራ ቢያክል፤ ምንም ያክል ክምር ድንጋይ ቢያክል፤ ጉምን አትንተራሰውም። ጉም ጉም ነው። መንተራስ ያለብን ደገፍ የሚያደርገንን ነገር ነው። ዝም ብሎ የማያዘልቀንን ነገር ተንተርሰን ወደ ጥፋት እንዳናመራ በተቻለ መጠን ሠላም፣ ሠላማዊ ንግግር፣ ውይይት የሚለውን አማራጭ ብንከተል መልካም ይሆናል ብዬ አስባለሁ። በዚሁ አግባብ ለመጓዝ ነው እኛ ያለን ፍላጎት እና አቋም።

ትግራይን በሚመለከት፣ ከድርድሩ ጋር ተያይዞ ድርድሩ ግልጽ አይደለም የሚል ይነሳል። መቼም ድርድሩ ግልጽ አይደለም የሚል ጥያቄ የአማራ ሲሆን ኦሮሞ ያነሳዋል፤ የኦሮሞ ሲሆን አማራ ያነሳዋል፤ የትግራይ ሲሆን ሌላው ያነሳዋል። ስለዚህ ባለቤቱ ሳይሆን ሌላው ሰው ድርድሩ ግልጽ አይደለም፣ አልተወከልኩም የሚል ጥያቄ በስፋት ይደመጣል። ግን ትክክል አይደለም። በፕሪቶሪያ ድርድር ከተደረገ በኋላ የፌዴራል መንግሥት በይፋ ለሕዝብ ገልጿል። ለተከበረው ምክር ቤት ደግሞ እዚያ የነበሩ ሰዎች መጥተው ሙሉ መረጃ ሰጥተዋቸዋል። አወያይተዋቸዋል። የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪ ስለነበር ለመላው ዓለም ድርድሩን አግሪመንቱን (ስምምነቱን) እንዳለ በድረገፁ በቀጥታ /ፖስት/ ለጥፏል። የተደበቀ ምንም ነገር የለም። በሠላም በድርድር ሰጥቶ በመቀበል ችግራችንን እንፍታ ነው ያልነው።

ከድርድሩ በኋላ ምን ተገኘ ለሚለው ጉዳይ በተደጋጋሚ ጥያቄ ስለሚነሳ የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ የሽግግር (ጊዜያዊ ) መንግሥት በትብብር በጣም ትልልቅ ድሎችን አስመዝግበዋል። ቀለል አድርገን የምናያቸው ትላልቅ ድሎች አስመዝግበዋል። ያ ድል የፌዴራል መንግሥት ሥራ ብቻ አይደለም፤ የተቋቋመው ጊዜያዊ መንግሥትም ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ያስገኛቸው አመርቂ ውጤቶች አሉ። የሚቀሩ ያልተሟሉ በርካታ ችግሮችም አሉ።

ሰላሙ ካመጣቸው፤ በትብብር ካሳካናቸው መካከል አንደኛው አየር መንገድ ነው። የአየር ትራንስፖርት አልነበረም። መቐለ፤ ሽሬ፤ አክሱምም በከፊል ጠግነናል ፤ አሁንም እየጠገንን ነው ። ለዚህም አየር መንገዱ ግማሽ ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ አውጥቷል። ጠግኖ ሥራ ለመጀመር አየር መንገድ ገንዘብ ኢንቨስት አድርጓል፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በብዙ መንገድ ረድቶ ፣ የፌዴራል መንግሥት ይሁንታና ድጋፍ ሰጥቶ የአየር ትራንስፖርት መጀመሩ ለብዙ ሰዎች እፎይታ ነው።ቢያንስ ቢያንስ ፅኑ ሕመም ያለባቸው ሰዎች በአየር መጥተው ሕክምና የሚያገኙበት ዕድል አግኝተዋል፤ ቢያንስ ቢያንስ።

ሁለተኛው ቴሌ ነው። ቴሌኮሙኒኬሽን በትግራይ ውስጥ ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ኦፕቲካል ፋይቨር ጠግኗል። ስልክ አልነበረም እንደምታውቁት። 475 የሞባይል ሳይቶች ጠግኗል። በ10 ከተሞች ድሮ ያልነበረ የፎር ጂ ሰርቪስ (አገልግሎት) ጀምሯል፡፤ በመላ ትግራይ ከ20ሺህ በላይ የቤት ስልክ ጥገና አካሂዷል። ለዚህም በመቶ ሚሊዮኖች ወጪ ተደርጓል። ዝም ብሎ አይደለም። ብዙ ወጪ ወጥቶበት ተደክሞበት። በፌዴራል መንግሥት፤ በክልሉ መንግሥት ትብብርና ጥረት የትግራይ ሕዝብ እንደሌላው አካባቢ ውሱንነት ቢኖርበትም የስልክ የመብራት አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ሆኗል።

መብራትን ብንመለከት እንደዚሁ ተበጣጥሰው የነበሩ በርካታ ሳይቶች ተጠግነው አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል። ባንክ ብቻ ብንወስድ በትግራይ ውስጥ 600 የሁሉም ዓይነት ባንኮች ቅርንጫፎች የሚጎላቸው ተስተካክሎ ብሔራዊ ባንክ 10 ቢሊዮን ብር ገንዘብ ሰጥቶ በትግራይ ውስጥ የባንክ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ቢሮ ብቻ አይደለም ብርም ተካትቶ ማለት ነው።

መብራት፤ ስልክ፤ አየር መንገድ፤ ቴሌ ያስገኟቸው የሰርቪስ አገልግሎት ዕድገት ከውጊያው በፊት ሆነ በውጊያው ጊዜ ከነበረው ጋር የሚወዳደር አይደለም። በውጊያው ጊዜ ምንም አልነበረም፡፤ ታውቃላችሁ፤ ትራንስፖርት የለም፤ መብራት የለም፤ ስልክ የለም። ይሄ ትልቅ እመርታ ነው። ሙሉ ግን አይደለም። አሁንም ተጨማሪ ጥረትና ሥራ ይፈልጋል። በቅርቡ የኮሙኒኬሽን ኦፊስ(ቢሮ) ያወጣው ሪፖርት ላይ እነዚህን ጉዳዮች አላካተተም። ቴሌኮም፤ መብራት፣ አየር መንገድ አልተካተቱም።

ከዚህ ውጪ ትግራይ ውስጥ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ከሞላ ጎደል፣ ሁሉም ሃይስኩሎች (ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች) ሥራ ጀምረዋል። ትምህርት አልነበረም፤ አሁን ትምህርት ተጀምሯል። በነፃ አይደለም፤ ብዙ ሥራ ተሠርቶ ነው። የፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴርም፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮም በትብብር በርከት ያለ ሥራ ሠርተው ትምህርት ጀምረዋል። ይሄ አሁን ያለው የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት ሥራ ውጤት ነው፤ መራከስ የለበትም። በትምህርት ጥራት በትምህርት መስፋፋት በመጽሐፍ የሚጎል ነገር እንደማንኛውም አካባቢ ሊኖር ይችላል። አጠቃላይ ካለመማር ግን ትምህርት መጀመር በእጅጉ የተሻለ ነው።

በጤናም እንዲሁ። ሆስፒታሎች ጤና ጣቢያዎች ሥራ ጀምረዋል። የጀመሩ ጤና ጣቢያዎች በንፅፅር እንደማንኛውም ክልል የሚጎላቸው ነገር ሊኖር ይችላል። ይሁንና አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። ለዚህም ቢሊዮን ወጥቶበት ነው የተሠራው። ኢንዱስትሪን በሚመለከት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ 217 ፋብሪካዎች ሥራ ጀምረዋል። መብራት ገንዘብ ሥራ ጀምረዋል ዝም ብሎ መክፈት አይደለም። ድጋፍ ይፈልጋል። እዛ ውስጥ ሰዎች ሥራ ያገኛሉ ማለት ነው። ግብርናን በሚመለከት በባለፈው ክረምት ትግራይ 630 ሺ ሄክታር መሬት አርሷል። ክልሎች የግብርና ሚኒስቴር የተወሰነ ትራክተሮች ፓምፖች ማዳበሪያ ምርጥ ዘር ለማገዝ ሙከራ አድርገዋል።

 አሁን ግን የፌደራል መንግሥት የውጭ ምንዛሪ በተለየ መንገድ ፈቅዶ 500 ትራክተሮች ለትግራይ ክልል ተገዝተው ጅቡቲ ደርሰዋል። 500 ትራክተር ማለት ቀላል ነገር አይደለም። እዛ አካባቢ ያለውን የእርሻ ሁኔታ ከነበረበት በእጅጉ ሊያሳድግ ይችላል። በፍጥነት ገብተው ሥራ እንዲጀምር ካደረግን 300 በላይ ፓምፖች የዚህ ዓመት ማዳበሪያ እንኳን 100 ሺ ገደማ ኩንታል ተልኳል። ይህ ሁሉም እዛም ባሉ ክልሉን በሚያስተዳድሩ ሰዎች በፌዴራል መንግሥትም በሚደረግ ድጋፍ የመጣ ውጤት ነው።

ይህ ጉዳይ በቂ ነው ወይ፤ ትግራይ ከነበረበት ችግር አንፃር በቂ ድጋፍ አግኝቷል ወይ፤ ይበቃል ወይ ከተባለ የለም ገና ነው። የኢትዮጵያ አቅም ውስን ሆኖ ነው እንጂ ከዚህ በላይ መታገዝ ይኖርባቸዋል። የተፈናቀሉ በመመለስ፣ የይገባኛል ጥያቄን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከክላሽ በመለስ በውይይት፣ በድርድር፣ በሪፈረንደም በመፍታት ያስፈልጋል፤ ክላሽ ኪሳራ ነው። ክላሽ ጥፋት ነው። ዘላቂ ድል አያመጣም።

ይህን ለማድረግ በእኛ በኩል ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር ጋር በመተባበር አቅም በፈቀደ መጠን እስካሁን በሠራናቸው ላይ የጎደለውን እየሞላን የሕዝብ ጥያቄ እየመለስን መሄድ እንፈልጋለን። ፍላጎታችን ይህ ነው። የምናደርገውም ይህኑ ነው። የተገኘው ድል ግን የሚራከስ አይደለም። በጣም በርካታ ድል ተገኝቷል። የሚጎሉ ጉዳዮች አሉ። እነርሱን ደግሞ እየተወያየን፤ እየሞላን ብንሄድ ለሁላችንም የሚበጅ ይመስለኛል።

ከሦስቱ ክልል ውጪ በሁሉም አካባቢ ያለውን ሠላምን በሚዛን ማየት ጥሩ ነው። እዚህ አካባቢ የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት እንድትገነዘቡት የምፈልገው የድህ እውነት ዓለም ስለሆነ አብዛኛው ፕሮፖጋንዳ ሰዎች በፍርሃት ስሜት እንዲሞሉ የሚያደርግ ነው። ለምሳሌ ከውጭ አገር ሰዎች ሲመጡ አደራ ቦሌ አካባቢ ስለሚያፍናችሁ ተጠንቀቁ ቤት ከገባችሁ እንዳትወጡ ይላሉ፤ ይህ የፕሮፖጋናዳው አካል ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው አንድ ዓመት ይህ ሁሉ ችግር አለ እያልን፤ በየትኛውም በአፍሪካ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በርከት ያለ ሚሊዮን ሕዝብ መስቀልን፣ እሬቻን፣ ጥምቀትንና ኢድን በአደባባይ በሁሉም ጫፎች ወጥቶ የሚያከብርበት ሀገር ናት። ጥምቀት ይህ ሁሉ ሚሊዮን ሰው ወጥቶ በሀገር ደረጃ ወጥቶ ሲከበር እሬቻ እንዲሁ ሲከበር በየትኛውም የአፍሪካ ሀገር በዚያ ቁጥር በአንድ ቀን ወጥቶ ሲያከብር አይታይም። እኛ አገር ትንሽ ባሕሉ ሥርዓቱ ለየት ያለ ነው።

ሠላም አለ። ችግር ደግሞ አለ። በሚዛን። ፕሮፖጋንዳ ብቻ ከሆነ ጥሩ አይመጣም። ሁለተኛ አርበኝነት ጦረኝነት ብቻ መሆን የለበትም። ሰው በሠላም አርበኛ መሆን ይችላል። በልማት አርበኛ መሆን ይችላል። በፅዳት፣ በማስታረቅ አርበኛ መሆን ይችላል። ዘራፍ ብሎ ክላሽ መያዝ ብቻ አይደለም አርበኝነት። ይህንንም ማረቅ ማስተካከል ያስፈልጋል። ሥልጣን በኃይል ብቻ የሚለውን እሳቤ ማቆም ያስፈልጋል። አሁን ባለንበት ዓለም ሥልጣን በኃይል ብቻ ማሳካት አይቻልም ። እነዚህ ጉዳዮች በብዙ ቦታ የሚጋደል ነገር እንድናይ አድርገውናል።

በእኛ በኩል በቀጣይነት ሦስት አራት ነገሮች እናካሂዳለን። አንደኛ ሕግ ማስከበር አጠናክረን እንቀጥላለን። እጃችሁን አጣጥፋችሁ ተቀመጡ የሚለውን ጉዳይ እንስማማም። አንቀበልም። አናደርግም። መንግሥት ነን አቅም በፈቀደ መጠን ሕግ ለማስከበር እንሠራለን። ሕግ ለማስከበር ስንሠራ በእያንዳንዷ ሰከንድ ለሠላም ዝግጁ የሆነ ኃይል ካለ በራችን ክፍት ነው። ለውይይት፣ ለንግግር፣ ለሠላም ክፍት ነው። ሕግ የማስከበሩ ሥራ ከውይይትና ከንግግር ውጪ እንዲሆንም አንፈልግም።

ሦስተኛ ዋናው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ሥራ አጥነት ነው። አብዛኛው ሰው ምክንያት ኖሮት አይደለም። ሥራ ፍለጋ ይሄዳል። ያግታል። ብር ይጠይቃል።ዓላማ መር ትግል ሳይሆን እገታ መር ትግል ነው ያለው። ይህን ደግሞ በርከት አድርጎ ሥራ በመፍጠር ወጣቱ ወደ ሥራ እንዲሄድ ማድረግ የመንግሥት ዋነኛ ተግባሩ ነው። ጥረት እየተደረገ ነው። ማጠናከር ይኖርብናል።

ከዚህ ውጭ ዋና ዋና የማንግባባበት ጉዳዮች ደግሞ በአካታች ሀገራዊ ምክክር መድረኩ እየታዩ መሠረታዊ መፍትሔ እያገኙ እንዲሄዱ ይደረጋል። በዚህ አግባብ ሠላማችንን ለማረጋገጥ ለማስቀጠል ጥረት ይደረጋል። እናንተ ግን ሠላምን ብታዩት መልካም የሚሆነው በእኛ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዓለም ያሉ የሰላም ተግዳሮቶች አሁን ያለው ዓለም ያለበትን ባሕሪም ታሳቢ ያደረገ ቢሆን ጥሩ ይመስለኛል።

ዲሞክራሲን በሚመለከት መንግሥት ወደ አምባገነንነት እየተቀየረ ነው፤ ዴሞክራሲ እየላላ ነው፣ ጥያቄዎች አሉ ለሚለው ጉዳይ በመጀመሪያ ዴሞክራሲ ከሌለ የሚታየው ይሄ ሁሉ አናርኪ ከየት መጣ። አናርኪን እኮ የሚወልደው ዴሞክራሲ ነው ። ዴሞክራሲ በሌለባቸው ሀገራት ሰው በሀገሩ ላይ ሆኖ ብቻም ሳይሆን ከሀገሩ ውጪም ትንፍሽ አይልም። እናውቃለን። እንደዚህ አናርኪው የበረከተው ዴሞክራሲን መለማመድ፤ ነፃነትን ማስተዳደር ችግር ስለገጠመን አይደለም ወይ? እንደዛ አይታሰብም ወይ? ዴሞክራሲ ወጥ ትርጓሜ እና አሠራር አለው ወይ? ወጥ እኮ አይደለም ዴሞክራሲ። ”Minimalist” የሚያስቡበት የዴሞክራሲ አይነትና ”Maximalis” የሚያስቡበት የዴሞክራሲ አይነት የተለያየ ነው። አንድ አይደለም ።

ዴሞክራሲ አዎ ሕዝብ ይመርጣል መንግሥት ያስተዳድራል። ጥቅል ትርጓሜ ትክክል ነው። “Majority rule Minority right “ጥቅል አባባል ነው። እኛ የትብብር ዴሞክራሲን ነው የምንደግፈው፤ የምናበረታታው። ለምን ቢባል ብዝኃ ሕዝብ ያለበት ስለሆነ የማይኖሪቲ ራይት በቂ አይደለም። ለአናሳው ውክልና ያስፈልጋል። ብዙኃኑ ይግዛ አናሳው መብት ያግኝ የሚለው እሳቤ አይሠራም። አናሳው ውክልና ስለሚያስፈልገው በመግባባት በሰጥቶ መግባባት አብረን ካልዘለቅን በስተቀር ብዙ ቁጥር ያለን፤ ለምሳሌ ብልጽግና አሸንፏል ብቻውን ይግዛ ብንል አይሆንም። ባያሸንፉም ሌሎች ፓርቲዎች ይግቡ። ከኛ ጋር ያስተዳደሩ። በብልጽግና ውስጥም በርካታ ጉዳዮችም ሊነሱ ይችላሉ። በኖርማል ኮታ ቢኬድ የማይታሰቡ፤ ከኮታ ባሻገር በመተው በማቀፍ ውክልናን በማረጋገጥ የሚሠሩ ሥራዎች ማለት ነው ።

እነዚህን ካላበረታታን በስተቀር የምናስበውን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት እንቸገራለን። ዴሞክራሲ በሕግ ብቻ አይመጣም። በእሴት በባሕል ግንባታ ጭምር ነው። እሴትና ባሕል ደግሞ በአምስት ዓመት አይገነባም። ውስጣችን ዴሞክራሲያዊ እሳቤ ሳይኖር በሕግ ብቻ ዴሞክራሲ ልናመጣ አንችልም። ያ ጊዜ ወሳጅ ሥራ ነው። ሐሰተኛ ንግግር የጥላቻ ንግግር፣ ሴራ፣ ውሸት፣ ቅጥፈት፤ የሚታይ የሚጨበጥን ነገር እንደሌለ አድርጎ መናገር ።

ለምሳሌ የዓድዋ መታሰቢያን እንኳን ኢትዮጵያዊ የትኛውም አፍሪካዊ ጊዜ ወስዶ ቢያየው ሊጠላው፣ ሊያራክሰው ሊያንኳስስ የሚችልበት እድል ምንም የለም። በመጠኑም እጅግ የሚያኮራ ነው። በያዘው የታሪክ ሀብትም በጣም አርኪ ነው ። አካታች ነው። ሁሉንም የሚያሳይ ነው። ለማንም ነፃ መሆን ለሚሻ ሀገር፣ ግለሰብ፣ ቡድን በአርዓያነት የሚያስተምር ታሪክ ያለው ነው። ይሄንን ጉዳይ እንኳን የሚያራክስ፤ የሚታይን ነገር እንኳን የሚያራክስ ኃይል አለ “በpost truth” ማሸነፍ ለአምስት ደቂቃ ብቻ ነው ።

አሁን ተናግረህ በዛ ጊዜ ውስጥ እምነት ከፈጠርክ ነገ ምን አይነት ጉዳት አለው ብሎ ማሰብ ቀርቷል። ግን እኛ እንደ ብልጽግና ሁሌም የምናምነው “experience more tiker than information” ብለን ነው። ኤክስፒሪያንስ በጣም ጠንካራ ነው፤ ከኢንፎርሜሽን በላይ። ለምሳሌ እኔ ስለአንድ ሰው እሳቸው መጥፎ ናቸው አይረቡም ብዬ በተደጋጋሚ ብናገር። ያ ሰውዬ ያንን ነገር ሰምቶ ሌላ ሰው መቶ አይ እሳቸው እኮ ጥሩ ሰው ናቸው ቢለው በቀላሉ ሃሳቡን አይቀይርም ። በተደጋጋሚ በነገርኩት መጥፎ ዜና፣  መጥፎ የውሸት ሪፖርት አዕምሮው ይያዛል። ነገር ግን ያንን ሰውዬ በአካል 30 ደቂቃ አንድ ሰዓት ቢያገኛቸው ወይ ጉድ ስለ እርስዎ የሰማሁትና እርሶ አንድ አይደሉም። ተሳስቻለሁ ብሎ ይቀየራል ።

ለምን ”Experience” የበለጠ ያስተምራል። እናንተ ስለ ዓድዋ የሰማችሁት ነገርና ዓድዋን በዓይናችሁት ስታዩት አንድ አይደለም። ኢንፎርሜሽን በተግባር ይቀለበሳል። የኛ አካሄድ በተግባር በሥራ ነገር እየቀየሩ መሄድ ነው። ምክንያቱም የኢንፎርሜሽን ሽሚያውና ውሸቱ ራሱ ሥራ ስለሆነ፤ ዋናውን ተግባር እንዳንሠራ ነው የሚያደርገን። በየጊዜው ይፈበረካል ለዚያ እየመለስን መኖር አንችልም ። በተግባር እየሠራን ሰው ከተግባሩ እየተማረ እንዲቀየር ማድረግ ነው የምንችለው ።

ታዲያ ለምን ፈተናችን በዛ? ኢትዮጵያ ውስጥ ለምንድነው ፈተና የበዛው፣ ግጭት የበዛው፣ ጸብ የበዛው? በጣም ወሳኝ ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን የነበረውን አካሄድ እንተው። በሪፎርም አግባብ እንሂድ አልን። ሪፎርም ከዚህ ቀደም የሄድንበት አግባብ አይደለም። ለምሳሌ ደርግ የንጉሡን ሥርዓት ሲያፈርስ ከንጉሡ ሥርዓት አገልጋዮች መካከል የሆነ ጄኔራል፣ የሆነ ሚኒስቴር ጉዞዬን ያበላሽብኛል ብሎ ካሰበ ማታ ገሎ ጠዋት በዜና ይናገራል። ችግር የለበትም። ማሰር ፖሊስ ጣቢያ መሄድ አያስፈልገውም። አብዮታዊ ርምጃ ይወስድበታል። አብዮታዊ ርምጃ አስር ሰዎች ላይ ሲወሰድ 100 ሰዎች ጭጭ ይላሉ። የሰው ባሕሪ ስለሆነ። እና ለውጥ በዚህ አግባብ እኛ አሁን ከምንከተለው መንገድ ይቀላል ።

ሁለተኛ ኢሕአዴግ ሲመጣ ታስታውሱ ከሆነ ብዙዎቻችሁ እንዳላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ ለምሳሌ መርካቶ ላይ አንድ ሰው ሰርቆ ሲሮጥ ሲያይ አንድ ታጋይ ምንም መያዝ አይጠበቅበትም ገሎት ይሄዳል። ፍርድ ቤት ማጣራት ምን ምን የሚባል ነገር የለም። በየከተማው ስንት ሰው እንደተገደለ ታስታውሳላችሁ። በዚያ መንገድ ሠላምን ማምጣትና በዚያ መንገድ ለውጥን መምራት በጣም ቀላል ነው። እኛ እንኳን መግደል ማሰርም ችግር ሆኗል። የምናስበው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ስለሆነ ። በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለውጥን መምራትና ማጽናት “በሪቮሊዩሽን” ስናደርግ ከነበረው ጋር በአንድ ሚዛን ካየነው አይሆንም። ሁለተኛው ከዴሞክራሲ ባሻገር ሚዲያ። ደርግ ሲመጣ የነበረው አንድ ሬዲዮና አንድ ቴሌቪዥን ነበር ያለው ። ማንኛውም መረጃ የሚሰጠው ከመንግሥት ነው። የሕዝብ ድርሻ መንግሥትን የሚለውን መስማት ነው። ብዙ አማራጭ ሚዲያ አልነበረውም ።

ኢሕአዴግ ሲገባም ከሞላ ጎደል የነበረው ሚዲያ ይመሳሰላል፤ ብላክና ኋይት ከለር ከመሆኑ ባሻገር። ኢቲቪ ነው ያለው፤ ፋና፣ ዋልታ የሚባል የለም። አሁን ዛሬ ቤጊ ላይ ሁለት ሰው ቢገደል፤ አሜሪካ ያለ ሰው ካለምንም ችግር ከአምስት ደቂቃ በኋላ ተጋኖ ከነፎቶው ሊያየው ይችላል። እኔ ግን 1985 ዓ.ም ከቤጊ ደምቢዶሎ ለመሄድ፤ መሄድ ስለማይቻል መንገድ ስለሌለ፤ ጋምቤላ ሄጄ ሳምንት ተቀምጬ፣ ከጋምቤላ ደምቢዶሎ የሚደርስ መኪና አጥቼ ተመልሼ ቤጊ ገብቻለሁ። እንኳን የዕለቱን ልሰማ ቀርቶ ለምን ስብሰባውን መገኘት እንዳልቻልሁ መናገር የምችልበት እድልም አልነበረኝም። ስልክ የለም፣ ትራንስፖርት የለም። ማንኛውም ኩነት ከከባቢው አልፎ ሀገርን መጫን (ኢንፍሌንስ) ማድረግ የሚችልበት እድል አልነበረውም፤ አልነበረውም ድሮም። ሚዲያ ሁለተኛው ችግር ነው።

ሦስተኛው ገንዘብ ነው። ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ሲመጣ፤ የኢትዮጵያ ጂዲፒ ፕላስ ወይ ማይነስ 10 ሚሊዮን ገደማ ነው። አሁን ያለበት ደረጃ አልደረሰም። ብሩ ውስን ነው ማለት፤ ጥይት ውስን ነው ማለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዛሬ ብዙ ሃብታሞች የሉም። የዛሬ ሀብታሞች ቀን ቀን ግብር ይከፍላሉ፤ ማታ ማታ ጥይት ይገዛሉ። ያኔ የነበሩ ሀብታሞች አይችሉም እንደዛ፤ ብዙ ገንዘብ የላቸውም።

ያ ብቻ አይደለም፤ ጂኦ ፖለቲክሱ ያመጣው ጣጣ አለ። ከባቢው ላይ ያኔ አሁን የምናወራት ሀብት በኛ ቀጠና ብዙ አልነበረም። ቢጠሉንም፣ ባይፈልጉንም ለማገዝ የሚያስችል አቅማቸው ውስን ነበር። አሁን በጣም ቀላል ነው ለነሱ በ100 ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር አውጥቶ ጠላትን ማገዝ ቀላል ነው። ያኔ በ84፣ በ85 ኦነግን ሌላ ሀገር አግዛለሁ ቢል፤ ቢያግዝ 10 ክላሽ ነው። ! ዛሬ ግን የጠየቁትን ሁሉ ሊገዛላቸው ይችላል። ገንዘብ ጊዜው ያመጣው ለውጥ ነው። ጂኦ ፖለቲክሱ እዚህ ውስጥ ሊገባ ይችላል።

ይህ ሁሉ ሆኖ ሲያበቃ፤ እኛ ምርጫ ቦርድ ላይ የወሰድነውን ሪፎርም አስታውሱ። ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ተቋም ሆኖ፤ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ እንዲችል፤ ሰብዓዊ መብት ገለልተኛ ሆኖ ሕግ ጥሶ ድብቅ አጀንዳውን ከውኖ ሳይሆን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሥራውን እንዲሠራ ነው። ፍርድ ቤት በንጽጽር ነጻ ሆኖ ጣልቃ ሳይገባበት ሥራውን እንዲሠራ፤ ተቋም እየገነባን ነው። በሕግ ሰው እየያዝን፣ በገንዘብ እየተገዳደርን፣ ልማት እያለማን፣ ሪፎርሙን ስለምንሠራ ከዚህ ቀደም ከምናውቀው ጋር አንድና ያው አይደለም።

ለምሳሌ የባለፈው ምርጫ እንደምታስታውሱት በንጽጽር ከየትኛውም ምርጫችን ይሻላል። የሚቀጥለው ደግሞ ከዚህ በይበልጥ የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ ይደረጋል። በዲሞክራሲ፣ በሚዲያ፣ በገንዘብ፣ በጂኦ ፖለቲክስ ምክንያት የኛ ሪፎርም “እንዲሁ ተነስቼ እቃወማለሁ” የሚል ሰው በሙሉ፤ ለምሳሌ ዲያስፖራ አካባቢ አሁን በተፈጠረው ሁኔታ “እቃወማለሁ” ሲሉ በርከት ያለ የሚዲያ አውትሌት (media outlets/ የሚዲያ አውታሮች) እንዲከፍቱ ፋይናንስ ተደርገዋል። ኢትዮጵያን የማይፈልጉ ሀገራት ለእነዚህ ባንዳዎች ሚዲያ ከፍተውላቸዋል፤ ገንዘብ ሰጥተዋቸዋል። ለእነርሱ ቢዝነስ ነው፤ ለነዛ ሀገር ማፍረስ ነው። ይሄ ከዚህ ቀደም እንደዛ ቀላል አልነበረም። ይሄንን ነገር የተከበረው ምክር ቤት በዚያው ልክ ቢገነዘበው፣ ቢያየው መልካም ይመስለኛል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ “እስር በዛ” የሚል ጥያቄ ተነስቷል። እውነቱን ለመናገር አሁን እንዳለው ሥርዓት አልበኝነት (anarchy)፣ እንዳለው ስድብ፣ ጥፋት እስር ቢበዛ ኖሮ፤ ፓርክ ሳይሆን የምንገነባው እስር ቤት ነው። በጣም ብዙ! በጣም ብዙ! መታሰር የሚገባቸው ሰዎች በየቀኑ ይታለፋሉ። ለምሳሌ እዚህ ሸራተን ጀርባ አንድ በኢትዮጵያ ደረጃ ውብ የሚባል መንገድ ሠርተናል። ሥራ ከጀመረ 15 ቀን ገደማ ቢሆነው ነው። በብዙ ልፋት ነው የተሠራው። ተመርቆ ሳምንት ሳይሞላው፤ ሰዎች እዛ የእግረኛ መንገድ (walkway) ላይ ቁመው ሽንት ይሸናሉ። በስንት መከራ በተሠራ ሥራ ላይ ማለት ነው። እነዚህ ሰዎች ቢታሰሩ አግባብ አይደለም? ለማጥፋት ነው የሚመስለው እንጂ፤ ካልጠፋ ቦታ እንደዛ አይነት ቦታ ላይ ሂዶ እንደዛ አይደረግም። ግን እኛ እስርቤት ሳይሆን ፓርክ ነው እየገነባን ያለነው።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ ከሆነ የተነሳው፤ ከመርማሪ ቦርዱ ጋር ቢያንስ ሦስት አራቴ ተወያይታችኋል፤ ሪፖርት አላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ከተያዘው አብዛኛው ሰው ተምሮ ወጥቷል። በሺህ የሚቆጠር ሰው ወጥቷል። በጣም በ100 የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው እስር ቤት ያሉት። እነሱም እየተጣሩ፣ እየተማሩ ሊፈቱ ይገባል። ሰው እስር ቤት አቆይቶ መቀለብ ለድሃ መንግሥት አያዋጣም። አስተምሮ መመለስ ያስፈልጋል። የታሰሩ ሰዎች እዚህም እዚያም አሉ፤ ተስፋ የማደርገው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚመራው ኃይል እየመረመረ፣ እያወያየ፣ እያሠለጠነ አብዛኛዎቹን ይፈታል ብዬ ነው። መሆን ያለበትም እንደዛው ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ከዚያ ጋር አብሮ የሚጨፈለቅ፣ አብሮ የሚታይ ነገር ካለ መፈተሽ ጥሩ ነው። እንዲሁ የመንግሥት አሠራር እንከን የለውም ብሎ መሄድ ጥሩ አይደለም። የምንፈጥረው ስህተት ካለ እየመረመርን ማስተካከል አለብን። ካጠፋን ይቅርታ መጠየቅ አለብን።

ሀገር ሲፈርስ ዝም ብለን አናይም፤ ሥራችን መጠበቅ ስለሆነ። ሀገር ጠባቂ ነን ብለን ጥፋት የምናመጣ ከሆነ መጠየቅ አለብን። እንደዚህ አይነቱን ቅድም እንደተነሳው በጣም በርካታ ሰዎች እኛው ውስጥ ሆነው የሚሰርቁ፣ የሚያጠፉ አሉ። መለዮ ለብሰው ሠላም ማስከበር ሲገባቸው ጥፋት ላይ የሚሳተፉ አሉ። ብዙዎቹ ይያዛሉ፤ እነሱም ይጠየቃሉ። 100 በመቶ የተሟላ ባይሆንም በውስጥ የእርማት ሥራዎች በስፋት ይሠራሉ። ዴሞክራሲን በዚህ አይነት ማየት ጥሩ ነው፤ ልምምድ ነው። ይህ ልምምድ ደግሞ የራሱ የሆነ ድካም፣ የራሱ የሆነ አሉታዊ ጎን እንዳለው መገንዘብ ጠቃሚ ይሆናል።

የጋራ ትርክትን በሚመለከት በጣም ትክክለኛ የያገባኛል ስሜት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በትናንትናው ስንፋጅ ነገን እያጣን ነው። ሰው ከትናንት ተምሮ፣ ዛሬን ሠርቶ ነገን ማነጽ ሲገባው ዛሬ ላይ ሆኖ በትናንትና እየተፋጀ ነገን እያጣ ነው። የተዘጋጁ ብቻ የሚወርሱት ስለሆነ ነገን በደንብ ካልተዘጋጀን ጥፋት ሊያመጣብን ይችላል። ለዚህም የሚያሰባስብ ትርክት ያስፈልጋል። ልክ እንደ ዓድዋ። ዓድዋ መደመርን በተግባር ያሳየ፤ የጋራ ትርክትን በአንድ ቦታ ያሳየ ፕሮጀክት ነው።

ልክ እንደእርሱ ንግግሮቻችንም ሰብሳቢ ቢሆኑ ይመረጣል። የሚያዋጣውም እሱ ስለሆነ። ነገር ግን አሁን ሰው መንግሥት የሚጠይቀው፤ መንግሥት የሚወቅሰው ደካማም ቢሆን መንግሥት ስላለው ነው። መንግሥት ባይኖረው እኮ አይጠይቅም፤ አይወቅስም። መንግሥት ለመውቀስ ያልታደሉ ጎረቤቶች እኮ አሉ። መውቀሳችን በራሱ ስላለን ነው። መጠየቃችን በራሱ ስላለን ነው። ያንን በጋራ ትርክት እየገነባን ተቋም እያደረግን ብንሄድ ያዋጣል ብለን ማሰብ ከሁላችን የሚጠበቅ ይመስለኛል።

መጪው ዘመን አደገኛ ነው። ቅድም ተነስቷል መጪው ዘመን አደገኛ ነው። ብዙዎች በብር የሰከሩበት፤ ብዙዎች በድህነት የቆረቆዙበት ዓለም ነው። መሣሪያ ሁሉም በየሰፈሩ የሚያመርትበት ጊዜ ነው። ማንም ማንንም አለቃ ሆኖ የሚያስተዳድርበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ‹‹የሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ›› እንደሚባለው ሰብሰብ ካላልን በስተቀር፤ ተቋም ካልገነባን በስተቀር ብዙ ኃይሎች ሊያዳክሙን ስለሚፈልጉ ለኢትዮጵያ መሰብሰብን የመሰለ ጸጋ የለም። ከዚያ ውጪ ያለው ነገር ኪሳራ ነው።

ድህነትን ማራገፍ፤ ብልጽግናን ለሀገራችን ለትውልድ ማልበስ ከሁላችን ይጠበቃል። ድህነትን የምናራግፈው በሥራ ነው። ብልጽግናን የምንለብሰው በትጋት፣ በልፋት ነው። ሌላ መንገድ የለውም። ይህንን አስቦ መሥራት ከሁላችን ይጠበቃል። ከእኛ የከፋ ችግር ያለባቸው ሀገራት ተወያይተው፤ ይቅር ተባብለው የጋራ ትርክት ገንብተው እንደ ሀገር እየተጓዙ ነው ።

ከእኛ የባሰ። ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ። መቼም ከአፓርታይድ የባሰ ነገር አፍሪካ ውስጥ አልነበረም። አፓርታይድ በጣም ዘርፈ ብዙ የሆነ ክፋት በውስጡ የያዘ አገዛዝ ነው። ግን ደቡብ አፍሪካውያኖች አዎ ትናንት በደል ነበር፤ ችግር ነበር፤ አብረን መሥራት አልቻልንም። ብዙ ነገር አጥተናል። ነገር ግን በሚያግባባን ትርክት ወደፊት መጓዝ አለብን ብለው ‹‹ትሩዝ ኤንድ ሪኮንስሌሽን›› የሚል ተቋም አቋቁመው ላለፈው ችግር እውቅና ሰጥተው እንደ ሀገር እየተጓዙ ነው። በሰብ ሰሐራ ትልቁን ኢኮኖሚ እየመሩም ነው። ችግራቸው ከእኛ የባሰ ነው።

በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ላይ የደረሰው በደል ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ላይ አልደረሰም። የእኛ በደል ስለሚያንስ ይረሳ አይደለም። እውቅና እንስጠውና እንገስግስ፤ እዚያ ቆመን ባንቀር። በጀርመን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ከዚያ በፊትም ከዚያ በኋላም ታይቶ በማይታወቅ መንገድ የተጨፈጨፈበት ነው። ሕጻን የለም፤ ሴት የለም፤ ትንሽ ትልቅ የለም። ያንን ችግር እውቅና ሰጥተን እንለፍ ብለው አልፈው ይኸው አሁን ጀርመን በአውሮፓ ትልቁን ኢኮኖሚ እየመራች ያለች ሀገር ናት።

ካናዳን ብንወስድ በብዝኃነት /ዳይቨርሲቲ/ ምክንያት በጣም የረጅም ጊዜ ጭቅጭቆች ያለባቸው ቢሆንም፤ ለዚያ ልዩነት እውቅና በፖሊሲ ሰጥተው መልቲ ካልቸራል (ብዝኃ ባሕል) እንዳለን እውቅና እንስጥ፤ ለቋንቋ እውቅና እንስጥ ብለው በሠላም እየቀጠሉ አሉ። ሩዋንዳ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጣም ከፍተኛ የሚባል ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸው ያን የሚያክል ሕዝብ አልቆ ሌላ መንገድ የለም እውቅናና እርቅ ነው ብለው ታርቀው እውቅና ሰጥተው የተሻለ ሥራ አፍሪካ ውስጥ እየሠሩ ካሉ መንግሥታት አንዱ ናቸው።

እኛ የተለየ ብለን የምንናገር በደል ይኖራል፤ ችግር ይኖራል እውቅና ሰጥተን፤ ተነጋግረን፤ ተወያይተን፤ እንዳይደገም ተምረን ማለፍ ጥሩ ይመስለኛል። ነገን ለማትረፍ ፤ነገን ለመዋጀት ትናንትናን አውቀን ሆን ብለን በእውቀት ማለፍ ያስፈልጋል። ግድ የለም ከነገው አይበልጥም ብሎ ማለፍ ይጠይቃል። አለበለዚያ ሁሌም በትናንትና ውስጥ ነው የምንኖረው ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምትሰሙት ፖለቲከኛ የሚባል፤ ተናጋሪ የሚባል ሁሉ በሀገሪቱ ሠላም የለም፤ አንድነት የለም፤ ዘረኝነት በዛ፣ ጥፋት በዛ ብሎ የማይናገር ነው። ይህንን ችግር እውቅና ሰጥቶ መናገር ጥሩ ነው። ችግሩን ለመፍታት ምን አደረኩኝ ነው ብሎ ራስን መጠየቅ ግን ያስፈልጋል። ችግሩን ስለተናገረ መፍትሔ ብቻውን አይመጣም። ችግሩን እውቅና ከሰጠን በኋላ ለመፍትሔው አብረን የምንተጋ መሆን አለብን።

አንድ ሰው ከጓደኞቹ ጋር ሊዝናና ወጥቶ መዋኛ ስፍራ ያያል። ይህ ሰው በበቂ ደረጃ ዋና የሚችል አይደለም ግን ከጓደኞቹ ጋር መዋኛውን ስፍራ ሲያይ ነሸጥ አደረገው እና አወላልቆ ዘሎ ገባ። እንደገባ ዋና ስለማይችል ማንቦጫረቅ ጀመረ፤ መጮህ ጀመረ፤ ድረሱልኝ አለ፤ እያለ እያለ እየሰመጠ ሄደ። ጓደኛቸው እየሰመጠ መሆኑን ያዩ ወዳጆቹ ተንጫጩ፤ ጮሁ፤ ተበላ፣ ጠፋ፣ አለቀ፤ ተወሰደ ጮሁ። አንዳቸውም ዘለው ውሃ ውስጥ አልገቡም። ብዙዎቹ ግን ጮኸዋል። እነሱ እየጮሁ በመንገድ ያልፍ የነበረ አንድ ሰውዬው ሲወራጭ ሊበላ እንደሆነ አይቶ ከነልብሱ፤ ከእነ ጫማው ዘሎ ገብቶ ዋኝቶ ያንን ሰው ሊበላ ከነበረበት ውሃ አውጥቶት የሚደረግ የመጀመሪያ ድጋፍ አድርጎ ሰውዬው መትረፉን ካረጋገጠ በኋላ ምንም ሳይናገር ጉዞውን ቀጠለ።

ሰውዬ እንደዚያ እየጮሁ እያለቀሱ ቢቀጥሉ፤ ሰውዬው ባይመጣ ኖሮ ይታደጉት ነበር ወይ ነው? ከነጫማው ዘሎ የገባው ሰው ነው የታደገው እንጂ የተንጫጩ ሰዎች አላዳኑትም። በመንጫጫት የምናመጣው ለውጥ የለም። ከነምናምናችን ዘለን ገብተን ለሠላም፣ ለልማት ስንሠራ ብቻ የተሟላ ለውጥ ይመጣልና በዚያ አግባብ ማየት ጠቃሚ ይመስለኛል።

ኮሚሽኑን በሚመለከት በተደጋጋሚ ሪፖርት ቀርቦልናል። የተቋቋመበት ዋና ዓላማ ችግር ስላለብን ነው። ችግር ባይኖር ኮሚሽን አናቋቁምም ነበር። ነገር ግን ኮሚሽኑ መልስ እስከሚያመጣ ድረስ እስከዛ ወንጀለኞች ካሉ ደግሞ አይነኩ አይባልም። ወንጀለኛ ካለ እየጠየቅን ለውይይት በራችንን እየከፈትን በኮሚሽኑ የሚገኙ ውጤቶችን ተቀብለን እንደሀገር በጋራ በመቀጠል ብንሠራ መልካም ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

በውስጣችን በኛ ፓርቲ በኛ መንግሥት ውስጥ በተሰገሰጉ ግለሰቦች ምክንያት በፖሊስ በወታደር በካድሬ በሕዝብ ላይ የሚደርስ ችግር አለ። ቅድም የተነሳው ምን እርምጃ እየወሰዳችሁ ነው ለሚለው ጥያቄ፤ በውስጣችን በጣም በርካታ የተሰገሰጉ ኃይሎች አሉ። የኛ አካሄድ የመጀመሪያው የሃሳብ ጥራት ለማምጣት የአቅም ግንባታ ሥራ መሥራት። ሁለተኛው በሂደት እያጠሩ እንክርዳዱን እየለዩ መሄድ ነው። ከዚህ አንፃር ባለፉት ስድስት ወራት በየደረጃው ካሉ አመራሮች ስምንት ፐርሰንት ገደማ ከሥልጣን ተነስተዋል ወይም ተሸጋሽገዋል። ከአራት ፐርሰንት በላይ ተባረዋል። ከአራት ፐርሰንት በላይ ከደረጃ ዝቅ ብለዋል። ይሄ በወታደሩም፣ በፖሊሱም፣ በካድሬውም ተግባራዊ ሆኗል። እኛ በከፍተኛ ደረጃ ውስጣችንን ለማጥራት ጥረት እያደረግን ነው። ግን አልጨረስንም።

በገጠር እንደምታውቁት አርሶ አደሮች ዶሯቸውን እንቁላል ካሳቀፉ በኋላ ጫካ ሲወጡ የቆቅ እንቁላል ካገኙ ይዘው መጥተው ያቺን ቤት ያለች ዶሮ ያሳቅፋሉ። የቆቅ እንቁላልና የራሷን እንቁላል ታቅፋ ጊዜው ሲደርስ የሚፈለፈሉ ቆቆችና ጫጩቶች ለአንድ እና ለሁለት ቀን በጋራ ዶሮዋ ስር ከቆዩ በኋላ ከፍ እያሉ ሲሄዱ በር ሲወጡ ቆቆቹ ትንሽ ለየት ፣ዶሮዎቹ ደግሞ ለብቻ፤ ትንሽ ሲቆዩ ደግሞ ራቅ፣ ከሳምንት 15 ቀን በኋላ ቆቅ ወደ ጫካ ይጠፋል፣ ጫጩቶች ይቀራሉ። ይሄን የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ያውቁታል።

እኛ የታቀፍነው የቆቅ እንቁላል ሊኖር ይችላል። ያ የታቀፍነው የቆቅ እንቁላል ጫጩት መስሎ ከጫጩት ጋር ተፈልፍሎ ሊሆን ይችላል። እራሱ ሂደት ግን እያጠራው ስለሚሄድ እየረገፈ ይሄዳል። ፈተናዎቹም /ቻሌንጆቹም/ የሚያሳዩት እሱን ነው። የተቀላቀለ ብዙ ነው፤ በብዙ ምክንያት፤ እየረገፈ፤ እየረገፈ ትክክለኛው የዶሮ ልጅ፤ የጊዜ ጉዳይ ነው፤ የፀና ፓርቲና መንግሥት እየተፈጠረ እንደሚሄድ ተስፋ ይደረጋል። በርካታ ችግሮች አሉ እያረምን እያረቅን የምንሄድ መሆኑን ለመግለፅ ነው።

የመጨረሻው ድርቅን በሚመለከት ነው። ከሠላምና ፀጥታ አንፃር ቢታይ የምለው ድርቅን በሚመለከት የተከበረው ምክር ቤት ወደኋላ መለስ ብሎ እንዲያስታውስ የምፈልገው ከመቶ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ በየአስር ዓመቱ እንደጥቁር እንግዳ ይጎበኘን ነበር። በየአስር ዓመቱ ድርቅ ይጠበቃል። በአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝብ አምስት ሚሊዮን ገደማ ቢሆንም በነበረው ድርቅ ከ 250 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሞቱ ድርሳናት ያሳያሉ። ከዚያ በኋላ በየዘመኑ ጉብኝት ያለ ቢሆንም በ1977 ዓ.ም የኛ ሕዝብ ቁጥር ከ35 እስከ 40 ሚሊዮን ገደማ የሚገመት ሊሆን ይችላል።

በየአስር ዓመት የነበረው ጉብኝት የኋላ ኋላ በየሦስት ዓመቱ ሆነ። በየሦስት ዓመቱ የሚጎበኘን ድርቅ ከአንድ ክልል በላይ አልፎ አልፎም ከአንድ ሀገር በላይ የሚሻገረውን ነው እንጂ በየዓመቱ ግን ኮሪደሮች አሉ። በየዓመቱ የተወሰነ ኮሪደር ድርቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት አለ። ተቋርጦ አያውቅም።

ጉዳዩ ድርቅ መኖር እና በረሃብ ምክንያት ሰው መሞት አለመሞት ላይ ነው። ድርቅ ለኢትዮጵያ ልክ እንደባሕላችን ልክ እንደ ዓድዋ ድል 100 ዓመት ሲጎበኘን የኖረ ጉዳይ ስለሆነ እንደአዲስ ንግርት የምናወራው ጉዳይ አይደለም። ነበር ባለፉት 100 ዓመታት ድርቅ እንደሚመጣ ብናውቅም በበቂ ደረጃ አምርተን ሰዎች በረሃብ እንዳይሞቱ ማድረግ ተስኖን ቆይተናል። ለዚህ ነው ምርት ማምረት አለብን የሚል ቁርጠኛ አቋም ወስደን በተለየ መንገድ ምርት ውስጥ የገባነው።

አሁን ዘንድሮ በትግራይ የተወሰነ አካባቢ፤ በአማራ የተወሰነ አካባቢ፤ ኦሮሚያ በምሥራቁም እንዲሁ ድርቅ አለ። ምንም ጥያቄ የለውም ድርቅ አለ። ይሄንን ድርቅ ማየት ያለብን እንደ ፖለቲካ አይደለም። ድርቅ መንግሥት አላመጣውም። “ኢንቫይሮመንታል ክራይስስ” አለ። ችግኝ እንትከል፤ ችግኝ ምን ያደርጋል ብለን። ድርቅና ረሃብ አለ ስንዴ እናምርት፤ ስንዴ ምን ያደርጋል ብለን። ድርቅ መጣ ብለን ብንጮህ ትርጉም የለውም።

ትርጉሙ ተባብረን ሰው እንዳይሞትብን ማድረግ ነው። ታስታውሳላችሁ አምና ቦረና ድርቅ ነበር። ተረባርበን ሰው እንዳይሞት አድርገናል። ከብቶች ቢሞቱም ሰው አልሞተብንም። ሶማሊያ ድርቅ ነበር፤ ተረባርበን ሁሉም ኢትዮጵያ አግዞ፤ የክልሉ መንግሥት ተረባርቦ ብዙ ድጋፍ ባልነበረበት ሁኔታ ሰው እንዳይሞት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። አሁንም የሚያጋጥመንን ድርቅ ትግራይ ተርቦ፣ የአማራ ክልል ተርቦ፣ ኦሮሚያ ክልል ተርቦ እዚህ ያለን ሰዎች በልተን ማደር አንችልም። ተባብረን ሰው እንዳይሞትብን ማድረግ አለብን።

ግን ድርቁን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ የምንጠቀም ከሆነ ጥፋት ነው። አሁን ባለፉት አራት ወራት ለምሳሌ ትግራይ ክልል፤ 500ሺ ገደማ ኩንታል እህል በመንግሥትና በተወሰኑ ደጋፊዎች ሄዷል፤ ምን ማለት ነው? ቢያንስ ሦስት አራት ወር ድረስ ሰው በምግብ እጥረት ምክንያት ሰው አይሞትም ማለት ነው። የትግራይ መንግሥት ምን ማድረግ አለበት? እነዚን ሀብቶች /ሪሶርሶች ውስን ቢሆኑ የከፋ ችግር ያለበት ቦታ ማድረስ አለበት። ሪሶርስ በትክክል ካልተሰራጨ ችግር ሊያመጣ ይችላል። ሪሶርሱ በቂ ካልሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አቅም እያለው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በልቶ እያደረ፤ አንድም ቦታ በረሃብ የሚሞት ሰው አይተን ዝም አንልም። ባለን አቅም ሁሉ ሕዝባችንን አግዘን ይቺን ጊዜ እንዲሻገር እናደርጋለን።

አሁን የሜትዎሮሎጂን ሪፖርት እንደምትሰሙት ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ በቂ ወይም ከበቂ በላይ ነው ተብሎ ይጠበቃል። ትራክተር ሲገባ፤ አግሬሲቭ ሆነን ከሠራን ቢያንስ ድርቁ ወደ ሚቀጥለው የማይሻገር ይሆናል። ካልሠራንስ ለሚቀጥለው ዓመትም ይቀጥላል። መሥራት ብቻ ነው መፍትሔው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት አልሠጠውም እንዴት ይባላል? 14 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ያወጣው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው። ረጂዎች የረዱት አራት ሚሊዮን ገደማ ነው። የመጀመሪያውን የምናወጣው እኛ ነን። ልማት ቀንሰን ሰው እንዳሞትብን ለእርዳታ የምናወጣው እኮ እኛ ነን፤ አሁንም እናወጣለን። ለምን? በድርቅ ምክንያት ሰው ተርቦ ሕይወቱ እንዲያልፍ መፍቀድ የለብንም፤ ቢያንስ ከአቅማችን በላይ ካልሆነ በስተቀር ።

እስከ አሁን ባለኝ መረጃ በረሃብ ምክንያት የሚሞት ሰው የለም፤ ያለው ችግር ምንድ ነው? ረሃብና አብሮ የሚመጣ በሽታ አለ። በትግራይ ብቻ ሳይሆን ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ብትወስዱ አዲስ የወባ ባሕሪ አለ። ያ የወባ ባሕሪ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሰው ይገድላል፤ ከዚህ ቀደም ይሰጡ የነበሩ መድኃኒቶችም ፈውስ አላመጡለትም። ወባ ሲጨመር፣ ተቅማጥ ሲጨመር፣ በምግብ እጥረት አቅም ማጣት ሲከሰት፤ በዚህ ላይ በሽታ ሲጨመር ሰው መቋቋም አቅቶት ሊሞት ይችላል። ይሄ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የሚሆን ነው።

አሁን የተከበረው ምክር ቤት እንዲለየው የምፈልገው ኢትዮጵያ ውስጥ ዘንድሮ ከምንግዜውም በላይ በታሪካችን አምርተን የማናውቀው ምርት አለን። በዘንድሮው በጋ 3 መቶ ሚሊዮን ሄክታር ነው ያረስነው። 120 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እንጠብቃለን። ይህንን አማና ዓመቱን ሙሉ አላገኘንም፤ ትልቅ ምርት ነው። ይህንን ምርት አርሶአደሩ ወንድምህ ተርቦ እየሞተ ነው ሲባል ዝም ይላል ብላችሁ አትጠብቁ፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነው አያደርገውም። መንግሥት እንኳ ባያደርግ ሕዝቡ ተጋግዞ ሰው እንዳይሞትበት ጥረት ያደርጋል፤ ማድረግም አለበት።

ይሄ ስንዴ መመረቱ የሚያማቸው ኃይሎች ግን አሉ። ይሄ ግልጽ ነው። ፈረንጆች ”I Cant Help It ” ልረዳው አልችልም እንደሚሉት እየተመረተ ነው። አልተመረተም ለማለት አንዴ ድርቅ መጣ፣ አንዴ ዋጋ አልቀነሰም፣ አንዴ ዳቦ ቤት እንደዚህ ሆነ በሚል ማጠልሸት አይቻልም። የተመረተውን ተቀብለን የቀረውን እየሞላን ነው የምንሄደው፤ የተመረተውን ለማራከስ ተብሎ የሚደረጉ ዘመቻዎች ብዙም ጠቃሚ አይደሉም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ትናንት እንዳደረገው ዛሬም የሚራብ ሰው ካለ ፕሮጀክት አጥፎ ሕዝቡ በረሃብ እንዳይሞት የሚችለውን ሁሉ ይሠራል፤ ከማን ጋር፤ ከሕዝቡ ጋር፤ ከባለሃብቱ ጋር፤ ከክልል መንግሥታት ጋር፤ ተባብሮ ሰዎች በረሃብ እንዳይሞቱ ያደርጋል። ይህን ለማድረግ የተከበረው ምክር ቤትም በእጅጉ እንደሚያግዝ ተስፋ አደርጋለሁ።

አንድ ሰው በእኛ ሰፈር ነበር፤ ይሄ ሰው ለዓመታት ይፀልያል፤ ጧትም፣ ማታም እግዚአብሔር ሆይ ሎተሪ እንዲወጣልኝ አድርግ፤ ጧት ሎተሪ ነው፤ ቀን ሎተሪ ነው፤ ማታ ሎተሪ ነው ልመናው፤ ለብዙ ዓመታት ሎተሪ እንዲወጣልኝ እርዳኝ፤ ድህነት ሰለቸኝ ይላል። አንድ ቀን እግዚአብሔር ቤቱ መጣ ይባላል። ልጄ ሆይ እባክህን ሎተሪ ቁረጥ አለው። ሎተሪ ሳይቆርጥ እባክህን ሎተሪ እንዲወጣልኝ አድርግልኝ የሚል ነገር፤ እግዚአብሔርን ግራ የሚያጋባውና የሚያስቸግረው ነገር ፤ እባክህን መልስ እንዲመጣ ሎተሪ ቁረጥ! አለው ይባላል።

እባካችሁ እንረስ፤ የሚታረስ መሬት አለን፤ ውሃ አለን፤ የሰው ጉልበት አለን፤ ድህነትና ልመናን ጌጥ አናድርገው፤ ተቸግረዋል ሊያልቁ ነው፤ ምናምን ሲሉን እንደ ሽልማት አንውሰደው፤ ኮሮና ሲመጣ ሊረግፉ ነው አሉን፤ እረገፍን እንዴ? አልረገፍንም እኮ! ሟርት ነው። ጦርነት ስንጀምር ታስታውሳለችሁ ረሃብ! ረሃብ !አሉ፤ እውነት ነው እንዴ? በአንድ በኩል አንዘናጋ ችግር ካጋጠመ ተረባርበን እንፍታ፤ ቦረና እንዳደረግነው፤ ሶማሌ እንዳደረግ ነው።

በአማራ ክልልም በትግራይ ክልልም ያለውን ችግር ተረባርበን ተደጋግፈን እንፍታ፤ ሰው እንዳይሞትብን። በተረፈ ግን ፖለቲካ አናድርገው። ምክንያቱም ስድስት ወር ያልፋል፤ ከስድስት ወር በኋላ የታለ የሞተ ሰው? የተባለው የታለ? ሲባል ማፈር ይመጣል። አንዳንዱ ከ1977ቱ ዓ.ም ያልተናነሰ ድርቅ አለ ይላል፤ ይህ ማለት አንድ ሚሊዮን ገደማ ሰው ይሞታል ማለት ነው። አንድ ሚሊዮን ካልሞተ ሰውየው እየዋሸ ነው ።

እኛ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ሳይሆን አንድም እንዳይሞት አቅማችን በፈቀደ መጠን እንፍጨረጨራለን። ከአቅም በላይ ከሆነስ? እርሱ ምን ይደረጋል። አሁን ግን ኢትዮጵያ ከተረባረበች ሰው እንዳይሞትባት ማድረግ ቢያንስ ለጥቂት ወራት ማቆየት ትችላለች የሚል እምነት ነው። በዚሁ አግባብ በትብብር መንፈስ በጋራ ብንሠራ መልካም ይሆናል። ከዚህ ውጭ ያለው መንገድ አይጠቅምም፤ በማይረባ ነገር ተወስደን የሚረባውን ነገር እንዳናጣ ብንተባበር መልካም ነው።

የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች አጠር አጠር አድርጌ ለመመለስ ያህል፤ ቀድሞ የተነሳው የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶቹን ለመጠገን የሄድንባቸው መንገዶችና የተገኙ ውጤቶችን በሚመለከት ቢብራራ የሚል ጥያቄ ነው። የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ፤ ስብራቱም እንደ ብዙ ስብራቶች የወረስነው ነው። ግን የማክሮ ስብራት ብቻውን ቢሆን ምናልባት በሪፎርሙ በሄድንበት መንገድ ውጤት ይመጣ ነበር። ነገር ግን ወዲያው ኮቪድ መጣ። ጦርነቶች ተበራከቱ። የአየር ንብረት ለውጥ ተስፋፋ። ዓለም ላይ በሙሉ አዳዲስ ስብራቶች እየተወለዱ ሄዱ።

በእኛ ሁኔታ ዓለም ላይ ካለው አጠቃላይ ቀውስ በተጨማሪ የውስጥ ችግራችን በሰፈር፣ በቡድን የምናደርጋቸው ግጭቶች፤ እንዲሁም የውጪ ጫና ላለፉት ዓመታት ጠንከር ያለ፣ የማይነገር ጫና ስለነበረ፤ በእነዚህ ድምር ሥራዎች የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶቻችንን በምናስበው ፍጥነት መጠገን አልቻልንም። ነገር ግን የማክሮ ፋይናንሻል መዛባትን ብንወስድ፣ የሚቀሩ አመላካቾች ቢኖሩም፣ የተሠራው ሪፎርም በብዙ ማሳያ ከፍተኛ መሻሻሎች ታይቶበታል። የፋይናንሻሉን ብቻ ብንወስድ እመርታው ከፍተኛ ነው። የብር ኖት ከመቀየር ጀምሮ ሲሠራ የቆየው ሪፎርም በተወሰነ ደረጃ መሻሻል እንዲታይ አድርጎታል። ቀጣይ ሥራ የሚፈልጉ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው፣ አሁንም ቀሪ አመላካቾች መታየት ያለባቸው መሆኑ ነው።

የፊሲካል ፖሊሲ አቅጣጫዎቻችንና ሥራዎቻችን አሁን ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥሉት መንግሥታትም ጭምር ፋይዳ ሊያመጡ የሚችሉ አንኳር ስብራቶች ተጠግነውበታል። ዝርዝሩን አልገልጽም። አሁን ግን አንደኛው አንኳር ስብራት በፊሲካል ፖሊሲ ለማረቅ የተሞከረው በሰብሲዲና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ በዕዳ መልክ ይከማች የነበረውን ሃብት “ሲስተማቲካሊ በሪፎርም” ለመቀነስ እየተሄደ ያለበት መንገድ ከፍተኛ የሆነ እመርታ እያመጣ ነው። ትልልቅ ውጤት የተገኘባቸው ዘጠኝ አስር ቦታዎች አሉ። አንደኛውን ብቻ እገልጻለሁ፤ ነዳጅ።

የነዳጅ ድርጅት በነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ ምክንያት 180/190 ቢሊዮን ገደማ ዕዳ ነበረበት። ይሄን ለመፍታት በሠራነው ሥራ አሁን ወደ 100 ቢሊዮን ገደማ ዝቅ አድርገነዋል። በሚቀጥሉት አራት አምስት ዓመታት ዜሮ ካደረስነው ይሄንን እዳ ከፍተኛ የሆነ ውጤት እኛጋ ባይታይም በሚቀጥሉት መንግሥታት ውጤቱ ይታያል። የተከማቸው ስብራት ጥገና ያገኛል። የኤሌክትሪክን ብቻ ብንወስድ 99 ከመቶ ዕዳ የነበረው ተቋም ምናልባት በሦስት ከበዛ በአራት ዓመት ውስጥ ልክ እንደ ህዳሴ ያሉ ፕሮጀክቶች ከመንግሥት፣ ከሕዝብ ቦንድ ሳይል ኢንቨስት ማድረግ ወደሚቻልበት ደረጃ ይሸጋገራል። እነዚህ ጊዜ ወሳጅ ግን በጣም ከፍተኛ እመርታ እየታየባቸው ያሉ ናቸው።

ትልቁ ክፍተት ያለው በሞኒተሪንግ ፖሊሲ ነው፤ ሃሳቡ ከሞኒተሪንግ ፖሊሲ ጋር ይያያዛል። ለምሳሌ ግሽበትን ለመቆጣጠር ብለን የምናደርጋቸው ቁጥጥሮች ቅድም እንደተነሳው በገንዘብ ዝውውር ላይ የሚያስከትለው ነገር አለ። ተቀማጭ ገንዘብ ጨምሯል። አምና ከቀረበላችሁ ሪፖርትም፤ ከዘንድሮ ስድስት ወር ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ጨምሯል። ተቀማጭ 1ነጥብ2 ትሪሊዮን ደርሷል። ይሄ የገንዘብ ዝውውሩን ስለሚቀንስ ግሽበት ላይ የሚያስገኘው ውጤት አለ። ትንሽም ብትሆን ውጤት ታይቷል።

ብድርን በሚመለከት ባለፉት 6 ወራት ከ170 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ተሰጥቷል። ከዚህ ውስጥ 83 ከመቶው ለግል ሴክተር የተሰጠ ነው። ይሄ ሲግኒፊካንት የሆነ ለውጥ ነው። ድሮ 70 ከመቶውን መንግሥት ከሚወስድበት 83 ከመቶውን ለግል መስጠት ከፍተኛ ለውጥ ነው። ባንኮችን ታድገናል፤ ንግድ ባንክና ልማት ባንክ ይወድቁ ነበር። ዝርዝሩን በሴክተር ስለምታዩት ጊዜ ላለመውሰድ አልገባበትም። ድነዋል፤ ችግር አላቸው፤ ሥራ ይፈልጋሉ። ግን የነበረባቸው ወገብ አጉባጭ ስብራት በተወሰነ ደረጃ ተቃሏል። እነዚህ በሞኒተሪንግና ፊሲካል ፖሊሲ ላይ የተወሰዱት እርምጃዎች ተሰናስለው፣ አንደኛው አንደኛውን እየደገፈ፣ በሁሉም “ኢንዲኬተርስ” የተሟላ ውጤት ለማየት እንዳንችል ያደረገን አጠቃላይ ቀውሱ ነው ማለት ነው።

እዳውን ወረስን የምናደርጋቸው ለውጦች ደግሞ አዳዲስ ቻሌንጆች ሲታከሉበት በተወሰነ ደረጃ በምናስበው ፍጥነት ልንፈታው አልቻልንም። በሴክተር ደረጃ ግን መለየት ጥሩ ነው፤ ኢኮኖሚን በማክሮ ደረጃ ካየን በኋላ በሴክተር ደረጃ፣ ለምሳሌ ግብርና እያደገ ነው ሲባል፤ ግብርና ካደገ ታዲያ ለምንድነው ማክሮው እንደዚህ የሆነው ይላል ሰው። ባሕሪው እንደዛ አይደለም፤ ግብርና ሴክተራል የልማት ዘርፍ ነው። ሴክተራል ስለሆነ በሴክተር ይታያል። ማክሮ ከሴክተር በላይ ነው የሚታየው።

በግብርና ከፍተኛ እመርታ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቷል። አምናም ዘንድሮም እድገቱ ይቀጥላል፤ የእድገት ተሸካሚውም እሱ ነው። ነገር ግን ግብርና ላይ የሠራነው ሥራ አሁን ከሠራነው በላይ መሥራት ብንችል ብዙ ቀዳዳዎቻችንን ከመድፈን አልፈን፤ ቢያንስ ቢያንስ ከልመና ነፃ እንድንሆን ያደርገናል። በኢንዱስትሪ “ኢትዮጵያ ታምርት” ብዙ ለውጥ አምጥቷል፤ አሁን አሁን ደግሞ ”ስታርትአፕስ” ላይ ጀማሪ፣ የሚፈጥሩ፣ የሚያሻሽሉ፣ እሴት የሚጨምሩ ወጣቶችን የማገዙ ሥራ ፈር እየያዘ ሲሄድ ኢንዱስትሪም ከፍተኛ የሆነ እመርታ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ማዳበሪያን ጨምሮ ትራንስፖርት ላይ ያመጣነው ውጤት እንደዚሁ እመርታ አሳይቷል። አይሲቲ ላይም በቴሌኮም ካመጣነው በላይ የካፒታል ማርኬት በቅርቡ እንጀምራለን። የካፒታል ማርኬት ሲጀመር ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ኢንፎርማል፣ ኢሌጋል የሆነ ሃብት ወደ ትክክለኛ ሃብት ገብቶ ብዙ ኢንቬስተሮች ለመፍጠር ያግዘናል። ካፒታል ማርኬት የዛሬ 10 ዓመት እንደ ወሬም ኢትዮጵያ ውስጥ ሊወራ አይችልም፤ አይታሰብም።

አሁን ተቋም ተቋቁሞ የሕግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። እነዚህ ጉዳዮች ፈር ይዘው የኢትዮጵያ ሶቨርን ዌልዝ የሚያስተዳድረው ተቋም አብዛኛውን ሃብቱን በሕግ፣ በቢዝነስ መምራት ሲጀምር ብዙ ለውጥ እንደሚመጣ ይጠበቃል። እነዚህ ሲሰናሰሉ ዘንድሮም ከ7/9 ከመቶ ገደማ እድገት እንጠብቃለን። ምን ማለት ነው የማክሮ ችግር አለብን፤ በሴክተር የምናስበው እድገት በፈለግነው ልክ መሥራት ይቀረናል። ያም ሆኖ ግን በዓለም ላይ ፈጣን ኢኮኖሚክ እድገት እያመጡ ካሉ ጥቂት ሃገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት።

ይሄ ወርልድ ባንክ፣ አይኤምኤፍ በተደጋጋሚ ሲገልጹት እንደምትሰሙት እድገት አለ። የቆዩ ስብራቶችና ተጨማሪ ሪስኮች አሉ። እነዚህ ኢኮኖሚው በማደግና በመፈተን መካከል ላይ እንዲወድቅ ያደረጉት ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እድገት የሚታይ ስለሆነ ልማቱ ምንም አስረጂ አያስፈልገውም። የመጣ ሰው ሁሉ የሚናገረው ስለሆነ፣ እናንተ በየቀኑ ስለምትኖሩበት ላይታወቃችሁ ይችላል።

የመጣ ሰው ሁሉ ምን ተፈጠረ፣ ነዳጅ አግኝታችሁ ነው ወይ፣ ገንዘቡ ከየት መጣ፣ ማን ረዳችሁ፣ መቼም ትችላላችሁ፣ ሠራችሁ ማለት ኃጢያት ስለሆነ ከጀርባችሁ ማን አለ? የሚሉ ጥያቄዎች ሁሌ ይነሳሉ። ማን ዲዛይን አደረገው፣ ማን ፋይናንስ አደረገው፣ የሚል ጥያቄ ሁሌም አለ። ምን ማለት ነው፣ አንተ አትችልም፤ የሆነ አካል እያገዘህ ነው፤ ሥራውን መካድ ስለማይቻል ባለቤቱን ነው መቀየር የሚሞከረው።

በገቢና ወጪ ስንመለከት፤ ገቢ ዘንድሮ 6 ወር ያቀድነው 270 ቢሊዮን ብር ነው። ያስገባነው 265 ቢሊዮን ብር ነው። ከመቶ ሲታይ 98 ከመቶ አከናውነናል። ከአምናው አንጻር ደግሞ ሲታይ 17 ከመቶ ብልጫ አለው። የጋራ ገቢን ስንመለከት በክልሎች መካከል፣ አምና 6 ወር፣ 22ነጥብ8 ቢሊዮን ነው ያከፋፈልነው። ዘንድሮ 27ነጥብ8 ቢሊዮን ጨምሯል። ትልቁ ችግር ግን ያለው፣ እዚህ ጋ የተከበረው ምክር ቤት ቢያየው መልካም የሚሆነው፣ የእኛ ገቢ ካለን ጂዲፒ አንጻር በጣም አነስተኛ ነው። አፍሪካ ውስጥ ከጂዲፒያቸው እስከ 30 ፐርሰንት የሚሰበስቡ ሀገራት አሉ። እነርሱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው። እንደነ ሞሮኮ ያሉ 30 ፐርሰንት ይሰበስባሉ። እኛ አካባቢ ያሉ ሀገራትም እስከ 15፤ ትንሽ ከዚያም ከፍ ያለ ይሰበስባሉ። የኛ ታክስ ከጂዲፒ አሁንም ከአስር በታች ነው። በቂ ገቢ በማይሰበሰብበት ሀገር ውስጥ በቂ ልማት ማምጣት አይቻልም። በታክስ ላይ ሪፎርም ያስፈልጋል። ሥራ ያስፈልጋል የሚለውን ሁላችንም በጋራ ብንይዝ፤ የኢትዮጵያም ሕዝብ በበቂ ደረጃ ታክስ እየተከፈለ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ሪፎርሞች ላይ ቢተባበር መልካም ነው። ቶሎ ሰብስበን አልምተን መውጣት ካልቻልን በስተቀር አይሆንም። አውሮፓ ውስጥ፣ ለምሳሌ ፈረንሳይን ብንወስድ 45 ፐርሰንት ታክስ ይሰበሰባል፤ ከጂዲፒያቸው። ምን ማለት ነው፣ አሁን እኛ በብር ከስምንት ትሪሊየን በላይ ጂዲፒ አለን። 45 ፐርሰንት ማለት 3.78 ትሪሊዮን ብር በዓመት እንሰበስባለን ማለት ነው፤ በእነርሱ ሂሳብ። እኛ ግን ታውቃላችሁ ያለንበትን ደረጃ፤ ሴክተሩ በገቢ ልክ በጂዲፒው ላይ የማሳደግ ሥራ መሥራትን ይፈልጋል።

ኤክስፖርትን በሚመለከት ከሸቀጦችና አገልግሎት አምና 10.7 ቢሊዮን ዶላር ነው ያገኘነው። ዘንድሮው ግማሽ ዓመት ባልሞላ፣ በአምስት ወር ወደ 4.5 ቢሊዮን ዶላር አግኝተናል። ከአምናው አያንስም የሚል ግምት ነው ያለው። ተጨማሪ ሥራዎች ግን ያስፈልጋሉ። ኤክስፖርታችን በአምናው ደረጃ ከሄደልን፣ ይህ አንድ መያዝ ያለበት ጥሩ ተቋም (ኢንፖርታንት ኢንዲኬተር) ነው።

ከኢንፖርት አንጻር አምና ያስገባነው 17 ቢሊዮን ገደማ ነው። ዘንድሮ በአምስት ወር ውስጥ 7.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንፖርት አስገብተናል። በኋላ የእዳውን እመጣበታለሁ። 7.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንፖርት ያስገባ ሀገር 30 ሚሊዮን አይከፍልም ብሎ መጠየቁ በጣም በጣም አሳፋሪ ነው። ኢትዮጵያ ከዚያ በላይ ናት። ገቢ ንግድን መተካት፤ ወጪ ንግድን ደግሞ ማብዛት በዘርፉ ብዙ ገቢ ማግኘት አሁንም ያላለፍነው ስብራት፤ ያልተጠገነ ስብራት ነው። ርብርብ ይፈልጋል። ከኢንቨስትመንት አንጻር አምና 3.4 ቢሊዮን ነው ያስገባነው። ዘንድሮ በአምስት ወር ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ከውጭ ኢንቨስትመንት መጥቷል።

የሥራ እድል እስካሁን በአምስት ወር ከ1 ሚሊየን በላይ የሥራ እድል ተፈጥሯል፤ በግማሽ ዓመቱ ከ150ሺህ ሰው በላይ በውጭ ሀገር ሚኒመም ዌጅ አለው። ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተልኳል። አንዱ የሥራና ክሂሎት ሚኒስቴር ትልቁ ውጤት የሚላከው ሰው እንደ ከዚህ ቀደም ደመወዝ የሚቀማ ምን እንደሚከፈለው የማይታወቅ ሰው ሳይሆን፤ ሚኒመም ዌጁን ተደራድሮ እዚህ በሚገኘው አካውንታቸው ገንዘባቸው እየገባ ስለሚሄዱ ከዝርፊያ ከመቀማት፣ ከመገደል የሚድኑበት መንገድ እንዲኖር ጥረት እየተደረገ ነው። ያም ሆኖ አሁንም ሰፊ ሥራ ያስፈልጋል። በየዓመቱ ሰው ይጨምራል፤ በየዓመቱ የሥራ ፍላጎት አለ። በዚያ ልክ ሥራ መፍጠር ላይ ተጨማሪ ጥረት ይፈልጋል።

ግሽበትን በሚመለከት ኢንፊሌሽን የብዙ ስብራቶች ድምር ውጤት ነው። በምንፈልገው ልክ ማምረት አለመቻላችን ነው ችግር የሚያመጣው። የምንፈልገውን ያክል ካላመረትን ለመግዛት እንገደዳለን፤ ስንገዛ ደግሞ ዋጋውን እኛ አንወስንም፤ የውጭ ምንዛሪ እኛ አንወስንም። በዚህ ምክንያት ብዙ መዛባቶች ይፈጠራሉ። እናንተም እንደምታውቁት የዓለም ዋጋው ደግሞ በበሽታው፣ በጦርነቱ፣ በድርቁ፣ ባለው አጠቃላይ ቀውስ ምክንያት እየተዛባ ስለሆነ፤ ግሽበት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት፤ ለትላልቆቹም ጭምር በጣም ፈታኝ እየሆነ ነው ያለው።

በኛ ሁኔታም የንግድ ሠንሠለቱ ባለበት ችግር ምክንያት የኢንፍሌሽንን ችግር በታሰበው ልክ ልንፈታ አልቻልንም። በእኛ በኩል ውጤት ታይቷል፤ 35 ከነበረበት ወደ 28 ዝቅ ብሏል። ነገር ግን በኢንፍሌሽን ላይ እየወሰድነው የነበረው ሪፎርም እንደ አንቲ ፔይን (ሕመም ማስታገሻ) ነው። በማስታገሻነት የሚታይ፤ ቆንጠጥ የሚያደርግ፤ በዘላቂነት ማከም የሚያስችል ሪፎርም መድፈር የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እየደረስን መጥተናል።

ሪፎርም በባሕሪው እንደ ዴንቲስት ነው፤ እንደ ጥርስ ሐኪም ነቃይ ነው። ሰው ጥርሱን ታሞ ጥርስ የሚያክም ሐኪም ጋር ከሄደ በኋላ ጥርስ ማከም በጣም የሚያም ፕሮሰስ ስለሆነ፤ ያ በሽተኛ ከቤቱ ሠላም መጥቶ ሐኪሙን ካየው በኋላ በሽታው የጨመረበት ይመስል በከፍተኛ ጥላቻ፤ አንዳንዱም በስድብ ነው ሐኪሙን የሚያየው። ምክንያቱም ሂደቱ በጣም አስቸጋሪ ነው። እረፍቱ የሚመጣው ሕክምናው ካለቀ በኋላ ነው። በሕክምናው ጊዜ እንደሌላ በሽታ ሳይሆን የጥርስ ሐኪም ሁሌም የሚገጥመው እርግማን ነው። ውሎ ካደረ በኋላ ነው ሰው እረክቶ ማመስገን ውስጥ የሚገባው። ሪፎርም እንደዛ ነው፤ ውጤቱ አይታይም፤ ያማል። እንደመጣ ሁሉም ሰው የሚቀበለው አይደለም፤ እየዋለ እያደረ ነው በኢኮኖሚያችን ውስጥ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው የሚረዳው።

ይህን ለማድረግ አንደኛ እኛ ያደረግነው ምርት ማሳደግ ነው። መጀመሪያ ስንዴ፤ ሩዝ አልን፤ ውጤት እያየንበት ነው። ስንዴን በሚመለከት፤ ስንዴ አለ ወይም የለም፤ የት ነው የሚመረተው? የሚል ጥያቄ ያላችሁ ሰዎች ወጣ ብላችሁ እዩ ነው መልሱ። አዲስ አበባ ስንዴ የለም፤ ወጣ ስትሉ ግን ሞልቷል፤ ወጣ ብሎ ማየት ነው። እናንተን አይመለከትም ይሄ ጥያቄ አየር ላይ ስላለ ነው። እኔ ግን የማየው በየዓመቱ 7 መቶ፤ 8 መቶ ሚሊየን ዶላር ለስንዴ እናወጣ ነበር። አሁን ለስንዴ አንድ ብር አናወጣም። አምናም ዘንድሮም። ሌላውን ትርፉን ትቼ ማለት ነው። እሱን ትተን ሌላ የሚጨበጥ፣ የሚታይ ነገር ማሳደግ ያስፈልጋል።

ስንዴ ለምግብነት ጥሩ ነው፤ ኒውትሪሽን ደግሞ ያስፈልጋል። ሌማት ባልነው ወተት፣ እንቁላል፣ ሥጋ፣ ማር እነዚህን ስንጨምርበት ደግሞ ሙሉ ይሆናል። አሁን የትኛውም ዓለም ላይ ትልቅ የሚባል ሆቴል ሄዳችሁ ቁርስ ስታዙ ከስንዴና ከሌማት ውጭ ምንም ነገር ቴብል ላይ የለም። ዳቦ፣ ፓንኬት፣ ማር፣ እንቁላል፤ ምናልባት ሥጋ፣ ሁሉንም በርከት በምግባችን ላይ፤ ምናልባትም በጠረጴዛችን ላይ ለማግኘት ያግዘናል። አቅጣጫው ይሄ ነው።

በሥራ ዶሮን በሚመለከት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፤ ምናልባት ከአምናው በእጥፍ እያደገ ነው፤ ይቀራል። ችግር ያለብን እኛ አይደለንም። ግራንድ ፓረንት ማግኘት አልቻልንም። በጥቂት ሀገራት የተያዘ ነው። እሱን ስንፈታ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶሮዎችን እናመርታለን። በየመንገዱ ዶሮ መጥበስና ዳቦ ገዝቶ እየበሉ መሄድ ኢትዮጵያ ውስጥ ወግ ይሆናል የሚል ተስፋ አለን። ስለዚህ ምርት ማምረት ነው። ለምርት ደግሞ መሥራት ነው። ድርቅ አለ፤ ረሀብ አለ ምናምን ሳይሆን ትራክተርና ውሀ ፈልጎ መሥራት ነው። ሥራ ብቻ ነው ውጤት የሚያመጣው። ካልሠራን፤ ከተቀመጥን ለውጥ አይመጣም። ሕገ ወጥ ንግድ ላይ እርምጃ መውሰድ ይፈልጋል። ኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ ግብይቱ ላይ እርምጃ እየወሰድን ነው። ከፍተኛ አሻጥሮች በየጊዜው ይያዛሉ። ትሰሙት ይሆናል፤ እሱን አጠናክሮ መሄድ ያስፈልጋል።

ደሃ ተኮር ሥራዎቻችን ላይ ይሁነኝ ብለን፣ አስበን መሥራት ያስፈልጋል። የደሃ ቤት መሥራት፤ ምግብ ማጋራት፤ ተማሪ መመገብ፤ ደሃ መመገብ የሚባል ነገር ብዙ እጅ አጠር ሰዎች ባሉበት ሀገር ላይ ያስፈልጋል። እንደዛ አይነት ሥራ እየሠራን ካልሄድን በራሱ ጊዜ ገበያው ብቻ እንዲወስን ካደረግን ብዙ ሰው ስለሚጎዳ ያንን ባሕል እያጠናከርን መሄድ ያስፈልጋል።

በዚህ ስድስት ወር መጠነኛ የሆኑ መሻሻሎች አሉ። በሚቀጥለው ስድስት ወርም እንደዛ እንደሚሆን ይጠበቃል። ሪፎርም እንደ ጥርስ ሐኪም ትንሽ ቆንጠጥ አድርጎ ማስተካከልን ይጠይቃል። ያ ማስተካከያ አሁን ላለው መንግሥት ላይጠቅመው ይችላል። ለትውልድ ግን በጣም ወሳኝ ነው። እንደዛ አድርገን፣ በጣም ጠበቅ አድርገን፤ አሁን ስብራቶቻችን ብለን የምንቸገርባቸው ነገሮች በተወሰነ ደረጃ እልባት ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ተስፋ አለ።

እዳን በሚመለከት፣ መቼም የዚህ የለውጥ መንግሥት ትልቁ ስኬት የሚያኮራ ድል ካለ እዳ ላይ ያለን አቋም ነው። በነገራችን ላይ ለእኛ ስብራት ሆኖ ያስቸገረን ብድር እኮ አይደልም። አራጣ ነው። ኮሜርሻል ሎን (ኮሜርሻል ብድር) ማለት አራጣ ማለት ነው። ምንም የማትሠራበትን ነገር፣ ባጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ወለድ አድርጌ እከፍላለሁ ብለህ ተበድረህ ማምጣት፤ ከዚያ ሥራውን ሳትሠራ ሌሎች ሀብቶችህን ማስወሰድ ማለት ነው።

በአራጣ የሚመጣ ልማት ‹‹ይቅርብን›› ኮሜርሽል ሎን የሚባል አያስፈልገንም›› ብለን ባለፉት አምስት ዓመታት አንድ ዶላር ኮሜርሻል ሎን አልወሰድም። መጥቶ  እንደሚሄድ መንግሥት የሚያዋጣው ከዛም ከዛም ለቀም ለቀም አድርጎ ሠርቶ መሄድ ነው። ግን ትውልድ ላይ ጫና ስላለው አናደርግም ብለን አምስት ዓመት አንድ ብር ከኮሜርሻል ሎን አልወሰድንም። በአንጻሩ ከ2011 አስከ 2015 ኢትዮጵያ 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ከፍላለች።

አንድ ብር ኮሜርሻል ሎን ሳንወስድ 9ነጥብ9 ቢሊዮን ዶላር ከፍለን የምንሠራቸውን ልማቶች አስቡት። እኛ ቢሮ ስንመጣ የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ የነበረው የጂዲፒያችን 32 ፐርሰንት ነው። የሀገር ውስጥን ሳይጨምር ማለት ነው። አሁን የውጭ ዕዳችን በ17 ፐርሰንት ዝቅ ብሏል። ዋናው ፍላጎታችን ከ10 ዝቅ ማድረግ ነው። የጂዲፒያቸውን መቶ ምናምን ፐርሰንት ዕዳ ያለባቸው ትላልቅ አገራት አሉ።

የእኛ ዓላማ ግን ከ10 ፐርሰንት ማውረድ ነው። ከ32 ወደ 17 ደርሰናል። በሚቀጥሉት ዓመታት ዝቅ እናደርገዋለን የሚል ግምት አለ። ዕዳ በመክፈል ነው የምንኩራራው። ትልቁ ሥራ የሠራነው ኮሜርሻል ሎን ባለመውሰድና የነበረውን የዕዳ ስብራት ከዚህም ከዚህም ተወሳስዶ መክፈል ላይ ነው።

ይህን እያደረግን ግን ለዓለም መንግሥታት ‹‹ይሄ ዕዳ አግባብነት የለውም፣ ችግር አለበት፣ ዕዳችሁን ተመልከቱ ›› የሚለውን ኢትዮጵያም፣ በጣም ብዙ አፍሪካ አገራትም በየአደባባዩ ይጮሁ ነበር። በዚያ ምክንያት “ኮመን ፍሬም ወርክ የሚባለው ዕዳ ከኮሜርሽያል ወደ ኮንሴንሽናል የሚያሸጋግረው ሥርዓት ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት ይጠና ነበር። የብድር ሥርዓቱ ችግር ስለነበረበት የፈጠነ ምላሽ አልተገኘበትም። በርካታ ሀገራት በዚህ ቅሬታ አለባቸው፤ ኢትዮጵያም ቅሬታ አላት።

አሁን ይሄ እንዳለ የዬሮ ቦንድ 33 ሚሊዮን ብር ዕዳን ማኔጅ ለማድረግ ኢትዮጵያ አልቻለችም የሚል ዜና ተሰራጨ። አንደኛ 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የከፈለች አገር፣ እሱ እንኳን ቢቀር፣ ዘንድሮ በአምስት ወር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር አውጥታ ኢምፖርት የከፈለች አገር። 33 ሚሊዮን መክፈል አቅቷት ነው ቢባል ተረት ተረት ነው።

በነገራችን ላይ የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት 33 ሚሊዮን ዶላር ማለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሁለት ቀን ገቢ ማለት ነው። 6ነጥብ 6 ገቢ አለው ማለት በቀን 16 . . . 17 . . . ሚሊዮን ዶላር ያገኛል ማለት ነው። ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት። ለሠላሳ ሚሊዮን የምትታማ አይደለችም። ይህን ለምንድነው የሚያራግቡት እጃችንን ለመጠምዘዝ ነው። ችግር አለ ብለን ያው እኛ ቶሎ ከውጭ ስንሰማ የምንቀበል ሕዝቦች ስለሆንን፣ ቆም ብለን ስለማናዳምጥ እጅ ለመጠምዘዝ የሚደረግ ሩጫ ነው።

ኢትዮጵያ ታዲያ ለምን አልከፈለችም? አቅሙ ካለ ለምንድነው መክፈል ያልተቻለው? የሚል ጥያቄ ከሆነ ይሄ አግባብነት ያለው ጥያቄ ነው። መልሱም ቀላል ነው። አንድ ከተሜ ገጠር ሄዶ በገጠር ያሉ ሰዎችን ሒሳብ ያስተምራል። ሒሳብ ሲያስተምር ‹‹ከአምስት ሲቀነስ አንድ ስንት ነው?›› ብሎ አርሶ አደሩን ይጠይቃል። አርሶ አደሩም ‹‹አላውቅም›› ይለዋል። ‹‹እንዴ፣ እንዴት አታውቅም፤ አምስት ፍየል ቢኖርህ ከአምስቱ ፍየል አንዱ ቢጠፋ ስንት ይቀርሃል?›› ሲለው ።‹‹ምንም አይቀረኝም›› ይላል አርሶአደሩ።

‹‹ያምሀል እንዴ፣ አምስት ፍየል ነው ያለህ፤ ከአምስቱ አንዱ ቢጠፋ ስንት ይቀርሀል? ሲለው «ምንም አይቀረኝም›› ይላል። እናም ሰውየው ግራ ይጋባል። አርሶ አደሩ ‹‹ምን መሰለህ ልጄ፣ አንተ ሒሳብ ታውቃለህ፤ አንተ ቁጥር ታውቃለህ፤ እኔ ደግሞ ስለፍየል አውቃለሁ፤ አምስት ፍየል ቢኖርህና አንዱ ቢጠፋ አራቱም ይከተሉታል እንጂ አይቀሩልህም። አንዱም አይቀርልህም።›› ዓለም ላይ የዕዳ ችግር አለ። አስተካክሉ ብለን ከሀገር ሀገር እየጮህን አንደኛውን ብቻ ብንከፍል ሁሉም ያን መንገድ ብቻ ስለሚከተል ለማመሳሰል ያደረግነው ነው ለማለት ነው።

ማዳበሪያን በሚመለከት፣ ጠያቂዋ እንዳነሱት አምና ችግር ነበረብን፣ ዘግይተን ነበር። በዚህ ዓመት በጣም ከፍተኛ የሆነ ሥራ ነው የሠራነው። ገና ክረምቱ እንዳበቃ ወደ 20 ቢሊዮን ብር ገዳማ አውጥተን ማዳበሪያ ገዝተናል። በሚገርም ሁኔታ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ቶን በላይ ገብቷል። ወደ አርሶ አደሩም እየደረሰ ነው ያለው። አምና በዚህ ጊዜ ገና ግዢ ላይ ነበርን። ዘንድሮ ግዢው አልቆ ከፊሉ ገብቶ፣ ከፊሉ እዚሁ ደርሷል። አስተማማኝ በሆነ መንገድ ከጊዜው ቀድሞ እንደሚደርስ ይጠበቃል።

ከተገዛና ከመጣ በኋላ በየመሀል ያለውን አሻጥር ደግሞ የብድር ኤጀንሲና ሕዝቡ ተባብሮ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ዘረፋው ማዳበሪያውም ላይ አለ። መኪና አስቁሞ መዝረፍ ላይም አለ። ሰው ማገት ላይም አለ። ‹‹ችግር አለና ስንዴ ካላመጣችሁ›› ላይም አለ። የልመናና የሌብነት መንፈሱ በጣም በጣም ትልቅ ነው። ይሄን በጋራ መስበር ያስፈልጋል። እንደተባለውም መሥራት አለብን ።

ደቡብ ምዕራብን በሚመለከትና የልማት፣ የደሞዝ፣ ጉዳዮችን በሚመለከት በደቡብ ክልል ውስጥ ‹‹ክልል እንሁን›› የሚል ጥያቄ ሲነሳ እዚሁ ምክር ቤት ላይ ‹‹ይሄ ክልልነት ለተወሰኑ ሰዎች ኮብራ ለመግዛት ነው እንጂ ለሕዝቡ ፋይዳ የለውም›› ብናስብበት፤ በሚል ተደጋጋሚ ሃሳብ አንስቻለሁ፤ ታስታውሳላችሁ፤ አንስቻለሁ። ማለት ሕዝቡ እፈልጋለሁ ካለ ‹‹አይሆንም›› እላለሁ ማለት አይደለም። ሕዝቡ ከወሰነ እኔም፣ እናንተም መገዛት ነው ያለብን።

አሁን እንደ ደቡብ ምዕራብ ያሉ ወይም አዳዲስ ክልሎች፣ በጣም ሀብታም ክልሎች፣ ለሌላው መትረፍ የሚገባቸው ክልሎች፣ ደቡብ ምዕራብ ማለት የምድር ላይ ገነት ማለት ነው፤ ምንም የሌለው ነገር የለም። በጣም በጣም ሀብታም የሚባል ክልል። ግን ማንም ሰው አንድ ግለሰብ፣ 10 ሺህ ብር ደሞዝ ኖሮት 20 ሺህ ብር ወጪ ካለው በየወሩ ዕዳ ውስጥ ነው ያለው ማለት ነው። 10 ሺህ ብር ገቢ ያለው ሰው ምርጥ መኪና አያምረውም ማለት አይደለም። ምርጥ ፎቅ አያምረውም ማለት አይደለም፤ ገቢው አይፈቅድለትም። ባለመቶው ሺህ ቪላ ቤት ይኖራል፣ ባለ አስርሺው ዝቅ ያለ ቤት ይኖራል። ሰው በገቢው ልክ ነው እንጂ ራሱን የሚያስተዳድረው ከገቢው ባሻገር ‹‹እነ እንትና ኮብራ ስላላቸው›› ካለ ነገሩ ይበላሻል።

አሁን እኔ አንደኛ መጠየቅ ያለብኝ ለክልሎች እናንተ ወስናችሁ ያስቀረነው ገንዘብ ካለ መጠየቅ አለብን። ከወሰናችሁት ገንዘብ በስድስት ወር መቶ ፐርሰንት ተሰጥቷቸዋል። ያስቀረነው ገንዘብ የለም። ሁለተኛ፣ ቅድም እንዳነሳሁት የጋራ ገቢ ከአምናው ዘንድሮ ጨምሯል። በጀትም ጨምሯል፣ የጋራ ገቢም ጨምሯል፣ በእናንተ የጸደቀ የቀረ ነገር የለም። ታዲያ ከየት አመጣለሁ፤ ለብቻ እኮ ብር አስቀምጥና ‹‹አንዳንዶች ሲቸግራቸው ቆንጠር እያደረክ ስጥ›› አላላችሁኝ እናንተ። ከየት ይመጣል። አሁን እኔ ዓለም ላይ ሄጄ በጀት ቸግሮኛልና ብር ካላመጣችሁ ብላቸው ማን ይሰጠኛል ‹‹ራስህን ቻል›› ነው የምባለው። የምራበው እኮ ችግረኛ ስለሆንኩ ነው።

ለምሳሌ ደቡብ ምዕራብ ገቢው አነስተኛ ከሆነ ዞን የሚባል ነገር ትቶ ክልልና ወረዳ ይሆናል ማለት ነው። በራሱ ሁኔታ። በኋላ አቅም ሲያገኝ ሊጨምር ይችላል። ኦሮሚያ ዞን ስላለ፣ አማራ ዞን ስላለ ዞን በዞን አደርጋለሁ ካለና ኮብራ ከገዛ ግን ሰው ይቸገራል ማለት ነው። ይሄን የክልሉ አመራሮች ይገነዘባሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሕዝቡም መገንዘብ አለበት። ኢትዮጵያ ባላት አቅምና እናንተ በወሰናችሁት ብቻ ነው እኛ የምናስተዳድረው፤ እኛ ማስተዳደር እንጂ መወሰን አንችልም።

ከአንዱ ክልል አንዱ ክልል ፌዴሬሽን ከወሰነው ቀመር ባሻገር መቀነስም መጨመርም አንችልም። ያም ሆኖ ግን ደቡብ ምዕራብ የልማት ጥያቄ የተባለው ደቡብ ምዕራብ ማለት እኮ ኮይሻ ያለበት ማለት ነው። ደቡብ ምዕራብ እኮ ሀላላ ኬላ ያለበት ማለት ነው። ጨበራ ጩርጩራ ያለበት ማለት ነው። ደንቢ ያለበት ማለት ነው። ካሉት የደቡብ ክልሎች እንደ ደቡብ ምዕራብ ትላልቅ ልማት ያለበት የለም።

 ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ቢጠይቅ ይገባዋል። ይሄ ማለት የፌዴራል መንግሥት አቅም ሲኖረውና ሲችል አያግዝም ማለት ሳይሆን፣ ክልሎች ግን የምንጠይቀው ያለን ሪሶርስ መሆኑን አውቀን በዚያ ልክ ወደ ልማት መግባት ይኖርብናል። ያ ካልሆነ እንቸገራለን። የፌዴራል መንግሥት የተለየ ገቢ ስለሌለው ሊያከፋፍል ይቸገራል የሚለውን መገንዘቡ ጠቃሚ ይመስለኛል።

ሕገ-ወጥ ፋይናንስ በጣም ትልቅ ችግር ነው። የሕግ ማዕቀፍ ላይ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። ቴክኖሎጂ ላይ፣ ተቋሙ ላይ ሪፎርም ተካሂዷል። ትብብር ከብዙ ሀገራት ጋር ተደርጓል፤ አሁንም ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ ይንቀሳቀሳል። የተከበረው ምክር ቤት ከዚህ ቀደም እንዳነሳሁት ምክር ቤቱ በድጋሚ እንዲገነዘብ የምፈልገው አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ መንግሥት በተቀናጀ መንገድ፣ በሆነ ክልል ልማት ማኅበር፣ በሆነ ክልል ኤንጂኦ /መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት/ በሚል ስም ብር ከኢትዮጵያ አያሸሽም። መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ በዚህች ሀገር ስቴት ኮራፕሽን/ መንግሥታዊ ሙስና/ የለም።

ይሄ መንግሥት እንደ መንግሥት ብር አያሸሽም፤ ያገኘናትን ስሙኒ ሁሉ እዚሁ ልማት ላይ እናውላለን፤ ለዚያ ነው ውጤት የመጣው። ሌላ ምስጢር የለውም። ግለሰቦች ግን ባላቸው ኔትዎርክ፤ ባላቸው ማዕቀፍ ብዙ ጥፋት እያደረጉ ነው፤ አልቆሙም። ይሄን ለመከላከል ተጨማሪ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።

እኔ እስካሁን ቢሮ በቆየሁበት ጊዜ ያገኘሁት ልምድ ዓለም ስለሙስና ትርጓሜ ሲያብራራ፣ አፍሪካ እንዴት ሙሰኛ እንደሆነች ሲናገር፤ ሙስና እንዴት ፀረልማት እንደሆነ ሲናገር እንጂ ከሙስና ጋር አልተባበርም ሲል አይቼ አላውቅም። የሚሰረቀው ገንዘብ ሁሉ የሚሄደው እዛ ነው። የተነገረን ቲዎሪው ነው እንጂ በተግባር ግን ትብብር ነው ያለው።

ከኢትዮጵያ የተወሰደ ገንዘብ የትኛውም ዓለም ቢኖር ይታወቃል። ይሄ የሌብነት ገንዘብ ነው ብሎ መመለስ ይቻል ነበር፤ ነገር ግን እስካሁን ባለው ሁኔታ ሃሳብ እንጂ ተግባር ስላልሆነ ትብብሩ እምብዛም ውጤት ያመጣ አይደለም።

ፕሮጀክቶችን በሚመለከት ስለተነሳው ጥያቄ አንድ ሀገር የምትለወጠው የምትበለፅገው በፕሮጀክት ነው። ሀገር ማለት የፕሮጀክቶች ድምር ማለት ነው። ፕሮግራም የሚሆነው ፕሮጀክት ሰደመር ነው። ሕዳሴ ግድብ፣ መንገድና የመሳሰሉት ፕሮጀክቶች ሲደመሩ ብልጽግናን ያመጣል። ፕሮጀክት በወጉ ያልመራ መንግሥት ፕሮግራም አይመራም፤ ብልፅግናን አያመጣም። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ተቋም የሌለበት፣ አሠራር የሌለበት ሁሉ ሰው እኩል የማይተጋበት ሀገር ሲሆን በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተጨማሪ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ለምሳሌ ዓድዋ እንደዚያ አምሮ ያያችሁት ክብርት ከንቲባዋ እና ቲማቸው/የሥራ ባልደረቦቻቸው/ በየቀኑ ማታ አምስት ሰዓት እየገመገሙ ስለመሩት ነው። እናንተ መኖራችሁን በስፍራው አላውቅም፤ ከንቲባዋ በየቀኑ ሳይት ላይ ግምገማ አላቸው። በትጋት ነው የሚመጣው፤ በሥራ ነው የሚመጣው፤ ኢንስቲትዩሽን የለም፤ ነግረህ ብቻ ይሳካ ማለት አይቻልም።

ሕዳሴም ይሁን ዓድዋ በየቀኑ በሚደረግ ክትትል እና አመራር ነው ውጤት የሚመጣው። እዚህ አካባቢ ደግሞ ያሉ ሰዎች ሁሉም ጋ መድረስ አይችሉም። በየደረጃው ያለ አመራር በወረዳም፣ በዞንም፣ በክልልም ያንን ባህሪ ተላብሶ ሥራን በየዕለቱ የሚከታተል መሆን አለበት።

ሁለተኛው ቁልፍ ነገር አለመርካት ነው። እርካታ የዕድገት ፀር ነው። ለምሳሌ አዲስ አበባ ላይ በጀመርነው ሪፎርም /ማሻሻያ/ ቦሌ አራት ኪሎ፣ ቸርችር ጎዳና፣ ፒያሳ አካባቢ ጅምር ለውጦች አሉ። ለከተማው አመራሮች እንደነገርኳቸው ይሄ ሥራ የዛሬ ወር ሁለት ወር ካለቀ በሚቀጥለው ሁለት ሦስት ወር መነጋገር ያለብን ከሣር ቤት ጎተራ፣ ወሎ ሰፈር፤ ከቦሌ መገናኛ፣ ከመገናኛ አራት ኪሎ፣ ስለማስፋት ነው እንጂ ቸርችር ስለተሠራ በቃ የሚባል ነገር አይሠራም። ያ ካለቀስ፤ ሲኤምሲና መገናኛን እንዴት እናገናኘው፤ አቃቂና ቦሌን እንዴት እናገናኘው ለቡና ሳርቤትን እንዴት እናገናኘው፤ መሐል ላይ የሚፈርስ የሚጠገን ካለ ማለት ነው። ይሄን ስናገናኝ እንዳልነውም አዲስአበባ ሙሉ ውብ ትሆናለች።

ለሌላውም ልምድ ታካፍላለች። ትጋት ክትትል ኖሮ እርካታ ግን ካለ አይሳካም። ዓድዋን ሠራነው ካልን አይሳካም። ዓድዋ ጀመርን እንጂ ገና ነው። የጀመርነውን ይዘን ተጨማሪ ጥረት እያደረግን ከሄድን ግን በሀገር ደረጃ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።

ልማት አደናቃፊዎች በጣም ብዙ ናቸው፤ በአሠራር፣ በሕግ፣ በኮሚቴ፣ በቅርስ። የቴሌኮሙኒኬሽን ሕንፃ ፈረሰ፤ ቅርስ ፈረሰ ብሎ የሚንጫጫ ሰው እኮ ነው ያለው። ምን ቅርስ አለው፤ ትናንትና ማንም የደረደረው ብሎኬት፤ ደንቃራና ለእይታ የማይመች ሲሆን ይፈርሳል፤ ቻይናም ይፈርሳል፤ አሜሪካም ይፈርሳል። ደግሞም መነካት የሌለባቸው ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ላሊበላ ይጠበቃል፣ ይታደሳል። ቅርስ እና ሕንፃን መለየት አለብን። ጎጆ ሁሉ ባየን ቁጥር ቅርስ እያልን ልማትን የምናደናቅፍ ከሆነ ያስቸግራል።

በዚህ አግባብ የተሳካልን አካባቢ እንዳለ ሁሉ ያልተሳካልን አካባቢም አለ። ለምን ያላችሁ ከሆነ የፖሊሲ ችግር ሳይሆን የመቀበል እና የማስፈፀም ችግር ስላለ ነው። ለምሳሌ የስንዴ ልማት ለሁሉም ክልል እኩል ፖሊሲ አለው፤ ለሁሉም ክልል እኩል ሥልጠና አለው። አንዳንዱ የተሻለ ይሠራዋል፤ አንዳንዱ በዚያ ልክ አይሮጥም፤ ይሄ መቀየር አለበት። በሌላውም ሥራ እንደዚሁ ማለት ነው።

አዲስ አበባ ከተማ በጽዳት ከተሳካለት አዳማ ለምን አይሳካለትም? ቢሾፍቱ ለምን አይሳካለትም? ኦሮሚያ በስንዴ ከተሳካለት ሶማሌ ለምን አይሳካለትም እያልን በልማት እያወዳደርን መሥራት ነው የሚጠቅመን፤ የሚያዋጣን። በዚህ አካሄድም ፕሮጀክቶች ፈር ይይዛሉ።

እኛ ድንጋይ አስቀምጠን ለመሥራት የማንፍጨረጨርበት ፕሮጀክት የለም። በተደጋጋሚ እንዳልኩት በሆነ በሆነ ጊዜ የተዘራውን ድንጋይ ለመልቀም እኛ አልመጣንም። የዘራውን ሰውዬ ሄዳችሁ ጠይቁት፤ ዝም ብሎ በየሄዱበት ድንጋይ እያስቀመጡ ቃል እየገቡ ተሄዶ አሁን በዚህ ተጀምሯል ቢባል አስቸጋሪ ነገር ነው።

በበጀት ስለሚሠራ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍላጎት ከፍተኛ ነው። ግድብ ይባላል፣ ውሃ ይባላል፣ ኤሌክትሪክ ይባላል። ለዚህ ሁሉ የሚበቃ ሀብት የለንም። እየመረጥን ነው የምንሠራው፤ በዚያ ቢታይ።

እኛም በፀጥታ፣ በኮንትራክተሮች፣ በክትትል እጥረት ምክንያት ጀምረን ያቋረጥናቸው የዘገዩ ፕሮጀክቶች አሉ፤ እነሱን እየገመገምን እናርማለን። በጣም ብዙ አሻሽለናል ዘንድሮ ትታዘቡ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ይቀጥላል አሁንም። እየገመገምን እናስተካክላለን። አብዛኛውን የሕዝብ ጥያቄ አቅም በፈቀደ መጠን ለመመለስ እንሞክራለን።

ከአፍሪካ ትስስር ጋር ተያይዞ የተነሳው አስፈላጊ ጥያቄ ነው። አፍሪካ ላይ በሁሉም መልክ መሠረተ ልማት መገንባት አለበት፤ ትስስሩ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አለበት። ያው አፍሪካ ላይ ከትብብር ይልቅ ውድድር ይበዛል፤ ኢትዮጵያ ከአንድ ቅርብ ካለ ሀገር የሆነ ነገር ከምትገዛ ከሩቅ ብታመጣ ይቀላታል። እዛም እንደዚሁ ነው። በትብብር ውስጥ ያለ ነገር ገና ችግር አለ።

ግን ባለፈው ዓመት ተኩል ገደማ ከኬንያ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ተስማምተናል፤ ታውቃላችሁ። አሁን ከታንዛኒያ ጋር ድርድር ጨርሰናል፤ በቅርቡ እንፈራረማለን። ከታንዛኒያ ጋር ከጨረስን ወደ ደቡብ ለመውረድ ዕድል ይሰጣል ማለት ነው። እንደሱ እያደረግን በመንገድም በኤሌክትሪክም እየተሳሰርን ከሄድን

 ልማትና የጋራ ጥቅም እያደገ ሲሄድ ሌላው ጉዳይ እየቀነሰ እንደሚሄድ ይታሰባል።

የስፖርት ጨዋታ ውድድር፣ ፉክክር፣ ቤቲንግ የሚባለውን በሚመለከት የተሟላ መረጃ ስለሌለኝ ብሔራዊ ሎተሪ ሁኔታውን አጥንቶ የሌሎች ሀገራት ልምድን ቀምሮ የሚሠራበትን መንገድ እንከተላለን። ብዙም መረጃ ስለሌለኝ አሁን ብዙ ማለት አልችልም። ነገር ግን ብሔራዊ ሎተሪ ዋናው ሥራው ይሄ ስለሆነ በእነሱ ተጠንቶ ትክክለኛና የሚሻለውን፤ ለትውልድ የሚበጀውን መንገድ እንከተላለን።

ቱሪዝምን በሚመለከት ሙከራዎች አሉ። ደስትኔሽን/ መዳረሻ/ ማልማት ላይ፤ የልማት ኢንዱ/ ግቡ/ እና ሰላሙ ላይ ካልሠራን የተሟላ ውጤት አይመጣም የሚለው ትክክለኛ አገላለፅ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹ይሄ መንግሥት ሥራው በቃ ችግኝ መትከል ብቻ ነው፣ አበባ መትከል ብቻ ነው፣ ማፅዳት ብቻ ነው፣ ፓርክ ብቻ ነው፤ ምን ያደርጋል›› የሚሉ ክሶች ይሰማሉ። እነዚህን ክሶች በሌላ ጥያቄ ማየት ጠቃሚ ይመስለኛል።

‹‹ኢትዮጵያ 99 በመቶ እምነት ያለው ሕዝብ ያላት ሀገር ናት›› ይባላል። ‹‹ሙስሊሙም ክርስቲያኑም አላህንም እግዚአብሔርንም የሚከተል ሕዝብ ያለባት ሀገር ናት›› ይባላል። ሙስሊሞች በቀን 5 ጊዜ ይሰግዳሉ፣ ይፆማሉ፣ አንሰርቅም ሃራም ነው ይላሉ፣ አንዋሽም ሃራም ነው ይላሉ፣ አልፎ አልፎም ሲያበላሹ ቶሎ ብለው ይቅር በለን ማረን ስታፎሮላ ይላሉ።

ለምንድነው የሚሰቃዩት፤ ሙስሊሞች በቀን አምስት ጊዜ የሚሰግዱት፣ የሚፆሙት ከብዙ ነገር ራሳቸውን አስረው ጠብቀው የሚኖሩት? ከሞቱ በኋላ ከአላህ ጋር ለመወዳደር፣ የአላህን ወንበር ለመውሰድ አንተ በቃህ እኛ እንምራ ለማለት ነው እንዴ? አይመስለኝም።

ክርስቲያኖች ፆመው ፀልየው፣ አንዳንዶች ገዳም ገብተው፣ ራሳቸውን ጎድተው፣ ቢችሉም ባይችሉም አንዋሽም፣ አንቀጥፍም ብለው ዕድሜያቸውን በሙሉ የሚሰቃዩት ከሞቱ በኋላ አምላክ ሆይ አሁን በቅቶሃል አንተ ወንበሯን ለቀቅ አድርግልንና እኛ እንቀመጥበት ለማለት ነው እንዴ? አይደለም።

ጥሩ ዛፍ፣ ጥሩ አበባ፣ ጥሩ ሽታ ያለበት ቦታ ለመውረስ ነው። ይሄ ሁሉ በምድር ላይ የምንሰቃየው ገነትን ለመውረስ ነው። ገነት ምንድነው? ጥሩ ዛፍ፣ ጥሩ አበባ፣ ጥሩ ሽታ ያለበት ነው፣ ሌላ ምስጢር የለውም፤ የሰው ልጅ ሙሉ ጥረት እስላምም ቢሆን ክርስቲያን መጥፎ መጥፎ የሚሸት ቦታ እንዳልሄድ፣ የሚያቃጥል ቦታ እንዳልሄድ፣ የሚያስጠላ ቦታ እንዳልሄድ፣ ንፁህ ቦታ ይሻለኛል ብሎ የሚሰቃየው እንጂ ለሥልጣን አይመስለኝም። ስንፆም ስንፀልይ የምንኖረው ለሥልጣን አይመስለኝም።

ገና ስንሞት ጥሩ ዛፍ ያለበት ቦታ ለመኖር ዕድሜያችንን ሙሉ የምንሰቃይ ሰዎች እንዴት አሁን ፓርክ አይሠራም እንላለን። ፓርክ ማለት እኮ ትንሹ የገነት ሞዴል ነው። ገነትን አያክልም፤ ገነት በጣም ብዙ ሰላም አለው፤ ብዙ ነገር አለው። እሱን ተስፋ እናደርጋለን። በምድር ላይ ግን ንፁህ ስፍራ ሲሠራ ችግኝ ሲተከል ውሃ ሲገደብ የሚጠላ ሰው ለምን በፆም በፀሎት ራሱን ያስቸግራል ነው ጉዳዩ። አልታይሜትሊ/ በመጨረሻ/ መውረስ የሚፈልገው እርሱን ስለሆነ ነው።

ቱሪዝምን ከገቢ አኳያ ብቻ ማየት የለብንም። የምንመኘውን የኑሮ ዘዬ ለመውረስ የሚደረግ ጥረት ነው። እዚያ ውስጥ ሥራ አለ። ቅድም አንስቼላችኋለሁ። ታችኛው ቤተመንግሥት ዛሬ ሦስት ሺ 400 ሠራተኞች አሉ። ባይታደስ አይሠራም ማለት ነው። ዩኒቲ ፓርክ በመቶ ሚሊዮኖች ገቢ አስገብቷል። ባይታደስ ገቢ የለም ማለት ነው። እንጀራ ነው። ማማሩ ብቻውን ሳይሆን ሥራ ፈጣሪና ገቢ አሳዳጊ መሆኑን ከግምት ማስገባት ጠቃሚ ይሆናል። እናም ይሄ መንግሥት አቅም በፈቀደ መጠን ችግኝ እንደተከለ፣ አካባቢ እንዳፀዳ፣ ትናንሽ ገነቶች እንደሠራ ዘመኑን ይጨርሳል።

ዲፕሎማሲን በሚመለከት፡- የዲፕሎማሲ ማዕከሉ ብሔራዊ ጥቅም ነው። ኢትዮጵያ ከየትኛውም ሀገር ጋር የምትዛመደውም፣ የምትነጋገረውም መሠረታዊ ፍላጎቷን ለመመለስ ነው። ብሪክስ የምትገባውም፣ ኢጋድ የምትገባውም፤ ለጥቅሟ ነው። ሌላውም እንደዚያው ነው። የእነዚህ የባለብዙ ወገን (መልታይ ላተራል) ተቋማት መመስረት ፋይዳቸውም ነገሮች ከግጭት ባሻገር በንግግር መፍትሔ እንዲያገኙ ማስቻል፤ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያመጡ ትብብሮችን ለመፍጠር ነው። ሆኖም ይሄ በተግባር እየተገለጠ አይደለም። ለአብነት፣ አሁን በዓለም ባንከ አልረካንም፤ ለደሃ ምቹ ተቋም አይደለም፤ መሻሻል አለበት እያልንም፤ ቢሆን ግን አብረን እንሠራለን። አሻሽሉት ትክክል አይደለም እያልን አብረን እንሠራለን።

በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አናምንበትም፤ ችግር አለበት፣ አድሎ አለበት። ትክክል አይደለም፤ ይስተካከል፤ ሪፎርም ይደረግ ብንልም አብረን እንሠራለን። ዲፕሎማሲ ማለት ባይመችህም ይለወጥ እያልክ በዚያ ማዕቀፍ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ በሕግ ማዕቀፍ መሥራት ማለት ነው። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቁ ነገሮች ከሁሉም የዓለም ጫፍ ጋር ለጋራ ጥቅም እንሠራለን።

እኛ ብሪክስ የገባነው የምዕራቡን ዓለም ለመተው አይደለም። ቢያንስ ቢያንስ ዛሬ እንኳን የብሪክስን ዋጋ ተረዱ፤ ብሪክስ ባንገባ ኖሮ እኮ ሁሉም የሌለንባቸው ተቋማት መግለጫ እንዳወጡብን እነሱም እኮ ያወጡብን ነበር። ስላለንበት እኮ ነው ቢያንስ ከአንድ መግለጫ የተረፍነው፤ ሌላው ቢቀር ማለት ነው። ዐረብ ሊግ እኛ ብንኖር ኖሮ የእኛን ድምጽ ሳይሰማ፣ የእኛን አቋም ሳያውቅ እኛ ላይ መግለጫ ያወጣ ነበር እንዴ፤ ምንም ሳንደመጥ እኮ የሚወጣብን የላችሁበትም ማለት እኮ ነው ።

እና ብሪክስ የገባነው ከምዕራቡም ከምሥራቁም ዓለም ጋር በትብብር ለመሥራት እንጂ አንደኛውን አቅርበን አንደኛውን ለማራቅ አይደለም። ከእኛ በላይ እኮ እኛ ምንድነን? ገባን ቀረን ምንድነን? እኛ እኮ ለምሳሌ ቻይናን እና አሜሪካን ብንወስድ እኮ ከማንም ሀገር በላይ የኢኮኖሚ ትስስር አላቸው ።

ሳዑዲና የተባበሩት ኤምሬትስ ከእኛ በላይ ከአሜሪካ ከአውሮፓ ጋር ትስስር የላቸውም? ጥቅም የላቸውም? ያን ጥቅም አንፈልግም ብለው ነው እዛ የገቡት፤ አይደለም። በመሰባሰብ ውስጥ የሚገኝ ጠቀሜታን ይበልጥ አልቆ ለመጠቀም ያለ ፍላጎት ነው፤ እናም እኛም ከምዕራቡ ዓለም ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነው ያለን፤ ከአሜሪካ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነው ያለን፤ ያ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ከአሜሪካ ጋር ያለንን ወዳጅነት በሌላ ወዳጅነት አንሽርም፤ ብንፈልግም አይቻልም፤ እሱን አጠናክረን ለሁሉም የምንሰጠውን ሰጥተን የምንቀበለውን ተቀብለን በሰላም መኖር እናስቀድማለን ።

የጎረቤት ሀገራትን በሚመለከት ግን በፖሊሲያችን እንዳመላከትነው የቅድሚያ ቅድሚያ ምንሰጠው ለእኛ ጎረቤቶች ነው። ለምሳሌ ያህል ሶማሌን ሕዝብ ብንወስድ፣ በዓለም ላይ ከሶማሊያ በላይ ከዋናው ሶማሊያ ውጪ ከኢትዮጵያ በላይ በርከት ያሉ ሶማሌዎች የሚኖሩበት ዓለም የለም። የሶማሌዎች ሀገር አንደኛ ሶማሊያ ሁለተኛ ኢትዮጵያ ናት ፤ ሦስተኛ ኬንያ ፣ ጂቡቲ ፣ አሜሪካ ፣ እንግሊዝ ሊባል ይችላል ።

ከሶማሊያ ቀጥሎ የሶማሌዎች ዋና መኖሪያ ግን ኢትዮጵያ ናት፤ ስለዚህ ደም እንጋራለን፣ ባህል፣ እምነት እንጋራለን፣ በጣም ብዙ ነገር እንጋራለን ማለት ነው።

የሶማሊያን መንግሥት የሚያፈራርስ የሶማሊያን መንግሥት ህልውናን የሚያጠፋ የሶማሊያን መንግሥት የሚጎዳ ፍላጎት ኢትዮጵያ የላትም። የተከበረው ምክር ቤት እንደሚያውቀው ባለፉት አስራ ምናምን አመታት የሶማሊያን ሰላም ለማስከበር በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሞተዋል፤ ሶማሊያ ውስጥ የምንሞተው የሶማሊያ ሰላም የእኛ ሰላም ስለሆነ ነው፣ የሶማሊያ ልማት የእኛ ልማት ስለሆነ ነው። ወንድም ሕዝብ ናቸው ብለን ስለምናስብ ነው።

ከኢትዮጵያ በላይ ለሶማሊያ የሞተ አንድም ሀገር የለም፤ መግለጫ ያወጣ አለ፤ የሞተ አንድም ሀገር የለም፤ ወደፊትም አይኖርም። በነገራችን ላይ የዛሬ ሁለት ወር ሦስት ወር ገደማ ከእናንተ ጋ ስለቀይ ባሕር በተወያየን ማግስት በሺህ የሚቆጠሩ የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች ሁርሶ አሰልጥነን ልከናል። በውስጣችን ክፋት ካለ እንዴት ሁርሶ አሰልጥነን ወደዛ እንልካለን? እኛ ከሶማሊያ ጋር ምንም ዓይነት ግጭት ምንም ዓይነት መጥፎ ንግግር ማድረግ አንፈልግም። ወንድሞቻችን ናቸው፤ በጋራ ትብብር ማድረግ እንፈልጋለን።

ቀይ ባሕርን በሚመለከት ያለው ጉዳይ እስካሁን እኛ ጩኸናል፤ ከአሁን በኋላ ግን የእኛ ጎረቤቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ቢጮሁ መልካም ይመስለኛል። ምን ማለት ነው? ታስታውሱ ከሆነ ለተከበረው ምክር ቤት ይሄንን ጉዳይ ሳቀርብ የሁቲ ውጊያ አልተጀመረም ነበር። ይሄ አሁን ያለው የጋዛ ጦርነት ስላልነበረ፤ ሁቲ ቢተኩስና ጂቡቲ ላይ የጂቡቲ ወደብ ሥራ መሥራት ቢቸገር ምን እንሆናለን ብያችሁ ነበር ታስታውሱ ከሆነ፤ ይኸው እኮ አየነው፤ ስድስት ወር ሳይሞላ የቀይ ባሕር ንግድ ሥርዓት እኛን ብቻ ሳይሆን ቀይ ባሕርን የሚጠቀሙ ሀገራት እነ ሕንድ እና ግብጽ ጭምር ሁሉም ችግር ላይ ነው ያሉት ።

የእኛ ጥያቄ ቀይ ባሕር ለእኛ በጣም በጣም ህልውናችን ነው ፤ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ነው ያለን፤ ከሌሎች ወንድሞቻችን ጋር ከጎረቤትም ከቅርብም ከሩቅም ሆነን እዛ አካባቢ ያለውን ሰላም እያረጋገጥን ልማታችንን የምናመጣበትን መንገድ ማረጋገጥ ያስፈልገናል።

እኛ ሞቃዲሾ ገብተን መሞታችን ትክክል ከሆነ፣ ሱዳን ዳርፉር ሄደን መሞታችን ትክክል ከሆነ ቀይ ባሕር ላይ ሽብር ሲፈጠር ሄደን እንሙት ሲባል እንዴት ጥያቄ ይሆናል፤ ያው እኮ ነው፤ ዋናው ሰላም እንዲመጣ መሥራት ነው ።

የሶማሊያ መንግሥት እኔ ስገምት ከኢትዮጵያ ጋር የመጋጨት ፍላጎት ያለው አይመስለኝም፤ ግን ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች ሶማሊያን እንደ ፕሮክሲ መጠቀም ይፈልጋሉ፤ ለዛ ደግሞ እኛ አንመችም፤ በሶማሊያ ወንድሞቻችን ላይ ምንም ዓይነት የከፋ ነገር ለማድረግ ፣ ለመናገርም ለማድረግም ዝግጁ አይደለንም ።

ይህን የሚመኙ ኃይሎች ለአንዳንድ ዲያስፖራ ወንድሞቻችን ሚዲያ እንደከፈቱላቸው ሁሉ ለአንዳንድ ሱማሌ ወንድሞቻችን የተወሰነ ነገር ሊደርጉላቸው ይችላሉ። ሊያዋጉን ግን አይችሉም። በእኛ በኩል ቢያንስ አንዋጋም ፣ አንፈልግም ፤እኛ የምንፈልገው ሶማሊያ አድጋ ጠንክራ በልጽጋ ለኢትዮጵያ ትልቅ ገበያ ሆና ከኢትዮጵያ ተጠቅማ ኢትዮጵያን ጠቅማ ማየት ነው። ይህ አቋማችን በሶማሌ ሕዝብም ይታወቃል።

ለሶማሊያ አንድነት እንደዚህ መንግሥት የሠራ የለም፤ ሶማሌላንድ እና ሶማሊያን ለማገናኘት ብዙ ጥረት አድርገናል፤ እኛ ነገም ሶማሌላንድ እና ሶማሊያ ሊስማሙ የመጀመሪያው ተደሳች ሀገር ኢትዮጵያ ናት ። የእኛ ፕሮጀክት እሱ አይደለም፤ የእኛ ፕሮጀክት ስጋት ነው፤ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ይዘናል፤ እባካችሁን ተረዱን ነው። አምስት ሺህ ኪሎሜትር ነው ሾሩ/የባሕር ክልሉ/። ይሄን ዓለም ተገንዝቦ በዓለም ሕግ እንዲዳኘን እንጠብቃለን።

ብዙ ፍላጎቶች አሉ፤ ብዙ ጩኸቶች አሉ፤ በዓለም ሕግ በቢዝነስ ሕግ መዳኘት እንፈልጋለን። ከማንም መቀማት አንፈልግም፤ የማንንም ሉዓላዊነት መንካት አንፈልግም፤ እናከብራቸዋለን፤ ወንድሞቻችን ናቸው፤ እንወዳቸዋለን።

በቸገራቸው ጊዜ እንሞትላቸዋለን፤ አሁንም ከሞላ ጎደል ምግብም እንጋራለን ፤ዋናዋ አምራች በቀጣናው ኢትዮጵያ ናት። ግልጽ ነው፤ ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ አራት ትላልቅ ወንዞች ይፈሳሉ፤ እነ ዋቢሸበሌ፤ ወደዛ ውሃ መፍሰሱ ትክክል ነው፤ በዚህ እኛም ደስተኞች ነን ብለን ነው የምናስበው እንጂ የእኛ ውሃ ነው እንዳይሄድ ብለን አናስብም፤ የእኛን ውሃ መጠቀም አለባቸው፤ ምክንያቱም ወንድሞቻችን ናቸውና።

አየር ላይ ብዙ ጩኸቶች ይሰማሉ፤ አቧራዎች አሉ። አቧራው ጨሰ ማለት የሚፈልጉ ሀገሮች ደግሞ አሉ።

 ከእኛ ተምረው መሰለኝ። እኛ ደግሞ አቧራውን ማሳረፍ እንፈልጋለን። እኛ የምንፈልገው ዐሻራ፣ ልማት ብቻ ነው ። ግርግር አንፈልግም።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ማንንም ሀገር ወርራ አታውቅም። ማንም ሀገር፤ የትኛውም ሀገር ወሯት አሸንፏትም አያውቅም። ሦስት አይደለም አስር ቢደመር ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይችልም። እኛ አንዋጋም፤ አንፈልግም ፤ ወደዚህ ከመጣ ደግሞ አይችልም። ለእሱ በቂ የሆነ አቅም አለን። ስጋት የለብንም።

እኛን ያሰጋን የሰፈር ጎረምሳ ነው እንጂ ወራሪ አይደለም። ስጋት የለብንም፤ ጦርነት አንፈልግም፤ ልማት እንፈልጋለን፤ ልማት እንደምንፈልግ በችግር ውስጥ ሆነን ልማት እያመጣን በተግባር አሳይተናል። ዓለም ይሄን ይገነዘባል። ዓለም ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ሲሆን ለምን በዚህ መንገድ እንደሚያይ ሁላችንም ቁጭ ብለን ታሪክ ማጥናት ይኖርብናል።

እኔም ገና ብዙ ያልገቡኝ ጉዳዮች አሉ። ለምንድነው ዓለም እንደዚህ አድርጎ ይህችን ሀገር የሚጫናት የሚለው ጉዳይ ብዙ አልገባኝም። አንዳንድ ጊዜ እንደ ፖለቲከኛ ሆኜ ለማየት እሞክራለሁ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በመንፈሳዊ ዓለም እንደሚባለው እውነትም የኪዳን ሀገር ሆና ይሆን እንዴ፤ ብዬ እጠረጥራለሁ፤ አላውቅም። ግራ ያጋባኛል፤ እናንተም መርምሩ ፤ እኔም እመረምራለሁ። ነገር ግን ፍትሐዊ የሆነ ዳኝነት ያለበት ዓለም ግን አይደለም። ጉልበት ያለው የተደራጀ የተሰበሰበ የሚያሸንፍበት ዓለም እንጂ በፍትህ የሚታይበት ዓለም አይደለም አሁን ያለው።

እኛ የጠየቅነው ግን በጣም በጣም ትንሿን ነው፤ ለ120 ሚሊዮን ሕዝብ ደህንነት የምትሆን ትንሿን ነገር ነው የጠየቅነው። አየር መንገድም ይሁን ቴሌም ይሁን የፈለጋችሁትን ከፍለን እንጠቀም ያልነው እኮ ብዙ ሀገራት ስለሚጠቀሙም ነው። ለምን የእኛ እንደዛ ክፉ እንደሆነ እኔም አልገባኝም፤ በሂደት እናየዋለን። ስጋት ግን የለብንም፤ ወደማንም አንሄድም፤ ማንም ከመጣብን ግን እራሳችንን እንከላከላለን። ብዙ ስጋት አይደርባችሁ።

ሕዳሴን በሚመለከት ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ለድርድር ዝግጁ ናት። በሕዳሴ ጉዳይ በንጹህ ውሃ ጉዳይ ከሱዳንም ከደቡብ ሱዳንም ከኬንያም ከሶማሊያም ከጅቡቲም ከኤርትራም ምንም ዓይነት ጥያቄ ቢነሳ ከእኛ የሚሰጥ ውሃ ስለሆነ የእነሱን ስሜት ለመረዳት የእነሱን ሃሳብ ለማድመጥና የእነሱን ችግር ለመፍታት ዝግጁዎች ነን።

ያው እንደምታስታውሱት፤ ኢትዮጵያ ውሃ ከያዘች የአስዋን ውሃ ይቀንሳል የሚል ፕሮፓጋንዳ ነበር፤ እኛ ውሃ ይዘን ጨርሰናል። ከአሁን በኋላ ውሃ መያዝ አጀንዳ አይደለም። እንደምታውቁት የአስዋን ውሃ አልቀነሰም። ነገር ግን የግብጽ ወንድሞቻችን በዚህ ጉዳይ የሚያነሱት ማንኛውም ጥያቄ ካላቸው አድምጠን ኮምፕሮማይዝ አድርገን(አቻችለን) የእነሱን መሻት ለመመለስ እንደ መንግሥት እንደ ሕዝብ ጥረት እናደርጋለን። የእኛ ነውና እንዳትናገሩ አንልም።

በእኛ በኩል ለሁሉም ጎረቤቶቻችን ንጹህ ውሃ እንሰጣለን። ይሄ ወደፊትም መቀጠል አለበት። ከእኛ የሚሰጥ ነገር ካለ አንከለክልም፤ ከእነሱ የምጠብቀው እነሱም እኛ ያለንን ጥያቄ እንደዚሁ ያስተናግዳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

እኛ ሰጥተን እኛም ተቀብለን ተከባብረንና ተጋግዘን የምንኖርበት ዓለም ቢሆን ይሻላል፤ የራስን ተጠቃሚነት ብቻ ማሰብና መንቀሳቀስ (አድቫንቴጅ መምታት) ሁልጊዜ አያዛልቅም። አሁን ያለው ትውልድ ያን ለመከላከል የሚቸገር ይሆናል። መጪው ትውልድ ግን እንደዚህ ዓይነት ነገር አይቀበልም። ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የምንሰጠውን ታሳቢ አድርጎ ለመስጠት ዝግጁ የሆነ ዝምድና ከሁሉም እንፈልጋለን። ለመነጋገር፣ ለመወያየት፣ ሰጥቶ ለመቀበልና ካለን ለማካፈል ከምንም ጊዜ በላይ እኛ ዝግጁ ነን።

አሁን ችግር እየሆነብን ያለው፣ የአንድ አካባቢ ገዢ ጦርነት ሄዶ ያሸንፋል፤ ሲመለስ ሃብታሙም፤ አዋቂውም፤ የሃይማኖት አባቱም ቤቱ እየሄደ እንኳን ደስ አለህ፤ እንኳን በድል ተመለስክ እያለ በአቅሙ እየሰጠ ሰላምታ ያቀርብለታል። አንድ ቡቱቱ የለበሰ ደከም ያለ ሰውም እንዲሁ ወደ ገዢው ቤት ካልገባሁ እያለ በር ላይ ሲጨቃጨቅ ይውላል። ዘበኞች አናስገባም ይሉታል።

በኋላ ገዢው እንግዶች ለመሸኘት ሲወጣ አንድ ሰው ሲጨቃጨቅ ይመለክትና ምን ፈልጎ ነው አስገቡት ይላል። ሰውዬው ሲገባ ከቡቱቶው ውስጥ ቪኖ/ መጠጥ/ ያወጣና እኔ ለማኝ ነኝ ፤ በጣም ድሃ ነኝ። በድል ተመልሰሃል፤ ደስ ብሎኝ ያለችኝን ሳንቲም አውጣጥቼ ይህችን ቪኖ ገዝቼ እንኳን ደስ አለህ ለማለት ነው የመጣሁት ብሎ ቪኖውን ሰጠው። ሰውዬው ልቡ ይነካና የት እንደሚኖር ምን እንደሚቸግረው ጠይቆት መሬት፣ ማረሻ ከብት፣ ቤት፣እንዲሰጠው ወስኖለት አመስግኖት ይለያያሉ።

ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ያው ሰውዬ ቡቱቱ ለብሶ በመምጣት ካልገባሁ ብሎ ይጨቃጨቃል። አጋጣሚ ሆኖ ንጉሡ ዛሬም ወጥቶ ሲያገኘው ደግሞ ምን ቀረህ? ባለፈው አግኝቼህ የለም ወይ? ምን ቸግሮህ ነው? ብሎ ሲያናግረው፤ አይ ጌታ ሆይ፤ ባለፈው ቪኖ አምጥቼ ነበር፤ ከጠጡት ጠርሙሴን ልውሰድ ብዬ ነው አለው ይባላል። አመሰግናለሁ።

 በጋዜጣው ሪፖርተሮች

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You